አውራው ሙዚቃ አምባ

አንድ ሰው ሙዚቃን ሲጫወት ምናልባትም በግሩም ድምጹ “ከሰማይ ወፍ የሚያረግፍ!” ተብሎለት ይሆናል። ከፒያኖ ፊት ሲቀመጥ “ይሄስ ድንጋዩንም በስሜት ያነዝራል!” የተባለለት ይሆናል። ብቻ ሌላም ይሆናል…የማይሆን የለምና።

ከሙዚቃ አውራዎቹ መካከል ለመሰለፍም በርከት ላሉት ዕድሉ አይጠፋም። ግን ግን…ራስን ችሎ አንድ የሙዚቃ አምባ ለመሆን ግን ዳዊት ይፍሩን መሆንን ይሻል። ሙዚቃ እርሱ ውስጥ ብቻ ሳትሆን እርሱም ሙዚቃ ውስጥ ነው። አምባ የመሆን ሚስጥሩ ከችሎታው ብቻ አይደለም። ከግል ብቃቱ ከፍ ብሎ በሙዚቃ መንደር ከባቢ ላይ ሁሉ እንደተንሰራፋ አየር ነው። ውስጡ ካለው ሙዚቃ ጋር ሙዚቀኞችም አሉበት። በሄደበት ሁሉ አምባውን እንደሠራላቸው ነው፡፡

በድምጹ ባያንጎራጉር ከሚያንጎራጉሩት ጋር አይጠፋም። ማይክ ጨብጦ ድምጹ ባይሰማም ከበስተጀርባ ግን ስምና ሥራው አለ። ሙዚቃ ሲባል ከየትኛውም ቦታና ጊዜ መከሰቱ አይቀርም። ስለሙዚቃ አምባ ካወጉ አውራውን ሳያነሱት አያልፉም። ዙፋን ተቀምጦ የሀገሩ ዳር ድንበር ሁሉ በስሩ እንዳለ ብርቱ ንጉሥ፤ ባይኖር እንኳን አለበት። ትናንትን በደንብ ያውቃታል። ከዛሬም ጋር በደንብ ይግባባል። እላይ ወጥቶ ከታላላቆች ጋር በሠራው ልክ እታች ወርዶም ከታናናሾች ጋር ይታያል። በትልቁና በትንሹ፣ በዘመንና ዘመን፣ በሙዚቃና በሙዚቀኞች መካከል ድልድይ የሆነ ሰው ነው፡፡

ዳዊት ይፍሩን በቃላት ከመግለጽ ይልቅ ሥራዎቹ ይበልጥ ይናገራሉ። ሮሃ ባንድ ሲታወስ ምስሉ የዳዊት ይፍሩ ነው። ቬነስ ባንድንም ቢጠሩት ድምጹ ከዳዊት ይፍሩ ነው። ዳሕላክ ባንድ አፍታ የማይዘነጋው ትዝታው ነው። …በአጠቃላይ “ባንድ” ሲሉ ዳዊት ይፍሩ ብለው ባይጠሩትም፤ ዳዊት ይፍሩ ግን ከውስጥ አለበት። በርሱ ፊታውራሪነት የተመሠረቱ ባንዶች በርከት ያሉ ናቸው። እርሱ ከሙዚቃ ጋር ያለው ተዛምዶ የተለየ ነው። ማን ይናገር ካሉ የሠራቸው ከ2 ሺህ 500 በላይ የሆኑ ሙዚቃዎቹ ይናገሩታል።

“ኸረ እንደው ግን ሙዚቃን መቼ ይሆን የተዋወቅካት?” ለሚሉት ሁሉ ገና የ11 ዓመት ልጅ ሳለ ጀምሮ እንደሆነ ይናገራል። ገብቶም ወጥቶም፣ ሄዶም ተቀምጦም የሚስበው አየር፣ የሚያስወጣው ትንፋሽ ሁሉ ሙዚቃ ነበር። ልክ እንደመንታ ወንድሙ በሄደበት ሁሉ እሱ አለ። ግን ይህን ሁሉ ነገር ዳዊት አያውቅም። እንዲያው በደመነብስ ወስዶ ሙዚቃ ላይ ይጥለዋል እንጂ ሙዚቀኛ ነው የምሆነው የሚል ሀሳብ እንኳን ውልብ አይልበትም። ደግሞ አሁንም ትልም ሕልም ሳይል ወደ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቲያትር ቤት ገባ።

ለአምስት ዓመታት ያህልም የሙዚቃ መሣሪያዎችን ተማረ። ጊታር፣ ኪቦርድ፣ አኮርዲዮን፣ ትንሽዬዋን ቲፓኒ ሁሉ ተማረ። “እኔ ሙዚቃን ለመማር ነው የገባሁት። ሂደቱ ነው ሙዚቀኛ ያደረገኝ። ስማርም ለጊዜ ማሳለፊያ፣ ለተዝናኖት ያህል ነበር” ይላል። ሲፈጥረውም የሙዚቃ ጥበብ መርጣ ዘይቱን አፍሳበት ነበርና በችሎታው ከተማሪዎቹ ሁሉ ላቀ፡፡

ሁሉንም በቄንጥ አሳምሮ ሲጫወት ደርሶ ትንፋሽ ላይ ግን ቆም አለ። እስካሁንም ድረስ ያልተፈታተሹት ከትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ነው። ከእነርሱ ጋር ፍቅርም ሆነ እልክ ያለው አይመስልም፡፡

ዳዊት ይፍሩ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ማነው? ሁሉም ሰው እርሱ ማለት ብሎ እንደሚመልሰው አንጋፋና ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ባለሙያ ነው። ግን ይሄ እውነት ብቻ የርሱን የሙዚቃ ውሃልክ አያመጣውም። ምክንያቱም በሙዚቃ ሕይወቱ ውስጥ ጥንቅቅ አድርጎ የሚያውቀው ሙያውን ብቻ አይደለም። የሙዚቃ ንፋስ የነፈሰባቸውን ባለሙያዎችንም ችሎታ አብጠርጥሮ የሚያውቅ ሰው ነው።

እያንዳንዱን ባለው ነገር ልኬት ሳያዛንፍም ማስቀመጥ የሚችል ነው። ካለፈውም በሉት ካለው ማን፣ በየትኛው ሥራው፣ ምን እንደሆነ በልበሙሉነት ይገልጸዋል። እድሜና ጤና ሰጥቶት የሁሉንም ዘመን ፈርጦች ተመልክቷል። ከመልካሙ ተበጀ እስከ ጥላሁን ገሠሠ፣ ከሙሉቀን መለሰ እስከ ማሕሙድ አሕመድ፣ አልፎም እስከ ኤሊያስ መልካ ከወዲሕኛው ዘመን ክዋክብት አብሮ በጋራ ያልሠራው የለም። ባይሠራ እንኳን የሁሉንም ሥራዎች ነገሬ ብሎ መፈታተሹ አይቀርም። ተማሪም አስተማሪም፣ አባትም ባልደረባም ሆኖ ያልተገናኘው የለም። ሙዚቃንም ሆነ ሙዚቀኛውን በማወቅ ደረጃ ምናልባትም በጣት ከሚቆጠሩት መካከል ፊተኛው ነው፡፡

ከጎበዝ ተማሪ ጀርባ ቢያንስ አንድ ጎበዝ አስተማሪ መኖሩ አይካድም። ውብ ሕንጻ ለማነጽ የሚችለው ውብ የሆነ ሙያ ያለው ብቻ ነው። ዳዊት ይፍሩን ስንመለከትም ከበስተጀርባው ሆነው የምንመለከተውን መልኩንና እሱነቱን የሠሩ ታላላቅ ጠቢባን ስለመኖራቸው ሁሌም የሚናገረው ነው። “የኔታ የሙዚቃው ጌታ!” እያለ ከእግራቸው ስር ቁጭ ብሎ ጥበብን የቀሰመባቸው በሀገራችን ሙዚቃ ውስጥ አውራ ስም ያላቸው ናቸው። አንደኛው ጸጋዬ ደባልቄ ነው። ፒያኖና ቅንብርን ደህና አስቀሰመውታል። ጌታቸው ደገፉም በፒያኖ አሉበት። ግን ከሁሉም በላይ የሆነ አንድ ሰው አለ፤ እሱም ሙሴ ነርሲስ ነው።

ዳዊት ወደ ባንዱ ጠጋ የማለቱን ዕድል ካገኘ በኋላ በቫዮሊን፣ ፒያኖ፣ በጊታር እንዲሁም በሙዚቃ ቅንብር ቀደም ሲል የጀመረውን መንገድ ጠርጎ ወለል አደረገለት። ውስጡ በነበረችው እርሾ አድርሶ፣ እሳቱን አቀጣጥሎ አበሰለው። ዳዊትም ከዚህ በኋላ ስለ ሙዚቃ ወስኖ ሳያንገራግር ስለመኖር እንዲያስብ አደረገው፡፡

የሙዚቃ መሣሪያዎቹን አሳምሮ በብቃት ከመጫወቱ አልፎም፤ ምስጋና ለታላላቅ የኔታዎቹ ይግባና እነርሱን እየተከተለ ሙዚቃ ማቀናበርም ጀማመረ። “ለሠርጓ ጠራችኝ” የመልካሙ ተበጀ ተወዳጅ ሙዚቃ ነች። ይህቺ ሙዚቃ ደግሞ የዳዊት ይፍሩ የአቀናባሪነት አሀዱ ናት። የተማረውን፣ ያየውንና የሰማውን የቅንብር ዕውቀት አሰባስቦ ጥበቡን በማፈርጠም አንድ ብሎ ይቺን ሚዚቃ አቀናበረ። መልካሙ ተበጀ ለጉድ ተሰማለት። ዳዊት ይፍሩም ተጨበጨበለት። “ይችላል!” አሉት። “እችላለሁ!” አለ። ብቃቱን እርሱም እነርሱም አረጋገጡ፡፡

የእርሱ የሙዚቃ ዥረት መፍለቅ የጀመረበት ትልቁ ወንዝ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ቤት ነው። በ1950ዎቹ አጋማሽ የሙዚቃ ትምህርቱን ሲማር እንኳን እንደ አቦሸማኔ ፈጣን ነበርና ሲጨርስ ደግሞ እሳት ለበስ ዳይኖሰር መሰለ። በፍጥነት የመልመድና የመከወን ችሎታው ላቅ ያለ ነበር። በነበራቸው ጉብዝና ተማሪውን ሁሉ ከኋላ ከሚያስከትሉት መካከል አንዱ ነበረና እየተማረ በወር 20 ብር ለኪስ ይከፈለው ነበር። የቲያትር ቤቱ ባንድ ሲመሠረትም የፊት መድረክ ተሰላፊ ነበር። ጥቂት የማይባል ጊዜ በባንዱ ውስጥ ሲሠራ ከቆየ በኋላ ቀጥሎ ወደ ሀገር ፍቅር ነበር ያመራው።

በዚያም የሙዚቃ ችሎታውን እያጠነከረው የተወሰነ ቆየ። በጊዜው የነበሩ እውቅ ሙዚቀኞች ሁሉ ሳይረግጡት የማያልፉት አንድ ቤት ነበርና ሦስተኛ መዳረሻውን ወደዚያው አደረገ። አሰገደች አላምረው ቤት የአብዛኛዎቹ ሙዚቀኞቹ መዋያና ማምሻ የነበረና አሁን “ክለብ” እንደምንለው ዓይነት ነበር። ጎበዞቹ ሁሉ ጎራ ብለው ሠርተውበታል። ለዳዊት ይፍሩም እጣ ክፍሉ ሆነና ገባ። ወዲያው እንደገባ ባይሆንም እምብዛም ሳይቆይ በገባበት እግሩ ተመልሶ መውጣቱ ግን አልቀረም፡፡

ዳዊት ይፍሩ ከሙዚቃ መሣሪያዎቹ ጋር ያልደረሰበት የለም። በቅንብር ከሠራቸው አንደኛው ግን የማሕሙድ አሕመድ “ሁሉም ይስማ” የሚለው አልበም ነው። ይህንን አልበም ሲሠራ ብቻውን አልነበረም። ወጣቱ ኤሊያስ መልካም በገሚሱ ላይ አብሮት ነበር። አልበሙ ከያዛቸው አሥር የሙዚቃ ስብስቦች 5ቱን ዳዊት፣ ቀሪ አምስቱን ደግሞ ባለጊታሩ ኤሊያስ መልካ ነበር የሠራው። በሌላ ጊዜም በጸጋዬ ዘርፉ አልበም ላይ ተገናኝተዋል። በጊዜው አልበሙን ሲሠሩ በጣም ተጠበው ከመሆኑም የጸጋዬ የአዘፋፈን ስልትም ግሩም ስለነበረ ገበያ ላይ ሲወጣ ሀገር ምድሩን ያጥለቀልቀዋል ብለው ቢጠብቁም እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ቀርቷል። ባይሆን በዚያው ሰሞን አብሮ የወጣው የንዋይ ደበበ “የ .ቅ .ትአ .ባ” ግን አቀባበሉና ተወዳጅነቱ የተለየ ነበር፡፡

ዳዊት ይፍሩ ራሱን የቻለ አንድ የሙዚቃ አምባ ነው እንድንል የሚያደርገን ሌላ ቢኖር ባንዶቹ ናቸው። በየበረሃው ድንኳን እንደሚጥል ሰው በሄደበት ሁሉ ባንድ ማቋቋም ይወዳል። ከሀገር ፍቅር ቆይታው በኋላ ከሙዚቃ መሣሪያዎቹ ጋር ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ይገኝ ነበር። በወቅቱም እርሱና የሥራ አጋሮቹ ተጠናክረው “ኤኩኤተርስ” የተሰኘ ባንድ መሠረቱ። የርሱ አሻራ ያረፈባቸው ባንዶች ቁጥር በርከት ያሉ ናቸው። በኋላም አይቤክስና ዳሕላክ ባንዶች ምርጡን ጥምረት ፈጥረው በሕብር ሲቆሙ ከውስጡ ሮሃ ባንድ ተወለደ። የሮሃ ውልደትም ቀዳሚውን ሚና ለዳዊት ይፍሩ ይሰጣል። ባንዱ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የነበረውን ሥራና ስም ለማንም አይነገረውም። በዚህ ባንድ ውስጥ ዳዊት ብቻ ከ200 በላይ በሆኑ የአልበም ሥራዎች ውስጥ እስትንፋሱን አኑሯል። በ1970ዎቹና 1980ዎቹ ገደማ ከተሠሩ ልብ አቅላጭ ሙዚቃዎች መካከል አብዛኛዎቹ የዳዊት ይፍሩ የጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡

ሁሉም ሰው ወዶ ከሚውልበት ቦታ ላይ ለመገኘቱና ለመቆየቱ ምክንያት የሚሆኑት ነገሮች ይኖሩታል። ታዲያ ዳዊት ይፍሩ ይህን ሁሉ ዘመን ከሙዚቃ ጋር በሙዚቃ የሚኖርበት ምክንያት ምን ይሆን? ብዙዎች ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሉት “ሙዚቃን ስለማፈቅር፣ ያለሙዚቃ መኖር ስለማልችል” ነው። ዳዊት ይፍሩ ግን በሚዲያዎችም ይሁን በጨዋታ “የምንሠራው አንደኛው ለስሜታችን፣ ሁለተኛ ለመታወቅ፣ ሦስተኛ ደግሞ ለገንዘብ ነው” በማለት እቅጯን ያስቀምጣታል። እንዲህ ሲል ግን አንድ ሁለት ብሎ በደረጃ ያስቀመጠው ቅደም ተከተሉ ሳይዛባ ነው። ከስሜቱና ከሙያ ፍቅሩ ወደ ሦስተኛው ዘሎ ገንዘብን አስቀድሞ አያውቅም። ብዙ ጊዜ ጥቅሙን ሳያሰላ የሚሠራ ሰው ነው። በተለይ ደግሞ በሮሃ ባንድ ውስጥ የተሠሩ አብዛኛዎቹ ሥራዎች በዝቅተኛ ክፍያ፣ አልፎም በነጻ የተሠሩ ናቸው፡፡

አሁን እድሜው ገፍቶ፣ ከብዙ ውጣውረድ ተራርፎ እንኳን ሁሉንም ያሰባሰበውን የሙዚቀኞች ማሕበርን በፕሬዚደንትነት ይመራል። በዘመኑ ሁሉ ያጠራቀመውን የሙያ ክሕሎትና የሕይወት መንገድ ፍኖት ማሕበሩንና አባላቱን በእግር ለመቆም መውተርተርን አስተምሯቸዋል። የራሱ የሆነ ቅንጣት የገቢ ምንጭ የሌለው ተቋም ሆኖ ፈተናውን ቢያበዛም የተሻሉ መስመሮችን በማስመሩ ዳዊት የሚታማ አይደለም፡፡

ከምትወደው የሙዚቃ ስልት ምረጥ ቢሉት ነብሲያው ትዝታ ላይ ታርፋለች። ውስጡ በድባቴ ተወቅቶ፣ መከፋት ሆድ ቢያስብሰው፣ ዝም ብሎ በዝምታ ጥቂት ውስጡን ለማድመጥ ቢፈልግ ትዝታ ትራሱ ናት። ትዝታ መውጫና መግቢያው ናት። ለካስ አንዳንዴ ከጣትም ጣት ይመረጣል። በጣም የሚወዱትንና አብዝተው የሚሳሱለት ልጅ ትተው ዙፋኑን ለሌላኛው ልጅ እንድንሰጥ የሚያደርጉን ምክንያታዊ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። አብዝቶ የሚያደምጠው ትዝታን ቢሆንም በሙያዊ ልቦናው ሲመለከት ግን የሚያደንቀው አንቺሆዬን ነው። የአንቺሆዬ ቃናዋ ይበልጥ ያውደዋል።

ከ45 ዓመታት በፊትም በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ በተቀነባበሩ ስብስቦች አልበም ሠርቶ ገበያ ቢያውለውም አድማጭ ግን አልነበረውም። ጊዜው በድምጻውያኑ ሙዚቃ ሽር የሚሉበት እንጂ በክላሲካል የሚተክዙበት ስላልነበረ እንደዛሬው አይታወቅም ነበር። አሁን ከዚያ ሁሉ ዓመታት በኋላ ግን “ያንኑ ደግሜ አድምጡልኝ ለማለት ተገድጄያለሁ” አለ እርሱም። ምስጋና ለቴክኖሎጂው ይግባና እኚህኑ ሥራዎቹን እንደ አዲስ በዩትዩብ ማሕደር ላይ አኑሯቸዋል፡፡

ትልቅ ሰው ራሱን ብቻ ሳይሆን ሰውንም ያውቃል። ከዳዊት ይፍሩ መልከ ወርቅ ባህሪያት መካከል አንዱን ቢሉ በየዘመናቱ አሁንም ድረስ ታላቅ ሥራ እየሠሩ ያሉትን አብጠርጥሮ የሚያውቅ መሆኑን ነው። ማወቅ ብቻም አይደለም በብዙ መድረኮች ከራሱ ይልቅ ስለሌሎች ሲያወራ ይደመጣል። አሁን ከሚመለከታቸውና ከሚያደምጣቸው እየጠቀሰ ትልቅነታቸውን ይናገራል። ወደላይ ማንጋጠጥ ብቻ ሳይሆን ወደታች ማቀርቀርም ያውቅበታል። ከጊዜው ወጣት የጥበብ ባለሙያዎች መካከል ላገኘው ሁሉም ይመሰክርለታል። የርሱ የትንሽነትና ትልቅነት ሚዛን ከሥራቸው ላይ ብቻ ነው። ከስር እየመጡ ያሉትን በሙያ ለማብቃት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው። “ወ .ትድ .ጻ .ያ . ከ .ዊ . ጋ . አ .ሬብ .ራብ .ውከ .ጡ . አ .ሬ .ቸ . ል .ራፈ .ደ . ነ .።ሥ . ከ .ጣእ .ራ .ሁግ . ሥ . ፈ .ጌየ .ሄ .በ . እ .ሜላ . አ .ደ .ሁ .” ሲ . ይ .ገ .ል .፡ “እ .ዴ . ነ . ዳ .ትይ .ሩከ .ሎ . ጋ . ሥ . ላ . በ .ሆ .በ . ጊ . በ .ዚ .ኞ . ላ . እ .ቀ .ደይ .ወ .ልይ .ሉ .?” አ .ውአ .ዱጋ .ጠ .።“ኸ . በ .ራ . የ .ይ .ነ .ን…እኔ በማንም ሆነ በሥራ ላይ ቀልጄ አላውቅም” ሲል ዳዊት ይመልሳል። ዳዊት ይፍሩ ለብዙዎች ኮስታራና ዝምተኛ ነው። ሲቀርቡት ግን ቀልደኛና ጨዋታ አዋቂ ነው። ከስድስት ዓመታት ወዲህ ግን የእውነትም ዝምተኛ መስሏል። ባለቤቱን በሞት ከተነጠቀ በኋላ ያለበት ሁኔታ ጥሩ አይደለም። ለተወሰኑ ጊዜያትም መከፋት በርትቶበታል። “መኖር አላሰኘኝም ነበር ግን ለልጆቼ ስል ነው የምኖረው” ነበር ያለው፡፡

የሙዚቃ አባው ዳዊት ይፍሩ ዛሬ ድረስ በሥራው ያገኛቸው ሽልማቶች በርካታ ናቸው። ለአብነትም በ2005 ዓ.ም ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትን ተጎናጽፏል። ትልቁን የሎሬት ሜዳይ ለማጥለቅም ችሏል። በተለያዩ ጊዜያቶች የተበረከቱለት ዋንጫና ሰርተፍኬቶች ከቤቱ ታጭቀዋል።

ዳዊትን ሙዚቀኛ ባትሆን ኖሮ… አትበሉት፤ ምክንያቱም ሙዚቀኛ አለመሆን አይችልም ነበር። የሆነበት አኳኋን መርጦ ሳይሆን ተመርጦ ነው የሚመስለው። በሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ገብቶ ሳያስበው ለመመለስ ከማይችልበት ረዥም መንገድ ደርሶ ነበር ሙዚቀኝነቱን አውቆና አምኖ የተቀበለው። አስቦና ሆነ ብሎ ሙዚቀኛ ስላልሆነ ከፈቃዱ ውጭ በሆነ በአንዳች የጥበብ ኃይል ነበርና ያለመሆን ምርጫ አልነበረውም። “ሙዚቀኛ ባልሆን ኖሮ የሚለው አይሠራም። ሙዚቀኛ ባልሆን ኖሮ ያው አይደለሁም ማለት ነው” ምላሹ። ገና በጨቅላ ልጅነቱ ሳለ አባቱ ትክ ብለው ይመለከቱትና “ይሄ ልጅ ወታደር ነው የሚሆነው” ይሉት ነበር። ግን አልሆነም። የእርሱ መክሊት ለጦር አውድማ ሳይሆን ለሙዚቃ አምባ ነበርና አውራ የሙዚቃ አምባ ሆኖ ኖረው።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You