አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው ከ79 ዓመታት በፊት ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ነበር።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመጀመሪያ እትሙ የፊት ገጽ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ምክንያት አምስት ዓመታት በስደት ከቆዩ በኋላ አዲስ አበባ ሲገቡ የሚያሳይ ፎቶግራፍና ስለጋዜጣው ዓላማ የሚገልጸውን ተከታዩን ጽሑፍ ይዞ ወጥቶ ነበር።
‹‹ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የረዳትነቱን ስራ ይሰራ ዘንድ ተመሰረተ። ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለኢትዮጵያ አዲስ በሆነው ዘመን ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚያስፈልገውን ስራ ሁሉ እያመለከተ፤ ይልቁንም ሕዝብ ለአገሩ፤ ለመሪውና ለንጉሰ ነገሥቱና ለንጉሰ ነገሥቱም መንግሥት ማድረግ የሚገባውን እየገለፀ የበጎን ስራ መንገድ የሚመራ እንዲሆን ይህ ጋዜጣ በግርማዊ ንጉሰ ነገሥት ተመሰረተ። ስራውም በሦስት ቃሎች ይጠቃለላል። እውነት፤ ረዳትነትና አገልግሎት።
እውነት ስንል በዚህ ጋዜጣ የሚነገረው ነገር ሁሉ መሰረቱ በፍጹም እውነትን እየተከተለ ለአንድ ጥቅም ብቻ ያልሆነና ለመላው ጥቅም የሚሰራ እንዲሆን ነው። አገልግሎት ስንል የኢትዮጵያን ነፃነት ለመመለስ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የራሳቸውን ጥቅም ሁሉ አስወግደው ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ሲሉ የሰው አቅም ሊሸከመው የማይችለውን ድካም ተቀብለው ማንኛውም ሰው ሊያደርገው ያልተቻለውን በኢትዮጵያ ሕይወት ውስጥ እስከዛሬ ድረስ ያልታየውን ስራ ከፍፃሜ ላደረሱ ለተወደዱ ንጉሰ ነገሥታችንና ላቆሙት መንግሥት የሚያገለግል እንዲሆን ነው።”
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሚያዝያ 27 ቀን አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁም ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ስራ ይጀመራል” ብለው ነበር። በጋዜጣው የመጀመሪያው ዕትም ላይ እንደሰፈረው፤ ጋዜጣው “አዲስ ዘመን” የሚለውን ስያሜ ያገኘው ከዚህ የንጉሰ ነገሥቱ ንግግር ነው።
በ60ኛ ዓመት ሲምፖዚየም ላይ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅኝት በሚል ርዕስ በ1993 ዓ.ም በታተመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኅትመት ሚዲያ ጆርናል ዶክተር ገብረመድህን ስምኦን “አዲስ ዘመን ከትናንት እስከዛሬ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አሳትመዋል። በዚህ ጽሑፍ እንደተጠቀሰው ጠላት ተባርሮ ንጉሠ ነገስቱ ወደ ሀገር እንደተመለሱ በግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ ዘመን የተሰኘ ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጣ መታተም ጀመረ። አዲስ ዘመን በታብሎይድ ቅርጽ በአራት ገጽ መታተም ሲጀምር ርዕሰ አንቀጽ፣ ቋሚ አምዶች ወይም ዜናዎች ያልነበሩት ሲሆን አብዛኞቹ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጋዜጦች ነበሩ። አልፎ አልፎም የውጭ አገር ዜናዎች ይጨመሩም ነበር። ጋዜጣው በይዘትም በቅርጽም እየተሻሻለ በ1940 ዓ.ም መጀመሪያ ወደ ብሮድሽት ተለወጠ። በቋንቋ አጠቃቀምና ሌሎች ተዛማች ጉዳዮች እየተሻሻለ መጣ።
አዲስ ዘመን ለ18 ዓመታት ሳምንታዊ ጋዜጣ ሆኖ ከቆየ በኋላ በኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መቋቋም የሚዲያ አትኩሮት ይሻል በሚል ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ በሳምንት ለስድስት ቀናት የሚታተም ዕለታዊ ጋዜጣ ሆኗል። ጋዜጣው ለ42 ዓመታት ሰኞ ቀን ሳይታተም ቆይቶ ከ1993 ዓ.ም በኋላ ሰኞን በመጨመር በሳምንት ለሰባት ቀናት በመታተም ላይ ይገኛል።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዕድሜና ታሪክ ሲወሳ የመጀመሪያ ዋና አዘጋጁን ብላታ ወልደጊዮርጊስን አለማንሳት ንፉግነት ነው። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሲመሠረት እንደ ዋና አዘጋጅ ፣ ኤዲተር ፣ ሪፖርተርና አራሚ ሆነው ማገልገላቸውን ጋዜጣው በ60ኛ ዓመት ልደት ዕትሙ አስፍሯል። የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት መከፈትን ተከትሎ ታህሳስ 23 ቀን በ1917 ዓ.ም ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ መታተም ሲጀምር ወልደጊዮርጊስ ሙያውን በመቀላቀል በረዳት አርታኢነት ማገልገል እንደጀመሩ ታሪካቸው ያመለክታል።
ከግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ጀምሮ ደግም ሳምንታዊ ለነበረው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጽሑፎችን በመጻፍ ፤ የአርትኦት ስራ በመስራትና የህትመቱን ሂደት በመከታተል አገልግለዋል። ጋዜጣው ዕለታዊ እንዲሆንም የእርሳቸው የለውጥ ፍላጎትና ተጽዕኖ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ይነገራል። በአዲስ ዘምን ጋዜጣ ታሪክ እንደ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ለረጅም ዘመናት በዋና አዘጋጅነት ያገለገለ ጋዜጠኛ የለም ፤ ከ1933 እስከ 1953 ዓ.ም ለሃያ አመታት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ሰርተዋል። ከ54 ዓመታት በፊት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 25ኛ ዓመት ልደት ሲከበር ብላታ ወልደጊዮርጊስ «የኢትዮጰያ ጋዜጠኞች አባት» የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ነበር።
ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ ኣደሙ “ረጅሙ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጉዞ ከግንቦት 30/1933 – ግንቦት 30/2006 አዲስ ዘመን እንደማሳያ” የሚል ርዕስ በሰጡት ጥናታዊ ጽሑፋቸው ፣ አዲስ ዘመን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ የነበረው ጉዞ በእጅጉ አድካሚ ፣ ባለሙያዎችም የመጻፍ ፍቅር እንጂ ከጋዜጠኝነት ጋር ብዙም ቅርርብ ያልነበራቸው ናቸው። ሆኖም ለዛሬውም ሆነ ለወደፊቱ ጋዜጠኝነት ፈር ቀዳጆች በመሆናቸው ክብርና ሞገስ ሊቸራቸው ይገባል ይላሉ።
አበረ አዳሙ በጥናታቸው እንዳሰፈሩት ፣ አዲስ ዘመን የጋዜጣነት መልክ መያዝ የጀመረው በጋዜጠኝነት ትምህርት ሰልጥኖ የመጣው ነጋሽ ገብረማሪያም ዋና አዘጋጅ ሆኖ ከተመደበበት ከሐምሌ 16 ቀን 1953 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ነጋሽ ቀደም ሲል “ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ” ላይ ይሰራ ነበር። በወቅቱ ጋዜጦችን በበላይነት የመምራትና የመቆጣጠር ስልጣን የነበረው ማስታወቂያ ሚኒስቴር በመሆኑ ነጋሽ ወደ አዲስ ዘመን እንዲዘዋወር የወሰኑት የማስታወቂያ ሚንስቴር ሚንስትር የነበሩት ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋሪያት ናቸው።
በውጭ አገር ዘመናዊ ጋዜጠኝነትን ለአራት ዓመታት ተምሮ የመጣው ነጋሽ አዲስ ዘመንን እንደተቀላቀለ ከተማረው ትምህርት ጋር ፍጹም ተዛምዶ የሌለው ጉዳይ ስለገጠመው ግራ ተጋባ። ብላታ ያዘጋጁት የነበረው አዲስ ዘመን በውዳሴ የተሞላ ፤ ነጋሽ የሚያውቀው ጋዜጠኝነት ሌላ ሆኑና ተቸገረ። በመጨረሻም የተማረውን ጋዜጠኝነት በስራ ላይ ለማዋል ከመሳፍንቱ ፣ ከንጉሠ ነገሥቱና ከበታች ሹማምንት ጋር ግብግብ ውስጥ ገባ።
በነጋሽ የዋና አዘጋጅነት ዘመን የዜና ፣ የአስተያየት ፣ የርዕሰ አንቀጽና የሌሎች ሀተታዎች ቦታዎች በቋሚነት ተመደቡ። ለመጀመሪያ ጊዜ ርዕሰ አንቀጽ የተጻፈውና የዋና አዘጋጁ ስም ጋዜጣው ላይ የወጣውም በዚህ ጊዜ ነበር። ነጋሽ በስሩ ለሚገኙት ጋዜጠኞች ስለ ዘመናዊ ጋዜጠኝነት ስልጠና ይሰጥም ነበር።
ነጋሽ ገብረ ማሪያም የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ከሆነ በኋላ አሀዱ ሳቡሬንና ብርሃኑ ዘሪሁንን የመሳሰሉ ጋዜጠኞች ከ “ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ” ወደ አዲስ ዘመን በመዘዋወራቸው ጋዜጣው መሰረታዊ ለውጥ ታይቶበታል። ከፍተኛ ተነባቢነት በማግኘቱም ዘመኑ “የአዲስ ዘምን ወርቃማ ጊዜ” ለመባል በቅቷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ፅሑፍ መምህር ዘሪሁን አስፋው “አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለስነ-ጽሑፍ ያደረገው አስተዋጽኦ” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ “አዲስ ዘመን ከተመሰረተበት ከግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ጀምሮ አሁን እስካለበት ጊዜ ድረስ ለስነ ጽሁፋችን ካደረጋቸው አስተዋጽኦች መካከል ዋና ዋና ያልኳቸውን በቅኝታዊ አካሄድ ተመልክቻለሁ። ጋዜጣው ከመጽሐፍ “ተመልከት” እስከ “ኪነጥበባት” ድረስ በአገሪቱ ስነ ጽሑፍ ጉዳዮች የተጫወተው ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው ሆኖ አላገኘሁትም። በአጠቃላይ ስለስነጽሁፍ ፣ ስለዘሮቹ ምንነትና ልዩልዩ ባህሪያት፣ ስለ ስነጽሑፋዊ ሂስ የተለያዩ መልኮች ፣ ስለ ልቦለድ ድርሰትና ስለተውኔት፣ እንዲሁም ስለተለያዩ ስነ ጽሁፍ ነክ ጉዳዮች በየአምዶቹ የወጡት ጽሁፎች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በታሪኩ ውስጥ ተንጸባርቀዋል። ራሱን የቻለ የስነጽሁፍን ጉዳይ የሚመለከት ጋዜጣ ወይም መጽሄት በሌለበት አገር የስነጽሁፍ ጉዳይ ሊንሸራሸር የሚችለው በሳምንታዊና በዕለታዊ ጋዜጦች እንዲሁም በመጽሄች ላይ ነው። … አዲስ ዘመን የዘመኑን የሥነጽሑፍ አቅጣጫ ማስያዝና ሥነፅሑፋዊ ሂስን ለማስለመድ በር ከፍቷል። ብዙ መፃሕፍት ባይታተሙም ያሉት እንዲነበቡ በማስቻል ጉልህ ሚና ነበረው” ብለዋል።
አዲስ ዘመን በንጉሠ ነገስቱ ዘመን በቀን 10 ሺ ብዛት የሚታተም ዕለታዊ የነበረ ሲሆን፤ ጋዜጠው 60ኛ አመቱን ባከበረበት 1993 ዓ.ም በቀን 40 ሺ ብዛት ይታተም ነበር። አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የይዘትና የቅርጽ ለውጥ አድርጎ በተሻለ ጥራት አንባቢዎቹ ዘንድ እየደረሰ ቢገኝም ፣ የጋዜጣው ዕለታዊ የህትመት ብዛት ወደ ኋላ ተመልሶ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ከነበረው የስርጭት ብዛት ጋር መስተካከሉ ስርጭቱን በማስፋት መስክ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
የትናየት ፈሩ