የቃተተው የባለቅኔው ብዕር እንደ መነሻ፤
ቃታቹ ብዕረኛ ፀጋዬ ገብረ መድኅን ሲሆን የቃተተበት ቦታና ዓመተ ምህረት ደግሞ በጌምድር፣ ደባርቅ 1963 ዓ.ም ነው። የመቃተቱ ሰበብ ከኅሊናው ጋር የሚያሟግተውና የሚያላትመው ታዛቢ ገጥሞት ነው። የሃሳብና የምናብ ታዛቢው አንድ ሰው ብቻ ይምሰል እንጂ ብዙዎች የተወከሉበት የግፉዓን ሕዝቦች ስብስብ ነው። ያውም እልፍ አእላፍት ወኪሎችን ያሰለፈ። መሪር ትዝብቱ ገንፍሎ ከስብዕናው ጋር የተላተመበት አድራሻ በመልክዓ ምድሩ ጠባብነት የጎንደሩ ደባርቅ ይሁን እንጂ በስፋት የተዘረጋው መሃሉን መነሻ አድርጎ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጥግ፣ ከምሥራቁ የፀሐይ መውጫ እስከ ምዕራቡ የአገራችን ዳርቻ የተንጣለለው ምድራችን ነው።
ባለቅኔው የህሊናውን የሙግት ህመም እህህ በማለት የገለፀው “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” በሚል ርዕስ በ152 ስንኞች (አንዳንዱ ቃል ስንኝ አከል ነው) ባዋቀረው ግጥሙ ውስጥ ሲሆን የሚገኘው ደግሞ በ1965 ዓ.ም በታተመው “እሳት ወይ አበባ” መድበሉ ውስጥ ነው። ጥቂት ወካይ ስንኞችን መዘን የሙሉውን ግጥም ዋና ጭብጥ በወፍ በረር ቅኝት እንደሚከተለው ለመዳሰስ እንሞክር።
“ይድረስ ላንተ ለማላውቅህ፣
ለወንድሜ ሩቅ ለማልፍህ፣
ለምታውቀኝለማላውቅህ፤ለምታየኝ ለማላይህ፣
ማነህ ባክህ!?
ሳትወደኝም ሳታምነኝም፤ አጢነህ ለምትፈራኝ፣
ሳናግርህ አጠንክረህ፤ አተኩረህ ለምትሰማኝ፣
እኮ ማነህ!?”
ብዕረኛው ፀጋዬ በራሱ ምናብ ራሱን የሞገተው ዘመነኛው ትውልድ ፊት ነስቶ በዘነጋቸው ዜጎች ላይ በማተኮር ነበር። “ሕዝባችን!” በሚል ማንቆለጳጰስና ሽንገላ እየተደለሉ ሥርዓቱ ወደ ዳር የወረወራቸውን ምንዱባን በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ ስምና ግብራቸውን እየዘረዘረ በማመልከት ጭምር።
“አኙአክ ነህ ወይስ ገለብ፣
ከዘር ተገፍተህ ተሰደህ፣
በንዳድ መቀመቅ ታጥረህ፣
በእልቂት አፋፍ ፈፋ ያለህ፤
አንተ ማነህ!?”
በማለት ምስኪኑን ወገን በውስጡ እያነባ በብዕሩ ይጠይቀዋል። የነፍሱ ጥዝጣዜ ሲበዛበትና የነፍሱ ጩኸት ሲያይልበትም ደግሞ ደጋግሞ “አንተ ማነህ!?” እያለ በምናቡ የሀገራችንን ዳርና መሃል በማሰስ ሞጋቹን ይፈልጋል።
“አገው ነህ ወይንስ ሺናሻ፣
ቅማንቴ ነህ ወይ ፈላሻ
ስምህ የሆነብኝ ግርሻ።”
የጥያቄ ናዳውን ማዥጎድጎዱን አልተወም። ማሕበረሰቡ ስብዕናውን አዋርዶ ዕደ ጥበቡን የሚያደንቅለትን ሸክላ ሠሪውንና የሸማ ጠቢቡን በጓዳውና በጎድጓዳው ውስጥ እየገባ በማሰስና “ማነህ!?” በማለት እየጠየቀ ከስም አልባው የማንነት መለያው ውስጥ ስሙን ይፈልጋል። እልፍ ብሎም እረኛና የከብት አርቢውን፣ ነጋዴውንና አራሹን በመንገዳቸው ላይ እያስቆመ መገፋቱን፣ አሳቢ አጥቶ መቆራመዱን እያስተዋለ በምናቡ ዓይን እንባውን፤ በብዕሩ ቀለም ብሶቱን ይተርክለታል።
ባለቅኔው የምናብ ተጓዥ ራሱን በቱሪስት እየመሰለ አለያም እንደ ጋዜጠኛ ማይክራፎኑን እየደገነ ሲያሻው እንደ ነጋዴ ከግመሎቹ ቅፍለት ፊት ፊት እየሄደ፣ እልፍ ሲልም እንደ ፖለቲከኛ የማስመሰያ ዓይነ ርግብ ተሸፍኖ ምናባዊ መልኩን እየለዋወጠ በተከሸኑ ቃላት የወገኖቹ ስቃይ ህሊናውን እያሳከከውና የምንዱባኑ ህመም እየጠዘጠዘው ሀገራዊ መልካችንን እንደ መስታወት ከህሊናችን ፊት ይገትርልናል። የራሱ አልበቃ ብሎት እኛንም ይሞግተናል።
“አንተ የእማማ ኢትዮጵያ ልጅ፣
እኔማ ሆኜብህ ፈረንጅ፤
ሃሳብ ለሃሳብ ለተጣጣን፣
ምን አጣላን ማን አጣላን!?
ማን እንዳንወያይ ገራን፤
እንደ ባቢሎን ኬላ ግንብ ለመተላለፍ የበቃን።
ማነው ምንድን ነው ወንድሜ፣
ሆድ ለሆድ የሚያናክሰን፣
ሳንርቅ የሚያራርቀን ሳናኮርፍ የሚያኳርፈን!?”
ባለቅኔው ራሱን ጠይቆ ለራሱ መልስ ቢያጣ ምንዱባኑ ወገኑ የተለጎመው አፉ ተፈትቶ መልስ እንዲሰጠው “ማነህ ባክህ!? ማነህ!?” በማለት እየጎተጎተው ምላሽ ሲያጣ የከፈተውን የግጥም በር ሳይዘጋ ገርበብ አድርጎ በመተው ሸክሙን እኛ ላይ አራግፎ ለዘመናት የተዳፈነ ዕሳት ጥሎብን አልፏል – በዘመን ተሻጋሪ ምናባዊ ግጥሙ።
ኑ እኛም እንዋቀስ!?
የትናንቱን የፀጋዬን መራር ትዝብት አቧራውን አራግፈንና በምናብ ላይ የተንጠለጠለውን ጥያቄ ወደ ምድር አውርደን “ሕዝባችን” እያልን ቀን ከሌት ስለምንዘምርለት ወገን ከአርምሞ ፀጥታ ውስጥ በመውጣት በባለቅኔ ብዕር ሳይሆን በታዛቢ አተያይ ጥቂት እንቆዝም።
ዛሬም ሀገሬ ሕዝባቸውን በማያውቁና ሥነ ልቦናው ባልበራላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ከተወረረች ሰነባብቷል። በእርሱ መወጣጫነት የሥልጣን መንበር ላይ ለመፈናጠጥ እርካቡን የእግራቸው መዳፍ ሥር ለማስገባት የሚፋለሙትን እንደ አሸን የፈሉ “እንጉዳይ ቡድኖች” በየሚዲያው ሲርመሰመሱ ነጋ ጠባ ማስተዋል እንደምን ስሜትን እንደሚያሳምም ማን በነገራቸው። “ኦ ዴሞክራሲ በስምህ ስንት ግፍ ተሠራ!” የሚለውን ጽሑፌን ያስታውሷል።
ቱንቢ የለሹን ርዕዮተ ዓለማቸውን በማግነን፣ ፍቺ አልባ ርዕያቸውን በመተረክ የሕዝብን ስም ደጋግመው እየጠሩ በደመ ነፍስ ሲፋተጉ ማስተዋልን ቤትኛ አድርገን ከተላመድን ዓመታት ተቆጥረዋል። “ኑሮ ካሉት ምንትስ ይሞቃል” እንዲሉ መሆኑ ነው። ሕዝባቸው አያውቃቸው ወይንም እነርሱ ሕዝባቸውን አያውቁ ሆድና ጀርባ ሆነው “እናውቅልሃለን” ሲሉ ያለማፈራቸው በራሱ ያሳፍራል።
የዝናብ ጠብታ ሳይቋጥር የመብረቅ ብልጭታ እያንጎዳጎደ ብቻ እብስ እንደሚል ደመና ሲጮኹ እንጂ ለሕዝብ የሚበጅ አንዳችም ተግባር ሲከውኑ አናያቸውም። ብዛታቸውን ከመስማት በስተቀርም ማንነታቸውን እንኳን ለመለየት መቸገራችን በራሱ መፍትሔ አልባ ችግር ሆኖብናል። እርግጥ ነው የተወጠነውን ብቻ ሳይሆን የተጠናቀቀውን ሀገራዊ ፕሮጀክት ጭምር ትንሹንም ሆነ ትልቁን ሲተቹና ሲያጠልሹ መዋልን ባህላቸው እንዳደረጉ በሚገባ እናውቃለን።
መልኩንና ጠረኑን የማያውቁትን ሕዝብ “ሕዝባችን” እያሉ ስሙን ጋሻ በማድረግ እንገፍ እንገፍ ማለትን ያውቁበታል። ጠጋ ብለው ችግሩን እየኖሩ ብሶቱን ለማዳመጥ ተጠይፈው በስሙ ሲነግዱ ማስተዋል ምንኛ ለትዝብት ይዳርጋል። አንድ እፍኝ ዘር ቆንጥረው ሳይሰጡ የተስፋ ሰብል ያስታቅፉታል። ኑሮውና ማጀቱ ጎሎበት ከፈጣሪ ጋር እየተዋቀሰ እንባውን ወደ ፀባኦት ሲረጭ እየተመለከቱ “በወኪልህ በእኛ ተስፋህን ጣል” እያሉ በሽንገላ ቃላት ሊፈውሱት ይሞክራሉ።
የገጠሩን ኑሮውን ስለማያውቁት የውሃ ጥሙን አይረዱለትም። በአዕምሯቸው ኖታ የጻፉለት እንጉርጉሮ “ሕዝባችን፣ ብሔራችን” የሚለው ብቻ ስለሆነ እንኳን እኛ የሩቅ ተመልካቾቹ ቀርቶ የእነርሱም ነፍስ እንደተጠየፈው መገመት አይከብድም። እነርሱ በደማቅ ከተማ ውስጥ በኦቶሞቢል እየተንፈላሰሱ፣ በተንጣለለ ቪላ ውስጥ እየኖሩ፣ ከብፌ ምግባቸው ውስጥ ዓይነት እንዳይሳሳና የውስኪ ጠርሙሳቸው እንዳይጎድል እየተጠነቀቁ ባቃዣቸው ጊዜ ሁሉ ብድግ እያሉ “ሕዝቡ እንድመራው የወከለው እኛን ነው!” በማለት እርስ በእርስ ተከፋፍለው ጦር ይወራወራሉ፤ በፕሮፓጋንዳ ጓል እርስ በእርስ ይፈናከታሉ። ባለቅኔው፤
“በፎቶግራፍ ዓይን እንጂ ዓይን ለዓይን የማንተያይ፣እኔ ለወሬ አንተን መሳይ፤ አንተ ለጭንቅ እኔን መሳይ።”
እንዳለው መሆኑ ነው።
የዛፍ ችግኝ ከመትከል ይልቅ አፈሩ እንዳይነካቸው በመጠየፍ ዳር ይዘው በመቆም መተቸትን ተክነውበታል። በገበሬው ማሣ ውስጥ ተገኝተው “አሻም!” እያሉ ከማበረታታት ይልቅ በየታላላቅ ሆቴሎች እየተንጎማለሉ “ሕዝባችን” በማለት ስሙን እንደ ማለዳ ጸሎት እየደገሙ በማነብነብ ይሳለቁበታል። “የተጨቆነው ብሔራችን፣ የተገፋው ወገናች!” እያሉ ክቡር ስሙን በአንደበታቸው ያሳድፋሉ።
ፀጋዬ ገብረ መድኅን ግጥሙን ከጻፈ ከሃምሳ ዓመት በኋላ ዛሬ በሕይወት ቢኖርና ለዳግም ትዝብት ቢጋበዝ የግጥም ሃሳብ የሚመዘው ከዚያው “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” ከሚለው ውስጥ ሊሆን እንደሚችል በግሌ እገምታለሁ። ስንኞቹን ከገጣሚው ከራሱ ተውሰንና አውዱን ከዛሬ ጋር አጣጥመን ትዝብትህን ግለጽ ብንለው እንዲህ የሚል ይመስለኛል።
“እኮ ማነህ የእምዬ ልጅ!?
ፖለቲከኛ የሚራገጥብህ፣
አክቲቪስት የሚደነፋብህ፣
ባለሥልጣን የሚሸነግልህ፣
የጋዜጠኛ ጋጋታ፤ ካሜራ እሚጋበዝብህ።
የሚተች የሚተረጉም የሚነድፍህ የማንም እጅ፣
የማነህ ደም የማነህ ቅጅ፣
አንተ የእማማ ኢትዮጵያ ልጅ!?”
እነዚህ የምናብ ስንኞች የሕዝባችን የገሃዱ ሕይወት መገለጫዎች ናቸው። ዛሬ ለሕዝብ የሚያስፈልገው የፖለቲከኞች የቅዠት ህልም ሳይሆን የእውን ተግባርና ምሳሌነት ነው። ለተናጋሪውም ሆነ ለአድማጩ የማይመጥን ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በውጤት የሚገለጽ ድጋፍ ነው። አንዲት ቅንጣት አስተዋጽኦ ያላደረገ “ስመ ፖለቲከኛ” ሕዝቡን “አለሁልህ!” እያለ ሲሸነግለው “ሕዝቤ የተባለው ሕዝብ” ሊሰጠው የሚገባው መልስ “መጀመሪያ ራስን ነፃ አውጣ!” የሚል ሊሆን ይገባል።
ሥልጣን አለኝ ብሎ የሚፎክረውም ቢሆን በሕዝቡ ላይ ሊፏልል ሲንደረደር “እረፍ!” እየተባለ ሊገሰጽ ይገባዋል። ከአፉ አንድም ቀን መልካም ቃል ወጥቶ የማያውቀውን “ሁሉን አወቅ ጨለምተኛ” ወጊድ የት ታውቀንና ተብሎ በማሕበር ቃል ሊገፈተር ይገባዋል።
ዛሬ የሕዝቡ ፍላጎት የሥልጣን ህልመኞችን ጉጉት ማርካት ሳይሆን ሰቅዞ በከበበው ወረርሽ እንዳይጠቃ መደገፍ ነው። ሕዝቡ ጮክ ብሎ የሚጠይቀው ማሣው ጦም እንዳያድር ከጎኑ ሆኖ የሚያበረታታውን ረዳት እንጂ የጠነዛ የፖለቲካ ኮቾሮ አይደለም። ሕዝቡ የሚናፍቀው ጭል ጭል የሚለው የኩራዙ ነበልባል በኤሌክትሪክ ብርሃን ተለውጦ ጨለማው እንዲወገድለት እንጂ በነበልባል አንደበት እንዲግለበለብ አይደለም። ሕዝቡ ተስፋ የሚያደርገው የዘራው ዘር በአንበጣና በአረማሞ እንዳይመክንበት እንጂ እንዲመፃደቁበትም አይደለም።
ሕዝቡ ማድመጥ የሚፈልገው የጦርነትን አዋጅና የግጭት ቅስቀሳ ሳይሆን ተከባብሮና አደጋግፎ የሚያኖርን የምሥራች ነው። በዘርና በቋንቋ መሸንገልን ሳይሆን በኅብረት የሚገኝን ሽልማት ነው። ይህን ማድረግ የተሳነውን ግለኛ ሕዝቡ በአንድ ቃል “ሕዝቤ ብለህ አትጥራኝ! አለሁልህ ብለህ አትሸንግለኝ! ለሞት ፍልሚያ አትቀስቅሰኝ! የት አውቄ ናልኝ አልኩህ? መቼስ ፈልጌህ ጠራሁህ? ሳልጠራህ አቤት አትበለኝ! ሳልክህ ወዴት እያልክ አታስጨንቀኝ!” በማለት አምርሮ ሊሞግተውና ሊያራቁተው ይገባል። “ከትናንት ተምሬ ለዛሬ የሰነቅሁት እውነታ ይህ ነው።” እያለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስጠነቅቀው ይገባል። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)
ይድረስ ለሚያውቅህ፤ ለማታውቀው “ሕዝቤ ባይ!”