
ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ናት። በየዘመናቱም ስሟን የሚያስጠሩ እና አርዓያ የሚሆኑ ልጆችን የምታፈራ ማህፀነ ለምለም ናት። ኢትዮጵያ የብዙ ስመ ጥር ግለሰቦች ሀገር መሆንዋ የታወቀ ቢሆንም ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው:: በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኙዋቸው ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ አገር ዕውቀት የቀሰሙ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሑራን እንደ ነበሩ ታሪክ ይነግረናል።
ኢትዮጵያ ከማህፀኗ ካፈራቻቸው ልጆቿ ውጪ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አይደሉም። በውትድርና፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ የውጭ ሀገር ዜጎች ብዙዎች ናቸው።
የተወለዱበትን ሀገር ትተው ለኢትዮጵያ በርካታ ውለታ የዋሉ እና ባላቸው ሙያ ሕዝብን እና ሀገርን ያገለገሉ የውጭ ሀገር ዜጎች በርካታ ናቸው ። ዛሬም ባለውለታነታቸውን ለመዘከር የተነሳነው ዕውቁን የኮንስትራክሽን ባለሙያን አልቤርቶ ቫርኔሮ እሸቴን ነው።
አልቤርቶ ቫርኔሮ እና ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በላይ ይተዋወቃሉ። በ1950ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ቀልባቸው በመሳቡ በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ ለመሳተፍ እና ሁለተኛዋ ሀገራቸው ለማድረግም ወዲያው ነበር የቆረጡት። ኢትዮጵያ በአየር ፀባይዋ፤ በእንግዳ ተቀባይነቷና እና ምቹ የመሥሪያ እና የመኖሪያ ስፍራ በመሆኗ አልቤርቶ ቫርኔሮን ለመሳሰሉ የውጭ ሀገር ዜጎች ሁልጊዜም ተመራጭ በመሆኗ አፈሯን የረገጡ ሁሉ ተማርከው ይቀራሉ፤ ወይንም ደግሞ አዘውትረው ይመላለሱባታል።
አልቤርቶ ቫርኔሮ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ነበሩ። ከታሪካዊ ሥራዎቻቸው መካከል የአፍሪካ አዳራሽ (የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን)፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት፣ ሂልተን ሆቴል፣ ሚሊኒየም አዳራሽ፣ የጅማ አባጅፋር አውሮፕላን ማረፊያ ማሻሻያ፣ የአብርኆት ቤተመጻሕፍት፣ የአንድነት ፓርክ እና የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት ሥራ ይገኙበታል።
ብዙ የኮንስትራክሽን ባለሙያ ባልነበረበት በ1950ዎቹ አልቤርቶ ቫርኔሮ ኢትዮጵያን በኮንስትራክሽን ዘርፉ ወደ ፊት እንድትራመድ ሙያዊ አበርክቷቸው ከፍ ያለ ነው። በወቅቱም ኢትዮጵያ በዘመኑ በኮንስትራክሽን ዘርፍም ተወዳዳሪ እንድትሆን ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የኮንስትራክሽን ሥራዎች የግድ የሚሉ ስለሆነ አልቤርቶ ቫርኔሮ በዘርፉ አስተዋፅዖ ባያደርጉ ኖሮ የአዲስ አበባ ድምቀት በእጅጉ በቀነሰ ነበር።
ለዚህ የአፍሪካ አዳራሽ (የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን)፣ አንዱ ማሳያ ሲሆን የዚህ ግዙፍ ሕንፃ መገንባት የአፍሪካን ዓለም አቀፍ እና አኅጉር አቀፍ ተሰሚነት በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል። ያለአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ አበባን አኅጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መቀመጫነት ለማረጋገጥ ከማለቻሉም በላይ ሕንፃው አሁንም ቢሆን በግርማ ሞገስ የተሞላ እና ዘመን የማይሽረው የሕንፃ ጥበብ የሚታይበት ነው።
በተመሳሳይም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በኪነ ውበቱ ዘላለማዊ የሆነ እና የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ ሕንፃ ነው። የኮንስትራክሽን ባለሙያው አልቤርቶ ቫርኔሮ ድንቅ ሙያዊ ችሎታ የተንፀባረቀበት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ዛሬም በግዝፈቱም ሆነ በውበቱ የአዲስ አበባ መለያ ሆኖ ዘልቋል። የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በኪነ ውበቱም ሆነ በተጠቀማቸው የግንባታ ግብዓቶች ዘመኑን የዋጀ እና አለፍ ሲልም ከዘመኑ ቀድሞ የተሠራ ነው ተብሎ በኮንስትራክሽን ባለሙያዎች የሚደነቅ ነው። ማዘጋጃ ቤቱ በከተማዋ እምብርት የሚገኝ ከመሆኑም ባሻገር አዲስ አበባን ሁሉ የረገጠ በሙሉ ከከተማዋ ጋር አብሮ የሚያነሳው እና የሚያስታውሰው ነው።
ማዘጋጃ ቤቱ አዲስ አበባን የሚያስተዳድሩ ከንቲባዎች መቀመጫ እና አልፍ ሲልም የከተማዋ ምክር ቤት መቀመጫ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ነው። ይኸው ሕንፃ ግዝፈቱም ሆነ በውበቱ ብዙዎቹን የሚያስደነግጥ እና የሚያስደምም በመሆኑም ብዙዎች ሕንፃውን አንዱ የታሪካቸው አካል አድርገው ወስደውታል።
በተለይም ቀደም ሲል የሠርግ ዝግጅቶች፤ ቲያትሮችና ከፍ ያሉ ሀገራዊ ትዕይንቶች የሚስተናገድበት ግዙፍ ሕንፃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙዎች ለሕንፃው ከፍ ያለ ትዝታና ክብር አላቸው። ሕንፃው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ እንዲሰጥ ተደርጎ ሲገነባም አልቤርቶ ቫርኔሮ ሙያዊ አቅምም አብሮ የተፈተነበት እና የተረጋገጠበት እንደሆነ እሙን ነው።
ከዚህ ባሻገርም አዲስ አበባ ከድሮ እስከ ዘንድሮ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ፋና ወጊ ሆና እንድትወጣ አልቤርቶ ቫርኔሮ ያበረከቱት አስተዋፅዖ ታሪክ ሲዘክረው የሚኖረው ነው። በአዲስ አበባ በኪነ ሕንፃ ውበቱ ብዙዎች የሚመርጡት እና የውጭ ሀገር ዜጎች ተቀዳሚ ምርጫቸው ከሚያደርጓቸው ሆቴሎች ውስጥ አንዱ ሆነው የሒልተን ሆቴል የተገነባውም በእኒሁ ድንቅ ባለሙያ እጅ ነው። ሒልተን ሆቴል በተለይም ሆቴሎች ባልተስፋፉበት በ1950ዎቹ ለአዲስ አበባ የሆቴል ቀንዲል ሆኖ ለብዙዎችን ማረፊያ እና መዝናኛ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል።
አንድ ለእናቱ ሆኖ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የሒልተን ሆቴል የአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ተሳታፊዎችን በብቸኝነት በማስተናገድ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። በወቅቱ የነበሩ ሰዎች እንደሚያስታውሱት እና እንደሚናገሩትም የበርካታ የአፍሪካ መሪዎች ምርጫ አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ሕንፃው ያለው ግርማ ሞገስ እና ውበት መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። ከዚህ ጥበብ ጀርባ ደግሞ የዕውቁ የኮንስትራክሽን ባለሙያ አልቤርቶ ቫርኔሮ ሰፊ ሙያዊ አስተዋፅዖ አለበት።
አልቤርቶ ቫርኔሮ ሙያዊ አስተዋፅዖ በዘመን የተገደበ አይደለም። ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከአለንበት ወራት እና ቀናት የዘለቀ ሙያዊ አስተዋፅዖ ለኢትዮጵያ አበርክተዋል። የእኒህ ባለሙያ ድንቅ እጆችም ዘመናትን ተሻግሮ በአብርኆት ቤተመጽሐፍት ላይ ተንፀባርቋል። በኪነጥበብ ውበቱ እና በግዝፈቱ የመዲናችን አንዱ መለያ የሆነው የአብርኆት ቤተመጽሐፍት ከንባብ አገልግሎቱ ባሻገር ለጉብኝት የሚመረጥ ድንቅ ቦታ ነው። አብርኆት ቤተመጽሐፍት የንባብ ጥማትን ለማርካትም ሆነ ለጉብኝት የሚመረጥ ቦታ እንዲሆን ካስቻሉት ዋነኛ መገለጫዎቹ ውስጥ አንዱ የግንባታው ጥራት እና ዲዛይኑ ናቸው። አብርኆት በዚህ ደረጃ አድናቆትን ሊያተርፍ የቻለውም በእውቁ ባለሙያ አልቤርቶ ቫርኔሮ በመገንባቱ መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ነው።
ባለ ብዙ ባህሎችና ቅርሶች መድበል ከሆነችው ኢትዮጵያ ከጥንታዊም ሆነ ከመካከለኛው ብሎም ከዘመናዊ ታሪኳ የሚቀዱ ዘርፈ ብዙ ሀብቶች አሏት። ከታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶቿም በተጨማሪ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስሕቦች ባለቤትም ነች። ይህንኑ እውነታ የተረዳው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) 16 ቅርሶቿን በመመዝገብ በአፍሪካ ግንባር ቀደም መሆኗን አረጋግጧል።
ከለውጡ ወዲህ መንግሥት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ግንባታዎች በስፋት በማከናወንና እና ለቱሪዝም ዘርፉ መጠናከር የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። እንደ ሀገርም መንግሥት ኢኮኖሚውን ወደ ፊት ያሻግራሉ ብሎ ተስፋ ከጣለባቸው የግብርና፤ ኢንዱስትሪ፤ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ጋር በአንድነት የቱሪዝም ዘርፉን የመሪነት ሚና እንዲኖረው አድርጓል።
ይህንኑ ሀገራዊ ራዕይ መሠረት በማድረግም ሀገራዊ ለውጡ ዕውን ከሆነበት 2010 ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማወቅ፤ በመለየት፤ በማልማትና በመጠቀም ረገድ እመርታዊ ለውጦች ታይተዋል። በአጠቃላይ ወቅቱ ለቱሪዝም ዘርፉ ትንሣኤ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አፍላቂነት እና መሪነት ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት የሚያበረታታ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለሸገር፤ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ በሚል ማሕቀፍ በሀገራችን የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ መልክ እንዲለሙ እና ለቀረው ዓለም እንዲተዋወቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ሥራ ተገብቷል። መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም ማዕዘናት ሀብቶችን በመለየትና በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እጅግ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በገበታ ለሸገር የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ የአንድነት፤ የወንድማማችት እና የእንጦጦ ፓርኮች ለአዲስ አበባ ድምቀት ሆነዋታል። ለወትሮው በቱሪስት መተላለፊያነት የምትታወቀው አዲስ አበባ የቱሪስቶች መቆያ የመሆን ዕድልም አግኝታለች። በገበታ ለሀገር ፕሮጀክትም የጎርጎራ፤ የኮይሻ እና የወንጪ የቱሪስት መዳረሻዎች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት ተጨማሪ ዕድሎችን ፈጥረዋል።
በዚህ ረገድ የአልቤርቶ ቫርኔሮ ሙያዊ አስተዋፅዖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እኒህ ዕውቅ የኮንስትራክሽን ባለሙያ የአንድነት ፓርክ እና የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት በማከናወን ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የእድገት ጎዳና የበኩላቸውን ሙያዊ አስተዋፅዖ አበርክተው አልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክትም ይህንን ብለዋል። ‹‹አልቤርቶ ቫርኔሮ ኅልፈት የተሰማኝን ኅዘን ለመግለጽ እፈልጋለሁ። ሥራቸው የሀገራችንን የግንባታ ከባቢ እና ታሪካዊነት ያላቸው ምልክቶችን ላቅ ባለ ደረጃ የቀረፀ ነው። የሥራ ውርሳቸው በነዚህ ብሔራዊ ምልክቶች እና በሚወክሉት የእድገት ትዕምርት ሲታወስ ይኖራል። ለነፍሳቸው ዕረፍትን፣ በዕረፍታቸው ላዘኑ ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን።›› በማለት ኅዘናቸውን ገልጸዋል።
እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን ዓምድ እውቁን የኮንስትራክሽን ባለሙያ አልቤርቶ ቫርኔሮ ላበረከቱት ዘመን ተሻጋሪ ሥራ አመሰገንን። ሰላም!
ይህንን ጽሑፍ ስናዘጋጅየተለያዩ ድረገጾችን በምንጭነት ተጠቅመናል።
በእስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም