
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር የነበራቸው ቆይታ በአራት ክፍል ተላልፏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተናገሯቸው በርካታ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች አንደኛው የበለጠ ቀልቤን ያዘው።
ጉዳዩ እንደ ፀጥታና ዲፕሎማሲ ከመሳሰሉት ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች የበለጠ ሆኖ ሳይሆን፤ ቀላል ሆኖ ግን ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ልብ መባል አለበት ብዬ ነው፤ መንግሥትም ሕዝብም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ስለሆነ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ፤ ልዕለ ኃያላን ናቸው በሚባሉት የዓለም ሀገራት የሚታየው ግዙፍ ሙስና ነው፤ ከታች ግን ሙስና የላቸውም። እንደ መታወቂያ ማውጣት ለመሳሰሉ ትንንሽ ነገሮች ሙስና የሚቀበል አገልግሎት ሰጪ የለም። ስለዚህ ይህ ገጽታቸውን ያሳምርላቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ ልብ እንበለው! አንድ የአፍሪካ ወይም የኢትዮጵያ ዜጋ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ሲኖር ጥቃቅን ሙስናዎችን አያይም። ስለዚህ የሀገራቸውን ሥልጣኔ ያደንቃል። “መሠልጠን እንዲህ ነው እንጂ!” ይላል።
የዓለም ሀገራት ዜጎች አውሮፓና አሜሪካን የሚያውቋቸው ከታች ባለው መደበኛ ሕይወት ነው። በመንግሥት ደረጃ፣ በትልልቅ ፕሮጀክቶችና ካምፓኒዎች ደረጃ የሚደረገውን ሙስና ተራው ዜጋ ሊያውቀው አይችልም።
ብዙ የምርመራ ዘገባዎችን ሰምተናል። ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋም(ለምሳሌ ፊፋ) የሚመሩ ቱጃሮች ሳይቀር በሙስና ተከሰዋል። ከመቀመጫችን ተነስተን ያጨበጨብንላቸውና ማምለክ በሚመስል ደረጃ የምናደንቃቸው የእግር ኳስ ተጫዋቾች በሙስና ሲታሙ ሰምተናል።
ግዙፍ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ካምፓኒ የሚመሩ ባለሀብቶች በሙስና ተከሰዋል። የሀብታም ሀገር መሪ ሆነው በሙስና ተከሰዋል። የዓለም የልዕለ ኃያላን አውራ ናት የምትባለው አሜሪካ ምርጫ በመጣ ቁጥር ተወዳዳሪዎች በሙስና ይታማሉ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እነዚህ ሀገራት በትንንሽ ሙስናዎች ስማቸው አይታማም። መደበኛ የሕዝብ አገልግሎት ለማግኘት የእጅ መንሻ የሚባል ኮተት የላቸውም። ይሄ ማለት ከመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከባለሀብቶች ይልቅ ሕዝቡ የተሻለ ሕግ አክባሪ እና የሞራል ባለቤት ሆኗል ማለት ነው፡፡
ለመሆኑ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታስ ምን ይሆን?
የአፍሪካንም ሆነ የኢትዮጵያን ስም የሚያጠፋው ትንንሽ ሙስና ነው። ይሄ ማለት ግን በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደረጃ አይኖርም ማለት አይደለም፤ ዳሩ ግን ሕዝቡ በዓይኑ አይቶ የሚያረጋግጠው ከታች ያለውን ትንንሽ ሙስና ነው፡፡
የውጭ ሀገር ዜጎች በቀላሉ የሚታዘቡት በአገልግሎት ማግኛ ቦታዎች ላይ የሚደረገውን ሙስና ነው። ይህ በአገልግሎት ማግኛ ቦታዎች የሚደረግ ሙስና መደበኛ አሠራር እስከሚመስል ድረስ ብዙ ቅጽል ስሞች እና የምስጢር ስሞች ሁሉ አሉት። “በእግርህ ነው የሄድክ ወይስ በእጅህ?” ዓይነት የምስጢር ስሞች የሙስና መግባቢያ እየሆኑ ነው።
በነገራችን ላይ ሕዝቡን ከመውቀሳችን በፊት የመንግሥት አሠራርም ለእንዲህ ዓይነት ብልሹ አሠራሮች ምቹ መሆኑን ልብ ማለት አለበት። አንድ ጉዳይ በቀላሉ ማስፈጸም ሲቻል ሰንሰለቱ እንዲበዛ ይደረጋል። ሰንሰለቱ በበዛ ቁጥር ለሙስና ተጋላጭ ይሆናል። አንዲት ትንሽ ጉዳይ ለማስፈጸም አራት አምስት መስኮት መሄድ የተለመደ ነው፡፡
የአንደኛው መስኮት አገልግሎት ሰጪ ሲኖር የሌላኛው መስኮት አገልግሎት ሰጪ ይጠፋል፤ በእዚያ ላይ አገልግሎት የሚሰጡት በተቋማዊ ሕግና መርህ ሳይሆን በግለሰባዊ ባሕሪያቸው መሠረት ነው። የአሠራሮች ውስብስብ መሆን ለሙስና ባሕል መዳበር መሠረት ሆኗል።
ደፈር ብለን እንናገር ከተባለ ግን ሕዝባችን ለሙስና ምቹ ነው። ደፋር እና ጠያቂ አይደለም። የራሱን የግል ጥቅም ብቻ ለማስጨረስ እንጂ እንደ ሀገር ምን ነውር አለው ብሎ ማሰብ እየቀረ ነው። እኔ ብቻ የዛሬን ልገላገል እንጂ የራሱ ጉዳይ የሚለው ብዙ ነው። “እኔ ተናግሬ ላይስተካከል” የሚል አጉል የስንፍና ልማድ አለ። ሁሉም እንዲህ እያለ ከተወው ታዲያ ማን ያስተካክለዋል?
የዛሬን ልገላገል እንጂ ብሎ ትቶት የሄደው ብልሹ አሠራር ነገ በሌላ መንገድ ራሱን ይጎዳዋል። “ሥራ ለሠሪው እሾህ ለአጣሪው” ነው ነገሩ። ስንሄድ ያደናቀፈን ድንጋይ ስንመለስ ካልተጠነቀቅን ወይም ድንጋዩን ካላነሳነው መልሶ እንደሚያደናቅፈን ማለት ነው። የዛሬን ልገላገል ብሎ መሄድ ለነገ እንቅፋት ማስቀመጥ ነው።
የዕለት የዕለቱን ብቻ እያሰቡና እያደረጉ መኖር ለልጅ ልጆች መጥፎ ነገር ማውረስ ነው። “ልጆቼን ላሳድግበት” የሚል ሰው ለልጆቹ የሰለጠነች ሀገር ነው ማውረስ ያለበት። አለበለዚያ ነገ ልጁ የሚቸገር ይሆናል ማለት ነው፤ ስደትን የሚመኝ ይሆናል ማለት ነው።
“አፈሩ ገራገር ምድሩ መቼ አሳጣን….!” እንዳለው ዘፋኙ፤ ስደትን የምንመኘው ሰው ሠራሽ በሆነ መንገድ የተበላሹ ነገሮችን ለመሸሽ እንጂ የኢትዮጵያ ተፈጥሮ የሚሸሽ ሆኖ አይደለም። ስለዚህ የሠለጠኑ ሀገራት እንዴት ቢያንስ በትንንሽ ነገሮች ይበልጡናል?
በነገራችን ላይ ሙስና ማለት የግድ ገንዘብ መስጠት ወይም መቀበል ብቻ አይደለም። ብዙዎች ሙስና ሲባል ቶሎ ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው ገንዘብ ከፍሎ የሆነ አገልግሎት ማግኘት ነው። ሙስና ግን ዓይነቱ ብዙ ነው።
በቀላሉ ከሚታወቁት የዝምድና እና የጓደኝነት ሙስናዎች ናቸው። ይሄ ማለት አንድን አገልግሎት ለማግኘት የእገሌ ዘመድ ነው አፋጥኑለት፤ የእገሌ ቤተሰብ ነው እንዲህ አድርጉለት እንደማለት ነው። ይህ ልማዳችን ከመሆኑ የተነሳ “የምታውቀው ሰው አለህ?” ብሎ መጠየቅ የተለመደ ሆኗል።
እዚህ ላይ አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ። የገንዘብ ሙስና ቢያንስ ጥፋት መሆኑ ይታወቃል፤ በገንዘብ ሙስና ከፍሎ ጉዳዩን ያስፈጸመ ሰው ያን ያህል በኩራት አይናገረውም። የሚገርመው ግን በዝምድና ወይም በጓደኝነት ወይም በሆነ የመግባባት አጋጣሚ በሚፈጸም ሙስና ጉዳዩን ያስፈጸመ ሰው እንደ ኩራት ነው የሚናገረው።
ብዙ ባለጉዳዮች ተሰብስበው እየጠበቁ እያለ፤ ከአገልግሎት ሰጪው ጋር ትውውቅ ያለው ሰው ዘው ብሎ ሲገባ አስፈቅዶ እንኳን አይደለም። ጭራሽ የእውቁልኝ አይነት ድርጊት(act) እያሳየ ነው የሚገባው። የዋዛ ሰው እንዳልመስላችሁ ከእንዲህ ዓይነት ሰው ጋር ቀረቤታ ያለኝ ሰው ነኝ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ከበታችነት ስሜት የሚመጣ ነው።
ይህ የዝምድና ወይም የጓደኝነት(በእንግሊዘኛው Nepotism የሚባለው ማለት ነው) ሙስና ከመለመዱ የተነሳ በድብቅ እንኳን መሆኑ ቀርቷል። አንድ ባለጉዳይ ከአገልግሎት ሰጪው ጋር ጓደኝነት ካለው ገና ሲገባ ሞቅ ያለ ሰላምታ ያቀርባል፤ እወቁልኝ ወዳጆች ነን መሆኑ ነው። ወረፋ የሚጠብቁትን ሰዎች አልፎ ለመሄዱ ምክንያቱን እየተናገረ ነው። እኔ እንደ እናንተ አይደለሁም የተለየ ቀረቤታ ያለኝ ነኝ እያለ መሆኑ ነው፡፡
እኛም ባለጉዳዮች አስመሳዮች ነን። ከአገልግሎት ሰጪው ፊት “ምን ስለሆነ ነው ከኋላ መጥቶ ለእሱ ቅድሚያ የምትሰጠው?” ብሎ የሚጠይቅ የለም፤ ቅር ቢለው እንኳን በውስጡ ያጉተመትማል ወይም ከጎኑ ካለ ሰው ጋር ይንሾካሾካል እንጂ ደፈር ብሎ አይናገርም።
ከአገልግሎት ሰጪው ጋር ትውውቅ የሌለው አንድ ባለጉዳይ ተሳስቶ እንኳን ወረፋ አልፎ ቢሄድ ግን ሁሉም በአንድ ድምጽ ይወርዱበታል፡፡
የአገልግሎት ሰጪው ዘመድ ወይም ጓደኛ የሆነ ሰው ያለወረፋው ሲገባ ግን ትንፍሽ የሚል ላይኖር ይችላል። ደፈር ብሎ የመናገር ልማድ ቢኖረን እንዲህ ዓይነት ብልሹ አሠራር ባሕል አይሆንም ነበር።
ኋላቀር ተብለን የምንወቀስባቸው ጉዳዮች በጣም ቀላል ነበሩ! በተለይም አገልግሎት አሠጣጥ ላይ የሚደረጉ ሙስናዎች ለሁሉም ሰው ተደራሽ ስለሆኑ ነውራችንን ያበዙታል። የሚማረር ሰው ይበዛል። ምንም እንኳን ራሱም የችግሩ አካል ቢሆንም “አይ! ይቺ ሀገር!” እያለ የሚያማርረው ይበዛል።
በእንደዚህ ዓይነት ትንንሽ ሙስናዎች የሀገር ገጽታ እንዳይበላሽ መንግሥት አሠራሩን ያስተካክል፤ ሕዝቡም የነቃ እና ብልሹ አሠራርን የማይታገስ ይሁን!
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም