ስኬታማ ሰዎችን ከሌሎች ሰዎች ከሚለዩዋቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛውና ዋነኛው ነጥብ መጥፎ አጋጣሚዎችን አቅጣጫቸውን አስቀይረው ለመልካም ነገር የመጠቀም ችሎታቸው መሆኑን ከሦስት ሳምንታት በፊት በዚሁ አምድ ላይ ለመጠቆም ሞክረን እንደነበር እናስታውሳለን። ችግር ሲገጥመን “ለምን ሆነ?” በሚል ጧት ማታ እያብሰለሰልን የበለጠ ችግር ውስጥ ራሳችንን ከማስገባት መፍትሔው ላይ በማተኮር ችግሮችንና የፈተና ጊዜያትን ከቀደሙ ችግሮቻችን ለመውጣትና እንዲያውም የበለጠ ስኬት ለማስመዝገብ እንደ መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምባቸው እንደምንችልም ለማሳየት ሞክረናል። እነሆ ዛሬም ከመሻሻል ይልቅ ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ በጭንቀትና በፍትሃት የበለጠ ችግር ውስጥ በመግባት ፋንታ አስተሳሰባችንን ከችግሮቹ በላይ በማድረግ እንዲህ ዓይነት የፈተና ጊዜያትን ዒላማቸውን አስቀይረን ለመልካም ለመጠቀም በሚቻልበት መንገድ ላይ ተጨማሪ ሃሳቦችን ይዤ መጥቻለሁ። ከዚህ ቀደም አይታው በማታውቀው መንገድ ክፉኛ ዓለማችንን እየተፈታተነ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሃገራችን የገባው ዘግይቶ እንደመሆኑ መጠን ስርጭቱ ከመቀነስ ይልቅ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።
ይህም ከእስካሁኑ የበለጠ ከበሽታው እንድንጠነቀቅ የሚያስገድድ ሆኗል። ለጊዜው እጃችን ላይ ያለው ራስን ከበሽታው የመጠበቂያና የመዳኛ መንገድ ደግሞ በቤት ውስጥ መቆየትና አካላዊና ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ብቻ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል። ምክንያቱም ከምንም በላይ ነጻነቱን በሚፈልገው የሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ ካልተንቀሳቀሱ ለመኖር እጅግ ከባድ የሆነበት የእኛ ሃገር የኑሮ ሁኔታ ሲጨመርበት በቤት የመቆየቱን ነገር ከባድ ስለሚያደርገው ነው። ያም ሆኖ ግን የምንፈልገውን ነጻነታችንንና የምንጓጓለትን ነጋችንን ለማየት ህይወታችንን ጠብቆ ለማቆየት ከዚህ የተሻለ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ አንችልምን ሳይሆን እንችላለንን አስቀድመን የቱንም ያህል ቢከብድ ፈተናውን በአሸናፊነት ለመወጣት መከላከያውን ተግባራዊ ለማድረግ እንገደዳለን። እንዲያውም ዓይናችንን ከፍተን በጠቢባኑ መንገድ ከተጓዝን ችግሩን ከመቋቋምና በአሸናፊነት ከመወጣት ባሻገር ቤት የምንቆይባቸውን ጊዜያት በህይወታችን ውስጥ ከዚህ ቀደም ያላሰብነውን በረከት ለመቋደስና ታላቅ ነገርን ለመፈጸም እንደ መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምባቸው እንችላለን። እንዴት አድርገን? ቀጣዩ ክፍል ይህን ጥያቄ የሚመልስ ይሆናል።
ፈጣሪ ፈቃዱ ሆኖ አስጨናቂው በሽታ ከምድራችን እስኪወገድ ድረስ ራሳችንንና ወገኖቻችንን በህይወት ለመጠበቅ ግድ ሆኖብን ቤት ውስጥ በምንቆይባቸው ጊዜያት በርካታ ሰኣታትን በብቸኝነት የምናሳልፍበት ዕድል ሰፊ ነው። ይህም ዘወትር በማይሞላው ዓለም ውስጥ ያለ እረፍት ከምንባዝንበት ፋታ ከሌለው የጥድፊያና የሩጫ ኑሯችን መለስ ብለን ለራሳችን ጊዜ እንድንሰጥና የእስካሁኑን ህይወታችንን ቆም ብለን እንድንመረምር ከዚህ ቀደም ያላገኘነውን መልካም አጋጣሚ ይፈጥርልናል። ምናልባትም በቀን ተቀን የኑሮ ትግላችን ላይ ተጠምደን፣ የትም ባላዳረሰን በተለመደው የድግግሞሽ ህይወት ላይ አተኩረን የተፈጠርንለትን ዋናውን ዓላማ ረስተን ትርጉም አልባ ህይወት ኖረን ለማለፍ እየተጣደፍን ይሆናል። “ራስን ማሸነፍ” በሚል ቅርብ አዳሪ ፍልስፍና ተሸንፈን “በልቶ የማደር” ግባችንን ለማሳካት ታላቁን “ሰምቶ የማደር” ዓላማችንን ሰውተን በከንቱ ኖሮ ለማለፍ እየሮጥን ይሆናል።
እናም ክፉውን ጊዜ ለማሳለፍ ቤት ውስጥ መዋላችን ከተለመደው ሞልቶ የማይሟላ የጥድፊያና የጫጫታ ኑሮ ወጥተን ትክክለኛውን የህይወት ጥሪችንን በመስማትና በማዳመጥ እውነተኛው የተፈጠርንለት ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ ዕድል ይሰጠናል። በምድር ላይ ሲኖሩ ደግሞ የተፈጠሩለትን ዓላማ ማወቅና ያንን ፈጽሞ ከማለፍ የበለጠ ታላቅ ነገር የለም። የሰው ልጅ በባህሪው ሲፈጠር እኩል ነው ከሚሉት ወገን እመደባለሁ። ይሁን እንጂ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ የተሻለ ብቃት እንዳላቸው በገሃዱ ዓለም የምንታዘበው ሃቅ ነው። አገላለጹ የተለያየ ይሁን እንጂ ሳይንሱም ሆነ መንፈሳዊው አስተሳሰብ ሰዎች ለአንድ ልዩ ዓላማ የተለየ ችሎታ ይዘው ሊወለዱ እንደሚችሉ ያምናሉ። ይህንንም እንደየቋንቋቸው “ተሰጥዖ”፣ “ፀጋ”… ወዘተ በማለት ይጠሩታል።
በአጠቃላይ ሲታይ ሰባት ዓይነት ተሰጥዖዎች እንዳሉ ይታወቃል። ስለሆነም በኮሮና ምክንያት ግድ ሆኖብን ክፉውን ጊዜ ለማለፍ በቤት ውስጥ በምንቆይባቸው ጊዜያት ከሰሞኑ እንደሚሰማው በቤተሰብ(በራስ አካል) ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት ዓይነት አሳዛኝና አስፀያፊ ተግባራት ላይ ከመዋልና በጥፋታችን ላይ ጥፋት፣ በኃጢአታችን ላይ ኃጢአት እየጨመርን የስቃይ ዘመናችን ከማራዘም ጊዜውን ራሳችን ለማዳመጥና ተሰጥኦዋችንን ለመለየት እንጠቅምበት። በመሆኑም በመጥፎው ጊዜ ውስጥ ያለውን መልካም ዕድል በማወቅና በጥበብ በመጠቀም መክሊታችንን በመለየት በህይወታችን ውስጥ ትርጉም ያለው ነገር ሰርተን ለማለፍ እንችል ዘንድ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኘኋቸውን ሰባቱንም ዓይነት ተሰጥኦዎች በዝርዝር አቀርባለሁ። የእርስዎ ተሰጥኦ ወይም መክሊት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ የሚችሉበትንና ይህንንም ተሰጥኦዎን ለማዳበርና አውጥቶ ለመጠቀም የሚችሉባቸው መንገዶችም አብረው ቀርቦልዎታል።
ከሁሉም ጋር በቀላሉ በመግባባትዎ በማህበረሰቡ ዘንድ “እርሱ እኮ እንኳን ሰው ድንጋይ ያናግራል” የሚል አድናቆት የሚጎርፍልዎት ከሆነ፣ ትርፍ ጊዜዎን ከጓደኞችዎ ጋር በመጫወትና ያገኙትን መረጃ በማጋራት የሚያሳልፉ፣ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት የመሳተፍ ልምድ ካለዎት ይህ ከምንም ተነስቶ የተፈጠረ ባህሪ ሳይሆን ከሰዎች ጋር የመግባባት ተሰጥዖን የተቸሩ በመሆንዎ ነው። ይህ ከሰዎች ጋር የመግባባትና የሰዎችን ስሜት የመረዳትና የመጋራት ባህሪዎ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተርፍልዎታል።
ታዲያ ይህንን ተፈጥሮ የሰጠችዎትን ችሎታ ለማዳበርና ተሰጥዖዎን በአግባቡ ለማውጣትና ለመጠቀም ሁሌም በቡድን ሥራዎች ላይ ይሳተፉ፣ ከቻሉ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይም ይሳተፉ፣ ተማሪ ከሆኑ የክፍል ጓደኞችዎን ያስጠኑ ወይም በማስተማር ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ይሁኑ። መምህርነት፣ የፖለቲካ ሙያ እንዲሁም አማካሪነት ከእርስዎ ተሰጥዖ ጋር አብረው የሚሄዱ ሥራዎች ናቸው። ዝነኛዋ ጥቁር አሜሪካዊት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ኦፕራ ዊንፍሬይ እና ሳይሰስቱ በሚለግሱት ሰብዓዊ የበጎ አድራጎት ተግባራቸውና ርህራሄያቸው በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፉትና የ“እናትነትን” ማዕረግ የተጎናጸፉት “እናት ቴሬሳ” የመግባባት ተሰጥዖ ያላቸው ዝነኞች ናቸው።
ተማሪ እያሉ በሂሳብ ትምህርት ጎበዝ ነበሩ? ሂሳባዊ ስሌቶችን ማስላት እንቆቅልሽ ጥያቄዎችን መፍታት ያዝናናዎታል? ነገሮችን በዓይነት በዓይነት መመደብ፣ የተለያዩ ክፍሎችን አንድ ላይ በመገጣጠም አንድ ወጥ ቅርፅ ማውጣት ያስደስትዎታል? እንዲህ ከሆኑ በቃ እርስዎ የአመክንዮ ተሰጥዖ ያለዎት ሰው ነዎት። እንግዲያውስ ደስ ይበልዎት። ሳይንቲስት፣ የፈጠራ ሰው፣ ኮምፒውተር ፕሮግራመር የመሆን ዕድልዎ ሰፊ ነው። በእነኝህ ሙያዎች ላይ ቢሰማሩም ተሰጥዖዎ ነውና ይሳካሎታል።
ታዲያ ይህንን ተሰጥዖዎን ማጎልበት ይኖርብዎታል። ለዚህ ደግሞ ልዩ ልዩ ዓይነት የአመክንዮ መጽሃፎችን ያንብቡ። እንደ ሶዱኮ ዓይነት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታን የሚጠይቁ ጨዋታዎችን ይጫወቱ። ተሰጥዖዎን ለማወቅና ለማውጣት ይጠቅምዎታል። የበርካታ ሳይንሳዊ ግኝቶች ባለቤት የሆነው ኒኮላ ቴስላ፣ የዘመናችን አልበርት አንስተይን እየተባለ የሚጠራው ታላቁ ሳይንቲስት ስቴቨን ሃውኪንግ እንዲሁም የዓለማችን ቁጥር አንድ ቢሊዮነሩ እና የኮምፒውተር ፕሮግራም ባለሙያው ቢል ጌትስ የአመክንዮ ተሰጥዖ ካላቸው ሰዎች መካከል የሚመደቡ ዝነኞች ናቸው።
እርስዎ ለቋንቋ ጥራት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ ዓይነት ሰው ከሆኑ፣ ለንግግርዎ የሚጠቀሟቸው ቃላት የሚያስጨንቅዎት ከሆኑ፣ አንድ ጽሁፍ አንብበው ሰዋሰዋዊ ግድፈቶችን መለየት ላይ የተካኑ ከሆኑ፣ ምናልባትም የተለያዩ ታሪኮችንና ግጥሞችን መጻፍ የሚያስደስትዎት ዓይነት ሰው ከሆኑ የእርስዎ ተሰጥዎ ቋንቋ ነው። ይህ ተሰጥዖ ዓይነት ቀደም ባሉት ጊዜያት እጅግ ላቅ ያለ ክብር የሚሰጠውና ለታላቅ ክብር የሚያበቃ ነበረ። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ የቋንቋ ችሎታው ከፍተኛ የሆነ ሰው በትምህርት ዓለም ስኬታማ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ስለሆነ ነው። ይህም ለሰው እስከ መጨረሻው ትምህርት ደረጃ የመዝለቅና ዶክተርነትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግን ለመቀዳጀት ስለሚያስችለው በህብረተሰቡ ዘንድ ክብርንና ዝናን የማግኘት አጋጣሚን ይፈጥርለታል። በጥንት ጊዜ ህዝብን የሚመሩና የሚያስተምሩ ሰዎች ከፍተኛ የቋንቋና የንግግር ችሎታ የነበራቸው አንደበተ ርቱዕ ሰዎች ነበሩ።
እናም እርስዎ የዚህ ተሰጥዖ ባለቤት ከሆኑ በድርሰት፣ የመድረክ ተናጋሪነትና የጥብቅና የሙያ ዘርፎች የመሰማራት ዕድልዎ በጣም ሰፊ ነው። ታዲያ ተሰጥዖዎን ለማጎልበትና በሥራ ላይ ለማዋል ተጨማሪ ልምምድ ማድረግ ካስፈለግዎት አጋዥ መንገዶችን እንጠቁምዎት። መጽሃፍትን ማንበብ የዘወትር ልማድዎ ያድርጉ፣ አጋጣሚውን አፈላልገው ያለክፍያም ቢሆን ጋዜጣ ወይም መጽሄት ላይ ይጻፉ ወደፊት መተዳደሪያ እንጀራዎ ሊሆን ይችላልና። ጨዋታ የሚወዱ ከሆነ እንደ መስቀለኛ የቃላት ምስረታ ዓይነት የቃላት ጨዋታዎችን ይጫወቱ። በተለያዩ የውይይትና የክርክር መድረኮች ላይ ይሳተፉ፤ የንግግር ችሎታዎን ያሳድግልዎታል።
የዚህ ተሰጥዖ ባለቤት ከሆኑ ታዋቂ ሰዎች መካከል አፍ በሚያስከፍት የንግግር ችሎታቸው የሚታወቁትና ታላቋን አገር ሁለት ዙር የመሯት አርባ አራተኛው ጥቁሩ አፍሪካ አሜሪካዊ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አንዱ ናቸው። እንደዚሁ “ህልም አለኝ” በሚል ንግግራቸው በዓለም ላይ ከፍተኛ አድናቆትንና ዝናን ያተረፉት በዓለም ቁጥር አንድ አንደበተ ርቱዕ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ታዋቂው የነጻነት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ይገኙበታል። ጃኔት ዲያዝና ጀ.ኬ ሮውሊንግስም የቋንቋ ተሰጥዖ የነበራቸው ዝነኞች ናቸው።
ከመደበኛው ረቂቅ እሳቤ ወጥተው ነገሮችን በዓይነ ህሊናዎ እየሳሉ የማሰብ ልምድ አለዎት? በስዕል ችሎታዎ ሰዎች ተደንቀውብዎት ያውቃሉ? የራስዎን ወይም የጓደኛዎን ቤት ሲያሰሩ በቤቱ ዲዛይን ሥራ ላይ ተሳትፈው ወይም እንዲህ ቢሆን ብለው አስተያየት ሰጥተው ያውቃሉ? መልስዎ አዎ ከሆነ እርስዎ አላወቁትም እንጂ የዕይታ ወይም የስዕል ተሰጥዎ የተቸርዎት በመሆኑ የወደፊቱ ምርጥ ሰዓሊ አለያም የተጨበጨበለት የህንጻ አርክቴክት ነዎት። የኮምፒውተር ሳይንቲስትና ዲዛይነርትም ከእርስዎ ተሰጥዖ ጋር አብረው የሚሄዱ ሙያዎች ናቸው።
ይህን ካወቁ ታዲያ ተሰጥዖም የግል ጥረት ካልታከለበት ከሚፈለገው ቦታ አያደርስምና በመደበኛውም በትርፍ ሰዓትዎም ተሰጥዖዎን የሚያዳብሩ ሥራዎችን ይስሩ። ለዚህም በትርፍ ጊዜዎ ፎቶ ግራፍ ማንሳት ትምህርትን ይከታተሉ፣ ረቂቅ እሳቤዎችን የወደፊት ህይዎትዎን ሊሆን ይችላል በዓይነ ህሊናዎ እየሳሉ በሚፈጥሩት አስደሳች ምስል እየተደሰቱ መዝናናት ይችላሉ። በእኛ አገር አልተለመዱም እንጂ እንደ ዮጋ ዓይነት የአዕምሮ ስፖርቶችንም ቢሰሩ ተሰጥዖዎን ለማውጣት በእጅጉ ይጠቅምዎታል። ምድር በፀሃይ ዙሪያ እንጂ ፀሃይ በምድር ዙሪያ እንደማትዞር ትክክለኛውን የሥርዓተ ፀሃይ አቀማመጥ ያረጋገጠው ጣሊያናዊው ተመራማሪ ጋሊሊዮ ጋሊሊና የኢንዱስትሪ ዲዛይነሩና ለኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ መሪ ሚና የተጫወተው የአፕል ኮምፒውተር መስራችና ሊቀ መንበር የነበረው አብዮተኛው ሳይንቲስት አሜሪካዊው ስቲቭ ጆብስ የዚህ ተሰጥዖ ባለቤቶች ናቸው።
ይህኛው ደግሞ “ማሰቢያቸው አካላቸው” የሆኑ አካላዊ ተሰጥዖን የተቸሩ ሰዎችን ይመለከታል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን በእንቅስቃሴና በሥራ የሚያስተምሩ ናቸው። የተማሩትን ለማስታዎስና በሥራ ላይ ለማዋልም የግዴታ ሥራ እየሰሩ መሆን ይኖርባቸዋል። ምናልባት ቢሮ ውስጥ ለረጂም ሰዓት ቁጭ ማለት አቅቶዎት “መቀመጫው ላይ እሾህ በቅሎበታል እንዴ” እየተባሉ በተደጋጋሚ የሚቀለድብዎትና የሚተቹና ከሆነ እርስዎ መክሊትዎን አላገኙ ይሆናል። አካላዊና የእንቅስቃሴ ተሰጥዖ ያላቸው ሰዎች በፍጹም አንድ ቦታ ረግቶ ቁጭ ማለት አልሆንላቸውም። ተፈጥሯቸው አይፈቅድላቸውም።
አዕምሯቸው የሚሰራውም ዕረፍት የሚያገኘውም አካላቸውን እያንቀሳቀሱ በሚሰሩት ከንክኪና ከእንቅስቃሴ ጋር የተገናኘ ሥራ ነው። አሁን የእርስዎ የነፍስ ጥሪ ምን እንደሆነ መገመት ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በደስታ ሊሰሯቸው የሚችሉ የሥራ ዓይነቶች እንደ ዳንስ፣ ስፖርት፣ ሩጫ፣ ትወና፣ ህንጻና ቅርጻ ቅርጽ ሥራ የመሳሰሉት ከአካላዊ እንቅስቃሴ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው የሙያ መስኮች ናቸው። ከልጅነታቸው ጀምሮ ከአካላዊ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ ጨዋታዎችን እየተጫወቱና መሰል ተግባራትን እያከናወኑ ቢያድጉ ተሰጥዖዋቸውን ለማውጣት ቀላል ይሆንላቸዋል። በዚህ ዘርፍ ታዋቂ ከሆኑ ሰዎች መካከል “ሙን ወክ” በሚባል የእሱ ብቻ በሆነ ተዓምራዊ አካላዊ እንቅስቃሴ በሚታይበት ዳንሱ በአድናቂዎቹ ዘንድ እንደ ልዩ ፍጥረት የሚታየው የፖፕ ሙዚቃ ንጉሱ ማይክል ጃክሰን አንዱ ነው። ዝነኛው አሜሪካዊ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ሚካየል ጆርዳንም ሌላው ልዩ አካላዊ ተሰጥዖን የታደለ ሰው ነበር። በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከሃያ አምስት ክብረ ወሰኖች በላይ የሰባበረውና በዓለም ዙሪያ “ከሌላ ፕላኔት የመጣው ሰው” እየተባለ የሚደነቀው የእኛው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴም የዚህ ተሰጥዖ ባለቤት ነው።
ይህኛው የተሰጥዖ ዓይነት ደግሞ ራስን የማዳመጥ፣ ወደ ውስጥ የመመልከትና በራስ መንገድ ሄዶ ስኬታማ የመሆን ለየት ያለ ጥበባዊና ፍልስፍናዊ ተሰጥኦ ነው። እነኝህ ከተግባቦትና ከግንኙነት ጠቢቦች በተቃራኒው በአብዛኛው ብቸኝነትን የሚያበዙና በከፍተኛ ደረጃ ውስጣቸውን ማዳመጥ የሚችሉ ዓይነት ሰዎች ናቸው። እናም እነዚህ ሰዎች በግላቸው በሚሰሯቸው ሥራዎች ከፍተኛ ስኬትን ማስመዝገብ የሚችሉ ጥበበኞችና አሳቢዎች ናቸው። ገጣሚ፣ የሥነ ልቦና ባለሞያነትና የአዕምሮ ሃኪምነት እንዲሁም ፈላስፋ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው። የብዙ እሳቤዎች አባት እየተባለ የሚጠራው ታላቁ ፈላስፋ አርስቶትል፣ ታላቁ የነጻነት ታጋይ ማህተመ ጋንዲና የአስራ አምስት ኣመቷ ተዓምረኛ የግል ህይወት ማስታወሻ ጸሃፊ አና ፍራንክ ራስን የማዳመጥ ስጦታን የታደሉ ዝነኞች ናቸው።
በዚህኛው ምድብ ውስጥ የሚካተቱት ደግሞ ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር ያላቸው፤ “ሙዚቃ ህይዎቴ” የሆኑትንና አዕምሯቸው የሚሰራው በጆሯቸው የሆኑ የመስማት ተሰጥዖ ባለቤቶችን ነው። ለእነዚህ ሰዎች ሙዚቃ ሁሉ ነገራቸው ነው። ሲያወሩም፣ ሲሰሩም፣ ሲያስቡም በዜማ ነው። እነኝህ የመስማት ተሰጥዖ ያላቸው ሰዎች በአብዛኛው በድምጻዊነት፣ በሙዚቃ አጫዋችነት(ዲ.ጄ)፣ ሙዚቃ አቀናባሪና ቀማሪነት ሙያዎች ላይ ይሰማራሉ። የዚህ ተሰጥዖ ባለቤት ከሆኑ ታዋቂ ሰዎች መካከል ገና በአምስት ዓመቱ በርካታ የሙዚቃ ድርሰቶችን የደረሰውና የሙዚቃ አባት የሚባለው ኦስትሪያዊው ዮሐንስ ወልፍጋንግ አማዲዮስ ሞዛርት፣ አሁን በሕይወት ካሉት ደግሞ ዝነኞቹ የፖፕ አቀንቃኞች አሊሻ ኪስና ዮዮ ይገኙበታል።
በእኔ ዕምነት በዚህ ምድር ላይ ትልቁ ደስታ ያወቁትን ማሳወቅ እና ሰዎች ተሳክቶላቸው በህይወታቸው ደስተኛ ሆነው ማየት ነው። በተቻለኝ መጠን ለማድረግና ለመሆን የምሞክረው ህልምና ዓላማዬም ይኸው ነው። እናም መልካም ተሰጥኦን የመፈለጊያና የማግኛ፣ በችግር ውስጥ ሆናችሁም መልካም ነገር የማድረጊያ ጊዜ እንዲሆንላችሁ ተመኘሁ። መልካም እያደረግን ፈጣሪ መፍትሔ ያጣልንለትን ችግራችን ይህንን ክፉ ወረርሽኝ እንዲያስወግድልንና መልካሙን ሁሉ እንዲያደርግልን እንጠይቅ። መልካም ጊዜ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
ይበል ካሳ