መግቢያ
ይህ ጽሁፍ የሚያጠነጥነው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ትብብሮች ከዘላቂ ልማት ግቦች በተለይም ከአምስቱ ምሶሶዎች ጋራ ማለትም ህዝብ፣ መሬት፣ ብልጽግና፣ ሠላምና አጋርነት እንዴት እንደሚዛመድ ለማሳየት እና ከዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ከአባይ ወንዝ አኳያ ያለውን ተያያዥነት ለአንባብያን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው።
የዓለማችን ግማሽ ያህሉ የመሬት ክፍል የሚገኘው በድንበር ተሻጋሪ የወንዝ ተፋሰሶች እና ሃይቆች ነው። 40 ፐርሰንት የዓለም ህዝብም የሚኖረው በእነዚህ ድንበር ተሻጋሪና ሃይቆች ተጋሪ ሀገራት ውስጥ ነው። 90 ፐርሰንቱ ሀገሮች እነዚህን የወንዞች ተፋሰሶችና ሃይቆች ይጋራሉ። በዓለማችን ላይ ወደ 276 የሚሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እንዳሉ በጥናት ተለይቷል። እነዚህን ድንበር ተሻጋሪ የወንዝ ተፋሰሶች በአግባቡ ማስተዳደር ካልተቻለ፤ ሀገራት (ህዝቦች እና ባለድርሻ አካላቶች) በቀጥታ የማይወጡት ችግር ውስጥ ያስገባቸዋል።
ከእነዚህ ወንዞች የሚገኘውን የውሃ አጠቃቀም ማለትም ለመጠጥ ውሃ፣ ለመስኖ፣ ለኢንዱስትሪ እና ለኃይል ማመንጫ እና ለመሳሰሉት በጥንቃቄ የውሃ ሀብትን አስተዳደር እና አጠቃቀምን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድን ተከትለን ከአላስተዳደርን የውሃ እጥረት ሊያስከትል ይችላል። ገፋ ሲሊም የግጭት መንስኤ ሊሆን ይችላል።
ይህንን የጋራ የወንዝ ተፋሰስ በአግባቡ ለመጠቀም እንዲያስችል እና አንዱ በሌላው ላይ ጉልህ የሆነ ጉዳት እንዳያደርስ እና ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ተብሎ ዓለምአቀፍ መመሪያዎችና መርሆዎች ተዘጋጅተዋል።
ከመቶ ዓመት በፊት ጀምሮ በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የትብብር ስምምነቶች ተደርገዋል። በዚሁ መሠረት በዓለም ላይ ከ400 በላይ የሚሆኑ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ሀይቆችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ስምምነቶች በተለያዩ አገሮች መካከል ተደርጓል። ከፍ ሲልም በዓለም አቀፍ ሕግ አጠቃላይ ማዕቀፍ ለመጓጓዣ ላልሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ሃይቆች ለመጠቀም የሚያስችል የተባበሩት መንግሥታት የውሃ ተፋሰስ ስምምነቶች መርህ ተረቆ በግንቦት 21 ቀን 1997 እ.ኤ.አ ተፈርሞ በነሐሴ 17 ቀን 2014 እ.ኤ.አ ወደስራ የተገባበት ሁኔታ አለ።
ከነዚህ ስምምነቶች በተጨማሪ የክልላዊ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች በደቡባዊ አፍሪካ ልማት ማኀበረሰብ “የዉሃ ሀብት ድርሻ የተከለሰ ስምምነት በደቡባዊ አፍሪካ ልማት ማኀበረሰብ በነሐሴ 7 2000 እ.ኤ.አ የተገባ ሲሆን በ መስከረም 22 2003 እ.ኤ.አ ወደ ስራ ተገብቷል እንዲሁም በተጨማሪ የሜኮንግ ወንዝ ተፋሰስን በዘላቂነት ለማልማት የትብብር ስምምነት በሚያዝያ 5 ቀን 1995 እ.ኤ.አ ተፈርሟል። ሌሎችም ለናሙና ያህል ወደ መጨረሻ ተጠቅሰዋል።
እንደሚታወቀው የተባበሩት መንግሥታት በ2030 እ.ኤ.አ የሚተገበር የ15 ዓመት “ዓለማችንን መለወጥ” (Transform our World) በሚል መፈክር የዘላቂ ልማት አጀንዳ ቀርፆና አፅድቆ በመተግበር ላይ ይገኛል። ይኸው የዘላቂ ልማት ግብ ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጋር እንዴት እንደተቆራኘ ከአምስቱ ቁልፍ ክፍሎች ጋር በማያያዝ ከዚህ እንደሚከተለው ይገለፃል።
1- “ህዝብ” – “በተለያየ ይዘትና መጠን የሚገኘውን ድህነትና ርሀብ ለመጨረሻ ጊዜ ከዓለማችን ለማጥፋት” የሚል አጀንዳ ሲሆን ይህም የሚሆነው የሰው ልጅ ፍጡር የሆነ ሁሉ ሙሉ ክብሩን፣ እኩልነቱን እና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን የሚያረጋግጥ የዘላቂ ልማት ቁልፍ ምሰሶ ነው።
እዚህ ጋር ህዝብ ሲባል ከእኛ አግባብ ጋር ሲያያዝ በናይል ተፋሰስ ውስጥ ያለውን ህዝብ ማለት ሲሆን ነገረ ግን በተናጠል ያለውን ህዝብ አንዱ ተጠቃሚ ሌላው የበይ ተመልካች የሚሆንበት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፤ ይህም ኢሞራላዊ፣ እራስወዳድነትነና ያለመተሳሰብን ሁኔታ ያንፀባርቃል። ከዚህ ምሶሶ ጋራ በተያያዘ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እጅግ በጣም ለሰው ልጅ አስፈላጊ ናቸው። ይሄውም ድህነትና ርሀብን ለማስወገድ የሚያስችል፣ ጤናን ለማስጠበቅ፣ የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት፣ ለስራ ፈጠራ፣የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ እርሻን ለማረጋገጥ ስለሚያስችል ነው። ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ፍላጎቶች ለማሟላት የጋራ የሆኑትን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች በትብብርና አጋርነት መልክ ብቻ እና ብቻ ማልማቱ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት በአሸናፊነትና በዘላቂነት የጋራ ተጠቃሚነት
የሚያረጋግጥ ሲሆን ብቻ ነው።
በዓለም ላይ 95 ፐርሰንቱ የእርሻ ሴክተር፣ 30 ፐርሰንቱ የኢንዱስትሪ ሴክተር እና 10 ፐርሰንቱ የአገልግሎት ሴክተር ሥራዎች በሙሉ በውሃ ጥገኝነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። 1.35 ቢሊዮን ሥራዎች (ከዚህ ውስጥ 42 ፐርሰንቱ የዓለም ንቁ የሥራ ሀይል ወጣቶች ናቸው) ሙሉ በ ሙሉ ከውሃ ጥገኝነት በተያያዘ የተፈጠረ ሥራ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ (የተ.መ.እ.ኤ.አ.የ 2016 የውሃ ሪፖርት)። በዓለም ላይ ሦስት አራተኛው ንቁ የሥራ ሀይል ዕድል የተፈጠረው በቀጥታ ከውሃ ጋር ተያያዥነት ባላቸው የሥራ ዓይነቶች ሲሆን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ውሃ ርሃብን ለማጥፋት፣ከድህነት ለመላቀቅ፣ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ ወሳኝና ቁልፍ የተፈጥሮ ሀብት ነው።
በአሁኑ ወቅት ከ 600 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝብ በናይል ወንዝ ላይ ተማምኖ የሚኖር ነው። 11 ሀገራትን ያካተተው የናይል ተፋሰስ ወንዝ የአፍሪካን 10 ፐርሰንት የመሬት ስፋት የያዘ ስሆን በ2050 በተተነበየው የሕዝብ ብዛት ወደ 1 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ለምሳሌ ያህል በገቢ አንፃር ሲታይ 40 ፐርሰንት የሚሆነው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ሕዝብ የሚኖረው በዓለም አቀፍ ከተቀመጠው የድህነት ወለል መለኪያ የቀን ገቢ ከ 1.25 የአሜሪካን ዶላር በታች ነው። በዚህ አንፃር ቡሩንዲ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከሕዝባቸው 81.3 ፐርሰንት እና 87.7 ፐርሰንት፣በተከታታይ እጀግ በጣም ደሀ የሚባሉ ሀገራት ሲሆን በተቃራኒው ግብፅ ግን ዝቅተኛው የነፍስ ወከፍ የቀን ገቢ 1.5 የአሜሪካን ዶላር በላይ ሲሆን ይኸውም ከአጠቃላይ ሕዝቡ 1.7 ፐርሰንት ነው ፤ ከዚህ አንፃር የኢትዮጰያ 37 ፐርሰንት ነው።
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ 110 ሚሊዮን ሲሆን እ.ኤ.አ በ2050 የተተነበየው ወደ 180 ሚሊዮን ያደርሰዋል ይህም ከ 11 ዱ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል። ከዚህ ውስጥ ወደ 40 ፐርሰንቱ ወይም 44 ሚሊዮን ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ እና ከ 72 ሚሊዮን በላይ እ.ኤ.አ በ2050 ሕዝብ በጥቁር አባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ ይሆናል። ታዲያ የዚህ ሁሉ ህዝብ የወደፊት እጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት አስቸጋሪ የሚሆን አይመስለንም። በተደጋጋሚ የሚነሳው ጉዳይ ኢትዮጵያ ብዙ የወንዝ ተፋሰሶች አሏት ለምን እነሱን አታለማም የሚባል አስተያየት ከግብፅ ወገን ብዙ ጊዜ ይነሳል። በአጭሩ ከላይ የተገለፀውን ህዝብ ወደ ሌላ ተፋሰስ ማሸጋገር ነው ወይስ ተፋሰሶቹን ከአንዱ ወደ ሌላው ማሸጋገር (Basin Transfer) ማለት ይሆን?
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት 83 ፐርሰንት የሚሆነው የኢትዮጰያ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ በሆነ መሠረታዊ በሆነ አኗኗር ሁኔታ፣ በጤና እና በትምህርት በመሳሰሉት በድህነት የምትማቅቅ ሀገረ ናት (Human Development Report, 2019) ከዚህ ጋር በተያያዘ ከ 10 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በየዓመቱ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚደረግለት ሲሆን ይኸውም ከድርቅ ጋር በተያያዘ መልኩ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ ላቅ ያለ ርሀብ፣ሞት እና ሕዝብን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የማስፈር ሁኔታዎች የተከሰቱበት ሲሆን የኢትዮጰያ ሕዝብ እና መንግሥት ይህን ሁኔታ ትዝታ ማድረግ ይኖርበታል ።
2- “መሬት”:- “”በመሬታችን ላይ አሁን ለሚገኘውና ወደፊት ለሚመጣው ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት እንዲያስችለን መሬታችንን ከመራቆት መከላከልና ይህንንም እርግጠኛ የሚሆነው ዘላቂ ፍጆታ እና ምርታማነትን ስናረጋግጥ እና የተፈጥሮ ሀብትን በዘላቂነት ማስተዳደር፣ ለአየር ንብረት ለውጥ አስቸኳይ እርምጃዎችን መውሰድ እንዲያስችል ሲደረግ መሆኑ ተወስኗል።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ቀጥተኛ የሆነ ከስነ – ምህዳራችን
ጋር ተያያዥነት አላቸው። ዘላቂ እና በፍጥነት ሊያገግም የሚችል ምህዳር እንዲኖር ማድረግ የሚቻለው የተቀናጀና መልካም የውሃ ሀብት አስተዳደር ሲኖረን ብቻ ነው።
መሬታችን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለሚኖሩባት ሕዝቦች አገልግሎቷን እንዳትሰጥ ከሚፈታተኗት አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ ነው። ዝቅተኛና ያልተመጣጠነ ዝናብ የሚያስከትለው ተደጋጋሚ ድርቅ ምክንያት ስብሎች የሚጨነግፉበት፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የአፈር መሸርሸርና የመሬት መራቆት፣ የጎርፍ አደጋ የመሳሰሉት የሚያደርስበት ዋናው ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች ናቸው።
ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን ችግር ብሎም በግድቦች ላይ ሊከሰት የሚችለውን የአፈር ደለል ለመግታት በራስጌ አካባቢ የተፋሰስ ልማት አስተዳደርንና ስነ – ምኀዳር አጠባበቅን መተግበር ያስፈልጋል። ይሄውም ሊተገበር የሚችለው ደን በመትከል፣ የእርከን ስራ በመስራት፣ ባጠቃላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የመሳሰሉትን በትብብር መስራት ሲሆን፤ ከግጭት እና ዛቻ ይልቅ አማራጭ የሚሆነው የታችኞቹ አገሮች ለዚህ ስራ ትብብር ማድረግና በንቁ መሳተፍ ሲችሉ ነው። ይህን የተፋሰስ ልማት ተግባራዊ በማድረግ የዝናብ ብሎም የወንዞችን ፍሰት መጠን በመጨመር የውሃ ድርሻ መጠንን በማረጋገጥ ግጭትን በማስወገድ የትብብርና የመተማመን መንፈስን ማጎልበት ይቻላል። ዝናብ ዘንቦ ውሃ በወንዙ ካልፈሰሰ ማንን መክሰስ ይቻል ይሆን!
3- “ብልፅግና”:- “ከተፈጥሮ ጋር በተስማማ መልኩ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በቴክኖሎጂ እድገቶች እንዲኖር ሁሉም የሰው ልጆች ብልፅግናን እንዲያጣጥሙ እና ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን እንዲያሟሉ ለማረጋገጥና ለማስቻል ተወስኗል።”
የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በጋራ ማልማት ለሀገራት ብልፅግና ቁልፍ ሚና ያለው ሲሆን በምንጭም ሆነ በወንዝ መልክ ውሃ ባለበት ቦታ ሁሉ ለሀገር ስልጣኔ መስፋፋት፣ለልማት፣ ለሥራ ፈጠራና ለጤና ጥቅም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ምንም አጠያያቂ አይደለም። ወደድንም ጠላንም ወደፊት ከነዳጅ በበለጠ ሁኔታ ውሃ ከፍተኛ የልማትና እድገት ዋና ወሳኝ የተፈጥሮ ሀብት ስለሆነ የውሃ ክፍፍል ድርድር ላይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ስለዚህ የጋራ የሆነ ሀብትን በጋራ ጥቅም ላይ መሠረት አድርጎ መልማት ከአልቻለ እና በአንድ ወገን ብቻ ከሆነ የዘላቂ ልማት ላይ የተቀመጠው “ብልፅግና“ ግብ እውን ማድርግ አይችልም።
ከዚህ እርዕስ ጋር ብናያይዝው፤ የግብፅ ዓመታዊ አጠቃላይ የነፍስ ወከፍ ገቢ 3‚000 የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ከ 10ው የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ሲነፃፀር ከ 0.5 እስከ 10 እጥፍ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ይልቃል ነገር ግን የኢትዮጵያ ወደ 1‚000 የአሜሪካን ዶላር ነው። ይህ ማለት ግብፅ በ 3 እጥፍ ብልጫ ኢትዮጵያን ትበልጣለች ማለት ሲሆን በብልፅግናው አኳያ ፍሕታዊ ባልሆነበት ሁኔታ ወንዛችንን ለማልማት ከፍተኛ ተፅእኖ እየተደረገብን ይገኛል።
በዓለም ከሚወጡ ሪፖርቶች መግቢያቸው ላይ “ኢትዮጵያ ከዓለም ደሃዋ ሀገር ናት” እየተባለ ነው። ስለዚህ ይህን መጥፎ ገፅታ ለመቀየር መንግሥት እቅድ አቅዶ ይህን መጥፎ ስም ለመቀየርና “ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና ወደ መካከለኛ ገቢ ትራንስፎርም” ያደረገች ተብሎ በዓለም ሪፖርቶች ላይ ለማስቀየርና ሕዝቡን ከለየለት ድህነት ለማውጣት የታላቁ ህዳሴን ግድብን ለመተግበር እየተጋች ትገኛለች። ይህንኑ እየፈጠነ ያለውን ሂደት የማራቶን ለማድረግ የተለያዩ ሴራዎች እየተደረገባት ይገኛል።
ለምሳሌ ያህል ግብፅ በመስኖ ልታለማው ከምትችለው 4.42 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 3.6 ሚሊዮን ሄክታሩን (81.4%) በላይ የሚሆነውን አልምታለች። ግብፅ በረሃማውን ጠፍ መሬት እና በመስኖ ለማልማት ያቀደቻቸውን ከቀጠለች ተጨማሪ ከ 9 ቢሊዮን ኪዪቢክ ሜትር የውሃ ፍላጎት በዓመት
ያስፈልጋታል (የምግብና እርሻ ድርጀት 2005 ሪፖርት)። ጥያቄው ይህ ተጨማሪ የውሃ መጠን ከየት የሚመጣ ነው? ሌሎች የውሃ መገኛ አማራጮችን የምታይ ከሆነ እሰየው ነገር ግን በፍትሐዊነት ያልተከፋፈለውን የናይል ውሃ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጋ ከሆነ ጥያቄ በከባዱ ይሰመርበታል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከሦስቱ ለናይል ከሚያበረክቱት ተፋሰስ ወንዞች ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ ልማት ሊለማ የሚችለው መሬት ውስጥ (58 % ከሀገሪቷ አጠቃላይ የመስኖ እምቅ አቅም የሚሸፍን ያም ወደ 5.7 ሚሊዮን ሄክታር – አውላቸው እና አያና 2003 ሪፖርት)፣ ከ 20‚000 ሄክታር በላይ በመስኖ አላለማችም። በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመስኖ የለማው መሬት ከ 6 – 7 % አይበልጥም። ኢትዮጵያ በዝናብ ከሚገኝ ውሃ ጥገኛ ሆና በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እያመረተች እንዴት ህዝቧን መመገብ እንደማትችል የታችኞቹ ሀገሮች ሊረዱ አቃታቸው?
በኃይል ማመንጨቱ አኳያ ስንመለከት፤ ግብፅ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ዘዴዎች በመጠቀም 45‚000 ሜጋ ዋት ኃይል እያመነጨች ለሕዝቧ 100% ኤሌክትሪክ ተደራሽ አድርጋለች። ከ 45‚000 ሜጋ ዋት ውስጥ 2‚100 ሜጋ ዋቱ ከ አስዋን ግድብ የሚመነጨ ነው። የኢትዮጵያ ያየን እንደሆነ ከተለያዩ የኃይል ማመንጫ ዘዴዎች በመጠቀም 4‚400 ሜጋ ዋት ብቻ እያመረተች ሲሆን የአንበሳው ድርሻ የሚወስደው ከውሃ ኃይል የሚመረተው ነዉ። በዚህም ስሌት የኤሌክትሪክ ተደራሽ የሆነው ሕዝብ ከ 44% አይበልጥም። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ግብፅ በ10 እጥፍ በኃይል ማመንጨት ከኢትዮጵያ ልዕቃ ትገኛለች። በተለይ ከ 80% የሚበልጠው የገጠር ሕዝብ የኢነርጂ ምንጩ ማገዶ በመሆኑ በጭስና በኩራዝ ህይወቱን እየገፋ ይገኛል። ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን ሲጠናቀቅ አሁን ያለውን የኃይል ማመንጨት አቅም ወደ 115% ያሳድገዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን አጠናቀን የኢኮኖሚ እድገታችንን ማረጋገጥና 190 አገሮች ሊተገብሩት የፈረሙትን የዘላቂ ልማት ግብን እውን ለማድረግ ይረዳታል። የዚህ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገሮችም የኃይል እጥረቶቻቸውን በእጅጉ የሚቀርፍ ሲሆን ለኢትዮጵያም የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያስገኝላታል።
ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገሮች በትብብር መንፈስ በመስራት ችግሮቻቸውን ፈተው ከድህነት ወጥተው ብልፅግናን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጀትም ለዚህ ተፈፃሚነት የበኩሉን ማድረግ ይጠበቅበታል።
ዘላቂ ልማት ግቦች ላይ እንደተቀመጠው መፈክር የሰው ልጅ የሆኑ ሁሉ ብልፅግናን እንዲያዳብሩ እና ሕይወታቸውን፣ ኢኮኖሚያቸውን፣ ማህበራዊና ቴክኖሎጂን ከተፈጥሮ ጋር በተጣጣመ መልኩ ማሳደግ እንዳለባቸው ይገልጻል። ከላይ በተቀመጠው ማነፃፀሪያነት መሠረት በማድረግ የትኛው ሀገር ነው ብልፅግና በተነፃፃሪነት ዓለምን እየቀጨ ያለው ኢትዮጵያ ወይስ ግብፅ ? ይህን ሚዛናዊ ያልሆነ የእድገት ልዩነት አንባቢያን ሊፈርዱት ይችላሉ።
4- “ሠላም”:— “ከፍራቻና ከግጭት የፀዳ፣ ሠላምን የማስፋፋት ተገቢና ሁሉን ማኅበረሰብ ያቀፈ እንዲሆን ስንወስን፤ ያለሠላም ዘላቂ ልማት እንደማይኖር — ያለ ዘላቂ ልማትም ሠላም የለም በሚል መሪ ሀሳብ ተወስኗል።”
ሠላምን ቀለል አድርጎ ማየት አግባብ አይደለም። በዓለም ላይ ሰላምን አጥተው የሚኖሩ ህዝቦች ከሌላው በላቀ ሁኔታ የሠላም አስፈላጊነት ይገነዘቡታል፤ ለምሳሌ ያህል የሶሪያ፣ የየመን፣ የሊቢያ ግጭቶች የመሳሰሉት ጥሩ ማሳያ ናቸው። ሀገሮች ወደ ግጭት ቢገቡ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፤ በግጭት የሚወድመው ዝንተዓለም የተገነባውን
መሠረተ ልማት ማውደም፣ ህዝቦችን ማፈናቀል፣ መሠረታዊ የሆኑ የምግብና የመጠጥ ውሃን ማሳጣት፣ ከማንም በላይ ህፃናትና እናቶች የመጀመሪያ ተጠቂ እንዲሆኑ ማድረግ ሲሆን ከሁሉም በላይ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት እንደ ቅጠል እንዲረግፍ ከማድረግ ውጪ። ስለዚህ መንግስታት ወደ ግጭት ለመግባት ከመወሰን በፊት ቆም ብለው በእርጋታና በጥሞና ችግሮቻቸውን ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። አደራዳሪዎች ወይም አሸማጋዮች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሁሉንም ተደራዳሪዎች አሸናፊ ባደረገ መልኩ ኃላፊነታቸውን በቅንነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሠላም አምጪ እና የአጋርነት ኃይል መሆን ሲገባው ያለመታደል ሆኖ የግጭት መነሻ እየሆነ ያለበት ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል። ሌሎች ሀገሮች በትብብር እየተጠቀሙ ይገኛሉ፤ የሆነ ሆኖ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ ውሃን ለእኔ ብቻ ልጠቀም በሚል ፉክክር ውጥረት ውስጥ የገቡ ሀገራት በጣም ጥቂት ናቸው። ነገር ግን አባይ ወንዝ ለምን የግጭት መንስሔ ሆነ ? የውሃ ሀብት አስተዳደር በተለይ ድንበር ተሻጋሪ ሲሆኑ ቁልፍ የትብብር ግፊት መሆን ይገባዋል። ስለዚህ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሠላምን ለማጎልበትና ለዘላቂ ልማት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ማንኛውም አካል ሊያጤነው ይገባል። ግጭት የሰው ልጅን ሕይወትና ሀብት ስለሚያወድም ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ግጭት መፍጠር በምንም ዓይነት መልኩ አሸናፊ በመሆን ሠላምን ማስገኘት አይችልም ይልቅስ ሠላምን ለመገንባት አስፈላጊዉን ክፍያ መክፈል አስማምቶና በትብብር መሥራቱ ለግጭት ከሚከፈለዉ የበለጠ ጥሩ መሆኑን መንግሥታት መረዳት ይጠበቅባቸዋል። “ትዳር በእልህ አይገነባም” እንደሚባለው ሁሉ የጋራ ሀብትም በእልህ ለእኔ ብቻ በማለት መጠቀም አይቻልም።
አንዳንድ ግብፃዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራኖች ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሆን ብለው የተሳሳተ መረጃና መጥፎ ስሜት ቀስቃሻ ሁኔታዎችን እየነዙ የሕዝብን አዕምሮና ልብ ለመግዛት በተለያየ የመረጃ ማሰራጫ መንገድ እያደረጉ ውዥንብር እየነዙ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ የግብፅ መንግሥትም ከኢትዮጵያ የሚፈሰውን የአባይ ውሃ በብቸኝነት ለመጠቀምና የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል የዲፕሎማሲ ሥራዋን ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፤ ከአሜሪካ እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወዲያ ወዲህ እየባዘነች ትገኛለች።
በእርግጠኝነት ሠላምን መገንባት የሚቻለዉ የግብፅ መንግሥት ትክክለኛውን የአባይ መነሻ ከኢትዮጵያ እንደሆነ እሱም የጋራ ሀብት እንደሆነና ለጋራ ጥቅም አብሮ መስራት ለሕዝባቸው በግልፅ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል ከዚያም ያለመግባባትን ለመፍታት ከተፋሰሱ አባል ሀገራት ጋር በትብብር በመሥራት የአህጉሩን ችግር በአህጉሩ የመፈታት መዕርህ መሰረት በመጠቀም በዘላቂነት ሠላምን ለማምጣት የሚቻለው በዚህ አማራጭ ብቻ መሆኑን ተረድተው ለስኬቱ መንገዱን መጥረግ አስፈላጊ ነው።
1- አጋርነት”:— “ሁሉንም ሀገራት ያሳተፈ፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትና ሁሉንም ህዝብ ያካተተ በተለይም የደሃዎችንና የደካማዎችን ፍላጎት ማሟላት ላይ ትኩረት ያደረገ የ2030 አጀንዳን ዓለም አቀፍ ትብብርን ለዘላቂ ልማት ለማስፍን የሚያስችል ማንኛዉንም አስፈላጊ ዘዴዎችን በመጠቀም ለመተግበር ተወስኗል።”
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች በተለይም አባይ በአጋርነት መርሆ መሠረት ሊሰራ ሲገባው ለእኔ ብቻ በሚል አሰተሳሰብ እየተራመደበት ከሆን ይህ የዘላቂ ልማት ግብ ለምን የሁሉም ሀገራት አጀንዳ ሆኖ ተቀረፆ ወደ ትግበራ ተገባ የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል። ብዙ ሀገራት የጋራ የሆነውን ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብት ለመጠቀም ውስብስብ ችግሮቻቸውን በትብብር በመፍታት በጋራ ለማልማት እየሰሩ ይገኛሉ፤ እነሱ ልዮነታቸውን የፈቱበትን መንገድ በመከተል የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ተግብረው ወደ ትብብርና አጋርነት መምጣት ያልተቻለው ለምንድ ነው? የዓለም ማኅበረሰብስ ይህን እውነታ ተረድተው የተፋሰሱ ሀገራት ወደ አጋርነት መንፈስ እንዲቀበሉ ግፊት የማያደርጉት ለምንድነው? ገለልተኛ መስሎ ከርቀት መመልከት ዳፋው ለእነሱም እንደሚደርስ ተረድተው ሀሳባቸውን ቢሰነዝሩ መልካም ይሆናል።
ግብፆቹ ለምንድነው እ ኤ አ የ 1929 እና 1959 የቅኝ ግዛት ውሎች የተፈፀመውን የአባይን ውሃ መጠን ግብፅና ሱዳን በብቸኝነት የመካፈል አባዜን የሙጥኝ ያለችው? ያውም የወንዙ መነሻ የሆነችውን ኢትዮጵያ ባልፈረመችውና
የውሃ ድርሻዋን ባልተካፈለችበት ሁኔታ!፤ ከሀገሯ ለሚመነጨው ውሃ ተካፋይ ሳትሆን የበይ ተመልካች ሁኚ ማለት ስግብግብነትና የእኔነት መንፈስ የሚያንፀባርቅ እንጂ የአጋርነትና ትብብር መንፈስ በጭራሽ የሌለው በመሆኑ በምንም መዕርህ ተቀባይነት የለውም። ይልቅስ ለዚህ መፍትሔው የዛሬ 10 ዓመት አካባቢ የተዘጋጀውን የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ (Nile Basin Cooperative Framework – CFT) እና የትብብር መግለጫ መርህን (Deceleration of Principle) በ 2015 እ. ኤ. አ. በ3 ቱ የምሥራቅ አባይ ተፋሰስ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሞላልና አለቃቀቅ የተፈረመውን ባልተሸረሸረና ባልተዛባ ሁኔታ ሲተገበር ብቻ ነው።
ከተፋሰሱ የራስጌ የሚገኘው የውሃ መጠን ላይ ብቻ የሙጥኝ ከማለትና ከመፋጠጥ ይልቅ ሌሎች የውሃ መገኛ አማራጮችንም ማየቱ ለግብፆቹ አስፈላጊና እስትራተጂካዊ መሆን ይገባዋል። ስለዚህ እነዚህን አማራጮች ግብፆች የመደራደሪያ ሁኔታዎች መሆናቸውንና ድርድር ውስጥ ለማካተት ሲቻል፤ ፍትሐዊነትንና ምክንያታዊነት የውሃ አከፋፈልን፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ አጋርነትነና ትብብርን ማረጋገጥ ያስችላል።
ግብፅ ከሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገሮች በአንፃራዊነት ያደገች ሀገር ናት አቅሙም ሀብቱም እውቀቱም ያላት ሀገር ስለሆነች አባይ ወንዝ ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ሌሎች የውሃ መገኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የውሃ ፍላጎቷን ብታለማ ቅንነት ካለ ማሟላት ትችላለች። ግብፅ የአንድ ምእተዓመት የሚሆን የውሃ ፍላጎቷ የምታሟላበትን እስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች ትገኛለች። ኢትዮጵያስ?
ኢታይፑ የሃይድሮ ፓወር ልማት የአጋርነት እና የትብብር ማሳያ ፕሮጄክት ምሳሌ
እ.ኤ.አ. 1973 ብራዚል እና ፓራጓይ ፓናማ ወንዝ ላይ የኢታይፑ ሃይድሮ ፓወር ፕሮጄክት ለመገንባት ስምምነት አድርገዋል። ይህ ፕሮጄክት 12‚600 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት አቅም ሲኖረዉ የታላቁ ህዳሴ ከሚያመነጨው ሁለት እጥፍ ነው። የዚህ ፕሮጄክት ግንባታ 16 ዓመት ፈጀቷል (እ.ኤ.አ. 1975 – 1991)። ይህ ስምምነት የታችኛዋን ሀገር አርጀንቲናን ያላካተተ ነበር። ነገር ግን በኋላ ላይ በኦክቶበር 19‚ 1979 ለውሃ ላይ መጓጓዧ ፍላጎት ላይ መሠረት ያደረገ የሶስትዮሽ ስምምነት በብራዚል፣ ፓራጓይ እና አርጀንቲና ተፈረመ።
ይህ የትብብርና አጋርነት ስምምነት እጀግ አስደናቂ በጣም አስቸጋሪ እና እንቅፋት ለሆነው የናይል ጉዳይ ምሣሌ ሊሆንና ችግርን ለመወጣት የሚያስችል የፖለቲካ ፍቃደኝነት የታየበት፣ በቂ የሆነ ድርድር ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ የተቀመጠለት ብሎም ቴክኒካዊና አሰተዳደራዊ መፍትሔ ያገኘ እና የጋራ የኢኮኖሚ ትስስር ያጎናፀፈ በመሆኑ ይህን ተሞክሮ በመውሰድና በመተግበር የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብርና የአጋርነትን ስምምነት በማድረግ የጋራ የሆነውን የውሃ ሀብት በጋራ የመጠቀም ጠንካራ መተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር ያስችላቸዋል።
ዓለም አቀፍ የተመረጡ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ትብብርና ስምምነቶች
ይህን ጉዳይ ለማንሳት የተፈለገበት ምክንያት በዓለም ላይ ብዙ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የትብብር ስምምነቶች ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሀገሮች ተፈፅሟል። ታዲያ የዓባያችን ጉዳይ ብቻ ራስ ምታት ሆነን የሚለውን ለመረዳትና እነዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ስምምነቶች በምን መልኩ ቢፈፅሙ ነው ሀገሮች ተስማምተው እየሰሩ ያሉት የሚለውን በአእምሮአችን እንዲመላለስና ወደ ፊት ዝርዝር ሁኔታዎችን ለማንበብ እንዲቻል ይረዳል በሚል ታሳቢነት ነው።
- ሜክሲኮ እና አሜሪካ በ 1889 እ.ኤ.አ ዓለም አቀፍ ድንበር እና የውሃ ኮሚሽን የማቋቋም ስምምነት አድርገዋል። አሜሪካ የራስጌ ሀገር ስትሆን ከግርጌዋ ሜክሲኮ ጋር በምን ዓይነት ስምምነት ላይ ደረሰች የሚለውን ለማየት የስምምነቱ ቁልፍ ነጥብ የሚከተሉት ናቸው፤
- የሁለቱ ሀገሮች የውሃው አጠቃቀም መብት በመጠን የተወሰነ ነው፤
- የተመደበው የውሃ ክፍፍል መጠን ችግር ከገጠመው ኮሚሽኑ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ መፍትሔዎችን ያፈላልጋል።
- ካናዳ እና አሜሪካ በ1909 እ.ኤ.አ ዓለም አቀፍ የጋራ ኮሚሽን አቋቁመው ድንበር ተሻጋሪ ገፀምድርና ከርሰምድር የውሃ ሀብትን ለማልማት ስምምነት አድርገዋል። ካናዳ የራስጌ አሜሪካ የግርጌ ሀገሮች ናቸው።
- የዚህ ስምምነት ፅንሰ ሀሳብ፤
- የድንበር ተሻጋሪ ውሃዎችን በእኩል እና በተመሳሳይ መብት መጠቀም፣
- በሁለቱም ሀገራት በኩል የውሃ ብክለትን መከላከል፣
- የውሃን አጠቃቀም በተመለከተ የሚከተሉትን ቅድም —ተከተል መከተል እንዳለባቸዉ ይደነግጋል፣ ይኸዉም፤ ሀ) ለቤት ውስጥና ለንፅሕና ለ) ለትራንስፖርት ሐ) ለኃይል ማመንጫና መስኖ በማለት ተቀምጧል።
- በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ላይ ከስምምነቱ ውጪ ቢደረግ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የጋራ ኮሚሽን ሁለቱን ሀገራት በመወከል ውሳኔ ይሰጣል።
ጥያቄ የሚሆነው ከላይ የተጠቀሱት ስምምነቶች ከግርጌና ከራስጌ ሲኮን ልዩነት ያለው ሲሆን የአሜሪካን ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ያደላ ይመስላል። እውነት አሜሪካ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የገነባችውን ኡቩር ግድብ ላይ የሚጠራቀመውን የዉሃ አስተዳደር መብት አሳልፋ ለሜክሲኮ ትሰጣለችን? ካልሆነ ለምን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ከፍተኛ የሆነ ግፊት እና ፈጣን የሆነ ስምምነት በማዘጋጀት ወደ ስምምነት እንዲገባ ለምን ፈለገች?
1- በማሊ፣ሞሪታኒያ፣ ሴኔጋል፣ ጊኒ እና ጊኒ ቢሳዋ መካከል የሴኔጋል ወንዝ ልማት ድርጅት በሚል በ 1972 እ.ኤ.አ. የተደረገ ስምምነት ነው። በወንዙ አጠቃቀም ላይ ያለመግባባት ቢፈጠርና ለችግር መፍቻነት የተቀመጠው ሂደት፤ ሀ) በዕርቅ ወይም በሽምግልና፣ ለ) በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት እና ሐ) በሔግ በሚገኘው የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲሆን ነው። እነዚህ የአፍሪካ ሀገሮች ከላይ የተጠቀሰውን ሂደት ሲከተሉ በተቃራኒው ግብፅ አሜሪካ፣ አረብ ሊግ ብሎም የተባበሩት መንግሥታት መውሰዱ አፍሪካዊያን ማሸማገል አይችሉም ነው ወይስ ከመጋረጃው ጀርባ የታቀደ ጉዳይ አለ?
2- በቤኒን፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ጊኒ፣ አይቮሪኮስት፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ እና ቡርኪናፋሶ መካከል በ 1963 እ.ኤ.አ የኒጀር ወንዝ ኮሚሽንን አቋቁመዋል፣
3- ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ በ 1977 እ.ኤ.አ የካጌራ ወንዝ ተፋሰስ አስተዳደርና ልማት ድርጅት በማለት አቋቁመዋል፣
4- ካምቦዲያ፣ ላዎ. ፒ. ዲ. አር፣ ታይላንድ እና ቬትናም በ 1957 እ.ኤ.አ የታችኛው የሜኮንግ ተፋሰስ ለማልማት ስምምነት አድርገዋል ተከትሎም የተለያዩ ስምምነቶች ተደርገዋል፣
5- ሕንድና ፓኪስታን በ 1960 እ.ኤ.አ ቋሚ ሒንዱስ ኮሚሽን በማቋቋም ስምምነቶች አድርገዋል።
ከላይ ከተጠቀሱት ባሻገር በጣም ብዙ ስምምነቶች ከሁለትና ከዚያ በላይ ቁጥር ያላቸው ሀገራት ስምምነቶች አድርገዋል። የእነዚህ የትብብር ስምምነቶች ይዘትና ዓይነት የተለያየ ቢሆንም የጋራ የሆነውን የውሃ ሀብት ለማልማት የሚያስችሉ ናቸዉ። የእነዚህ ስምምነቶች ውጤቶችና ተሞክሮዎች ለአባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገሮች ሊሰራ አይችልም ወይ? በእርግጥ ከ 10 ዓመት በፊት የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በስድስት ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ብሩንዲ የፈረሙት ሲሆን ከእነዚህ ዉስጥ አራት ሀገራት ማለትም ኢትዮጰያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ በፓርላማዎቻቸዉ አፀድቀው ሌሎችን ሀገራት እየተጠባበቁ ይገኛሉ። የግርጌ ሀገሮች ግብፅና ሱዳን ይህን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንዳልፈረሙ ይታወቃል።
ማጠቃለያ
የድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ተፋሰስ ትብብር የዘላቂ ልማት ግቦችን ለመተግበር በጣም አስፈላጊ እና ከተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ጋር እውነተኛና ቀጥተኛ ዝምድና ያለው ሲሆን የባለድርሻ አካላት ለትግበራው ያላሰለስ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በመተማመን ላይ የተመሠረተ ትብብር በናይል ተፋሰስ ሀገራት እንዲኖር በታችኞቹ ሀገራት ጎልቶ የሚወራውን “ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ”፣”የውሃ ደህንነት” እና ”ታሪካዊ መብት” የሚለውን ጊዜው ያለፈበትን አባባል በመተው ”ፍትሐዊነትና ምክንያታዊነት” በሚለው ዓለም አቀፍ መርህን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀው የናይል ተፋሰስ አጠቃላይ የስምምነት ማዕቀፍ (CFA) በሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት መፈረምና የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን በማቋቋም ለዘላቂ ሠላም መተባበር ሲቻል ነው። በተጨማሪም ስለ ታላቁ ህዳሴ የውሃ ሙሌት በተመለከተ የታችኞቹ ሀገራት ግድቡ በታቀደለት ጊዜ እንዳይሞላ ከማንገራገር ይልቅ ሳይንሳዊና ቴክኒካል በመሆኑ መንገድ በዙሪያ ጠረጴዛ በመነጋገርና የመግለጫ መርህውን (DOP) በተቀመጠው አካሄድ በመከተል ብቻ ወደ ትብብርነትና አጋርነት መንፈስ መተግበር ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ በምንም ዓይነት መልኩ የታችኞቹን ሀገሮች የመጉዳት ዓላማ የላትም፤ ህዝቧም ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበትና ሰብአዊነት የሚሰማው አብሮ የመብላት ባህል
ያለው ነው። ነገር ግን ከሯሷ ሀገር የሚፈልቀውን የውሃ ሀብት የመጠቀም መብት አላት ስለዚህ ይህ የተፈጠሮ ሀብቷን የታችኞቹን ሀገራት ጉልህ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ በማልማት ህዝቧን ከከፋዉ ድህነት በማውጣት ወደ ብልፅግና ጉዞዋን ታሳልጥበታለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣የአፍሪካ ህብረት፣የአውሮፓ ህብረት እና ለፍትሕና ለእውነት የሚተጉ የዓለም ማኅበረሰብ ጉዳዩን በማጤን የድንበር ተሻጋሪ የሆኑትን የናይል ወንዝ በፍታሐዊነትና በምክንያታዊነት ለመጠቀም እንዲቻልና ከእሱ ጋር ተያያዥ የሆኑትን የዘላቂ ልማት ግቦችን ትብብርንና አጋርነት ለማስፈጸም የራሳቸውን ያልተቆጠበ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል።
ሁሉም የናይል ተፋፋሰስ ሀገሮች ከላይ የተዘረዘሩትን የተለያዩ የትብብርና የአጋርነት ስምምነቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መልካም የሆኑትን እንደ አርአያ በመውሰድ መተማመን ላይ በተመሰረት የጋራ ራዕይና የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር የክልሉ ዘላቂ ስላምን ማስፈን ይኖርባቸዋል።
በአሁኑ ጊዜ የዓለም እራስምታት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኮረት በማድረግ ሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ይህን ተፅዕኖ ለመቀነስ እንዲያስችል የእራስጌ ሀገሮች ላይ የተፋሰስ ልማትና የስነ – ምዕዳር አጠባበቅ ላይ በትብብርና በአጋርነት ቢሰራ ውጤታማ ከመሆኑም ባሻገር የሚያነዛንዘውን የውሃ መጠን ይገባኛል ጥያቄ ጥሩ መፍትሄ ይሆናል።
አንባቢያን እላይ በተለያየ መለኪያ የተገለጸውን የኢትዮጰያና ግብፅ ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብቷን አልምታ መቼ ነው ሕዝቧን ከድህነት የምታላቅቀው? ይህን የጥቁር አባይ ውሃ ለኃይል ማመንጫ ያውም የውሃ ፍጆታ በሌለዉ (Non – consumptive) መልኩ መጠቀሟ እንደ ሀጢያት ተቆጥሮባት ፍዳዋን የምታየው። ማንም ህሊና ያለው በቅንጭብ የቀረበውን እውነታ አንብቦ የራሱን ግምት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስቀመጥ ይችላል።
ክፍል — ፪
አማራጭ የውሃ መገኛዎች ለግብፅ – በወፍ ምልከታ
ግብፅ የውሃ መገኘትና አስተማማኝነቱን ለማረጋገጥ ከናይል ከምታገኘው የወደፊት የውሃ ክፍፍል መጠን በተጨማሪ ሌሎች የተለያዩ የውሃ መገኛ አማራጮችና ማተለቂያ እንዳሏት የተለያዩ ጥናቶች ያመለከታሉ። እነሱም በተወሰነ መልኩ መጠቀም የጀመሩበት ሁኔታ አለ ነገርግን በሙሉ አቅማቸው መጠቀም እንደሚኖርባቸው ይህ ፅሑፍ እንደሚከተለው ያስረዳል።
የከርሰምድር ውሃንማልማት(GroundwaterResourcesDevelopment)
ግብፅ ከፍተኛ የሆነ የከርሰምድር ውሃ ክምችት አላት። አስዋን ግድብ ወደ 160 ቢሊዮን ኩዪቢክ ሜትር የመያዝ አቅም አለው ይህም ናስር ሰው ሰራሽ ሀይቅ ተብሎ ይጠራል። ከዚህ ሀይቅ በስርገት ወደ መሬት ውስጥ ይገባል በተጨማሪ ከውሃ ቦይ መሄጃም እንዲሁ በስርገት የከርሰምድር ውሃ ሆኖ በብዛት ተጠራቅሞ ይገኛል። እንዲሁ በተጨማሪ በሲናይ በምዕራብ ግብፅ በረሃዎች ከፍተኛ ክምችት ይገኛል። ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ኑቢያን ሳንድስቶን (Nubian Sandstone Aquifer) የሚባለዉ የከርሰምድር ውሃ ክምችት መገኛ ሲሆን ይህ ብቻ ወደ 200‚000 ቢሊዮን ኩዪቢክ ሜትር እንደሚሆን ይገመታል። ከናይል ሸለቆና ዴልታ በአጠቃላይ እስከ 500 ቢሊዮን ኩዪቢክ ሜትር የከርሰምድር ውሃ ክምችት ይኖራል። በአጠቃላይ ግብፅ ለአንድ ሺህ ዓመት በላይ የሚበቃ 200‚ 500 ቢሊዮን ኩዪቢክ ሜትር የሆነ ከፍተኛ መጠን የከርሰምድር ውሃ ክምችት አላት። ታዲያ ጥያቄዉ ይህ የዉሃ መጠን ጥቅም ላይ የሚውለው መቼ ይሆን? ስለዚህ ይህ አንዱ የውሃ መገኛ ስለሆነ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባትና ግብፅ ከኢትዮጰያ የሚፈሰው ላይ ብቻ የሙጥኝ ከማለት ይልቅ ይህን የከርሰምድር ውሃ ማልማት ይጠበቅባታል።
1- የውሃ ፍጆታ አጠቃቀምን በአግባቡ ማስተዳደር (Implementation of Water Demand Management)
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ግብፅ የናይል ውሃ ሃላፊነት ባልተሞላዉ ሁኔታ፣ ቆጣቢ ባልሆነ ዘዴ እና አባካኝ በሆነ መንገድ ዉድ የሆነዉን ንፁሕ ዉሃ የተለያዩ ጥቅሞች ለመጠጥ ውሃ ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለኢንዱስትሪዎች ለመሳሰሉት እያባከኑ ይገኛሉ። የብክነቱ መጠን ከዚህ እንደሚከተለዉ ይገለፃል።
- መጠጥ ውሃ:— የግብፅ መንግሥት የናይል ውሃን እያጣራ ለህዝቡ በዝቅተኛ ክፍያ ያድላል። ይህ በዝቅተኛ ክፍያ የሚታደል ውሃም በአብዛኛው ክፍያ አይፈፀምበትም። በዚህ ምክንያት የውሃ አጠቃቀሙ ከፍተኛ በመሆኑ ለብክነት የተጋለጠ ነው። የግብፅ ህዝብ የነፍስ ወከፍ የውሀ ፍጆታ 200 ሊትር በሰው በቀን ሲሆን ይህ መጠንም ከአዉሮፓ ሀገራት የውሀ ፍጆታ የላቀ ነዉ። በዚህ ስሌት ዓመታዊ የነዋሪዎች የውሃ ፍጆታ ከ 5.5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በላይ ይሆናል። 80 ፐርሰንቱ ውሃ ወደ ፍሳሽነት የሚቀየር እንደሆነ ይገመታል በተጨማሪም የውሃ ብክነቱም ከ 35% በላይ ነው። የኢትዮጵያን ያየን እንደሆን በአማካኝ የውሀ ፍጆታ 40 — 50 ሊትር በሰው በቀን አይበልጥም ይኸውም በፈረቃና በተቆራረጠ መልኩ ነው። ስለዚህ ይህ የሚባክን ውሃ በአግባቡ ለመጠቀም እንዲያስችል የግብፅ መንግሥት ፖሊሲውን በመከለስ የውሃ ፍጆታ አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ የውሃ ቁጠባ እንዲለማመድ ማድረግ ይኖርበታል። በዚህ መልኩ የውሃ መገኛ መጠንን መጨመር ይቻላል።
- የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ማሻሻል:—ግብፅ የናይል ውሃን በመጠቀም የመስኖ ልማት በማልማት የምግብ ዋስትናዋን እና ኢኮኖሚዋን እያሳደገች ትገኛለች። የእርሻ ምርቷ በዋናነት ሩዝ፣አትክልት፣ ሸንኮራ አገዳ፣ስንዴ፣ቦቆሎ እና ጥጥ የመሳሰሉት ናቸው። ኤክስፖርት ያደረገቻቸዉ ፍራፍሬም በእኛ ሀገር ይገኛሉ። እነዚህ ምርቶች የውሃ ፍጆታቸው ከሚጠቀሙት የመስኖ ዘዴ ጋር ተደምሮ ወደ 63 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በዓመት ይሆናል። የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ብቃትም ከ 70% በታች ነዉ። ይህን የውሃ አጠቃቀም ከብክነት ለማዳን የተለያዩ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ይቻላል ለምሳሌ ያህል የጠብታ መስኖ (drip irrigation) እና የመርጨት (sprinkler irrigation) የመሳሰሉትን መተግበር ያስፈልጋል። የመስኖ ውሃ አጠቃቀም አስተዳደር እና የውሃ ቦዮችን እንደገና በመጠጋገን ያለአግባብ የሚባክነውን እስከ 22 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በዓመት የውሃ መጠን ማዳን ይቻላል።
- የኢንዱስትሪ ውሃ አጠቃቀም:—ግብፅ ብዙ ኢንዱስትሪዎች አሉዋት ለምሳሌ የጨርቃጨርቅ፣ የወረቀት፣ የብረት፣ አልሙኒየም፣ ሲሚንቶ፣ የተለያዩ ኬሚካሎች እና የእርሻ ኢንዱስትሪ የመሳሰሉት ሲሆኑ የውሃ ፍላጎታቸውም እስከ 8 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በዓመት ይሆናል። ስለዚህ እንደ አማራጭ የፍሳሽ ውሃን እና ከእርሻ ተረፈ ውሃን በማጣራት ኢንዱስትሪዎች መጠቀም እንዲችሉ በማድረግ የውሃ ፍላጎትን ማሳደግ ይቻላል።
- የፍሳሽ ውሃንና ከእርሻ ተረፈ ውሃን በማከም እንደገና መጠቀም (Reuse of Wastewater and Agricultural drainage water) – እንደሚታወቀው 80 ፐርሰንት የሚሆነው የውሃ ፍጆታ ወደ ፍሳሽ ውሃነት የሚቀየር እንደሚሆን የሚገመትና የሚባክን ነዉ። ስለዚህ ይህን የፍሳሽ ውሃ በማከም ለተለያዩ ጥቅሞች እንደገና መጠቀም ይቻላል። እንዲሁም ከመስኖ እርሻ የሚተርፈውን ውሃ ቀጥታ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ሙሉ በሙሉ ከመልቀቅ የተወሰነውን በማከም እንደገና ለተለያዩ ጥቅሞች ማዋል ይቻላል። ስለዚህ እስከ 10 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜት በዓመት የሚሆነው ከፍሳሽና ከመስኖ ተረፈ ውሃ በማከም እንደገና መጠቀም ይቻላል።
- ወደ ሜዲትራንያን ባህር የሚገባውን የውሃ መጠን መቀነስ – የናይል ወንዝ ውሃ ከዴልታ ድልድይ በኋላ በሁለት ቦይ ተከፍሎ በሮሴታና ደሜታ ቅርንጫፍ አካባቢው ያለውን የእርሻ መሬት በማልማት ወደ ሜዲትራንያን ባህር ይገባል። ይህ ተረፈ ውሃ እስከ 12 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ እንደሚሆን ይገመታል። ይህን ያህል መጠን ውሃ ወደ ባህሩ ከመልቀቅ አብዛኛውን መጠን ለተለያየ ስራ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላልና ሊታሰብበት ይገባል።
- ከአስዋን ግድብ/ ከናስር ሀይቅ የሚተነዉና የሚሰርገውን የውሃ መጠንን መቀነስ – በዓመት ከአስዋን ግድብ/ ከናስር ሀይቅ ከ 10 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ በትነትና በስርገት መልክ ይባክናል። ይህ መጠን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊጨምር ይችላል። ይህን በትነትና በሥርገት መልክ የሚባክን ውሃ መቀነስ የሚቻለው የታላቁ የህዳሴ ግድብን እውን ሲሆን ነው። ይህ የሚሆነው ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል አመንጭቶ የተመጣጠነ ውሃ ሲለቀቅ ነው። ይህን ግብፆቹ ጠንቅቀው ያውቁታል ነገርግን ለምን አልዋጥ እንዳላቸው ለመረዳት ብዙ የድርጊት እይታዎችን ማየት ይቻላል። በተጨማሪም የህዳሴ ግድቡ ወደ ሱዳንና ግብፅ ግድቦች የሚገባዉን የደለል መጠን እጅጉን
ይቀንስላቸዋል ያም ለደለል ማስጠረጊያ የሚያወጡትን ወጪ ይቀንስላቸዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግ ቢያንስ እስከ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውሃ መጠን በተጨማሪ ማግኘት ይቻላል። ስለዚህ አዋጭ የሚሆነው የታችኞቹ ሀገሮች መተማመን ላይ በተመሠረት በትብብር መንፈስ በጋራ መስራት ለሁሉም ሀገራት ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ሲረዱ ነዉ።
§ ቶሽካ ሸለቆ ልማት እና የሠላም ቦይ ፕሮጄክቶች – እነዚህ ሁለት ፕሮጀክቶች ከናይል ተፋሰስ ውጪ ታቅደዉ ብዙ ሕንፃዎችና መሠረተልማት ተሟልቶለት አዲስ የሠፈራ ቦታ የተገነባበት እና ህዝብ ከሌላ ቦታ በማስፈር የመስኖ ልማት ለማልማት ታስበዉ እየተሰሩ ያሉ ናቸዉ። ይህንኑ እውን ለማድረግ 14‚200 ካሬ ኪሎ ሜትር የእርሻ መሬት የተዘጋጀ ሲሆን መሬቱን ምርት ሰጪ እንዲሆን ከአስዋን ግድብ የተጠራቀመውን ለም አፈር በማጓጓዝ ጠፍ መሬትን እንዲታረስ ማስቻል ነው። ይህን ቶሽካ የእርሻ መሬት ለማልማት ከአስዋን ግድብ በዓመት ወደ 5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ በመውሰድ ሲሆን ግብፅ ይህን ስታደርግ ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎቹን የተፋሰስ ሀገሮች አላማከረችም። በመጀመሪያ ምዕራፍ ትላልቅ ፓንፖችን በመትከል እና 320 ኪሎ ሜትር በጣም ሰፊ የውሃ መሄጃ ቦይ በመስራት እና በሁለተኛው ምዕራፍ የውሃ መሄጃ ቦይ እስከ 800 ኪሎ ሜትር በ 2025 እ. ኤ. አ. ለማድረስ የታለመ እና 2.8 ሚሊዮን ሥራ ለመፍጠር፣ ኢንዱስትሪንና ቱሪዝምን ለማስፋፋት የታሰበ ፕሮጀክት ነዉ። ይህ ፕሮጀክት 80 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን አስቡት ከታላቁ እዳሴ 5 ቢሊዮን ዶላር ጋር።
ሌላዉ የሲውዝ ቦይን አቋርጦ በሰሜናዊ ሳይናይ ኤል — ሠላም የውሃ ቦይን በመስራት 2‚605 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የመስኖ እርሻ መሬትን በማዘጋጀት የማስፋፊያ ስራ ታቅዶ እየተሰራ ያለ ነው። ይህ ፕሮጀክት ዓላማዉ የግብፅን የማህበራዊ የሚያረጋጋ (ተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሰፋ ያለ መኖሪያ ቦታን ለማዘጋጀት)፣ እራስን ለማስቻል እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት እንዲያስችል ታልሞ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ነዉ። ይህም ተጨማሪ ውሃ ከናይል ወንዝ የሚፈልግ ነው። የፕሮጀክቱ ወጪ እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። ግብፆቹ እንደፈለጉ የናይል ውሃ ሲጠቀሙ ኢትዮጵያ ግን ፍጆታ የሌለዉን (Non-consumptive) የኃይል ማመንጫ ለማልማት አቅዳ ስትሰራ ከመተባበር ይልቅ በተቃራኒ መሆን ምን የሚሉት ጉዳይ ነዉ።
- የባህር ውሃን አክሞ ጥቅም ላይ ማዋል (Desalinization of Sea Water) – ሌላው መታየት ያለበት አማራጭ የሜዲትራንያንና የቀይ ባህርን ጨዋማ ውሃን በማጣራት ለተለያዩ ጥቅሞች ማዋል ይቻላል። ስለዚህ ግብፆች በቅርባቸው የሚገኘውን ይህን የውሃ ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ጨዋማ ዉሃን የሚያጣራ ቴክኖሎጂ ቀለል ያለ እና እርካሽ እየሆነ ስለሆነ መለማመዱ ቢኖር!
ማጠቃለያና መደምደሚያ
ግብፅ ከራስጌ ያለው የውሃ መጠን ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ከላይ የተገለፁትን የውሃ መገኛ አማራጮች ላይ የበለጠ ትኩረት ብታደርግና አላስፈላጊ የሚባክነውን ከፍተኛ የውሃ መጠን ለማዳን ጠንክራ ብትስራ ተጠቃሚ ትሆናለች ይህንኑ ሀሳብ ለህዝቧ በግልፅ ማሳወቅና እስትራቴጂ ነድፋ መንቀሳቀስ ይጠበቅባታል። ይህን ለመፈፀም ቅንነት፣የፖለቲካ ፍቃደኝነት፣ ፖሊሲ የማሻሻልና የትብብር መንፈስ ማጎልበት ሲቻል ነው።
የላይኞቹ የተፋሰስ ሀገሮች ከላይ የተገለፁት የተለያዩ የውሃ መገኛ አማራጮችን በመረዳትና ተግባራዊ ለማድረግ የታችኞቹን ሀገራት ማሳመን በትብብር መንፈስ ቴክኒካዊ መፍትሄዎች ላይ በመነጋገር የጋራ የሆነዉን የዉሃ ሀብት ለማልማት በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነ ምሁራኖች ከሀገራችን የሚፈሰውን የአባይ ውሃ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባትና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጠቀሜታ ለዓለም ማህበረሰብ በሚገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ማሳወቅ ያስፈልጋል ለምሳሌ ቀጣይነት ያለዉ የዲፕሎማሲ ሥራ፣ የዓለም የውሃ ቀን፣ የዓለም የውሃ ሳምንት እና የተለያዩ ዓመታዊ ከውሃ ጋር ተያያዥነት ካላቸው ስብሰባዎችና ኮንፍረንሶች በባለሙያዎች በመላክ ለዓለም ማኀበረሰብ ማስረዳቱ ሚዛናዊ እይታና አስተሳሰብ እንዲኖር ማድረጉ ላይ አጥብቆ መስራት ያስፈልጋል። ከዚያ በተጨማሪም የሀገር ዉስጥ እዉቀትን ለማሳደግ እንዲያስችል ከአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ ስለ ወንዞቻችን የትምህርት ሥርዓት ዉስጥ መካተት ይኖርበታል
እንዲሁም የዉሃ ሀብት ምርምር ኢንስቲትዩት ቢቋቋም ጥሩ ይሆናል።
- ውሃን እያጣራ ለህዝቡ በዝቅተኛ ክፍያ ያድላል። ይህ በዝቅተኛ ክፍያ የሚታደል ውሃም በአብዛኛው ክፍያ አይፈፀምበትም። በዚህ ምክንያት የውሃ አጠቃቀሙ ከፍተኛ በመሆኑ ለብክነት የተጋለጠ ነው። የግብፅ ህዝብ የነፍስ ወከፍ የውሀ ፍጆታ 200 ሊትር በሰው በቀን ሲሆን ይህ መጠንም ከአዉሮፓ ሀገራት የውሀ ፍጆታ የላቀ ነዉ። በዚህ ስሌት ዓመታዊ የነዋሪዎች የውሃ ፍጆታ ከ 5.5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በላይ ይሆናል። 80 ፐርሰንቱ ውሃ ወደ ፍሳሽነት የሚቀየር እንደሆነ ይገመታል በተጨማሪም የውሃ ብክነቱም ከ 35% በላይ ነው። የኢትዮጵያን ያየን እንደሆን በአማካኝ የውሀ ፍጆታ 40 — 50 ሊትር በሰው በቀን አይበልጥም ይኸውም በፈረቃና በተቆራረጠ መልኩ ነው። ስለዚህ ይህ የሚባክን ውሃ በአግባቡ ለመጠቀም እንዲያስችል የግብፅ መንግሥት ፖሊሲውን በመከለስ የውሃ ፍጆታ አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ የውሃ ቁጠባ እንዲለማመድ ማድረግ ይኖርበታል። በዚህ መልኩ የውሃ መገኛ መጠንን መጨመር ይቻላል።
- የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ማሻሻል:—ግብፅ የናይል ውሃን በመጠቀም የመስኖ ልማት በማልማት የምግብ ዋስትናዋን እና ኢኮኖሚዋን እያሳደገች ትገኛለች። የእርሻ ምርቷ በዋናነት ሩዝ፣አትክልት፣ ሸንኮራ አገዳ፣ስንዴ፣ቦቆሎ እና ጥጥ የመሳሰሉት ናቸው። ኤክስፖርት ያደረገቻቸዉ ፍራፍሬም በእኛ ሀገር ይገኛሉ። እነዚህ ምርቶች የውሃ ፍጆታቸው ከሚጠቀሙት የመስኖ ዘዴ ጋር ተደምሮ ወደ 63 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በዓመት ይሆናል። የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ብቃትም ከ 70% በታች ነዉ። ይህን የውሃ አጠቃቀም ከብክነት ለማዳን የተለያዩ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ይቻላል ለምሳሌ ያህል የጠብታ መስኖ (drip irrigation) እና የመርጨት (sprinkler irrigation) የመሳሰሉትን መተግበር ያስፈልጋል። የመስኖ ውሃ አጠቃቀም አስተዳደር እና የውሃ ቦዮችን እንደገና በመጠጋገን ያለአግባብ የሚባክነውን እስከ 22 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በዓመት የውሃ መጠን ማዳን ይቻላል።
- የኢንዱስትሪ ውሃ አጠቃቀም:—ግብፅ ብዙ ኢንዱስትሪዎች አሉዋት ለምሳሌ የጨርቃጨርቅ፣ የወረቀት፣ የብረት፣ አልሙኒየም፣ ሲሚንቶ፣ የተለያዩ ኬሚካሎች እና የእርሻ ኢንዱስትሪ የመሳሰሉት ሲሆኑ የውሃ ፍላጎታቸውም እስከ 8 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በዓመት ይሆናል። ስለዚህ እንደ አማራጭ የፍሳሽ ውሃን እና ከእርሻ ተረፈ ውሃን በማጣራት ኢንዱስትሪዎች መጠቀም እንዲችሉ በማድረግ የውሃ ፍላጎትን ማሳደግ ይቻላል።
- የፍሳሽ ውሃንና ከእርሻ ተረፈ ውሃን በማከም እንደገና መጠቀም (Reuse of Wastewater and Agricultural drainage water) – እንደሚታወቀው 80 ፐርሰንት የሚሆነው የውሃ ፍጆታ ወደ ፍሳሽ ውሃነት የሚቀየር እንደሚሆን የሚገመትና የሚባክን ነዉ። ስለዚህ ይህን የፍሳሽ ውሃ በማከም ለተለያዩ ጥቅሞች እንደገና መጠቀም ይቻላል። እንዲሁም ከመስኖ እርሻ የሚተርፈውን ውሃ ቀጥታ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ሙሉ በሙሉ ከመልቀቅ የተወሰነውን በማከም እንደገና ለተለያዩ ጥቅሞች ማዋል ይቻላል። ስለዚህ እስከ 10 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜት በዓመት የሚሆነው ከፍሳሽና ከመስኖ ተረፈ ውሃ በማከም እንደገና መጠቀም ይቻላል።
- ወደ ሜዲትራንያን ባህር የሚገባውን የውሃ መጠን መቀነስ – የናይል ወንዝ ውሃ ከዴልታ ድልድይ በኋላ በሁለት ቦይ ተከፍሎ በሮሴታና ደሜታ ቅርንጫፍ አካባቢው ያለውን የእርሻ መሬት በማልማት ወደ ሜዲትራንያን ባህር ይገባል። ይህ ተረፈ ውሃ እስከ 12 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ እንደሚሆን ይገመታል። ይህን ያህል መጠን ውሃ ወደ ባህሩ ከመልቀቅ አብዛኛውን መጠን ለተለያየ ስራ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላልና ሊታሰብበት ይገባል።
- ከአስዋን ግድብ/ ከናስር ሀይቅ የሚተነዉና የሚሰርገውን የውሃ መጠንን መቀነስ – በዓመት ከአስዋን ግድብ/ ከናስር ሀይቅ ከ 10 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ በትነትና በስርገት መልክ ይባክናል። ይህ መጠን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊጨምር ይችላል። ይህን በትነትና በሥርገት መልክ የሚባክን ውሃ መቀነስ የሚቻለው የታላቁ የህዳሴ ግድብን እውን ሲሆን ነው። ይህ የሚሆነው ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል አመንጭቶ የተመጣጠነ ውሃ ሲለቀቅ ነው። ይህን ግብፆቹ ጠንቅቀው ያውቁታል ነገርግን ለምን አልዋጥ እንዳላቸው ለመረዳት ብዙ የድርጊት እይታዎችን ማየት ይቻላል። በተጨማሪም የህዳሴ ግድቡ ወደ ሱዳንና ግብፅ ግድቦች የሚገባዉን የደለል መጠን እጅጉን ይቀንስላቸዋል ያም ለደለል ማስጠረጊያ የሚያወጡትን ወጪ ይቀንስላቸዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግ ቢያንስ እስከ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውሃ መጠን በተጨማሪ
ማግኘት ይቻላል። ስለዚህ አዋጭ የሚሆነው የታችኞቹ ሀገሮች መተማመን ላይ በተመሠረት በትብብር መንፈስ በጋራ መስራት ለሁሉም ሀገራት ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ሲረዱ ነዉ።
§ ቶሽካ ሸለቆ ልማት እና የሠላም ቦይ ፕሮጄክቶች – እነዚህ ሁለት ፕሮጀክቶች ከናይል ተፋሰስ ውጪ ታቅደዉ ብዙ ሕንፃዎችና መሠረተልማት ተሟልቶለት አዲስ የሠፈራ ቦታ የተገነባበት እና ህዝብ ከሌላ ቦታ በማስፈር የመስኖ ልማት ለማልማት ታስበዉ እየተሰሩ ያሉ ናቸዉ። ይህንኑ እውን ለማድረግ 14‚200 ካሬ ኪሎ ሜትር የእርሻ መሬት የተዘጋጀ ሲሆን መሬቱን ምርት ሰጪ እንዲሆን ከአስዋን ግድብ የተጠራቀመውን ለም አፈር በማጓጓዝ ጠፍ መሬትን እንዲታረስ ማስቻል ነው። ይህን ቶሽካ የእርሻ መሬት ለማልማት ከአስዋን ግድብ በዓመት ወደ 5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ በመውሰድ ሲሆን ግብፅ ይህን ስታደርግ ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎቹን የተፋሰስ ሀገሮች አላማከረችም። በመጀመሪያ ምዕራፍ ትላልቅ ፓንፖችን በመትከል እና 320 ኪሎ ሜትር በጣም ሰፊ የውሃ መሄጃ ቦይ በመስራት እና በሁለተኛው ምዕራፍ የውሃ መሄጃ ቦይ እስከ 800 ኪሎ ሜትር በ 2025 እ. ኤ. አ. ለማድረስ የታለመ እና 2.8 ሚሊዮን ሥራ ለመፍጠር፣ ኢንዱስትሪንና ቱሪዝምን ለማስፋፋት የታሰበ ፕሮጀክት ነዉ። ይህ ፕሮጀክት 80 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን አስቡት ከታላቁ እዳሴ 5 ቢሊዮን ዶላር ጋር።
ሌላዉ የሲውዝ ቦይን አቋርጦ በሰሜናዊ ሳይናይ ኤል-ሠላም የውሃ ቦይን በመስራት 2‚605 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የመስኖ እርሻ መሬትን በማዘጋጀት የማስፋፊያ ስራ ታቅዶ እየተሰራ ያለ ነው። ይህ ፕሮጀክት ዓላማዉ የግብፅን የማህበራዊ የሚያረጋጋ (ተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሰፋ ያለ መኖሪያ ቦታን ለማዘጋጀት)፣ እራስን ለማስቻል እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት እንዲያስችል ታልሞ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ነዉ። ይህም ተጨማሪ ውሃ ከናይል ወንዝ የሚፈልግ ነው። የፕሮጀክቱ ወጪ እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። ግብፆቹ እንደፈለጉ የናይል ውሃ ሲጠቀሙ ኢትዮጵያ ግን ፍጆታ የሌለዉን (Non-consumptive) የኃይል ማመንጫ ለማልማት አቅዳ ስትሰራ ከመተባበር ይልቅ በተቃራኒ መሆን ምን የሚሉት ጉዳይ ነዉ።
- የባህር ውሃን አክሞ ጥቅም ላይ ማዋል (Desalinization of Sea Water) – ሌላው መታየት ያለበት አማራጭ የሜዲትራንያንና የቀይ ባህርን ጨዋማ ውሃን በማጣራት ለተለያዩ ጥቅሞች ማዋል ይቻላል። ስለዚህ ግብፆች በቅርባቸው የሚገኘውን ይህን የውሃ ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ጨዋማ ዉሃን የሚያጣራ ቴክኖሎጂ ቀለል ያለ እና እርካሽ እየሆነ ስለሆነ መለማመዱ ቢኖር!
ማጠቃለያና መደምደሚያ
ግብፅ ከራስጌ ያለው የውሃ መጠን ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ከላይ የተገለፁትን የውሃ መገኛ አማራጮች ላይ የበለጠ ትኩረት ብታደርግና አላስፈላጊ የሚባክነውን ከፍተኛ የውሃ መጠን ለማዳን ጠንክራ ብትስራ ተጠቃሚ ትሆናለች ይህንኑ ሀሳብ ለህዝቧ በግልፅ ማሳወቅና እስትራቴጂ ነድፋ መንቀሳቀስ ይጠበቅባታል። ይህን ለመፈፀም ቅንነት፣የፖለቲካ ፍቃደኝነት፣ ፖሊሲ የማሻሻልና የትብብር መንፈስ ማጎልበት ሲቻል ነው።
የላይኞቹ የተፋሰስ ሀገሮች ከላይ የተገለፁት የተለያዩ የውሃ መገኛ አማራጮችን በመረዳትና ተግባራዊ ለማድረግ የታችኞቹን ሀገራት ማሳመን በትብብር መንፈስ ቴክኒካዊ መፍትሄዎች ላይ በመነጋገር የጋራ የሆነዉን የዉሃ ሀብት ለማልማት በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነ ምሁራኖች ከሀገራችን የሚፈሰውን የአባይ ውሃ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባትና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጠቀሜታ ለዓለም ማህበረሰብ በሚገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ማሳወቅ ያስፈልጋል ለምሳሌ ቀጣይነት ያለዉ የዲፕሎማሲ ሥራ፣ የዓለም የውሃ ቀን፣ የዓለም የውሃ ሳምንት እና የተለያዩ ዓመታዊ ከውሃ ጋር ተያያዥነት ካላቸው ስብሰባዎችና ኮንፍረንሶች በባለሙያዎች በመላክ ለዓለም ማኀበረሰብ ማስረዳቱ ሚዛናዊ እይታና አስተሳሰብ እንዲኖር ማድረጉ ላይ አጥብቆ መስራት ያስፈልጋል። ከዚያ በተጨማሪም የሀገር ዉስጥ እዉቀትን ለማሳደግ እንዲያስችል ከአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ ስለ ወንዞቻችን የትምህርት ሥርዓት ዉስጥ መካተት ይኖርበታል እንዲሁም የዉሃ ሀብት ምርምር ኢንስቲትዩት ቢቋቋም ጥሩ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012
ኢንጅነር አበራ ተስፋዬ