አዲስ አበባ፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ)‹‹የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወደ ሀገር የተመለሰው ጦርነት ለመክፈት አይደለም ፤ አሁን የትግል ምእራፍ ተዘግቷል፤ በጫካ ያለ የኦነግ ሃይል ወደ ካምፕ እንዲገባ እንፈልጋለን ሲሉ የኦነግ ምክትል ሊቀመንበር አስታወቁ።
ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፣ ኦነግ ያለፈውን እና ወደፊት የሚያጋጥሙትን እድሎች በማገናዘብ የትጥቅ ትግል ምእራፍን በመዝጋት ሰላማዊ ትግልን መርጧል፤ ይህንን ደግሞ የድርጅቱ አባላት፣ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ሃይል እና ደጋፊዎች አክብረው መቀበል አለባቸው።
ምክትል ሊቀመንበሩ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ በመወሰን ወደ ሀገር ከገባን በኋላ ወደ ትጥቅ ትግል የሚመልሰን ምክንያት የለም ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከኤርትራ ወደ ሀገር ሲመለስም በታላቅ እምነት ራሱን ለመንግስት አሳልፎ በመስጠት ነው ያሉት አቶ አራርሶ ፣ኦሮሚያ ውስጥ በምንቀሳቀስበት ወቅትም ችግር አጋጥሞን አያውቅም ብለዋል፡፡ መንግስት ሃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ እየተወጣ እንደነበረም ገልፀዋል።
በጫካ ውስጥ ታጥቆ ያለው የኦነግ ሃይል አርዳይታ ገብተው የነበሩ የኦነግ ጦር አባላት አያያዝ ላይ ጥያቄ ነበራቸው ያሉት አቶ አራርሶ፣ ወደ ማሰልጠኛ ካምፕ ከገባን በኋላ አያያዛችን መልካም ካልሆነስ የሚል ጥያቄ እንደነበራቸውም አስታውቀዋል። ይህ ጥያቄም መንግስት እና ኦነግ ባዋቀሩት የጋራ ኮሚቴ አማካኝነት የኦነግ ታጣቂዎችን ወደ ካምፕ ለማስገባት እየተደረገ የነበረው እንቅስቃሴ እንዲጓተት እና ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
መንግስትም የሰጠው ጊዜ በመጠናቀቁ እና ከዚህ በኋላ አልታገስም በማለት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የፀጥታ ሃይልን በማሰማራቱ የተፈጠረው ግጭት እስካሁን እንዲቆይ አድርጓልም ሲሉም ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡
በግጭቱ ጫካ ውስጥ የሚገኙ የኦነግ ታጣቂዎች፣ የሰላማዊ ሰዎች እንዲሁም የኦሮሚያ እና የፌዴራል መንግስት የፀጥታ ሃይሎች ህይወት መጥፋት እንዳልነበረበት ተናግረው፣ ሁኔታው የሚያሳስባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኦሮሞ ሃይሎች አንዱ አንዱን ለማዳከም የሚያደርጉት ጉዞ ጠላትን የሚያስደስት መሆኑን ተናግረው፣ ለችግሩ ትኩረት በመስጠት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ለመፍታት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።
እርስ በእርስ መጋጨት፣ መካሰስ፣ መወነጃጀል እና መተኳኮስ ቀርቶ አሁን የተገኘው ለውጥ መሬት መያዝ አለበት፤ ስለዚህ ችግሮቻችንን በውይይት እንፈታለን ሲሉም አስታውቀዋል።
ህዝቡ በተደጋጋሚ በኦዲፒ እና በኦነግ መካከል ያለው ግጭት እንዲቆም ሲጠይቅ ነበር ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ አሁንም ቢሆን ጠላት እንደሚፈልገው ኦሮሚያ የጦርነት እውድማ ትሆናለች በሚል ስጋት ሊገባን አይገባም ብለዋል።
ትልልቅ ችግሮችን እየፈታን መጥተናል፤ ሁለታችንም ለአንድ ህዝብ የታገልን በመሆኑ የቀሩ ትናንሽ ችግሮችንም በውይይት እንቋጫለን ሲሉም ተናግረዋል።
ስምምነታችን ስራ ላይ ውሎ በሁሉም አቅጣጫ የሚንቀሳቀስ የታጠቀ የኦነግ ሃይል ካምፕ ይግባ ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ እንደ ድርጅት ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወስነን የመጣን በመሆኑ ማንኛውም አይነት ጥያቄ ካለ ካምፕ ከገቡ በኋላም ማቅረብ እንደሚቻል ተናግረዋል።
አቶ አራርሶ “የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኦነግን አናግረው ወደ መንግስት በመሄድ አንድ ላይ ሊያገናኙን እቅድ ይዘዋል፤ ውይይቱም እንደሚሳካ እምነት አለን፤ የሚያሳልፉትን ውሳኔም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንቀበላለን” ብለዋል።
ከዚህ በኋላ ከሰላማዊ ትግል እና ውይይት ውጪ የታጠቀ ሃይል ጫካ ተቀምጦ ድንጋይ እየተንተራሰ የዛፍ ፍሬ እና ስራስር እየተመገበ መኖር መቆም አለበት፤ አንዱ አንዱን ማዳከምም አማራጭ አይሆንም ሲሉም አስገንዝበዋል። በአንድነት በመሆን አሁን የተገኘውን ለውጥ ወደ ትክክለኛ የዴሞክራሲ ምዕራፍ ማሻገር የሁላችንም ድርሻ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011