በትግራይ በላዕላይ አድያቦ ዓዲ-ዳዕሮ ከተማ በቅርቡ ድብልቅልቅ ያለ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዶ ነበር። ሰልፉ የተጠራው የአንድ የፖሊስ አባልን ነውረኛ ድርጊት በመቃወም ነበር። የፖሊስ አባሉ 50 የሚደርሱ ሴቶችን (አብዛኛዎቹ ባለትዳሮች ናቸው ተብሏል) በተለያዩ ጊዜያት ወሲባዊ ጥቃት ሲሰነዝርባቸው ኖሮ በሕዝብ ተጋለጠና ፖሊስ እጅ ወደቀ። እናም ሰውየው እንደማንኛውም ተራ ወንጀል በ6ሺ ብር ዋስ መለቀቁ ሲሰማ የከተማው ሕዝብ በቁጣ ገንፍሎ በድንገት አደባባይ ወጣ።
በቁጣ ውስጥ ሆኖም «እንዴት እንዲህ ዓይነት ወንጀለኛ በዋስ ይለቀቃል?» ሲል ጠየቀ። በተለይም ደግሞ አጥፊው ፖሊስ የአመራር አባል ነው መባሉ በሕዝብ ውስጥ የተዳፈነውን ቁጣ ይበልጥ አቀጣጥሎታል። ሥልጣንን መከታ አድርጎ ባለትዳር ሴቶችን ጭምር አስገድዶ መተኛት ከነውርም በላይ ነው ሲል ድርጊቱንም፣ ፈጻሚውንም አውግዟል።
እጅግ የሚገርመው፤ የዚህ ሕዝብ ነበልባል ቁጣ ሳይሰክን ከትናንት በስቲያ ሌላ አሳዛኝ ዜና ተሰማ። «በትግራይ ሓውዜን ከተማ አንዲት የ6 ዓመት ታዳጊ በፖሊስ አባል ወሲባዊ ጥቃት ደረሰባት» የሚል። ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ታዳጊ ላይ የተከሰተው ነውረኛ ድርጊት ሰሚውን ሁሉ አንገት ያስደፋ ነበር።
በአማራ ክልል የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከልሎ የተከሰተው ያለዕድሜ ጋብቻ ነው። በምሥራቅ ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ያለዕድሜ ጋብቻው በስፋት የተስተዋለው ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ነው።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የትምህርት ቤቶች መዘጋት ወላጆች እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ደግሞ 585 ያለዕድሜ ጋብቻዎች ተፈጽሟል።
በሌላ በኩል የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሕግን በመተላለፍ ሊፈጸሙ የነበሩ ከአንድ ሺ በላይ ያለዕድሜ ጋብቻዎች እንዲቋረጡ አድርጌያለሁ ብሏል።
አዎ!..መሰል የሴቶች ጥቃት ችግር በትግራይ ብቻ የቆመ ሳይሆን ድፍን አገሩን ያጥለቀለቀ ከሆነ ሰነበተ። «ቅድስት አገር» ተብላ በምትታወቀው አገራችን ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 101 ሕፃናት በአባቶቻቸው ጭምር ተደፈሩ የሚል አስደንጋጭ ዜና ለመስማትም በቅተናል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ቤት መቆየት ዓላማው ሕይወት ማትረፍ ነው። የአንዱን ሕይወት ለማትረፍ የሌላውን ማጨለም ውስጥ መገባቱ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት ነው።
ይገርማል!… እነሆ የኮሮና ወረርሽኝ የዓለም ሕዝብን አስጨንቋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሰባት ሚሊዮን ዘሏል። 406 ሺ በላይ ሰዎች ወደማይቀረው ዓለም ሄደዋል። በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ብቻ የሞቱት ከ112 ሺ በላይ ደርሰዋል። ወደኢትዮጵያ ስንመለስ ከትናንት በስቲያ ብቻ በ24 ሰዓት ልዩነት 137 ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘዋል። በጠቅላላው 2 ሺ 156 ሰዎች ተይዘዋል። ሰዎች ከቤት ባለመውጣት፣ ንክኪን በመቀነስና ርቀትን በመጠበቅ እንዲጠነቀቁ እየተመከረ ባለበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት ደግሞ የቤት ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት ለመፈጸም የሚነቃቁ ሰዎች መኖራቸው በራሱ ገራሚ ነው።
ጥቃት ምንድነው?
ጥቃት ኃይልን በመጠቀም የሚፈጸም ድርጊት ነው። ኃይልን ወይንም ሥልጣንን በመጠቀም ያለተጎጂዎች መልካም ፈቃድ የሚፈጸም የመብት ጥሰት ነው። ጾታዊ ጥቃት ማለት ማንኛውም በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሥርዓተ ጾታ ያልተማከለ የኃይልና የሥልጣን ግንኙነት በመመርኮዝ በሌላው ላይ የሚደርስ ጉዳት/ጥቃት ወይንም ማስፈራራትን ይመለከታል።
የቤት ውስጥ ጥቃት ከሌሎች ጥቃቶች ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የራሱ የሆነ ዓይነተኛ ባህርያት አሉት። ከእነዚህም ውስጥ ጥቃት አድራሹ ለተጠቂው ያለው ቅርበት፣ በሁለቱ መካከል ያለው እምነት በጥቃቱ ምክንያት መሸርሸር፣ ያልተመጣጠነ የኃይል/ሥልጣን ግንኙነት፣ የድርጊቱ ተደጋጋሚነት፣ ጥቃት አድራሹ ተጠቂውን ለመቆጣጠር ያለው ፍላጎት ይጠቀሳሉ።
እንዲህ ዓይነት ክፉ ድርጊቶች በተለያየ ምክንያት ቤት ውስጥ ታፍኖ ስለሚቀር እንጂ ማህበረሰቡ የተለማመደው ይመስላል። ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እንዲህ ዓይነቱን እኩይ ድርጊት ከማህበረሰቡ ጋር በማያያዝ አጥብቀው ከሚኮንኑት አንዱ ናቸው። «..ልጆች በጠባቂዎቻቸው፣ መከታዎቻችን ባሏቸው ሰዎች ሲደፈሩ ከማየት የበለጠ የሚሰቀጥጥ ሰይጣናዊ ተግባር የለም» ይላሉ። በእርግጥም እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት እንደተራ ወንጀል ብቻ መውሰድ ከበድ ይላል።
አንዳንዶች በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት መስፋፋት አንዱ መንስኤ የቅጣት ማነስ ነው ብለው ያስባሉ። «ያዝ እጅዋን፣ ዝጋ ደጅዋን» እያለ የሚዘፍን ማህበረሰብ አስገድዶ ክብረንጽህና የደፈረ አምስት ዓመት የተፈረደበትን ሲሰማ ይጎመዥ እንደሆን እንጂ አይማርም ይላሉ ዶ/ር በድሉ። በእርግጥ የቅጣቱ ማነስ ወይንም የሕጉ መላላት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው ወይንም የለውም ለማለት ጥናት ይፈልጋል። ይህም ሆኖ የሕግ አካላት ለወንጀል ድርጊቱ የሚሰጡት ሕሊናዊ ግምት በራሱ በቅጣት መክበድና መላላት ላይ አስተዋጽኦ ያለው የመሆኑ ጉዳይ የአደባባይ ምስጢር ነው።
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አስመልክቶ የሚሰጡ ፍርዶች ሁሌም እንዳወዛገቡ ነው። ጥቃቱ ከተጎጂው ባልተናነሰ ማህበረሰቡ ላይ የሚያሳርፈው ሥነልቦናዊ ጉዳት በዋዛ የሚታለፍ አለመሆኑ ዋናው ነገር ነው።
ከሰባት ዓመታት ገደማ በፊት በሕንድ አንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪን አውቶቡስ ውስጥ ለስድስት ደፍረው ለሞት የዳረጉ ግለሰቦች ማህበረሰቡን በቁጣ አነቃንቀዋል። የ23 ዓመቷ የፊዚዮቴራፒ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የተደፈረችው በአውቶቡስ ውስጥ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ የሞተችውም ደፋሪዎቿ ባደረሱባት ከባድ ድብደባ ነበር።
ከስድስቱ ደፋሪዎች አንደኛው እስር ቤት ሳለ ራሱን ሲያጠፋ ፤ የ17 ዓመት ወጣት የነበረው ሌላኛው ሦስት ዓመት ታስሮ እንደ አውሮፓውያኑ 2015 ላይ ተፈትቷል። በቅርቡ በስቅላት የተቀጡት አራቱ ናቸው።
የሕዝቡን ቁጣ ተከትሎ የሕንድ ፍርድ ቤት በአጥፊዎች ላይ የሞት ፍርድ ቅጣት ከማሳለፉ በተጨማሪ ፀረ አስገድዶ መድፈር ሕግ እንዲያወጣ አስገድዶታል።
በኢትዮጵያ በ1949 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 589 /2/ /ሀ/ መሠረት እንዲህ ዓይነቱ ጥፋት ከ1 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ያስቀጣ ነበር። በ1997 ዓ.ም በወጣው አሁን በሚሠራበት የወንጀል ሕግ ቁ. 627 /1/ መሠረት ግን ከ5 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም በተጠቂዋ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት፣ የአዕምሮ ጉዳት ወይም ሞት ያስከተለ እንደሆነ ቅጣቱ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ደንግጓል።
ይህም ሆኖ ፍርድ ቤቶች መካከለኛውን ቅጣት የመምረጥ አዝማሚያዎች ያሳያሉ። አጥፊዎችን ከ5 እስከ 10 ዓመት ባለው ውስጥ የሚቀጡበት ጊዜ የበዛ ስለመሆኑ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህ ተደጋጋሚ ክስተት ሆን ተብሎ በወንዶች እንደሚሰራ ደባ አድርገው በመቁጠር ነገሩን ከጾታ ጋር አስተሳስረው ለሚያዩ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ትችት በር ከፍቷል።
እንደማሳረጊያ
የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ በቤት ውስጥ የመቀመጥ የጤና ሰዎች ትዕዛዝ የቤት ውስጥ ጥቃቶች እንዲበራከቱ መንገድ መክፈቱ እየተነገረ ነው። በጥቃቱ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ሰለባ የመሆናቸው ነገር እየተነገረ ነው።
በሌሎች አገራት ደግሞ የቤት ውስጥ ቆይታ ለዓመታት ጸንተው የቆዩ ትዳሮች የመፍረስ አደጋ አስከትሏል። ለምን የሚለው ራሱን ችሎ ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም ባለትዳሮቹ ከሥራ ውጥረት አረፍ ብለው ራሳቸውን መመልከት ሲጀምሩ ወይንም በቅጡ ለመተዋወቅ ጊዜ ማግኘታቸው ለአለመግባባት መንስኤ ሳይሆን እንደማይቀር የብዙዎች ግምት ሆኗል።
ሰሞኑን ደግሞ የ101 ሕፃናት ጥቃት ጉዳይ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የክስ ፋይል እንዳልተከፈተበት ወ/ሮ መዐዛ አሸናፊ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በትዊተር ገጻቸው መግለጻቸው በብዙዎች ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል።
እርግጥ ነው፤ ጉዳዩ ገና በተጠቂ ቤተሰቦች ክስ አልቀረበበት ይሆናል፤ ፖሊስ እጅ ደርሶ ምርመራ እየተደረገበት ሊሆን ይችላል። በተለያየ ምክንያት ገና ወደፍትህ ተቋማት ሳይደርስ ቀርቶም ሊሆን ይችላል። ግን ጉዳዩ ተዳፍኖ እንዳይቀር መረጃው አለኝ ያለው የአ/አ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ከሚመለከተው አካላት ጋር በመሆን ሊከታተለው ይገባል።
ሌላው ትልቁ ጉዳይ ከአመለካከት ጋር ተያይዞ ብዙ ሥራ ሊሰራበት የሚገባው ወንዶችን በሙሉ አጥፊ አድርጎ የማየትና የመፈረጅ አባዜ መስፋፋት ነው። ወንዶች የማህበረሰቡ ግማሽ አካላት ናቸው። ጥሩ እና መልካም ወንዶች የመኖራቸውን ያህል አጥፊ ወንዶችም አሉ። ከሴቶችም ቢሆን ራሳቸውን ለጥቃት ከማመቻቸት ጀምሮ የአንዳንድ ወንዶች የአጥቂነት ፍላጎትን በማሟላት ረገድ የሚተባበሩ ሴቶች፣ ጥቃት ደርሶም ዝምታን የሚመርጡ እናቶች፣ እህቶች ጭምር መኖራቸው የማይታበል ሐቅ ነው። እናም ወንዶችን ያገለለ የሴቶች መብት ጥያቄ የተሟላ መልስ ሊያገኝ አይችልም።
ከምንም በላይ ደግሞ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ጥቃቶች ከንፈር መጥጦ ከማለፍና የአንድ ሰሞን የመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ አድርጎ ከማለፍ በዘለለ የሚሰሩ ሥራዎች አለመኖራቸው ያሳስባል። ሥራዎች አሉ ከተባለም የመጣ ለውጥ ባለመኖሩ እንዳለ የሚቆጠር አይሆንም። በመንግሥት በኩል የተለያዩ የሴቶች አደረጃጀቶችን ከመፍጠር አልፎ የሴቶችን ጉዳይ ብቻ ሥራዬ ብሎ የሚከታተከል የሚኒስቴር መ/ቤት አቋቁሞ በየዓመቱ በጀትና አስፈላጊው ሁሉ ያደርጋል። ግን በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከመቀነስ ይልቅ መልካቸውን እየለዋወጡ መቀጠላቸው የሚነግረን አንድ ብርቱ ነገር አለ። ይኸውም ጥቃቶቹን ማስታገስ የሚያስችል መሬት የወረደና የሚታይ ሥራዎች ማከናወን አለመቻሉን። እናም የጥቃት ሪፖርቶችን በማቅረብ ብቻ ችግሮቹ አይቀረፉም። በሰዎች ጭንቅላት ላይ መስራትን ይጠይቃል። የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣና ኅብረሰተቡ ራሱን፣ ቤተሰቡን አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ እንዲያስተምር በማድረግ ረገድ የሚከናወኑ ጥረቶች ጠንክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
በተጨማሪም ት/ቤቶች (አንደኛ ደረጃን ጨምሮ) ልጆች በሚረዱት መልኩ የሥነጾታ ትምህርቶችን የሚሰጡበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት።
በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚገኙ ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜ ሊሰጡ ይገባል። ጥቂት የማይባሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ለቤት ሠራተኞችና ሞግዚቶች ወይንም ለዘመድ አዝማድ ብቻ ለረዥም ሰዓታት ትተው ወደሥራቸው መሄድ አዲስ ነገር አይደለም። በተለይ በኢኮኖሚ አቅማቸው ሻል ያሉ ቤተሰቦች ገንዘብ መክፈል መቻላቸው ብቻ ለልጆቻቸው የተሻለ አያያዝን እንደሚያስገኝላቸው ማመናቸው የችግሮች ሁሉ ቁንጮ ነው። እናም ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚሳልፉትን ጊዜ ማሻሻል፤ ከተቻለም ከእናትና አባት አንዳቸው ልጆችን በሙሉ ጊዜ መከታተል የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸትን የቤት ውስጥ ጥቃትን በመቀነስ ረገድ ያለው አዎንታዊ ሚና ግዙፍ ነው።
የእኛ ማህበረሰብ በእስከዛሬው ሁኔታው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አጥቂዎችን የመደገፍ አዝማሚያ የሚከተል ነው። የተጠቃች ሴት ስትገኝ «ምን ልትሰራ ቤቱ ሄደች? ምን አንቀለቀላት? እርቃንዋን እየሄደች ታዲያ ላትደፈር ነው?…» በሚሉ ደፋሪዎችን አበረታች፣ ተጠቂዎችን ኮርኳሚ የውግንና ገለጻዎች ካልተላቀቀ ችግሩ ከመሰረቱ መፍታት አዳጋች መሆኑ አይቀሬ ነው።
የጥቃት ክሶች ወደፍትህ አካላት እንዳይደርሱ አጥቂዎች የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ነው። ከተለመዱት እርምጃቸው አንዱና ዋናው ማስፈራራት ነው። በትናንሽ ጥቅማጥቅም ተጠቂዋንና ቤተሰቧን መደለልም ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት ተጠቂዎች በከባድ ጫና ውስጥ እንዲወድቁ ይገደዳሉ። ስለዚህ አንዲት ተጠቂ ሴት በሕግ ጉዳይዋን ስትከታተል ደህንነቷ በጠበቀ መልኩ እንዲሆን የምትቆይበት ሥፍራ ያስፈልጋታል። በአገራችን የተጠቂ ሴቶች ማቆያዎች ቢኖሩም በቂ አለመሆናቸው ሁሉንም ለማስተናገድ እንዳላስቻለ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይኼ እንዲስተካከል መንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ብዙ ሥራ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
(ፍሬው አበበ)