አንድ ገበሬ ማሳው ላይ በቆሎ እየዘራ አፈር ይመልሳል። የተዘራ በቆሎን ከአፈር ውስጥ አውጥቶ የሚበላ ዝንጀሮ ደግሞ ቁጭ ብሎ በአንክሮ ይመለከተዋል። ገበሬው ሥራውን ጨርሶ ወደ ቤቱ ለማቅናት ሲነሳ ዝንጀሮ ከነበረበት ጉብታ ወርዶ ተጠጋው። ከዚያም «ምንድን ነው ስትዘራ የነበረው» ብሎ ጠየቀው። ገበሬውም ከአፈር አውጥቶ ለመብላት አይመችምና «ተልባ ነው የዘራሁት» አለው። በዚህ ጊዜ ገበሬውን ያላመነው ዝንጀሮ «ለማንኛውም ጭረን እናየዋለን» አለው።
ኢትዮጵያም በአባይ ጉዳይ ከግብጽ ጋር በምታደርገው ድርድር እየተከተለች ያለችው ይህን ጭሮ የማየት ፖሊሲ ነው። ግብጽ አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት የሚሳተፉበት ድርድር እንዲካሄድ ጥያቄ ስታቀርብ ኢትዮጵያ አሻፈረኝ ያላለችው ለዚህ ነው። ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ሌባ ጣታቸውን እያወዛወዙ ተደራዳሪዎቹ ወደ ዋሽንግተን እንዳያመሩ አስጠንቅቀው ነበር። ተደራዳሪ ቡድኑ ከቤተ መንግሥት እንጂ ከማህበራዊ ድረ ገጽ ትዕዛዝ ስለማይቀበል በድርድሩ ሂደት ሲሳተፍ ቆየ። በኋላ አክሮባቲስቷ አሜሪካ በብርሃን ፍጥነት ከታዛቢነት ወደ ዳኝነት ስትሸጋገር ኢትዮጵያ መድረኩን ጥላ ወጣች።
ከሰሞኑም ግብጽ ዳግም የሦስትዮሽ ድርድሩን ለመጀመር ፈቃደኛ መሆኗን አሳውቃለች። እንደተለመደው «ግብጽን ማመን ቀብሮ ነው» ባዮች ኢትዮጵያ ወደ ድርድሩ እንዳትመለስ እያሳሰቡ ነው። እነዚህ ወገኖች በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከድርድር መድረኮች መራቅን መፍትሄ አድርገው መቁጠራቸው ያስገርማል። ሰግተን የምናፈገፍግበት ምንም ምክንያት የለም። ጭሮ በማየት ፖሊሲ የምናጣው አንዳች ነገር የለማ! እንዲያውም ሁነኛ ጊዜ የመግዣ ስልት ነው።
80 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ ይዞ እየተምዘገዘገ ሱዳንንና ግብጽን አርሶ ከበረሃው ንዳድ ተርፎ ሜዲትራኒያን ባሕርን የሚቀላቀለው አባይ 86 በመቶ አዋጪዎች ሆነን አንገታችንን መስበር የማይታሰብ ነው። ቀና ብለን በየትኛውም የድርድር መድረክ ላይ መሳተፍ አለብን።
ግብጻውያን የሚወዙት ኢትዮጵያ በምትለግሳቸው ደም ነው። «የደማችን ጠብታ ነው» የሚሉት አባይ ከአገራቸው ማህጸን የሚጎርፍ የኢትዮጵያውያን ደም መሆኑን ማስታወስ አይፈልጉም። ሕይወት ለሚቀጥለው ደም እንጂ ለለጋሿ እውቅና የማይሰጡ ራስ ወዳዶች ናቸው። እንጂማ ቱርኮች ግብጽን በሚገዙበት ዘመን የወንዙ ባለቤት ለሚሏት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ሃምሳ ሺ የወርቅ ሳንቲም ይከፍሉ እንደነበረ ሁሉ እነርሱም በተለያየ መንገድ አጉራሻቸውን መደገፍ ነበረባቸው። እርግጥ ነው በቂ አይደለም እንጂ ግብፅ የመንግሥት ተቃዋሚዎችን ጦር መሣሪያ በማስታጠቅና በማሰልጠን ጭምር ኢትዮጵያን ስትደግፍ ኖራለች።
«ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነኑኝ» እንዲሉ ጭራሽ ከውሃው «ንክች ታደርጉና ወዮውላችሁ» ባይ ሆና ቁጭ ብላለች። በ2005 ዓ.ም የአባይ ወንዝ የፍሰት አቅጣጫ እንዲቀይር መደረጉን ስትሰማ የሆነችውን ማስታወስ በቂ ነው። በወቅቱ አገሪቱን ይመሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት ሞርሲ «እኔ ሳልሞት ግብጽ አትጠማም» ሲሉ የጦርነት ነጋሪት ጎስመው ነበር።
በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ከ2ሺህ ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ርቀት አለ። ግብጽ ጦርነት ምርጫዋ ከሆነ በሱዳንና ኤርትራ ሰፍራ ነው ኢትዮጵያን ማጥቃት የምትችለው። ይህ ደግሞ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ከኢትዮጵያውያን ጋር ካላቸው ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ ወዳጅነትና አንድነት አንጻር የማይታሰብ ነው።
ግብጽ አባይን በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ወርራለች። ሐረርን እስከ መያዝም ደርሳ ነበር። የግብጽ ሠራዊት ጦር መወርወር እንጂ መመከት ስለማይችል የኋላ ኋላ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቷል። በአፄ ዮሐንስ ዘመን የሆነውንም ብንመለከት ኅዳር 8 ቀን 1868 ዓ.ም ማለዳ፣ ጉንደት ላይ የግብፅ ጦርን ገጥመው ድባቅ መትተውታል። ይህ ሽንፈት ያልተዋጠላቸው ግብጾች ከአራት ወራት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያ ላይ 25 ሺህ ጦር አዝምተው በጉራዕ ሦስት ቀናት የወሰደ ውጊያ ቢያደርጉም የለመዱትን የሽንፈት ጽዋ ከመጋት አላመለጡም። የግብጽ የጦር ኃይል የአሸናፊነት ታሪክ የለውም። በ1970ዎቹ ወደ የመን 70 ሺህ ጦር አዝምተው፣ የየመን ሁቲዎች 20ሺዎቹን ገድለው አባረዋቸዋል:: በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን የሽንፈት ታሪክ የለንም።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግብጽ አሁንም የመጣሁላችሁ ዱብ ዱቧን አላቆመችም። ዘሪፐብሊካ የተሰኘው የጣሊያኑ ጋዜጣ ከሳምንት በፊት ባወጣው ዘገባ ግብጽ ከጣሊያን መንግሥት 24 ሚግ ጀቶች ፣ 24 ኢሮ ተዋጊዎችን ፣ አንድ ወታደራዊ ሳተላይት፣ 20 ወታደራዊ ሰራጊ መርከቦችንና ስድስት ተዋጊ መርከቦችን መግዛቷን አስነብቧል። ጋዜጣው ለጣሊያን የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ሽያጭ ነው ያለው ይህ የግብጽ ግዢ ኢትዮጵያ ላይ የምትፈጥረው ሁለንተናዊ ጫና አንድ አካል ነው። ኢትዮጵያን ለመጫን የማትጫነው በተን የለምና በቅርቡ ወታደራዊ ትብብሮችን በመመሥረት ሰበብ ለደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የጦር መሣሪያ ድጋፍ በማድረግ መልዕክት አስተላልፋለች።
ግብጽ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሚያገለግል ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ባለቤት ናት። ከባሰም የቀይ ባሕር ውሃን አጣርታ መጠቀም ትችላለች። ዱባይ ጠጥታ የምታድረው ጨዋማ ውሃን አጣርታ ነው። የግብጽ ሚዲያዎች ግን ኢትዮጵያን በርካታ ወንዞች ያሏት አማራጨ ብዙ ፤ ግብጽን ደግሞ በአባይ ወንዝ ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነች ምስኪን አድርገው ያቀርባሉ።
በአንጻሩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ግድቡን አጀንዳ የሚያደርጉት ግንባታው የተጀመረበት ቀን በሚከበርበት ሰሞን ነው። እልፍ ካለም ግብጽ አንዳች ኃይለቃል በወረወረች ቁጥር የፕሮፖጋንዳዋ ሰለባ ሆነው የመልስ ምት ለመስጠት ነው። የአባይ ጉዳይ ለግብጽ ሚዲያዎች የዘመናት፣ ለእኛዎቹ ደግሞ የዘመቻ ሥራ ነው። ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን፣ በጉያዋ የሚገኙ ዲፕሎማቶችንና ማህበረሰቡን ተደራሽ የሚያደርግ ጥልቀትና ተከታታይነት ያለው ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል።
ሀይ ባይ ያጡ ማህበራዊ ሚዲያዎች የግብጽ ልሳን ሆነው በሚያስተጋቡት ፕሮፖጋንዳ ትውልዱ በስጋት ከመጠመቁ በፊት በጭንቀት የሚናጡት ግብጾች ነበሩ። በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የዝናብ መጠን ኖሮ የወንዙ ፍሰት ሲቀንስ የጥንቶቹ ግብጻውያን «ኢትዮጵያውያን ገድበውት ወይም ጠልፈውት ነው» እያሉ መጨነቅ መጠበብ ዕጣ ፈንታቸው ነበር። በየጊዜው አማላጅ እየላኩ የዓባይ ወንዝ እንዳይጠለፍባቸው ደጅ ይጠኑ ነበር። አፄ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ አፄ ዐምደ ጽዮን፣ አፄ ሰይፈ አርእድና ሌሎችም የዓባይን ወንዝ አቅጣጫ እንቀይራለን እያሉ ግብጾችን እያስቦኩ የሚፈልጉትን ሲያደርጉ ኖረዋል። ዛሬ ግን የኢትዮጵያን ማሊያ ለብሰው ለግብጽ የሚጫወቱ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች በርክተው ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኗል።
ግብጽ በአባይ ጉዳይ ላይ ብቻ የሚሰሩ 14 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ይዛ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ስትረባረብ ፤ ኢትዮጵያ 114 የፖለቲካ ድርጅቶችን ፈልፍላ ገመድ ጉተታ ላይ ቆይታለች። አሁን ግን ያ ዘመን እያበቃ ይመስላል። መንግሥት እኔ ብቻ አውቅላችኋለሁ ከሚል ብሂል ተላቅቆ በውጭና በአገር ውስጥ ካሉ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ጋር በጋራ እየመከረ ነው።
«ግድቡ የኔ ነው» በሚል ንግግራቸው በሚታወቁት ብርቅዬ ልጇ የሚመራው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድንም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ ስምምነት ላይ እንዲደረስ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው። ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም «ግብጽን የሚጐዳ ነገር አንሠራም፤ የግድቡ ዋነኛ ተጠቃሚዎች ግብጽና ሱዳን ናቸው።» በማለት እውነታውን ለማሳወቅ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከሳምንት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በያዝነው ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 605 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል። ባለፈው ሚያዝያ ወር ብቻ 79 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን 13 ነጥብ 54 ቢሊዮን ብር አዋጥተዋል። የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን ጫፍ የደረሰውን ግድባችንን በማጠናቀቅ ድንቅ ሕዝቦች መሆናችንን ለዓለም እናሳያለን!
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
የትናየት ፈሩ