በአስር ዓመቱ ሀገራዊ የልማት እቅድ ትኩረት ከተሰጣቸውና የምጣኔ ሀብት ምሰሶ ተደርገው ከተለዩ ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው። ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የቱሪዝም ሀብት አንፃር ዘርፉ ትኩረት ከተሰጣቸው የምጣኔ ሀብት ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑ የሚያስገርም አይሆንም። ይህን እምቅ ሀብት በማልማት ዘርፉ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ድርሻ ያለው አበርክቶ እንዲያድግ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ። በቅርቡ የተመረቀው ‹‹ቤኑና›› መንደርም ከእነዚህ ስራዎች መካከል የሚመደብ ነው።
‹‹ቤኑና›› መንደር ከመተሃራ ከተማ አቅራቢያ፣ ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በቅርብ ርቀት፣ በሰቃ ሐይቅ ላይ የተገነባ ድንቅ የቱሪስት መዳረሻ ሀብት ነው። ለመዝናኛ መዳረሻነት ተብሎ የተገነባው ይህ ሀብት፣ ግርማ ሞገስ ባላቸው አዋሽ እና አሰቦት ብሔራዊ ፓርኮች አቅራቢያ ይገኛል። በእነዚህ ዋና ዋና የቱሪስት መስህቦች አቅራቢያ በመገኘት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ያለው ‹‹ቤኑና›› መንደር የመዝናኛ፣ የኢኮቱሪዝምና ተፈጥሮን ያማከሉ ተሞክሮዎች ማዕከል የመሆን እምቅ አቅም ያለው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ፍላጎትን የሚደግፍ ነው። መንደሩ የተገነባው በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥትና በግሉ ዘርፍ ትብብር ነው።
መንደሩን መርቀው የከፈቱት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ‹‹ቤኑና›› ይቻላል በተግባር የታየበትና የፈተናዎች መብዛት ሀገርን ከመለወጥ የሚያስቆም እንዳልሆነ ማረጋገጫ መሆን የቻለ ድንቅ ስራ እንደሆነ ይገልፃሉ። ‹‹ቤኑና መንደር ‹ይቻላል›ን በዓይናችን ያየንበት፣ በእጃችን የጨበጥንበት፣ የኢትዮጵያን ብልጽግናና የኢትዮጵያን መለወጥ መሰረት ለመጣል ለሚሹ ሀገር ወዳድ ዜጎች ፈተና ሀገርን ከመቀየር የሚያስቆም እንዳልሆነ፤ ሕልም ያለው፣ የሕልም ጉልበትን መመንዘር የቻለና የተባበረ ሁሉ፣ የተዘነጋ ስፍራንም ቢሆን ገነት ማድረግ እንደሚቻል ከፍተኛ ትምህርት የተወሰደበት እና ‹ይቻላል› መፈክር ሳይሆን የሚታይና የሚጨበጥ ነገር መሆኑን በውል ትምህርት የቀሰምንበት ቦታ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ እንደሚያስታውሱት፣ ዛሬ ውብና ጽዱ ሆኖ የሚታየው ‹‹ቤኑና›› በተገነባበት አካባቢ ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት አንዲት ዘለላ ሳር ማየት ብርቅ ነበር። አካባቢው ሙሉ በሙሉ በረሃ ነበር። ‹‹በወቅቱ የነበረን መሪ ቃል ከበረሃ ወደ እርሻ ስፍራ (From Desert to Farmland) የሚል ነበር። ይህን በረሃ ለእርሻ ምቹ ወደሆነ ስፍራ መቀየር፣ አፈሩንና ውሃውን ማከም እንዲሁም አካባቢውን መለወጥ አለብን። እዚህ ቦታ (በሰቃ ላይ) ከተሳካልን የትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ ላይ ሊሳካልን የማይችል ቦታ አይኖርም። በስፍራው ከፍተኛ ሙቀት አለ፤ ለመጠጥ የሚሆን ውሃ የለም፤ አፈሩ በአሲድ የተበላ ነው፤ ለኑሮ ምቹ አይደለም የሚባልን ይህን ስፍራ መለወጥና ምቹ ማድረግ ከቻልን በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ ብንሄድ ከዚህ የከፋ ፈተና ሊገጥመን ስለማይችል ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት መጣል ይቻላል የሚል ሙሉ እምነት ነበረን። እጅግ በጣም ፈታኝና አድካሚ ስራ ነበር። ከስራውም በተጨማሪ ለሕዝብ እንደሚሰራ ሳይሆን ለሌላ ዓላማ እንደሚሰራ ስፍራ የሚነገሩ ፕሮፓጋንዳዎች ሲታከሉበት ይህን ስራ በቁርጠኝነት መፈፀም ቀላል አልነበረም›› በማለት ስለስራው ፈታኝነት አስታውሰዋል።
‹‹ቤኑና›› አስቸጋሪ የአየር ፀባይን ብቻ ሳይሆን አሉባልታዎችንም ጭምር ተቋቁሞ ስራን በድል የማጠናቀቅ ምሳሌ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ያብራራሉ። ‹‹ስለ ‹ቤኑና› እንኳን ለሕዝባችን፣ በአካባቢያችን ላሉ ሰዎችም ማሳመን ከባድ ነበር። ከቦታው አስቸጋሪነት የተነሳ ይህ ነገር በዚህ መልክ ሊያልቅ ይችላል ብሎ ያሰበ ብዙ ሰው አልነበረም። ነገር ግን በጽናትና በትብብር እውን ሆኗል›› ብለዋል፡፡
ይህም ከዚህ ቀደም የነበሩ አሉባልታዎች በሙሉ ትክክል እንዳልነበሩ ሰው በዓይኑ በማየት፣ በውስጡ በመሄድ ለመገንዘብ እድል እንዲያገኝ እንደሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ይህ ስፍራ የተሰራው ለሕዝብ ነው። እስካሁን በደንብ ያልተገለፀበት ምክንያት በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በትብብር የሚሰራ እና በባህሪው በጣም ፈታኝ ስለነበር እንዲሁም የሁሉንም ጉልበት አስተባብረን ሙሉ ውጤት እስከምናመጣ ድረስ በዝምታ ጀምረን በዝምታ የጨረስነው ፕሮጀክት ስለሆነ ነው›› ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ መንግሥትና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ትብብር እንዲሁም ከግል ዘርፍ ጥቂቶች በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ከፍተኛ ድጋፍ በማድረጋቸው በትብብር መንፈስ በረሃ የነበረውን አካባቢ ገነት ማድረግ ተችሏል። በረሃ የነበረውን ስፍራ ገነት ያደረገ እጅና አዕምሮ መላው ኢትዮጵያን በዚህ መንገድ ገነት ለማድረግ መነሻ የሆነ ትምህርት እንደቀሰመ ምንም ጥርጥር የለውም።
በስፍራው አስቸጋሪ የአየር ፀባይ ምክንያት እርሻው፣ የሌማት ትሩፋቱ፣ ኮንስትራክሽኑና በሌሎች የመንደሩ ግንባታ ሂደት ውስጥ የነበሩ ስራዎች፣ በስራዎቹ ውስጥ የተሳተፉ ተዋንያንን በእጅጉ የተፈተኑ ቢሆንም፣ ባለሀብቶቹም ሆኑ ባለሙያዎቹ የበለጠ እውቀትና ልምድ አግኝተው በረሃን ማልማት እንደሚቻል በተግባር አሳይተዋል፤ ከፍተኛ ድጋፍም አድርገዋል። ‹‹ቤኑና››ን የመሰለ ውብ መንደር እውን ማድረግ የቻለውም ፈተናን በጽናት የመቋቋምና የመተባበር ብቃት ነው።
‹‹ቤኑና›› አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የወተትና ስጋ ውጤቶች የሚመረቱበትን የእርሻና የሌማት ትሩፋት ተግባራትን አካትቶ የያዘ መንደር ነው። አትክልቱና ፍራፍሬው እንዲሁም የወተትና ስጋ ውጤቶቹ የእረፍትና የመዝናኛ ጊዜያቸውን በመንደሩ ለማሳለፍ ወደ መንደሩ ለሚያቀኑ እንግዶች ምግብነት ይውላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ስለመንደሩ የእርሻና የሌማት ትሩፋት ተግባራት ሲያስረዱ ‹‹ቤኑና ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ዘይቱን፣ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ መንደሪን እና የመሳሳሉት በስፋት የለሙበትና ለምግብነት የሚውሉበት ሪዞርት ነው‹›› ብለዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ እርሻን ለሪዞርቱ ሙሉ በሙሉ ግብዓት አድርገን ለመጠቀም የሚያስችል ስራ ተሰርቶበት የተሳካ ውጤት ተገኝቶበታል። እርሻው በርካታ ሰዎች የስራ እድል እንዲያገኙ አስችሏል።
ከእርሻው በተጨማሪ የሌማት ትሩፋትን በሚመለከት በዚህ ስፍራ ግመሎች፣ ላሞች፣ ፍየሎች፣ ዶሮዎች እና ሌሎች አሉ። በቀን ከ400 እስከ 500 እንቁላል ይመረታል። ለግቢው የሚያስፈልገው እንቁላል፣ ስጋና ወተት ከዚሁ ይመረታል። እያንዳንዱ ሪዞርት ከእርሻውም ሆነ ከሌማቱም በዚህ መንገድ ስራ እየሰራ ከሄደ ራሱን መመገብ መቻሉ ብቻ ሳይሆን የሚፈጥረው የስራ እድል እና የሚቀይረው አካባቢ ትልቅ እንደሚሆን ማየት ይቻላል፡፡
‹‹ቤኑና›› በየትኛውም ዓለም ከሚገኙ ሪዞርቶች ጋር ሊስተካከል የሚችል ጥራት ያለው መሰረተ ልማቶችን የያዘ ቦታ እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፣ መንደሩ ለትራንስፖርት ምቹ ከመሆኑ ባሻገር፣ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች የቱሪስት መስህቦችን በቀላሉ ለመጎብኘት እድል እንደሚፈጥርም ያስረዳሉ፡፡
ሪዞርቶቹ የተሰሩበት ጥራት በአምስት ኮከብ ደረጃ እንዲታዩ የሚያስችላቸው ነው። ከአዲስ አበባ የሚነሳ ሰው ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል በመኪና ተጉዞ ‹‹ቤኑና›› መድረስ ይችላል። መንደሩ ከደረሰ በኋላም አንድ ሳይሆን ሁለት ብሔራዊ ፓርኮችን የማየት እድል አለው። ወደመንደሩ የሄዱ ሰዎች ወደፊትም ሆነ ወደኋላ ቢጓዙ ሊጎበኙ የሚችሉ በርካታ ቦታዎችን ማግኘት ስለሚችሉ ኢትዮጵያን መጎብኘት ለሚፈልጉ ሰዎች አካባቢው ምቹ ስፍራ ይሆናል።
ከ‹‹ቤኑና›› መንደር በቅርብ ርቀት ላይ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ይገኛል። እንግዶች ወደ መንደሩ ከመጡ በኋላ ወደ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ሄደው በፓርኩ የሚገኙ አዕዋፍትና እንስሳትን እንዲሁም ፏፏቴዎችንና ፍልውሃዎችን የመጎብኘት እድል ያገኛሉ። ከፓርኩ በቅርብ ርቀት ላይ ደግሞ በአፋር ክልል በገበታ ለትውልድ የሚሰራው ፕሮጀክት ይገኛል። የአሰቦት ፓርክም በአካባቢው የሚገኝ ድንቅ የመስህብ ስፍራ ነው። በአካባቢው ባሉ ቦታዎች ላይ የተፈጥሮ ፍል ውሃዎች፣ ሃይቆችና ፏፏቴዎች ስለሚገኙ ከዚህ ቀደም በውጭ ሀገራት የምናያቸውንና የምንቀናባቸውን ነገሮች በዚህ አካባቢ በስፋት የማየት እድልን የከፈተ ነው። ሰዎች የዱር እንስሳትና ሌሎች ነገሮችን ለማየት ወደ ሌሎች ሀገራት ከመሄድ ይልቅ በሀገራቸው የተሻለ የመጎብኘት እድል እንዲያገኙ ያስችላል። በአጠቃላይ አካባቢው የኢትዮጵያን ልክ ለማወቅ የሚያግዝ ድንቅ ስፍራ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን መንደሩን ለጎብኚዎች ክፍት በማድረግ እንግዶችን የማስተናገድ ስራው እየተጀመረ በመሆኑ ሰዎች እስከሚለማመዱና የቦታውን ውበት እስከሚያዩ ድረስ የጎብኚዎች ፍሰቱ ውስን ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን በአካባቢ የሚኖረው የቱሪስት አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያድግ ይገልፃሉ።
ስካይላይት ሆቴል የ‹‹ቤኑና›› መንደር ሪዞርቶችን የማስተዳደር ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በ‹‹ገበታ ለሀገር›› የተገነቡ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እያስተዳደረ የሚገኘው ሆቴሉ፣ በወንጪ፣ በጎርጎራና በሃላላ ኬላ የሚያከናውናቸውን አመርቂ ተግባራቱን በ‹‹ቤኑና››ም እንዲደግማቸው ኃላፊነት ተጥሎበታል።
‹‹እኛ ለሕዝባችን ቃል በገባነው መሰረት ትልቅ ሕልም አለን። ሕልማችን የበለፀገችና የተለወጠች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ማስረከብ ነው። ይህ ሕልም ግን በየዕለቱ በስራ፣ በትጋት የማይገለጥ ከሆነ ስለማይመነዘር ሕልማችንን በስራና በጥረት በመግለጥ ውጤት በማሳየት፣ ውጤቱም ብዙ ሰዎችን እየሰበሰበ እንዲሄድ በማድረግ የኢትዮጵያን መፃኢ ጉዞና መልክ የማስዋብና የማላቅ ስራችንን እንቀጥላለን። ከቤተሰብና ከወዳጅ ጋር በመምጣት ይህን ስፍራ በማየት የኢትዮጵያን ልክ እንድናውቅና እንድንማር ለብዙዎቻችን ጠቃሚ ስለሚሆን ይህን ስፍራ በማየት የኢትዮጵያን ውበት ማድነቅና መግለጥ የምንችል ሰዎች መሆን አለብን›› ብለዋል።
በአርባምንጭ፣ በጅማ፣ በሱማሌ፣ በገረአልታ፣ በሐይቅ፣ በደምቢና በሌሎች አካባቢዎች የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናቀቁ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በቱሪዝም ሴክተር የጀመርነውን እንቅስቃሴ አጠናክረን በመቀጠል የኢትዮጵያን ልክ ለዓለም እንገልጣለን። ብልጽግናን በኢትዮጵያ ለማየት የሚያስችል መሰረት እንጥላለን። ልጆቻችን ለማኝ ያልሆኑ ኢትዮጵያን እናስረክባቸዋለን። ይህን ከማድረግ ሊያቆመንና ሊገታን የሚችል ኃይል የለም›› ብለዋል፡፡
‹‹ቤኑና›› ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን በርካታ ቅንጡ የመዝናኛ ስፍራዎች ካሉባቸው የበለጸጉ ሀገራት የመጡ ሰዎችን ጭምር ያስደነቀ ውብ መንደር መሆን ችሏል። በመንደሩ ምርቃት ላይ የተገኙ የሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ለ‹‹ቤኑና›› ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር እና የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ተወካይ ዳረን ዌልች፣ በፕሮጀክቱ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ሕልምና ለሀገራቸው ማደግ ያላቸውን ሃሳብ እንዳዩበት ይናገራሉ። ‹‹በስራው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ያላቸውን ትልቅ ሕልም አይቻለሁ። ይህን ሀገር ለማሳደግ ያላቸውን ሃሳብም ተመልክቻለሁ። የተገነባው ሪዞርት አስደናቂና ደረጃውን የጠበቀ ስፍራ ነው›› ሲሉ አስታውቀዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ገና ሁለት ወራት ብቻ እንደሆናቸው የሚናገሩት በኢትዮጵያ አውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር፣ ኢትዮጵያ የታላላቅ ታሪኮች ባለቤት እንደሆነች ጠቅሰው፣ የተከናወነው ስራ አስደናቂ እንደሆነና በአካባቢው በርካታ አስደሳች ነገሮችን እንደተመለከቱ ይገልፃሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፣ አካባቢው ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሃብቶች ተሰናስለው ውብ ገጽታን ያላበሱት አስደናቂ ስፍራ በመሆኑ መንደሩ የተላበሰው ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ምቹ ነው። የመንደሩ ግንባታ ለአካባቢው ነዋሪ የስራ እድል ይፈጥራል። ስፍራው ለማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም (Community-Based Tourism) ተምሳሌት መሆን ይችላል። ስራው ኢትዮጵያ ቱሪዝምን ከሀገር በቀል የግብርና ስራ ጋር በማጣመር እያከናወነች ያለችው ዘርፈ ብዙ ተግባር ማሳያ ነው።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር መርየም ሳሊም በበኩላቸው ‹‹ባየሁት ነገር ተደምሜያለሁ። የሚታየው ነገር ሁሉ እረፍትን የሚሰጥ ነው። ከቤተሰቦቼ ጋር በድጋሚ መጥቼ እጎበኘዋለሁ። ሰዎችም ወደዚህ ስፍራ መጥተው እንዲዝናኑ እጋብዛለሁ›› በማለት ስለመንደሩ አስደማሚነት ያስረዳሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም