ሙስናን በማጋለጣቸው በደል የደረሰባቸው ግለሰብ ቅሬታና የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ

በአሁኑ ጊዜ ሥራቸውም ነዋሪነታቸውም አዲስ አበባ ከተማ ነው – አቶ ሕዝቅኤል ማራ። ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጡትም ወድደውና ፈቅደው ሳይሆን ባጋለጡት የሙስና ወንጀል የተነሳ ጉዳት ይደርስባቸዋል በሚል ነው፤ ሙስና ፈጻሚዎቹ በግለሰቡ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ በሚል ከለላ ተሰጥቷቸው ይሠሩ ከነበረበት ከሐዋሳ ከተማ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

ቅሬታ አቅራቢው

ቅሬታ አቅራቢው አቶ ሕዝቅኤል ማራ፣ ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የምርመራ ዘገባ ቡድን ብቅ ያሉበት ዋናው ምክንያት ተደራራቢ ቅሬታ ስላለኝ ነው ይላሉ። እርሳቸው ይሠሩ የነበረው በቀድሞው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባላስልጣን የሕግ አገልግሎት ኃላፊ በመሆን ነው። በኃላፊነት እየሠሩ ባሉበት ጊዜ የተፈጸመ ከባድ የሙስና ወንጀል ነበር። ያንን ከባድ የሙስና ወንጀል ለሚመለከተው ማለትም ለፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙሥና ኮሚሽን አካል አቅርበው ተቋሙም በምርመራ እንዲጣራ አድርጎ ምርመራ ጀምሮ እንደነበር ያስረዳሉ።

ይሁንና ለፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙሥና ኮሚሽን ምርመራ እያደረገ ባለበት ሰዓት በአጋጣሚ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙሥና ኮሚሽንን የመክሰስ ስልጣን ተረከበ። ስለዚህም መዝገቡ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተላለፈ። የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሙሥና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት መዝገቡን አይቶ በመዝገቡ ውስጥ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው እነዚያ ጉዳዮች ይሟሉ ብሎ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መዝገቡን ላከ ይላሉ። ከዚያ በኋላ ግን እርሳቸው እናደተናገሩት፤ መዝገቡ የት እንደገባ አያውቁም። ወደላከው አካል ወደ የሙስና ወንጀሎች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዘንድ ይመለስ አይመለስ የሚያውቁት ምንም ነገር እንደሌለ ጠቅሰው፤ “ከእኔ ተሰውሮብኛል” ሲሉ ይናገራሉ።

እንዲያውም ይላሉ ቅሬታ አቅራቢው፣ የተፈለገው ነገር አንዳች ጥያቄ እንዳላነሳ በመሆኑ ካለሁበት ሥፍራ እንዳልገኝ ተደርጓል። እኔም ይህ ጫና ሲበዛብኝ ለመሸሽ ተገድጅያለሁ ሲሉ ቅር መሰኘታቸውን ይናገራሉ።

ነገር ግን በዚያን ወቅት ማለትም በ2008 ዓ.ም ጥቅምት ወር ቅሬታቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አቅርበው ጋዜጣውም ቅሬታውን ተቀብሎ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ባክኖ እንዳይቀር በሕግ አግባብ እንዲታይ ለማድረግ ጥቅምት 6 ቀን 2008 ዓ.ም ለሕትመት ማብቃት ችሏል የሚሉት አቶ ሕዝቅኤል፣ ይህ ከሆነ በኋላ በተወሰነ ደረጃ እንቅስቃሴ ተደርጎ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሁንና ጫናው ይበልጥ እየበረታባቸው መጣ። የቀረበውን መረጃ መሰረት አድርገው ይበልጥ ማጣራትና ጉዳዩን መመርመር መቅደም ሲገባው በእርሳቸው ላይ ይበልጥ ጫናው እያየለ መምጣቱን ያስረዳሉ። የደረሰባቸው ጫና ቀላል ሳይሆን እስከ ከሥራ ማስወገድ የደረሰ ነው። ይህ የተደረገባቸው ከአንዴም ሁለት ጊዜ እንደሆነ ያስረዳሉ።

አቶ ሕዝቅኤል፣ “በወቅቱ ከሥራ እንድወገድ ያደረገኝ እሰራበት የነበረው ተቋም ደቡብ መንገዶች ባለስልጣን በወቅቱ የነበሩት ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በፌዴራል ሥነ- ምግባርና ፀረ-ሙሥና ኮሚሽን ወደሥራዬ እንድመለስ የሚያስችል ደብዳቤ ለባለስልጣኑ ጻፈ፤ ይሁንና እነርሱ ወደሥራዬ ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበሩም። ጉዳዩ ለፍርድ ቤት ቀርቦ ፍርድ ቤት ወደሥራ እንድመለስ አድርጓል። ከተመልስኩ በኋላ አንድ ሰባት ወር ያህል እንደሠራሁ እንደገና ከሥራ ገበታዬ አባረሩኝ። እንደገና እኔ መባረሬን ለሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አቅርቤ እና ፍርድ ቤቱም አይቶ ወደሥራዬ እንድመለስ ወሰነ። ሁለቴም ከሥራ ባስወገዱኝ ሰዓት ግራ የተጋባሁ ቢሆንም በጊዜው ደግሞ መንግሥት ወደሥራዬ እንድመለስ አድርጎኛል። ” ይላሉ።

ይሁንና የሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወደሥራው ይመለስ በሚል በወሰነው ውሳኔ ላይ ባለስልጣኑ ለሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠየቀ። የሐዋሳ ከተማ ክፍተኛ ፍርድ ቤት በእነርሱ ይግባኝ ከእርሳቸው መልስ ተቀብሎ ድጋሚ ውሳኔ ሰጠ።

የሰጠውም ውሳኔ “የስር መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክል ነው። ተጠሪዬ ወደሥራው መመለስ አለበት። ” በሚል ነው። እነርሱ ግን በዚያ ውሳኔም አልተስማሙም። ድጋሚ ለደቡብ ከልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመለከቱ። ደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስቀርባል ብሎ በመዝገቡ ላይ ብይን ከሰጠ በኋላ በድጋሚ ከአቶ ሕዝቅኤል መልስ ተቀብሎ ለእርሳቸው ወሰነ። “የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ትክክል ነው፤ ስለዚህ ወደ ሥራ መመለስ አለበት፤ ምክንያቱም ከሥራ እንዲሰናበት የሚያደርግ ምንም ነገር የለም” ብሎ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ። ከወሰነ በኋላ በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ በድጋሚ ለፌዴራል ሰበር ድጋሚ ቅሬታ አቀረቡ።

በዚህ መካከል ደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወሰነው ውሳኔ መነሻ አቶ ሕዝቅኤልን ወደሥራ መለሷቸው። “እኔ ሥራ ገብቼ ባለሁበት ክርክሩ አልተቋረጠም። ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር እነርሱ አቤቱታ አቀረቡ። ባቀረቡት አቤቱታ መልስ ስጥ ተብዬ መልስ ሰጥቼ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በማጽናት ወደ ኃላፊነት ሥራዬ እንድመለስ አጠቃላይ የተቋረጡ ጥቅማጥቅሞችም እንዲከበሩ ውሳኔ ሰጠ። በዚያ ውሳኔ መሰረት መፈጸም ሲገባው እስካሁን ያ ውሳኔ ሊፈጸም አልቻለም። የመዝገብ ቁጥሩም ሰበር መዝገብ ቁጥር 114489 ነው፤ ይህ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረ ገጽ በግልጽ የተቀመጠ ውሳኔ ነውና ታገኙታላችሁ።” ይላሉ።

አመልካች የሆነው የደቡብ መንገዶች ባለስልጣን ቀደም ብሎ መከራከሪያ ያላደረገውን ከአንድ ዓመት በፊት የካታቲት 4 ቀን 2006 ዓ.ም ተጽፏል የሚለውን በሙያ ብቃት ተጠሪ (አቶ ሕዝቅኤል) ይዞት የኖረውን የሥራ መደብ በሹመት የሚመደብበት ሆኗል በማለት ያቀረበው ክርክር ታማኝነት የሌለውና በፍርድ የተሰጠውን ውሳኔ እና የአፈጻጸም ትዕዛዝ ላለመፈጸም በቂ እና አሳማኝ ምክንያት አለመሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በማረጋገጥ አመልካች ተጠሪን የሕግ አገልግሎት ኃላፊ ሥራ መደብ ከእነ ሙሉ ጥቅሙ እንዲመድብ የሰጠው ውሳኔ ስለፍርድ አፈጻጸም በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 378 ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ በመሆኑ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የለበትም በማለት ወስነናል ብሎ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ውሳኔ ሰጥቷል። እስካሁን ይህን ውሳኔ የሚያስፈጽም አካል አልተገኘም ይላሉ። በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ ማመልከታቸውን ያስረዳሉ።

ነገር ግን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለው ነገር ቢኖር ውሳኔው ተግባራዊ ያልሆነው ቅሬታ አቅራቢው ባለመምጣታቸው ነው የሚል ነው። ይሁንና እኔ የቀረብኩት 112 ጊዜ ነው። በስር የአፈጻጸም መዝገብ አለ። ይህን ከመዝገቡ ማየት ይቻላል። 112 ጊዜ መቅረቤን ግልጽ ሆኖ ሳለ “ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ቅሬታ አቅራቢው አልቀረበም” በሚል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ምላሽ ሰጥተዋል። የሕግ የበላይነት አለመከበሩ ቅር እንዳሰኛቸው ይናገራሉ።

ከደረጃቸው ዝቅ፤ ከአካባቢያቸውም ውልቅ እንዲሉ ያስደረጋቸው የሙስና ትግል የቱ ነው?

አቶ ሕዝቅኤል፣ በደቡብ ክልል መንገዶች ባለስልጣን የሕግ አገልግሎት ኃላፊ ሆነው እየሠሩ ባሉበት ወቅት በሲዳማ ዞን ጢጥቻ ዳዬ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ውል ጋር የተያያዘ የክፍያ ጥያቄ ወደባለስልጣኑ ይመጣል። በዚያን ወቅት የባለስልጣኑ ሥራ አሥኪያጅ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ይሰጡበት ዘንድ ወደ አቶ ሕዝቅኤል ይመራሉ።

እርሳቸውም ጉዳዩን ከሕግ አኳያ በሚመረምሩበት ወቅት ውሉ በግልጽ የተቀመጠው በ18 ሚሊዮን ብር ነው። ክፍያ የተፈጸመው ግን 35 ሚሊዮን ብር መሆኑን ያጤናሉ። በመሆኑም አስተያየት ስጥ በተባሉት መሰረት ከውል ውጭ ክፍያ መፈጸሙን ጠቅሰው በዚህ ጉዳይ የሚሰጡት አስተያየት እንደሌለ ይናገራለ። ያንን በማለታቸው ብቻ በባለስልጣኑ መጠመድ መጣ ይላሉ።

ይሁንና እርሳቸው አስተያየት ባይሰጡበትም የፕሮጀክቱ ክፍያው ተፈጽሟል። “በወቅቱ ከሥራ ስላገዱኝ የቀረ ሒሳብ የተባለውን ምን ያህል መሆኑን ማወቅ አልቻልኩም” ይላሉ። ነገር ግን የቀረ ሒሳብም መከፈሉን እንደሚያውቁ ይናገራሉ።

በእርግጥ ይላሉ ቅሬታው አቅራቢው፣ ከባድ ሙስና የተካሔደበት ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም። በደቡብ ክልል ደረጃ የተፈጸመው ሙስና ምን ያህል እንደሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሰነድ ማስረጃ አቅርበዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሰነድ ማስረጃውን ያቀረቡበት ምክንያት ሲናገሩ እንደገለጹት፤ ለሚመለከታቸው ተቋማት ማለትም ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙሥና ኮሚሽንና ለደቡብ ክልል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን አቅርበው መፍትሔ በማጣታቸውና ጉዳዩ በተቋማቱ ዘንድ ሊታይ ባለመቻሉ ነው። በመሆኑም ጉዳዩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት በኩል ለሚመለከተው አካል እንዲተላለፍ ተጨባጭ የሆነውን ማስረጃ አቅርቤያለሁ ይላሉ። ይሁንና ጉዳዩ ምን እንደተደረገ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

እንደዚያ በመሆኑ እና ምንም አይነት ሒደት ባለማየታቸው ወደእርሳቸው ጉዳይ ዞር ብለው ጉዳያቸውን በሕግ አግባብ ፍትህ እንዲያገኝ መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ያስረዳሉ። ይሁንና የእርሳቸውን ጉዳይ ፍርድ ቤት በፍርድ ያረጋገጠውን የሚያስፈጽምላቸው አካል አጥተዋል። ፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ “የተደረገው ነገር ትክክል አይደለም፤ ወደሥራ ገበታቸው ወደሕግ አገልግሎት ኃላፊነታቸው እንዲመደቡ፤ የታገዱባቸው ጥቅማጥቅሞች እንዲከፈሉ” በሚል በ2009 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጥቷል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው አቶ ሕዝቅኤል፣ ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የወሰነውን ውሳኔ የእራሱ ውሳኔ እሳካሁን አለማስፈጸሙን ይጠቅሳሉ። ይህ ውሳኔ በነበሩበት ቦታ ሆነው ሥራቸውን እንዲሠሩ የሚል መሆኑን እንደሆነም ያስረዳሉ። ይህ የዓቃቤ ሕግ ትዕዛዝም ሆነ የፍርድ ቤት ውሳኔ አልተፈጸም። ይህ ጉዳይ ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ጭምር እንደወጣ ያስታውሳሉ።

በዋናነት እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሙሥናን መታገል ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳይከበር የሚያደርግ አይደለም። ስለዚህ በሕገ መንግሥቱ የተወሱ ውሳኔዎች አንደኛ ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የእራሱን ውሳኔ ለማስፈጸም የተቸገረበት ምክንያት ምንድን ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ። ሁለተኛ ደግሞ ፍርድ ቤት ፍርዱን ለማስፈጸም እርሳቸው ከ110 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በአፈጻጸም መዝገብ ቁጥር 0816 ላይ ማስረጃ ይገኛል። ነገር ግን እሱ ማስረጃ እያለ “ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ያልቻልነው ቅሬታ አቅራቢው ባለመምጣቱ ነው” ብሎ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወቅቱ እንደዚያ ማለቱ ከእውነት የራቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለምን እንደዚያ እንደተደረገ ማወቅ እንደሚሹ ይገልጻሉ።

ስለዚህ በዚህ ምክንያት ፍርዱ እስካሁን አለመፈጸሙን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢው፣ ፍርዱ ባለመፈጸሙና ውሳኔው ተግባራዊ ባለመሆኑ በእርሳቸው ላይ በጣም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ያመለክታሉ።

ሙሥና በማጋለጣቸው የደረሰባቸው ጉዳት

ቅሬታ አቅራቢው እንደሚሉት፤ በዚህ የሙሥና ትግል የደረሰባቸው ከባድ የጤና መቃወስ ነው። የደረሰባቸው ጉዳት የጤና ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ ችግር ተጋላጭ እንደሆኑ አድርጓቸዋል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ሙሥናን በማጋለጣቸው በነበሩበት ሥፍራ ሆነው እንዳይሠሩ ጉዳት አድራሽ ይኖራል ተብሎ በመስጋት የመጣ ነው። እርሳቸው ከነበሩበት ማኅበራዊ መስተጋብር ውጪ ሆነው እንዲሄዱ በመደረጉ ‹‹ተፈናቃይ ሆኛለሁ›› ይላሉ። አሁን እየሠሩ ባሉበት “እኔ ማንም የለኝም፤ በቅርብ ርቀት ሊያግዘኝ የሚችል አካል ባለመኖሩም ጉዳቴ ከፍ ብሏል” ሲሉ ያስረዳሉ። ለዚህ ምክንያቱ ካሉበት እንዲፈናቀሉ በመደረጋቸው ነው።

ዋናው ጉዳታቸው ግን በጤንነታቸው ላይ ያለው ከባድ ችግር ነው። በከፍተኛ ሆስፒታል ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። የሀገርን ሀብት ለመታደግ በመንቀሳቀሴ የተዳረግኩት ለበሽታ ነው። ለሕዝብ እና ለመንግሥት ጉዳይ እራሴን አሳልፌ ሰጥቼ በመታገሌ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰብኝ በጣም የጤና ቀውስ ውስጥ እገኛለሁ።

አንደኛ ከለላውን የሚያስፈጽም አካል አጥቼያለሁ። ሁለተኛ ፍርዱንም የሚያስፈጽም አካል አጥቻለሁ። ሶስተኛ አሁን ባለሁበት ቦታ እየሠራሁ ያለሁት ከወር ደመወዜ አራት ደረጃ እና አስር እርከን ተቀንሶብኝ ነው ይላሉ።

በዓቃቤ ሕግ ውሳኔና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ውሳኔ ባገኘሁት በእራሱ ደመወዝ እየተከፈለኝ ያለው ከመጀመሪያ መደቤ የቀነሱት አራት ደረጃና አስር እርከን ነው። ስለዚህ ይህም እንዲስተካከል እሻለሁ። አንድ ግለሰብ ከአንዱ ወደ ሌላው መሥሪያ ቤት በሚዘዋወርበት ጊዜ ጥቅሙም፣ መብቱም ሆነ ግዴታውም ስለሚዘዋወር እንዲያስተካክሉልኝ ለፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ ማስረጃዎችን አያይዤ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ለዋና ዳይሬክተሩ አቅርቤ ነበር የሚሉት አቶ ሕዝቅኤል፣ ይሁንና እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ይጠቅሳሉ።

ደቡብ ክልል በነበሩበት ሰዓት ሙሥና በማጋለጣቸው ከሥራ አባርረዋቸው የነበረ መሆኑን የገለጹት ቅሬታ አቅራቢው፣ ወደሥራዬ እንድመለስ ውሳኔ ተወስኖልኝ ነበር። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ወደሥራ ሲመልሱኝ ውስጣቸው የበቀል ጥማት በመኖሩ ምክንያት ወደነበርኩበት መደብ አይደለም ይላሉ። ወደሥራ ሲመልሷቸው በወቅቱ ወደኃላፊነቱ መመለስ ሲገባቸው እነርሱ ግን ወደሥራ የመለሷቸው የሕግ ኤክስፐርት በሚል በደረጃ 13 ነው።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ከቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች መንገዶች ባለስልጣን የተጻፈላቸው ደብዳቤ ደረጃው 13 ነው። ፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በደረጃ 13 ነው ብለው በሚጠይቁበት ሰዓት ‹ደረጃ 13 የእኔ መደብ አይደለም። በቀል የተፈጸመበት ነው›› የሚሉት አቶ ሕዝቅኤል፣ በዋናነት ሕግ ተጣሰ ያሰኛቸው ጉደይ ሙስና በማጋለጣቸው የመንግሥትን ሀብት ያለአግባብ እንዳይባክን በመታገላቸው በሥራ ገበታቸው ዝቅ ተደርገው እንዲሠሩ መደረጉ ነው። እርሳቸው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ነገር ይህ የተደረገባቸው እርሳቸውን ለመበቀል በመታሰቡ ነው።

‹‹ከለላ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ስዛወርም በሕገ መንግሥቱም ከለላ ተደርጎልኛል፤ ከለላ አለኝ፤ በመደቡ ላይ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ ማለትም ደረጃ 17 ላይ ከለላ አለኝ ብዬ ከለላውን ጭምር የዓቃቢ ሕግ ውሳኔንና የፍርድ ቤት ውሳኔን ሁሉንም አያይዤ አስተካክሉልኝ ብዬ ለፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አቅርቢያለው። ያቀረብኩትን ለማስተካከል አሉታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሳይሆኑ ቀና ሰዎች ናቸው። ነገር ግን ለማስተካከል የተቸገሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ አልገባኝም። ይህ ጉዳይ ቢጠየቅ ጥሩ ነው›› ሲሉ ቅሬታቸው ይገልጻሉ።

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ላይ ያሉ ኃላፊዎች መልካሙን ማድረግ ይችላሉ የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ ማስረጃዎቹ የዓቃቤ ሕግ ውሳኔ፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርደ ቤት ሰበር ውሳኔ አለ። በዚህ ውሳኔ መሰረት በደረጃቸው ላይ በቀል መፈጸሙን የሚያሳዩ ነገሮች ስላሉ በቀሉን ለማስወገድ ደረጃቸውን ማስተካከል እደሚችሉ አስረድተዋል።

ለፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ደብዳቤ ተጽፎ የመጣው ደረጃ 13 መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሕዝቅኤል፣ ለአገልግሎቱ ደብዳቤውን መነሻ አደርገው ደረጃ ቢሰጡኝም፤ የፍርድ ቤት ውሳኔ ስላለ በውሳኔው መሰረት ማስተካከል ሲገባ መስተካል አልቻለም ይላሉ።

ወደ ፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ተዛውረው እየሠሩ የሚገኙት ቅሬታ አቅራቢው፤ የተዛወሩት የቀድሞው የፍትህ ሚኒስትር፤ የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በጉዳዩ መጉላላታቸውን በማየት የደረሰባቸው ችግር ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ሁኔታዎች እስከሚስተካከሉ በሚል ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው እንዲሠሩ ደብዳቤ እንደጻፉላቸው ያስረዳሉ።

በወቅቱ ሲዛወሩ ሚኒስትሩ በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መሰረት ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው እንዲሠሩ የተወሰነ መሆኑን አውቆ የሚቀርብለትን የትምህርት እና ሥራ ልምድ ማስረጃ መሰረት በማድረግ እንዲመደቡ አስታውቃለሁ የሚል ነው። እነርሱ ግን በዚህ መሰረት አልመደቡኝም በማለት ቅሬታቸው ያስረዳሉ።

በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዳላቸው የሚጠቅሱት አቶ ሕዝቅኤል፤ የሥራ ልምድ ከ28 ዓመት በላይ እንዳላቸው ያመለክታሉ። ‹‹አሁን ላይ እየተከፈለኝ ያለው ግን የጀማሪ ደመወዝ ነው። ስለዚህ 28 ዓመት ያገለገልኩት ዜሮ ሆኗል ማለት ነው ይላሉ። በውሳኔው ደብዳቤ መሰረት ያልተፈጸመበት ምክንያት እና ለመፈጸም የቸገራው ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም›› በማለት ቅሬታቸውን ይናገራሉ።

ቀድሞ የነበሩበት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች መንገዶች ባለስልጣን ቢሮ ደረጃ 17 ላይ እንደነበሩ በፍርድ ቤት ስለተረጋገጠ በደረጃ 17 እርከን 10 ላይ እንዲመደቡ የሚል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መስጠቱን ይጠቅሳሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ማስረጃ ቀርቦለት በውሳኔው አረጋግጧል። ይህን ማስረጃ ለፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ አገልግሎት አቅርበው በውሳኔው መሰረት እንዲፈጸምላቸው መጠየቃቸውን ያስረዳሉ።

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ቀና ሰው ስለሆኑ ለሚመለከተው የሥራ ክፍል ጉዳዩን እንደመሩት የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢው፤ የተመራለት ክፍል ምን አድርጎ እንደመለሰ ግን እንደማያውቁ ገልጸዋል።

‹‹አሁንም በዋናነት የእኔ ጥያቄ ሕግና ሥርዓት ይከበር ነው የሚሉት አቶ ሕዝቅኤል፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እፈልጋለሁ ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ይገልጻሉ። ከደረሰብኝ ጉዳት አንጻር የምናገረው እራሱ የጎዳት እየመሰለ ነው።

ወደ ፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ከተመደብኩ በኋላ በደረጃ 16 የቅርንጫፍ ዴስክ ኃላፊ ተደርጌ ተመድቤ ነበር የሚሉት አቶ ሕዝቅኤል፤ እየሠሩ ባሉበት በማያውቁት መንገድ በደብዳቤ እንደተነሱና የደብዳቤው ይዘት ቀድመው ይሠሩበት ወደነበረው የሥራ መደብ ተዛውረው እንዲሠሩ የተወሰነ መሆኑን ስለማሳወቅ የሚል መልዕክት ያዘለ መሆኑን ይገልጻሉ።

ደብዳቤው ደረጃ 13 ላይ ተመድበው እንዲሠሩ የሚገልጽ እንጂ በዚህና በዚያ ምክንያት ነው ዝቅ የተደረጉት የሚል ይዘት አልተገለጸበትም ሲሉ ያስረዳሉ። አቶ ሕዝቅኤል፣ በተመደቡበት የሥራ መስክ ካሉት ኃላፊዎች ጋር ተግባብተው ሥራቸውን እየሠሩ እንደሚገኙም ያመለክታሉ።

በሁኔታው ከፍተኛ የሞራልና የሥነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚጠቁሙት ቅሬታ አቅራቢው፣ ከባድ ሆኖ የዘለቀባቸው የጤና ጉዳቱ ነው፤ ይህን ሁሉ ተሸክመው የአቅማቸውን እየሠሩ ይገኛሉ። ነገር ግን ዋናው የእርሳቸው ጥያቄ ብዙ ዋጋ የከፈልኩት የሀገርና ሕዝብ ሀብት ጉዳይ ስለሆነ ውሳኔው ይታወቅ የሚል ነው።

የሰነድ ማስረጃዎች

ሰነድ አንድ፡- የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በታህሳስ ወር በቀን 19/2008 ዓ.ም በሰበር መዝገብ ቁጥር መ/ቁጥር 114489 ተጠሪ የስር ፍርድ ቤት በሰጠው የአፈጻጸም ትእዛዝ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል። የሀዋሳ ክተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪን ይግባኝ መዝገብ ቁጥር 17220 ከመረመረ በኋላ በፍርድ ቤት ሥነ ሥርአት ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል። ተጠሪ የሰበር ሰሚ አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አቅርቦ፣ የክልሉ የሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 64396 የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ አመልካች ተጠሪ ወደ ነበረበት የሕግ አገልግሎት ኃላፊነት ባለመመደብና በፍርድ የተሰጠን ውሳኔ ላለመፈፀም ቦታው የሹመት ነው በማለት ያቀረበው ክርክር የሕግ ድጋፍ የሌለው መሆኑን ገልፆ፣ አመልካች ተጠሪን በዋናው ውሳኔ በተወሰነው መሰረት በሕግ አገልግሎት ኃላፊ የሥራ መደብ ላይ በመመደብ ተጠሪ በሜሪት ሊያገኝ ጥቅማጥቅምና ደመወዝ ሊከፍለው ይገባል። ተጠሪ እስካሁን ያልተከፈለው ውዝፍ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ክፍያ ካለ ተጠሪ ማግኘት ካለበት ጊዜ ጀምሮ በባለሙያ ተሰልቶ እንዲከፈለው በማለት በመዝገብ ቁጥር 64396 ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም ውሳኔ ሰጥቷል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዝገብ ቁጥር 64396 ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ፀንቷል። በዚህ ፍርድ ቤት ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ መነሳቱን ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

ሰነድ ሁለት፡- የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ሕዳር 03/ 2009 ዓ.ም ቀድሞው ደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የደቡብ መንገዶች ባለስልጣን አመልካች አቶ ሕዝቅኤል ማራ ማመልከቻ መጻፋቸውን በመጥቀስ ባለስልጣኑ በፊት በሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንና በፍርድ ቤቱ እንዲፈጸሙ የታዘዙትን ትእዛዞች ያለመፈጸም፣ ያለማክበር፣ የሕግ የበላይነትን የመጣስና ከሕግ በላይ መሆንን የሚያመላክት ስለሆነ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ግምት ውስጥ በማስገባት በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት ወደ ነበረበት የሥራ መደብ እንዲመለሱ የሚያትት ደብዳቤ መላኩ የሰነድ ማስረጃ ያመለክታል።

ሰነድ ሶስት፡- የፍትህ ሚኒስትር ደብዳቤ

የቀድሞው ፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በወርሃ ሚያዝያ፣ በቀን 30/2014 በደብዳቤ ቁጥር ፍ/ሚ01/ፅ-4/6353 ለፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የአቶ ሕዝቅኤል ማራን ምደባ ይመለከታል በሚል አርዕስት በተጻፈ ደብዳቤ አቶ ሕዝቅኤል፣ ሙሥናን በመጠቆማቸውና በመመስከራቸው የተነሳ ከፍተኛ በደል እና ስቃይ የደረሰባቸው ናቸው። በመሆኑም የተጨማሪ የበቀል ርምጃ ሰለባ እንዳይሆኑ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በተደጋጋሚ ለፍትህ ሚኒስቴር ማመልከታቸውን በመጥቀስ ጥበቃ እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ሲመዘን ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ (4) ንኡስ አንቀጽ (1) ከተዘረዘሩት የጥበቃ አይነቶች ውስጥ በተለይ በንኡስ ፊደል (ወ) ላይ የሥራና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ መርዳት በሚል በተደነገገው መሰረተ ቀደም ሲል ሲሠሩበት ከነበረው የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንገዶች ባለስልጣን ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው እንዲሠሩ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ስለሆነም የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፤ አቶ ሕዝቅኤል ማራ፣ በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መሰረት ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው እንዲሠሩ የተወሰነ መሆኑን አውቆ የሚቀርብለትን የትምህርትና የሥራ ልምድ ማስረጃ መሰረት በማድረግ እንዲመደቡ ሚኒስትሩ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ይገልጻል።

ሰነድ አራት፡- የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት

ሰነድ አንድ፡- የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በቀን 11/10/2017 በደብዳቤ ቁጥር ሰማ/ሰሀ/1722/668 ለድርጅታችን በላከው ደብዳቤ ስማቸው የተጠቀሱት የተቋማችን የሕግ ጉዳዮችና የሰነዶች ዝግጅት ባለሙያ IV የሆኑት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቁጥር 1/12/12511 ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓም በተፃፈ ደብዳቤ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል አመልካች ወደ ተቋሙ ሲቀላቀሉ ይሠሩ የነበረበት ደረጃና አሁን ላይ እየሠሩ የሚገኙት ደረጃ ምን እንደሆነ በሚገልጽ ደብዳቤው አቶ ሕዝቅኤል ማራ ታንጋ 1ኛ ወደተቋማችን ተመድበው ሲመጡ የነበራቸው ደረጃ XIII የነበረ መሆኑን፤ 2ኛ አሁን ተመድበው የሚያገኙት በደረጃ XIV መሆኑ እየገለጽን፤ 3ኛ ተጠቃሹ ተዘዋውረው ሲመጡ ደረጃ XVII ነበርኩ ሶስት ደረጃ ዝቅ ተደርጌ ተቀንሶ ተመድቤያለሁ ብለው ያቀረቡት በተቋማችን በኩል ያልተቀነሰና ተጠቃሹ ተመድበው የመጡበትን ደብዳቤዎች አድርገው ልከዋል።

ሀ. ተጠቃሹ ከፍትህ ሚኒስቴር በቁጥር ፍ/ሚ01/ፅ-4/6353 ሚያዚያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲመደቡ የተፃፈው ደብዳቤ 1ገጽ ፎቶ ኮፒ፤ ለ. ለሲቪል ሰርቪስ ማብራሪያ ጥያቄ ያቀረብንበት ሠማ/14.06/493 መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ደብዳቤ ገጽ ፎቶ ኮፒ፤ ሐ. ተጠቃሹ በ20/7/2014 ዓ.ም እስከ ሁለት እርከን ድረስ ዝቅ ብዬ እንድመደብ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የትብብር ደብዳቤ እንድንጽፍለት የፃፈው ማመልከቻ 1ገጽ ፎቶ ኮፒ እንዲሁም መ. ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በቁጥር ሲስኮ 1.1/ጠ21/29/14 ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ስለተጠቃሹ ምደባ ደመወዝ እና ደረጃ በተመለከተ የተሰጠ ማብራሪያና ተዘዋውረው እንዲሰሩ የተስማማበት ደብዳቤ 1 ገጽ ፎቶ ኮፒ፤ ሠ. የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንገዶች ባለስልጣን በቁጥር ሠ11/34/38 በ05/11/2014 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የተጠቃሹ የሥራ አፈፃፀምና ደረጃ XIII መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ 1ገጽ ፎቶ ኮፒ አያይዘን ለተከበረው የፌደራል ዓቃቤ ሕግ መላካቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ልከዋል።

ውድ አንባብያን፣ የአቶ ሕዝቅኤል ማራ፣ ዋና ጥያቄ የሆነው የሕዝብና የመንግሥት ንብረት በሙሰኞች ተዘርፎ ተደበስብሶ መቅረት የለበትምና መዝገቡ ከወዴት ደረሰ የሚል ሲሆን፣ ለዚህ ምላሽ ይሆነን ዘንድ የሚመለከታቸውን ተቋማት ጠይቀን በቀጣይ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።

በአስቴር ኤልያስና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You