‹‹የክረምት ወራት›› ከሚባሉት የመጀመሪያውን እነሆ የሰኔ ወርን ተቀብለናል። ሰኔ ከልጅ እስከ አዋቂ ይታወቃል። የዘንድሮን አያርገውና የሰኔ ወር በተማሪዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። አገር አቀፍ ፈተናዎች የሚሰጡበት ነው። ከመስከረም ጀምሮ አብረው የቆዩ ተማሪዎች የሚለያዩበት ነው። ለተፋቀረም ለተጣላም የሰኔ ወር ልዩ ቦታ አለው። ሰኔ 30 የሚለው ቃል ራሱ ለብዙ ነገሮች ርዕስ ሆኗል።
የሰኔ ወር ለአዋቂዎችም እንዲሁ ልዩ ቦታ ያለው ነው። በተለይም በገጠር አካባቢ ብዙ መሥሪያ ቤቶች ይዘጋሉ። የእረፍት ጊዜ የሚጀመርበት ነው። ለአርሶ አደሮ ደግሞ የበለጠ በሥራ የሚተጋበት ነው።
ሰኔ ለመንግስትም እንዲሁ ልዩ ወር ነው። የበጀት መዝጊያ ወር ነው። በዚህ ወር በዓመቱ የተከናወኑ ነገሮች ትርፍና ኪሳራ ይታወቃል። የከሰረውም የተረፈውም በጀት የሚታወቀው በዚህ ወር ነው።
ወደ ኪነ ጥበብ ስናመጣው እንግዲህ የሰኔ ወር የክረምት መጀመሪያ ነውና ብዙ የተዘፈነለት ነው። ክረምት የቅዝቃዜ ወቅት ነው። በሬዲዮ የምንሰማው አንድ የተለመደ ነገር አለ። ‹‹አየሩ ቀዝቀዝ ያለ ስለሆነ ሞቅ ያለ ሙዚቃ ጋብዙን›› ይባላል። እርግጥ ነው አሁን አሁን እንደበፊቱ ሙዚቃ በሬዲዮ መጠበቅ ቀርቷል። ብዙዎች በኪሳቸው ይዘውት የሚዞሩት ነው።
ክረምትን መሰረት አድርገው የተዘፈኑ ዘፈኖች ራሱ አሉ። እነዚህ ዘፈኖች ከሰኔ ወር ጀምሮ በተደጋጋሚ ይደመጣሉ። ከዚህ በላይ ግን የሚበልጠው የአርሶ አደሩ እና የእረኞች እንጉርጉሮ ነው። የክረምት ወር ለእረኞችም ልዩ ወር ነው። ምክንያቱም በደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል (ሰሜን ኢትዮጵያ) በክረምት ወራት በሰብል ይሸፈናል። እረኞች ደግሞ እነዚህ ሰብሎች በከብት እንዳይበሉና እንዳይበላሹ ይጠብቃሉ። በዚህ የጥበቃ ወቅት ያንጎራጉራሉ።
አርሶ አደሩም የሚያንጉራጉረው በክረምር ከበሬው ጋር ነው። በሬዎቹን ያወድሳል፤ እርሻ እያረሰ ወኔውን በዘፈን ያጠነክራል፡በዛሬው ጽሑፋችንም የምናየው የአርሶ አደሩን እንጉርጉሮ ብቻ ነው (የእረኞችን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)። እነዚህ የአርሶ አደሩ እንጉርጉሮዎች በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ የስነ ቃል ሀብቶች ናቸው።
የስነ ፅሁፍ መጀመሪያው ስነ ቃል እንደሆነ የስነ ጽሑፍ ሰዎች ይመሰክራሉ። በተለይ ግጥም ደግሞ መነሻው ስነ ቃል ነው። የስነ ቃል ነገር ከተነሳ በቀጥታ የምንሄደው ወደ ገበሬው ነው። እንግዲህ የአገራችን ገበሬ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የኪነ ጥበብም የጀርባ አጥንት ነው ማለት ነው።
ወቅቱ የክረምት ወቅት መሆኑ የገበሬውን ስነ ቃል እንድናስታውስ ያስገድደናል። በዚህ ወቅት ከሌላው ጊዜ በተለየ በሥራ የሚወጠርበት ነው። ይህን በሥራ መወጠሩን ደግሞ እያንጎራጎረ ነው የሚወጣው። በተለይም አሁን የእርሻ ወቅት እንደመሆኑ በሬዎቹን እያሞገሰ ነው የሚያርስ። በሰብል ስብሰባና በሌሎችየግብርና ሥራዎች ሁሉ የሚላቸው የየራሱ ስነ ቃሎች ቢኖሩም ለዛሬው ወቅቱን መሰረት አድርገን በእርሻ ወቅት የሚባሉትን ብቻ እናስነብባችኋለን።
ገበሬው ገና በጠዋት በሬዎቹን እንደጠመደ ‹‹በሬውን ከበሬ እርፉን ከገበሬ አስማማልኝ!›› ብሎ ለፈጣሪው በመንገር ይጀምራል። በሬዎች ተመሳሳይ ባህሪ ከሌላቸውና ካልተናበቡ ለእርሻ ያስቸግራሉ፤ ቀንበርም ሊሰብሩ ይችላሉ፤ ‹‹በሬ እና በሬ መከሩ፣ ቀንበር ሰበሩ›› የተባለውም ለዚህ ነው። እርፍ ማለት ገበሬው በእጁ የሚይዘው ከሞፈሩ ጋር የተዋደደ ቋሚ እንጨት ነው። እንግዲህ ለከተማ አንባቢዎች አንዳንድ መብራራት ያለባቸው ቃላት ስላሉ እናብራራለን!
የገበሬ ህልውናው በሬው ነውና በእርሻ ወቅትም ሆነ በሰብል ስብሰባ ጊዜ የሚያወድሰው በሬውን ነው። በእርሻ ወቅት የሚጠቀማቸው የቃል ግጥሞችም የበሬውን የእርሻ ውለታ የሚገልጹ ናቸው።
ገና በጠዋት በሬ እንደጠመደ ገበሬውም ሆነ በሬዎች ድካም አይሰማቸውም። ድንጋዩን ከድንጋይ እያፋጩ ያስጮሁታል። ከእርሻ ማሳ ግርጌ ላይ ደግሞ ድንጋይ አይጠፋም። ይህ የድንጋይ ስብስብ አረንዛ ይባላል። ገበሬውም ጠዋት እርፍ ጨብጦ በሬዎችን ‹‹ትለም›› ማለት ሲጀምር እንዲህ ብሎ ይፎክራል።
አረንዛው ሲጮህ እንደ ሮቢላ
ማን ይጠመዳል ከወይኖ ጋራ!
ሮቢላ ማለት አውሮፕላን ለማለት ሲሆን ወይኖ ደግሞ ለበሬ ከሚወጡ ስሞች አንዱን የተጠቀምኩት ነው። ለገበሬውም ሆነ ለበሬዎች ፈተና የሚሆንባቸው አረንዛ(ድንጋይ) ብቻ ሳይሆን ሰርዶ ጭምር ነው። ሰርዶ የሚባለው ወፍራም የሳር ዓይነት በጣም ጠንካራ ነው። ሰርዶ የመሬት አፈር በውሃ እንዳይሸረሸር በሚያደርገው አስተዋፅኦ ገበሬዎች ቢወዱትም ለእርሻ ግን አስቸጋሪ ነው። ዳሩ ግን ገበሬውና በሬዎች ጠንካራ ከሆኑ ይህን ሰርዶ ይበጣጥሱታል። ለዚህ ወኔው እንዲህም ብሎ ይፎክራል።
አረንዛ ገፊ ሰርዶ ቅልቅል
ሻሽ የመሰለ ማኛ ሚያበቅል
ማረሻው ሀዲድ ሞፈሩ ወይራ
ሰርዶ አራጋፊ እንደ ጨጓራ!
‹‹ሻሽ የመሰለ›› የተባለው መነኩሴዎች የሚያደርጉትን ሻሽ ነው። ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ መነኩሴዎች የሚያደርጉት ሻሽ ነጭ ነው፤ ገበሬው የሚያመርተውን ማኛ ጤፍ እንደ ነጭ ሻሽ ንጹህ መሆኑን ለመግለጽ ነው።
በሬዎች ልክ እንደ ሰው ሁሉ ይላመዳሉ፤ ይግባባሉ። አንድ በሬ አብሮት ሲያርስ ከቆየው በሬ ጋር ቢለያይ ከሌላ ጋር ቶሎ አይላመድም። ከሌላ በሬ ጋር ከተጠመደ ባህሪያቸው ያስቸግራል። ሆኖም ግን ገበሬው ጎበዝ ከሆነ እነዚህን በሬዎች ያግባባቸዋል። በዚህ ጀግንነቱም እንዲህ እያለ ያንጎራጉራል።
ድብ እና ድቡን አደባላቂ
የተኳረፈ በሬ አስታራቂ!
ድብ የሚባለው በእርሻ ማሳ ውስጥ የሚገኝ የእርከን አይነት ነው። ይህ የእርከን አይነት ከድንጋይ ብቻ ሳይሆን ከአረምና ሌሎች ቅጠላቅጠልና የሳር አይነቶች የሚሰራ ሲሆን በጊዜ ብዛት ወደ ለም አፈርነት ይለወጣል። ገበሬው ይህንን ድብ ያፈርስና ሲታረስ የቆየው ማሳ ላይ ሌላ ድብ ይሰራል። የነበረው ድብ አዲስ አፈር ስለሚኖረው ለሰብል በጣም ተስማሚ ነው። ለዚህ ነው ‹‹ድብ እና ድቡን አደባላቂ!›› ብሎ የሚፎክር።
በዚህ የሥራ ውጥረት ውስጥ ሆኖ እንኳን ፍቅር ደግሞ አለ! የሚወዳት ልጅ በዚያ አካባቢ ካለፈች ልቡ ይሰረቃል። በዚያ ባታልፍ እንኳን ፍቅር ነውና በልቡ ውስጥ መጥታ ድቅን ልትል ትችላለች። ያኔ ትኩረቱ ከበሬዎች ይልቅ እሷ ላይ ይሆናል ማለት ነው። በእንዲህ አይነቱ የፍቅር አጋጣሚ ደግሞ እንዲህ እያለ ያንጎራጉራል።
በሮችን ጠምጄ እርፉ ሲያንገላታኝ
መጣች ያገሬ ልጅ ሥራ ልታስፈታኝ!
የሚወዳትን ልጅ ለማግኘት ሌላም ዘዴ ይጠቀማል። ከቤታቸው ተቀጥሮም ቢሆን መሥራት እሷን ለማግኘት ያግዘዋል። ገበሬዎች አራሽ መቅጠር የተለመደ ነው። በሚወዳት ልጅ ፍቅር የተጠመደ ገበሬ እንዲህ ብሎ ያንጎራጉራል።
ምነው ባደረገኝ የአባትሽ አራሺ
ዘር አለቀ ብየ ቀን እንዲጠራሺ!
ገበሬው ማረስ እንደሚያኮራ ደጋግሞ ይናገራል። በአንፃሩ አለማረስ ደግሞ ለልመና እና ለብድር እንደሚዳርግ በእንጉርጉሮው ይገልጻል። ልመና፣ ብድር እና ስርቆት አሳፋሪ እንደሆኑ ይናገራል። በሰነፍ ገበሬም ይሳለቁበታል፤ በነገር ወጋ ያደርጉታል። ይሰማው ዘንድም የጠንካራ ገበሬን ውጤት በእንጉርጉሮ ይነግሩታል።
ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ
ወፍጮው እያጓራ መስከረም ዘለቀ
ያላረሰ ገበሬ በተለይም በክረምት ወራት በጣም ይቸገራል። በቤቱ ውስጥ ያለው ወፍጮ ምንም ነገር ስለማይፈጭበት ድምጹ አይሰማም። በጎበዝ ገበሬ ቤት ግን ብዙ የሚፈጭ ነገር ስለሚኖር ሁሌም የወፍጮ ድምጽ አይጠፋም። ሰነፍ ገበሬ ያንን እየሰማ አንዴ ፈጣሪውን ያማርራል፤ አንዴ ደግሞ ነገሩን የስንፍና ውጤት ሳይሆን መተት ተደርጎበት እንደሆነ አድርጎ ያስባል። የስንፍነው ውጤት መሆኑን ደግሞ እንዲህ ይነግሩታል።
እሾሁን መንጥረህ አትረስና
ሰርዶውን በጣጥሰህ አትረስና
‹‹አሟረቱብኝ›› በል ከመደብ ተኛና!
እንዲህ አይነቱ ሰነፍ ገበሬ ሰበቡ ብዙ ነው። ምን ዋጋ አለው! ማንም ገበሬ የፈጣሪ ቁጣ ነው ወይም የአርባ ቀን ዕድሉ ነው ብሎ አይተወውም፤ በነገር ወጋ ማድረጉን አይተውትም።
በበጋ እንዳይሰራ ፀሐይ እየፈራ
በክረምት እንዳያርስ ዝናብ እየፈራ
ልጁ ‹‹እንጀራ›› ሲለው በጅብ አስፈራራ!
ከችግሩ ያላነሰ እንዲህ መሳለቂያ መሆኑ ያሳስበዋል። በየሰርጉና በየደቦው እንዲህ መሰደብ ሲመረው ጠንክሮ ይሰራል። ገበሬው ስርቆትና ብድር ነውር እንደሆነ ደጋግሞ ይናገራል።
ማረስ ነው እንጂ እጅ እስኪቆስል
ምንድነው ስርቆት ውሻ ይመስል!
እያለ የስርቆትን ነውርነት ይናገራል። በገጠር አካባቢ የአንዳንድ ሰዎች ውሻ ተገቢውን እንክብካቤ አይደረግለትም። ታስቦ ምሳ እና ራት አይሰጠውም። ያ ውሻ ሲርበው ያለው አማራጭ ሰርቆ መብላት ነው። ሰነፍ ገበሬን ከዚህ ውሻ ጋር ነው የሚያመሳስሉት።
ድሃ ገበሬ ስርቆትን ቢፈራ እንኳን ወደ ብድር መሄዱ የግድ ነው። የብድሩ ነገር ትንሽ መረር ያለ ነው። በቀጥታ የተበደረውን አይደለም የሚመልስ። የተበደረውን እህል በወሰደው ልክ የሚመልስ ቢሆንም የጉልበት ሥራ ሰርቶ ነው የሚሰጠው። ከዚህ አለፍ ሲልም ሌላ የከፋ ነገር አለ። ማሽላ ተበድሮ ጤፍ ይከፍላል፤ ይህን የሚያደርገው አምኖበትና ተነግሮት ነው። ይህ አይነት ብድር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለመግለጽ ገበሬው እንዲህ ይላል።
ሲያርሱ ውሎ ሲያርሱ ነበር ማደር
የነቀዘ ማሽላ በጤፍ ከመበደር!
የጓያ ምርት ብዙም ተወዳጅ አይደለም። ሆኖም ግን ችግሩ የከፋ ሲሆን የሌለው ገበሬ ጓያም ሊበደር ይችላል። ጓያ አህያ እንኳን አይበላውም(አህዮች ባቄላ ነው የሚወዱ)፤ ይህን የጓያ ብድር ለመግለጽም እንዲህ ተብሏል።
ሲያርሱ ውሎ ሲያርሱ ነበር ማደር
እርኩስ የጠላውን ጓያ ከመበደር!
እንግዲህ ጠንክሮ የሚያርስ ገበሬ ይህ ሁሉ ችግር አይገጥመውም ማለት ነው። ልጆቹ አይራቡም፣ ብድር አይሄድም። ይህን ኩራቱን በእርሻ፣ በሰርግና በሌሎች አጋጣሚዎችም ሲያንጉራጉር እንዲህ ይላል።
ያርሳል ያሳርሳል ያወጣል እዳሪ
ሚስቱን አይላትም ‹‹ሂጂ ተበደሪ!››
የመጨረሻው ስንኝ፤ ሚስቱን አይላትም ‹‹ቆጥበሽ እደሪ!›› ተብሎም ይነገራል። እዳሪ ማለት ያደረ ለማለት ሲሆን ሳይታረስ የቆየን የእርሻ ማሳ አለሳልሶ ለእርሻ ምቹ ማድረግ ማለት ነው። እንዲህ አይነቱ ማሳ ዘወትር ከሚታረሰው በተለየ ምርታማ ነው።
ከጎበዝ ገበሬ ቤት ምንም ነገር አይጠፋም። የዓውዳመት በዓላትም ሆነ ሌላ ጉዳይ ሲኖር የሚደገስ ነገር አይጠፋም። ጠንክሮ ባላረሰ ገበሬ ቤት ግን እንኳን ለድግስ የሚሆን ለዕለት ጉርስም ይቸግራል። ከቤቱ እንግዳ ሲመጣ እንኳን የሚቀርብ ነገር ይጠፋል። እንደ ባህልና ወጉ በቡና ጠጡ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚቀርብ ይጠፋል። ለእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ነው ገበሬው እንዲህ ብሎ ማንጎራጎሩ
ጎበዝ እርሻ እረሱ ከእርሻ አትመለሱ
ቡና እንኳን ሲፈላ ይቸግራል ቁርሱ!
እነዚህ የስነ ቃል ግጥሞች እንደቀላል የሚታዩ አይደሉም። ጥልቅ መልዕክት ያላቸው ናቸው። የሕዝብ ስነ ቃል ስለሆኑ እንጂ ታትመው ገበያ ላይ ከሚሸጡ ግጥሞች በላይ ጥልቅ ፍልስፍና ያላቸው ናቸው። ዳሩ ግን አሁን አሁን እየተረሱ ነው። ምሁራን በእነዚህ ላይ ጥናት አያደርጉም፤ መገናኛ ብዙኃንም እነዚህን የቃል ግጥሞች ሲጠቀሙ አይታይም። የግብርና ፕሮግራም በሚቀርብባቸው ፕሮግራሞች እንኳን ለገበሬው እነዚህን የቃል ግጥሞች ማሰማት ያስፈልግ ነበር። ከመረሳታቸው በፊት በጽሑፍ ተሰንደው ሊቀመጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
ዋለልኝ አየለ