“አይዞሽ ገለቴ …!?”

በቴዲ አፍሮ “ቀነኒሳ አንበሳ፤”የተቀነቀነለት ታላቁና ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እኤአ በ2009 በበርሊን የዓለም ሻምፒዮን አሸንፎ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጠ እያለ፤ በ1500 ሜትር ውድድር በአንደኝነት ልታጠናቅቅ ትንሽ ሲቀራት የስፔኗ አትሌት ናታሊያ ሮድሪጌዝ ጠልፋ ትጥላትና ወርቅ የማሸነፍ ዕድሏ ይጨናገፋል። ጉልበቷም ክፉኛ ይጎዳል። ሆኖም ከወደቀችበት ተነስታ ሕመሟን እንደ ምንም ችላ ተነስታ ውድድሩን ጨርሳ 10ኛ ሆና አጠናቃ ግን ደግሞ ለሕክምና ስትወሰድ ሲያያት የቀጥታ ጋዜጣዊ መግለጫውን አቋርጦ ወደ ገለቴ ዞሮ “አይዞሽ ገለቴ! አይዞሽ! አይዞሽ በቃ! ምን እናድርግ! ምንም ማድረግ አይቻልም! አይዞሽ!” ይላታል። የሚያሳዝነው ገለቴን ጠልፋ የጣለቻት ናታሊያ መቀጣትና መጠየቅ ሲገባት ወርቅ ማሸነፏ ዛሬ ድረስ ግራ እንዳጋባ አለ።

በዓለም የአትሌቲክስ አደባባይ ይህ ግፍና ፍርደ ገምድልነት ሲፈጸምባት ያየው ቀነኒሳ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት “አይዞሽ ገለቴ” ያላት መጽናኛና ቁጭት ዛሬ ግዘፍ ነስቶ ሥጋ ለብሶ እንደገና በአሳዛኝ ሁኔታ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ “አይዞሽ ገለቴ!” ለማለት ተገዷል። በወቅቱ ተገቢውን ትኩረት ባያገኝም ይህ ንግግር ተምሳሌታዊ ጭምር ነው። ሴት ሀገር ናት። ሴት እናት ናት። ሴት ሚስት ናት። ሴት እህት ናት። ሴት ልጅ ናት።

አይዞሽ ገለቴ ሲባል! አይዞሽ ሀገሬ! አይዞሽ እናቴ! አይዞሽ ባለቤቴ! አይዞሽ ልጄ! አይዞሽ እህቴ! ማለት ነውና። ይህ ድምፅ ግን ከዚህ ባሻገር ተቋማዊና መዋቅራዊ ሊሆን ይገባል። ይሄን መሰል ግፍ በገለቴ ሊበቃ ይገባል። ለመግቢያ ያህል ይሄን ካልሁ ወደ ሰሞነኛው አስደንጋጭና አሳዛኝ ከፍ ሲልም ጀግኒትን ልንጠብቃትና ልንደርስላት ባለመቻላችንና ከጥቃት ልንታደጋት ሲገባ ችላ በማለታችን ልናፍርበት ወደሚገባው የአትሌቷ አሳዛኝ ታሪክ እና ከሪፖርተር ወደ አገኘሁት የአርፋጁ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መግለጫ እንለፍ።

ከአትሌቷ ከግል ሕይወት ጋር ተያይዞ መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ በዚህ ደረጃ ገፍቶ አደባባይ ይውጣ እንጂ፣ በሌሎችም በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ሲፈጸም የነበረ፣ አሁንም እየተፈጸመ የሚገኝ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጉዳዩን ይፋ አድርጎታል።

‹‹እንደ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አትሌትም የኢትዮጵያ አትሌቶች ብዙ ጥሩ ጎን እንዳላቸው ሁሉ፣ ጥሩ ኑሮ የሚኖሩ የመኖራቸውን ያህል፣ በዚያው ልክ ደግሞ ለሀገራቸውና ለሰንደቅ ዓላማቸው ከሠሩት በተጓዳኝ መጥፎ ሥራና በመጥፎ ሕይወትም የሚኖሩ ስላሉ፣ ይህን ክፍተታቸውንና ድክመታቸውን በመጠቀም ብዙ ግፍና በደል የሚደርስባቸው አሉ። እኛም እንደ ፌዴሬሽን ከእነዚህ አትሌቶች ጎን የምንቆም መሆናችንን ለሕዝባችን ለማሳወቅ ዛሬ የመገናኛ ብዙኃንን የጠራነው፤›› በማለት መግለጫውን የጀመሩት የፌዴሬሸኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን፣ መግለጫው ያስፈለገው ደግሞ ገለቴ ቡርቃ ከሰሞኑ ከግል ሕይወቷ ጋር ተያይዞ ለመገናኛ ብዙኃን ባጋራችው ከግል ሕይወቷ ጋር የተያያዘ በደል፣ ‹‹አትሌቷ ያለችበትን ሁኔታና እንደተቋም ምን ማድረግ ይኖርብናል፤›› የሚለውን ለመግለጽ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።

ገለቴ ቡርቃ በግል ሕይወቷ ላይ እየደረሰ ያለውን ብሶትና መከራ የእሷ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችም ብዙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተመሳሳይ ችግር የሚደርስባቸው ስላሉ፣ እነሱንና የወደፊቶቹ ተተኪ አትሌቶች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይደርስባቸው፣ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በሞራልም በተወሰነ ደረጃ ከጎናቸው መሆናቸውን ለመግለጽ እንደሆነ ያብራሩት ኮማንደር ስለሺ፣ በዋናነት ግን ዓለም አቀፉ ተቋም የአትሌቶችን ሁለንተናዊ ደኅንነት ለመከላከል (Safe Guarding) በሚል አዲስ መመሪያ ለአባል ፌዴሬሽኖች አውርዷል። መመሪያው ሴቶች፣ ወንዶችና ሕፃናት ሁሉም ምንም ዓይነት የመብት ጥሰት ሳይደረግባቸው፣ በነፃነት እንዲወዳደሩ የሚያስችል ነው። በመሆኑም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የመመሪያውን አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን፣ መመሪያው ተግባራዊ የሚሆንበትን ሁኔታ አስመልክቶ የደረሰበትን ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።

መመሪያው በአሁኑ ወቅት በኬንያና በደቡብ አፍሪካ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ያሰረዱት ኮማንደር ስለሺ፣ በቅርቡ ወደ ኃላፊነት የመጣው የፌዴሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድም ላለፉት ሦስት ወራት መመሪያውን የተመለከቱ ዝርዝር ሰነዶችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል። መመሪያው ሕግ እንዲሆን፣ ኃላፊነቱ የፌዴሬሸኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን የሚዘጋጅ ስለመሆኑ ጭምርተናግረዋል፡፡

ኮማንደር ስለሺ በተጨማሪም መመሪያው የፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ሌሎችም የፍትሕ አካላትን የሚያካትት ስለመሆኑ ጭምር አክለዋል። መመሪያው ተግባራዊ የሚሆነው ደግሞ ልክ እንደ አበረታች ንጥረ ነገር (ዶፒንግ) ሁሉ፣ መንግሥት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊያፀድቀው የሚገባ እንደሆነም አስረድተዋል።

ዎርልድ አትሌቲክስ ለአትሌቶች የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥበቃ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን ያወረደው ይህ መመሪያ፣ በአኅጉር ደረጃ በኬንያና በደቡብ አፍሪካ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ያስረዱት ኮማንደር ስለሺ፣ ለመመሪያው አስፈላጊነት ማጣቀሻ ሲሉ ያከሉት ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2021 15,000 እና 10,000 ሜትር ተወዳዳሪ የነበረችው ኬንያዊት አትሌት አግነስት ቲሮፕ ላይ በባለቤቷ

አማካይነት ግድያ እንደተፈጸመባት፣ በሌሎችም ሀገሮች የዚህ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙን ተከትሎ ችግሩን ለመከላከል ደግሞ መመሪያው የግድ ተግባራዊ መደረግ ያለበት መሆኑን ነው ያስረዱት። ችግሩ በዋናነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ላይ ጎልቶ የሚታይ እንደሆነ፣ ጥቃቱ በወንዶችም ላይ እንደሚፈጸም ተናግረዋል።

የገለቴን ጉዳይ በተመለከተ ሕግ የያዘው ጉዳይ በመሆኑ ምንም ማለት እንደማይፈልጉ ያከሉት ኮማንደር ስለሺ፣ ነገር ግን ገለቴ በበርካታ ውድድሮች አብራቸው የሮጠች መሆኗ፣ ባለቤቷንም በተወሰነ መልኩ የሚያውቁት እንደሆነና አልፎ አልፎ በመሐላቸው ችግሮች እንደነበሩና አንዳንድ አለመግባባቶች እንደነበሩ፣ አለመግባባቱን ተከትሎ በተለያየ መልኩ ድጋፍ እንደምትሻ፣ ላለፉት አንድ ዓመታት ያህልም ከልምምድ የራቀች ስለመሆኗ መስማታቸውን ጭምር አስረድተዋል። ኢትዮጵያውያን ሊያውቁት የሚገባው ነገር ቢኖር ተመሳሳይ ችግር የሚገጥማቸው በጣም ብዙ ገለቴዎች መኖራቸውን ነው፣ አሉም ብለዋል።

ዎርልድ አትሌቲክስ ለአባል አገሮች ያወረደውን መመሪያ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የፌዴሬሽኑ የሕክምና ባለሙያ አያሌው ጥላሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹መመሪያው ‘እኛ’ ኢትዮጵያውያን ካልሆነ ሌሎች ሀገሮች ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። አሁን ላይ ግን ሰነዱን አዘጋጅተን ጨርሰናል፤›› ብለው፣ ‹‹አትሌቶች ይህንን በመሰለ ጉዳይ አደባባይ ሲወጡ በግሌ ‹‹የሐዘን ቀኔ ነው፤›› ከ30 ዓመታት በላይ ከአትሌቶች ጋር ቆይቻለሁ። አትሌቶቼ ይለፋሉ፣ ይታገላሉ፣ ባሎች አሠልጣኞችና ማናጀሮች ፊሸካ ይነፋሉ፣ አትሌቶቻችን ደግሞ ወርቅ፣ ብርና ነሐስ ያመጣሉ። መንግሥት ይደሰታል። ሰንደቅ ዓላማ ከፍ እንዲል ምክንያትም ናቸው። ነገር ግን ከጀርባቸው ትልቅ ችግር አለ። ከጀርባቸው እስከ ሞት የሚያደርስ፣ እስከ ልመናና ስደት የሚያደርስ ነገር አለ። የት? ኢትዮጵያ ውስጥ። የተደበቀ የሚያለቅስና የሚያነባ ዓይን በጣም በብዙ አለ። ‹‹አትሌቶቻችን፤›› በማለት በጥቅሉ አደባባይ የወጣውን የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን መከራና ስቃይ ምን ያህል ሥር የሰደደ እንደሆነ በግልጽ ተናግረዋል።

‹‹ዎርልድ አትሌቲክስ ሁለንተናዊ ጥበቃ ለሴትም ለወንዱም አትሌት፣ ለአሠልጣኙም፣ ለማናጀሩም በተቃራኒው ደግሞ ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ ወንጀል የሚሠሩትን የሚከታተል (Safe Guarding) ዓለም ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፤›› የሚሉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሴፍ ጋርዲንግ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ1923 ጀምሮ እንደሆነ፣ መመሪያው በተለይም በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በኩል ብዙ የተሄደበት መሆኑ፣ እኛስ ወደሚለው ስንመጣ ደግሞ አሁን ላይ ሰነድ አዘጋጅተን ያጠናቀቅንበትና ገና ወደ ሥራ ለመግባት እየሄዱ ስለመሆኑ ነው ያስረዱት።

መመሪያው ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በተጨማሪ በዩኔስኮና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ብዙ እንደተሠራበት ያከሉት (ዶ/ሩ)፣ ‹‹እኛ ጋ ግን በጣም ዘግይቷል። ምክንያቱ ደግሞ ዎርልድ አትሌቲክስ መመሪያውን አምኖበት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ በመሆኑ ነው። አትሌቶች እየተሸጡ ወደ ሌላ ሀገር መዘዋወርን ጨምሮ በአሠልጣኞች፣ በማናጀሮች፣ እንዲሁም በፌዴሬሽኖች አማካይነት የፆታ ትንኮሳ፣ የሀብት ዝርፊያ፣ የጉልበት ብዝበዛ እየበዛ ሲመጣ ነው።

ይህ መመሪያ ተግባራዊ እንዲደረግ ግድ እያለ የመጣው። ወንጀሉና ዝርፊያው በዋናነት እየተበራከተ የመጣው ደግሞ በአሠልጣኙ፣ በማናጀሩና ፌዴሬሽኑን ጨምሮ በራሳቸው በአትሌቶቹ ነው። ለዚህም ነው ዎርልድ አትሌቲክስ ከእንግዲህ ይብቃ በሚል መመሪያውን አስገዳጅ ያደረገው፤›› ብለው፣ አባል አገሮች በጉዳዩ የአደጋ ትንተና (Risk Assessment) በማካሄድ አትሌቶች ከሚደርስባቸው ሁሉን አቀፍ ችግርና መከራ እንዲከላከሉ ዎርልድ አትሌቲክስ በፅኑ የሚያምን ስለመሆኑ ጭምር አያሌው ጥላሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል። ፌዴሬሽኑ ምንም እንኳ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀመርኩ ቢልም ትንሽ ሃሳብ ላዋጣ።

በምሥራቅ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አትሌቶች ብዝበዛን፣ አዕምሯዊ እና አካላዊ ጥቃትን እና ከሥራ በኋላ ያለመረጋጋትን ጨምሮ ስጋታቸው እየጨመረ ነው። ለሀገራዊ ኩራት እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ቢኖራቸውም፤ እንደ ሀገር ባለውለታነታቸው ተገቢው ጥበቃና ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑ የተደጋጋሚ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል። የትምህርት፣ የጤና እና የተቋማት ማሻሻያ በማድረግ የአትሌቶችን ደኅንነት፣ ክብር እና እድገት የሚያረጋግጥ ክልላዊ የጥበቃ ማሕቀፍ ያቀርባል።

የምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ በአትሌቲክስ ብቃታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ቢያገኙም፣ ብዙ አትሌቶች በተለይም ወጣቶች እና ሴቶች ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋልጠዋል። ከዚህም በላይ እስከ ግድያ የደረሰ ጥቃት የተፈጸመባቸው አትሌቶች መኖራቸው አይዘነጋም። በአሠልጣኞች፣ ወኪሎች እና ተቋማት የሚደርስባቸው እንግልት እና ብዝበዛ፤ በዚህ የተነሳ የደረሰባቸው የአካል እና የአዕምሮ ጤናን ችላ ማለት፤ የሕግ ጥበቃ እና ከለላ አለመስጠት፤ በአትሌቲክስ ተሳትፏቸውም ሆነ ጡረታ ከወጡ በኋላ በቂ የሆነ ድጋፍ የማይደረግላቸው መሆኑ በደሉን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል። እነዚህ በደሎችና ግፎች በግንዛቤ ውስንነት፣ በአስተዳደር ደካማነት እና በተቋማዊ እንዝህላልነት የተነሳ ዛሬ ላይ ደርሷል። የመፍትሔ ሀሳቦችን ወይም የፖሊሲ ሀሳቦችን ላንሳ፦

  1. አትሌቶችን ለመጠበቅ ሁሉን አቀፍ የሕግ እና ተቋማዊ ማሕቀፍ መፍጠር።
  2. የአትሌቶችን አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ደኅንነት ማረጋገጥ።
  3. አትሌቶች በትምህርት፣ በማማከር እና የፋይናንሺያል እውቀት ኖሯቸው በዘላቂና አዋጭ ኢንቨስትመንት እንዲሠማሩ መደገፍና መከታተል።
  4. አትሌቶችን ያማከለ የተጠያቂነት እና የደኅንነት ባህል መገንባት።

እንደ ድፍረት ካልተቆጠረብኝ ቁልፍ የፖሊሲ ምክሮችን ላክል፤

  1. የሕግ እና ተቋማዊ ማሻሻያ፦ የአትሌቶች ጥበቃ ሕግ በኢትዮጵያ በማውጣት ከክልላዊ አጋሮች ጋር መስማማትና መሥራት። በስፖርትና ባህል ሚኒስቴር ወይም በተጓዳኝ አካል ስር የአትሌት ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋም። በሁሉም የስፖርት ፌዴሬሽኖች እና የአትሌቲክስ አካዳሚዎች ውስጥ የጥበቃ ኦፊሰሮችን መመደብ።
  2. የጤና እና የጤንነት ጥበቃ፦

የግዴታ የጤና እና የአዕምሮ ጤንነት ምርመራዎችን በየጊዜው የሚተገበርበትን አሠራር ተቋማዊና መዋቅራዊ ማድረግ።

የስፖርት ሳይኮሎጂ አገልግሎቶችን መስጠት እና አሰቃቂ በደልና ግፍ ለተፈጸመባቸው አትሌቶች ተከታታይነት ቀጣይነት ያላቸው የድጋፍና የክብካቤ መርሐ ግብሮችንና የጊዜ ሰሌዳዎችን ማዘጋጀትና ተግባራዊነታቸውን በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት ያሻል።

  1. የትምህርት እና የሙያ ድጋፍ ማድረግ፦ ከስፖርት ሥልጠናዎች ባልተናነሰ የአካዳሚ እና የሙያ ሥልጠናዎችን ማመቻቸት፤ የአሠልጣኝነት ፈቃዶችን እንዲያገኙ፤ በሥራ ፈጠራ ላይ ድጋፍና ሥልጠና መስጠትን ጀምሮ የአትሌቶችን የጡረታ ሽግግር በአግባቡ መከታተልና መደገፍ አንዱ ቁልፍ የፖሊሲ አካል ሊሆን ይገባል። እንዲሁም የአትሌቶችን የፋይናንስ እውቀት እና የሕግ ግንዛቤ የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎችን ድጋፎች ጎን ለጎን ማካሄድ ያስፈልጋል።
  2. ፆታን ከግምት ያስገባ የጥበቃና የከለላ ስልት መንደፍ፦ በተለይ ሴት አትሌቶችን ለሚያሠለጥኑ አሠልጣኞች ጥብቅ የሥነ ምግባር ደንቦችን ማዘጋጀት እና የአሠልጣኞችን የኋላ ታሪክ ወይም ዳራ የሚመረምር አሠራር ማበጀት ያስፈልጋል። እንዲሁም ሴት አትሌቶች በሥልጠና እና በውድድር ወቅት ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ እና መጠለያ ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ ፕሮቶኮል ማስቀመጥ ግድ ይላል። በሴቶች የሚመሩ የምክር አውታረ መረቦችን ወይም የሜንቶር ትስስሮችን መፍጠር፤ ሴቶችን ወደ አመራርነት የሚያመጣና የሚያበቃ አሠራር ማስቀመጥ ሌላው ቁልፍ የፖሊሲ ሀሳብ ነው ማለት ይቻላል።
  3. የማኅበረሰብ እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ (Community and Stakeholder En­gagement)፦ አሠልጣኞች እና በአንድም በሌላ መልኩ ከአትሌቶች ጋር የሚሠሩ ሰዎች አትሌቶችን ከጥቃት ለመከላከል እንዲችሉ እና አንዳንዶቹም የፆታዊ ጥቃቱ ፈጻሚ ወይም ተባባሪ እንዳይሆኑ የሥነ ምግባር ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል። በተጨማሪም የአትሌት ቤተሰቦችን እና ማኅበረሰቦችን በአትሌቶች መብት እና ሊያጋጥማቸው በሚችል ጥቃት ላይ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ ማሳተፍ ያሻል። የአትሌቶችን ግላዊነት /privacy/ እና ክብር ለመጠበቅ ለሚዲያው እንዲሁ ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል።
  4. ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ትብብሮችን መፍጠር፦ የአትሌቶችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ ቀጣናዊና አኅጉራዊ ቻርተር ማዘጋጀት። አቅምን ለመገንባት እና ፕሮግራሞችን ለማስፋት ከዩኔስኮ፣ ከ ILO፣ ከኦሎምፒክ ኮሚቴዎች እና ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር መተባበር። በአኅጉራዊና በዓለማቀፋዊ መድረኮች እና ጉባኤዎች ምርጥ ልምዶችን መጋራት ያሻል።

ይሄን ለመፈጸም የትግበራ እቅድ ወይም መርሐ ግብር ማዘጋጀት ይገባል። ዕቅዱ የሚከተሉትን ተግባራት ያካትታል። የደኅንነት ሕግ ማርቀቅና እና ማፅደቅ፤ በዚህ ሂደት የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ፓርላማ፣ የሕግ ባለሙያዎችንና የሕዝብ ምክክር መድረኮችን ማመቻቸት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። እንዲሁም የኦምቡድስማን እና የሪፖርቲንግ ሥርዓቶች መዘርጋት፤ በዚህ ዙሪያ የሚሠራ የብሔራዊ የአትሌቶች ምክር ቤት ማቋቋም፤ ለፌዴሬሽኑም ሆነ ለኦሎምፒክ ኮሚቴው ሠራተኞች ሥልጠና መስጠት፣ የድንገተኛ አደጋ ማሳወቂያ የግንኙነት መስመር መሠረተ ልማት መዘርጋት፤ በትምህርት ቤቶች፣ በአትሌቲክስ ክለቦች የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን ማስጀመር የዕቅዱ አካል ሊሆን ይገባል።

ይህን ዕቅድ ያስቀመጠውን ግብ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማሳካት የክትትል እና የግምገማ አግባብ ሊቀመጥ ይገባል። በስፖርት ተቋማት ውስጥ በየስድስት ወሩ የደኅንነት ኦዲት ማካሄድ፤ የአትሌቶች ስምና ማንነት ሳይገለጽ የአሰሳ ጥናቶችን ጥቆማዎችን እና የአስተያየት መስጫ ስልቶችን መቀየስ ያስፈልጋል።

ማጠቃለያ

አትሌቶችን መጠበቅ ሥነ ምግባራዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያም ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ላይ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው። ኢትዮጵያ በምሳሌነት መምራት፣ ሻምፒዮኖቿን በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ በመጠበቅ እና በማብቃት ላይ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ አርዓያ መሆን ትችላለች።

“አይዞሽ ገለቴ !”

ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)  fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You