ታህሳስ 7 ቀን 1965 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ አራት ሰዎችን አጭበርብሮ ገንዘብ በመቀበሉ ስለተቀጣ አታላይ ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
ጋኔን እጎትታለሁ ሲል የነበረው አንድ ሺ ብር ተቀጣ
“ጋኔን ጎትቼ በማነጋገር ከሕመማችሁ አድናችኋለሁ፤ ኮከብ ቆጥሬ ሀብት እንድታገኙ አደርጋችኋለሁ” ብሎ ከአራት ሰዎች በድምሩ 435 ብር አታሎ የወሰደው አንድ አባይ ጠንቋይ አድራጎቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት የአዲስ አበባ አንደኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቅጣት የወሰነበት መሆኑ ትናንት ተገለጠ።
ተከሳሹ ሐሰን መሐመድ ይህንን ወንጀል የፈጸመው ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ ወር 1964 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በልዩ ልዩ ቀበሌዎች በመዘዋወር ነው። ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ ወሮች መካከል ባሉት ጊዜዎች ሕገ ወጥ ብልጽግናን ለማግኘት አቅዶ ከወይዘሮ ሠናይት ፈቄ 140 ብር፣ ከአቶ ግራኝ ከድር 260 ብር፣ ከአቶ አብዱል ፊቃ 10 ብር ፣ ከአቶ ከሊስ አሊ 20 ብር በድምሩ 435 ብር አታሎ በመውሰዱ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 661 የተደነገገውን ሕግ በመተላለፍ መስከረም 29 ቀን 1965 ዓ.ም በአቃቢ ሕግ ክስ ቀርቦበታል።
ተከሳሹ ከወንጀል ድርጊቶቹ መካከል ለታመሙት ሰዎች ልዩ ልዩ ፈሳሽ መድኃኒት ገንዘብ ተቀብሎ መስጠቱን ፤ ለዚህም ሥራ ፈቃድ የሌለውና ጥፋተኛ መሆኑን በፍርድ ቤቱ በሰጠው መልስ አምኗል። “ጋኔን ስቤ አነጋግሬ መድኃኒት እሰጣለሁ ፤ ኮከብ ቆጥሬ ሀብት እንድታገኙ አደርጋለሁ” ብሎ ለማታለሉ ቢክድም ቀደም ብሎ በፖሊስ ጣቢያ በፈቃዱ በሰጠው ቃል ማመኑን በፍርድ ቤቱ ላይ የቀረቡት የሕግ ምስክሮች አረጋግጠውበታል።
ሐሰን መሐመድ ለመፈጸም የማይችለውን ተግባር አደርጋለሁ ብሎ የፈጸመውን የማታለል ወንጀል በከፊል ራሱ ሲያምን የቀረው በሕግ ምስክሮች ስለተረጋገጠበት የአንድ ሺ ብር መቀጫ እንዲከፍል ፤ ለመክፈል ባይችል እጁ ከተያዘበት ቀን አንስቶ በአንድ ዓመት እስራት እንዲቀጣ የአንደኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ኅዳር 21 ቀን 1965 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፈርዶበታል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
የትናየት ፈሩ