ልክ እንደ አሁኑ የሰው ልጅን የመኖር ህልውና የሚፈታተንና የጤና፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ተፈጥሮአዊ ቀውስ ሲያጋጥም የስነ ልቦና፣ የስነ አእምሮ እና ማህበራዊ ሰራተኞች ሚና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዙሪያ በኮቪድ 19 የተጠቃው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡
ይህ ደግሞ የዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚ መለወጥን፣ የማህበራዊና ጤና ሥርዓት መዛባትን በመፍጠሩ ይህ ሁኔታ የሰው ልጅን ተለምዶአዊ የቀን ተቀን ግላዊና ማህበራዊ የአኗኗር ዘይቤ ከእለት ወደ እለት እየለወጠው ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ሰዎች ለከፍተኛ ፍርሀት፣ ውጥረት፣ ጭንቀት፣ ድብርት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ስጋት፣ ወዘተ ተጋላጭ ሆነዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች ደግሞ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ እንዲሁም ሥነ አእምሮአዊ ድጋፍና እንክብካቤ፣ ስልጠና እና ትምህርት፣ እንዲሁም ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡
በተለይ ለህመሙ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ስለ አእምሮ ጤና ዝቅተኛ ግንዛቤ ላላቸው ሰዎች እንዲሁም በወረርሽኙ ምክንያት በሀገር ላይ በተከሰተው ስጋትና ፍርሀት ለጠቅላላው ህዝብ እንዲሁም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በአገልግሎቱ ስራ ላይ በቀዳሚነት ለሚገኙ በሆስፒታሎች እና በኳራንታይን ወይም ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች፣ የጤናውን አገልግሎት ድጋፍ ለሚሠጡ ሰራተኞች ለምሳሌ የፅዳት፣ የጥበቃ፣ የሹፌርና፣ የቀብር አስፈፃሚ ሰራተኞች፣ የምግብ አገልግሎት አቅራቢ ሰራተኞች፣ የጥገና ሰራተኞች፣…ወዘተ እንዲሁም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በአመራርነትና በማስተባበር የሚሰሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሰራተኞች የስነ ልቦና እና የአእምሮ ጤና ለመጠበቅ የባለሙያዎች አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡
ከሀገራችን ኢትዮጵያ ጠቅላላ ህዝብ ቁጥር ከ20 እስከ 25 ፐርሰንት የሚጠጋው ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ በሚደርስ የሥነ ልቦና እና የአእምሮ ጤና ችግሮች ተጠቂ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት (እ.ኤ.አ. 2015) ጥናት ያሳያል፡፡ ይህም ጉዳይ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በአንድ አገር የፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ በአኗኗርና የልማት እንቅስቃሴ ላይ ጫና የሚፈጥር እንደሆነ አሳስቧል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገሮች የሥነ ልቦና እና የአእምሮ ጤና ችግሮች በሰፊው ተጠቂ የሆኑ ሀገራት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
አሁን በደረሱበት የአእምሮ ጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ትኩረት አንጻር የኮሮና በሽታ ወረርሽኝ የሚያስከትለው ሥነ ልቦናዊ እና አእምሮአዊ ጤና ችግሮችን ለመከላከል፣ ለማከምና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሆኔታዎች ሊፈጥር እንደሚችል በማንሳት እያንዳንዱ ሀገር ከወረርሽኙ ጋር የሚፈጠሩ ተጓዳኝ የአእምሮ ጤና ችግሮችን ከወዲሁ በጥንቃቄ በመከታተል አስፈላጊውን እርዳታና ህክምና ለመስጠት በሚያስችል መልኩ በቂ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ (ግንቦት 15 ቀን 2020) በሰጡት መግለጫ መክረዋል፡፡
ስለዚህ ከህመም ያገገሙ፣ ቤተሰባቸውን በወረርሽኙ ምክንያት በሞት ያጡ፣ ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ፣ ከተለያዩ ሀገሮች ወደ ሀገር ውስጥ በተለያየ መንገድ በአየር፣ በውሃ እንዲሁም በየብስ ትራንስፖርት ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የግዳጅ ማቆያ ውስጥ ያሉና ግዳጃቸውን የጨረሱ ሰዎች ወደ ማህበረሰቡ በማቀላቀል እና መልሶ በማቋቋም በሚደረገው ስራ የስነ ልቦና፣ የሥነ አእምሮ እና የማህበራዊ ሠራተኞች ድጋፍ ትልቅ ሚና አለው፡፡
የእነዚህ ባለሙያዎች አገልግሎት ከፍተኛ የአእምሮ ጥንካሬ፣ ጊዜንና በአብዛኛው ከሰው ባህሪ ጋር የተገናኘ በመሆኑ በባለሙያዎች ላይ አእምሮአዊ፣ ስሜታዊ እና አካላዊ ጫና ማሳደሩ የማይቀር ስለሆነ ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን እንዳለበትም ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡
በመሆኑም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የስነልቦና እና ማህበራዊ አገልግሎት (Psychosocial Service) ባለሙያዎች ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡
- በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚሰራ ማንኛውም ተግባር ላይ የሰው ልጅ ባህሪን በመተንተን፣ በመግለፅ፣ መጪውን በመተንበይ እና የባህሪ ለውጥ በምን መልኩ ሊመጣ እንደሚችል ያማክራሉ እንዲሁም ሳይንሳዊ ሥነ ዘዴዎችን በመጠቀም የግለሰቦችና የማህበረሰቡ ባህሪ ለውጥ እንቅስቃሴ ተግባር ላይ ይሰራሉ፤
- የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከኮሮና ወይም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል እና መቆጣጠር ስራ ጋር ቀን ተቀን እያገለገሉ ያሉ ባለሙያዎች ላይ ከስራቸው ጫና እንዲሁም ከግለሰባዊ ስብዕና ማንነታቸው ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸውን የስነ ልቦና እና ሥነ አእምሮአዊ ችግሮች ድጋፍ እና እርዳታ ይሰጣሉ፤
- የመጀመሪያ የስነ ልቦና ህክምና እርዳታ (Psychological First Aid) ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁሉ ድጋፍ ይሰጣሉ፤
- ከኮሮና ወይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ የተሳሳቱ አመለካከቶች፣ ዕምነቶችና ዕውቀትን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ለማምራት የሚያስችሉ ሳይንሳዊ መንገዶችን ይጠቁማሉ እንዲሁም እንዲስተካከሉ የራሳቸውን ሙያዊ እገዛ ይሰጣሉ፤
- ከኮሮና ወይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለስነ ልቦና እና አእምሮአዊ ችግር የተጋለጡ ግለሰቦችን (ለምሳሌ በህመሙ የተያዙ፣ ከህመም ያገገሙ፣ ቤተሰባቸውን በወረርሽኙ ምክንያት በሞት ያጡ፣ ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ውስጥ የገቡ፣ ከተለያዩ ሀገሮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የግዳጅ ማቆያ ውስጥ ያሉና ግዳጃቸውን የጨረሱ፣ በአጠቃላይ ለምልሀት ህዝቡ … ወዘተ) ያማክራሉ፣ ያግዛሉ፤ በኮሮና ወይም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ማህበረሰቡ ላይ የደረሰውን የስነ ልቦና ጫና በተለይም ህፃናትን፣ ታዳጊዎችን፣ ወጣቶችን፣ እናቶችን፣ አረጋውያንን ወይም በዕድሜ የገፉ ሰዎችን፣ አካል ጉዳተኞችን እንደ ዕድሜአቸው እና የችግራቸው መጠንና ዓይነት ያማክራሉ፣ ይደግፋሉ፤
- የኮሮና ወይም ኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል፣ መቆጣጠር እና የማከም አገልግሎቱን ለሚመራው የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የክልል ጤና ቢሮዎች እና በተዋረድ ለሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች በስነ ልቦናዊና አእምሮአዊ ጤና አገልግሎት ዙሪያ ያማከራሉ ፣ ይደግፋሉ፤
- የኮሮና ወይም ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተመለከተ የስነ ልቦና እና ማህበራዊ እንዲሁም የሥነ አእምሮአዊ ጤና አገልግሎት ማስተግበሪያ መመሪያዎች፣ ስታንዳርዶች፣ ፕሮቶኮሎች፣ የድርጊት መርሀ ግብሮችን ያዘጋጃሉ፤ እንዲተገበር ያስተባብራሉ፣ ይተገብራሉ፤
- በኮሮና ወይም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የሚተላለፉ የጤና ተግባቦት ስራዎች (መረጃዎች፣ ማስታወቂያዎች፣ ሙዚቃዎች፣ መዝሙሮች፣ ነሺዳዎች፣ የባለሙያ ትንታኔዎች …. ወዘተ) የማህበረሰቡን ስነ ልቦና፣ ሃይማኖታዊ ህግጋቶች፣ ማህበረሰባዊ እሴቶች፣ ልምዶችና ባህሎችን በማይጥስ መልኩ እንዲተላለፉና ከተላለፉም አስፈላጊው ማስተካከያ እና እርምት እንዲደረግባቸው የሚዲያ ተቋማትን፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ያማክራሉ፣ ያግዛሉ፤
- በኮሮና ወይም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በማህበረሰቡ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ድህረ ወረርሽኝ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ጫናዎችንና ችግሮችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ አስፈላጊ ጥንቃቄዎች እና እገዛዎች እንዲደረጉ ይጠቁማሉ፡፡ እንዲሁም መልካም አጋጣሚዎችን የማህበረሰቡ ዕሴትና ባህል ሆኖ እንዲቀር ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ጋር ተባብሮ እንዲሰራ አስፈላጊውን የሙያ ድጋፍ ያደርጋሉ፤
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012
ወርቅነህ ከበደ
(ሳይኮሎጂ ት/ቤት – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)