ከራሱ መስፋፋትና ምቾት በስተቀር ለማንም ለምንም ዴንታ የሌለውና በነጮች የቅፅል ስም አረጓዴው ሰይጣን ወይም በእኛ ሀገር አጠራር የእንቦጭ አረም ለማንም ለምንም ምንም የውሃ ዘር ሳያስተርፍ በቁጥር ብዙና በመጠናቸውም ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉ ኩሬዎችን፣ ሀይቆችን ወ.ዘ.ተ ውሃቸውን እንደስፖንጅ እየመጠጠ የውሃ ማዕበል ከወዲያ ወዲህ ይሉባቸው የነበሩትን የውሃማ አካላት በማድረቅ እንኳንስ ውሃ የነበረባቸው ሊመስሉ ይቅርና እንደ አረብ ሀገር የበረሃ መሬት ልብስ አልባ በማድረግ የውሃማ አካላትን ህይወት በማመሰቃቀል ወደር ያልተገኘለት ራሰ ወዳድ አረም ነው።
“ርሀብን የማያውቅ ለተራበ አያዝንም” እንዲሉ ልክ እንደ እንቦጭ ሁሉ ግብፅም ከራሷ ምቾት እና ዕድገት ውጭ የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች በህይወት የመኖር ብሎም ዕድገት እና ብልፅግና ወደጎን በመተው “በሰው ቂጣ እጇን ትቃጣ” እንዲሉ በራሳችን ወንዝ በራሳችን ግድብ እኔ ካልፈቀድኩ ብሎ የሞተና የበሰበሰ ሃሳብ ይዞ መቃዠት ምን የሚሉት ነው?
ከተወሰኑ ዓመታት በፌት የነበሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግብፅ በጥጥ ምርት ከአለም አራተኛ፣ በእህል ምርት እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ደግሞ በአፍሪካ መሪ ስትሆን የአፍሪካ ቀዳሚ አይብ አምራች ሀገርም ናት። ከዚህም በተጨማሪ 800 ሺህ ሜትሪክ ቶን አካባቢ ዓሳ ከአባይ ወንዝ ላይ እያመረተች ያለ ሲሆን ቁጥራቸው በሚሊዮን የሆነ የቀንድ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች፣ ዶሮዎች እንዲሁም ወደ 3.2 ሚሊዮን የሚጠጉ ጎሾች የአባይን ወንዝ ተከትለው ኑሯቸውን የመሰረቱ ናቸው። በዚህ ብቻ ሳታበቃም እስከ 75.3 ቢሊዮን ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በየዓመቱ ከአባይ ወንዝ ታመርታለች። ከዚህም ምስር (ግብፅ) በእየዓመቱ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን ታፈሳለች። ስለሆነም ግብፅ 100 % የመብራት እና 98 % የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ለዜጎቿ በማዳረስ የበርሀ ገነት የሆነች ሀገርን በመፍጠር ዜጎቿን በተንደላቀቀ ህይወት ታኖራለች። ኢትዮጵያ ግን ካብራኳ ከሚመነጨው ሀብቷ ስትጎዳ እንጂ ስትጠቀም ያየ የለም። ብዙ አፈሯና ማዕድኗን በልጇ አየተነጠቀች ለባዕድ ሃገራት ስጦታ ስትቸር ኖራለች እንጂ። አሁን ግን የቀረውን አፈርም ሆነ ማዕድናችን ከአባይ እወደድ ባይነት
የምንታደግበት ጊዜ ነው።
እዚህ ላይ አንድ ነገር በግልጽ ማየት ይቻላል። ይህም ምንድን ነው ግብፅ የአባይን ወንዝ እንደፍላጎቷ ለተለያዩ ነገሮች የማንንም ፈቃድ ሳትጠይቅ በስፋት እየተጠቀመች ኢትዮጵያ ግን በተለያዩ ተፈትሮአዊ ክስተቶች እየተፈተነች ማለት በተደጋጋሚ ድርቅ በአንበጣ ወረርሽኝ እና ሌሎችም ፈተናዎች ቢያጋጥሟትም፤ የአባይ ወንዝ ለመስኖ ብሎም ለፈርጀ ብዙ ግልጋሎት ቢያስፈልጋትም ከታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ጋር የሚኖረውን ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል እውን ለማድረግ የአባይ ወንዝ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ ለመጠቀም ግድብ መገንባቱ ምኑ ላይ ነው ሀጢያቱ ? ነገር ግን እንደ እንቦጭ አይነት ባህሪ የተዋረሳት ግብጽም የጣናን ሀይቅ እና በዙሪያው ያሉ አካለትን ለማጥፋት ፈታኝ እንደሆነው እንቦጭ ሁሉ ግብፅም በህዳሴው ግድብ ላይ የምታሳድረው ጫና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተቃጣ የመኖርና ያለመኖር ወይም የህልውና ጉዳይ እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ አውቆ በአንክሮ ሊመለከተው ይገባል።
እንደሚታወቀው የአትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት ያደረገው በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ነው። የእኛ ሀገር ግብርና ደግሞ በከባድ የተፈጥሮ ተፅዕኖ ስር ያለ እና የተፈጥሮ ባህሪያት ሲለዋወጡ የሚለዋወጥ እና አስተማማኝ ያልሆነ ነው። በዚህም የግብርናው ኢኮኖሚ ምንም እንኳን የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ቢሆንም የተረጋጋ ባህሪ የሌለው እና በሚከሰቱ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ኩነቶች ሂደቱ እና ምረታማነቱ ብዙ ጊዜ ሲታወክ ይታያል። ስለሆነም በማይቋርጥ ሂደት ውስጥ ምርት እና ምረታማነትን ለማሳደግ የመስኖ እርሻ መተኪያ የሌለው አማራጭ ነው።
የኢትዮጵያ ግብርና በማያቋረጥ ሂደት ውስጥ ለመከወን የመስኖ እርሻ መተኪያ የሌለው አማራጭ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ በውል ቢረዳም የታለቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ ለማዋል መወሰኑ የሚያሳየው የኢትዮጵያን ህዝብ ጨዋነትና ለግብፅ ህዝብ ያለውን አከብሮት ነው። ነገር ግን ግብፅ ግድቡ ለምን አላማ እንደሚውል በትክክል እያወቀች “ሹም ነገር ሲፈልግ የዶሮ ሻኛ አምጡልኝ ይላል” ዓይነት እያደረገች ትገኛለች። ይህም ምንድን ነው “ሌባና ሌባ ተጣሉ በሰው ገለባ” እንዲሉ እንግሊዝና ግብፅ በኋላም ሱዳንን በመጨመር ነገር ግን የውሃውን ባለቤት ኢትዮጵያን ሳያሳትፍ በተከወነ የቅዠት የቅኝ ግዛት ውልን እያነሱ ቢጥሉት ምንስ ሊኖረው ይችላል።
“ምስክር ያለው ሙግት አያዳግትም ለመርታት” እንዲሉ ኢትዮጵያ ግን በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የያዘችው አቋም በአጥኝዎች የተጠና እና በግብፅ ላይ ሊያሳድረው የሚችለው ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደሌለው በባለሙያዎች የተረጋገጠ ስለሆነ በድርድር ቢያልቅ ኢትዮጵያ ያነሳችው ሃሳብ በፍጹም የበላይነት እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህዝብ ያሉበት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድርብርብ ችግሮች ናቸውና ህሊና ያለው ማንም አደራዳሪ ሆነ ተደራዳሪ በዕውር ድንበር ሃምሳ ሚሊዮን የንፁህ መጠጥ ውሃ እና ሃምሳ ሚሊዮን የኤሌክትሪክ ብርሃን በማያገኝ ህዝብ ላይ የምንተግዴ ውሳኔ እንደማያስተላልፉ ይታመናል። ነገር ግን ይህ ኢትዮጵን በጦርነት ማስፈራራቱ ለማንም አይበጅም። ምክንያቱም የኢትዮጵያን ጦረኝነት ከግብፅ በላይ የሚያውቅ ማግኘት ለአሳር ነው። ይህንንም የኢትዮጵያንና የግብጽን ታሪክ የመረመረ በቀላሉ የሚገነዘበው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ግብጽን አንበርክከው ቅኝ የገዟትን እነ ሜቄዶንያንና ሮማን ኢምፓየር ኢትዮጵያን ለመያዝ ለምን እንዳልሞከሩ ሴኔካ እና ዌንስ የተባሉ የታሪክ ምሁራን የፃፏቸውን የታሪክ መዛግብት ወደ ኋላ ሂዶ ማየት ምላሽ ይሰጣል።
በዚህ አጋጣሚ አንዳንድ የታሪክ ሰዎች እንደሚሉት የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የሚለው ቃል የአገውኛ ቋንቋ መሆኑን ስንቶቻችን አውቀን ወይም ሰምተን ይሆን። ይህን ስም ንጉስ ቅዱስ ላሊበላ እንደሰጡት አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ። ለምን ብሎ ለሚጠይቅ ንጉስ ቅዱስ ላሊበላ ነጭ እና ጥቁር አባይን ድንጋይን በድንጋይ የማቅለጥ ተክኖሎጂ ተጠቅመው ዓባይን ገድበውት ነበር። በመሆኑም ካርቱም የሚለው ቃል በአገውኛ ማገድ ወይም ማቆም መሆኑን ለመረዳት ይቻላል። ነገር ግን መሰሪ የሆኑት ግብፆች በንጉሱ በእግር በጃቸው በመግባት የሚችሉትን የማታለል ችሎታቸውን በመጠቀም በወቅቱ የተጀመረውን የንጉሱን ስራ እንዳስተዋቸው የታሪክ ድርሳናት ይጠቅሳሉ።
በመጨረሻም ግብፅ አሁን ያለውን ግትር እና እኔ ብቻ ልብላ፣ ልደግ፣ ልስፋፋ የሚል የእምቦጭ አቋሟን በመተው ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ላይ እስካልመጣች ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለበትን የታሪክ ኃላፊነት በቆራጥነት ሊወጣ ይገባል መልዕክቴ ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2012
በአሸብር ሀይሉ