በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጡ የስፖርታዊ ውድድሮች ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ እየተከናወኑ ይገኛል።በኢንተርኔት በመታገዝ ቨርቹዋል ስፖርታዊ ውድድሮችን የተለያዩ ሀገራት በማካሄድ ላይ ናቸው።በኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ የቨርቹዋል የአትሌቲክስ ውድድሮች ለሁለተኛ ጊዜ ማካሄድ ተችሏል።ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በማድረግ ከሳምንታት በፊት አንጋፋ አትሌቶች የተሳተፉበትን ሩጫ በተሳካ ሁኔታ ማድረግ ችሎም ነበር።ታላቁ ሩጫ የመጀመሪያውን ልምድ መሰረት በማድረግ 500 የሚሆኑ አትሌቶች የተሳተፉበት በኢንተርኔት የታገዘ «ደህና ቆዪ ኢትዮጵያ» በሚል የ5ኪሜ ሩጫ ውድድር ለማዘጋጀት በቅቷል።የሩጫ ውድድሩ ግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ነበር በይፋ የተጀመረው።በውድድሩ 500 ተሳታፊዎችን በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ በሚጫን ስትራቫ (Strava) በተሰኘ የሩጫ ማስተናበሪያ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ሲያፎካክር ቆይቷል።በአዲስ አበባ ስታዲየም ግንቦት 29 ቀን 2012 ዓ.ም በተዘጋጀ የመዝጊያ ውድድር ፍፃሜውን አግኝቷል። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ ትልቅ የታሪክ ስፍራ ያለው ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ፣አትሌት ጌጤ ዋሚ ፣አትሌት ሙክታር ኢንድሪስና አትሌት ነጻነት ጉደታ በውድድሩ ፍፃሜ እለት በተካሄደ ሩጫ በልዩ ሁኔታ ሊጠናቀቅ ችሏል።
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ከግንቦት 24 እስከ 29 ቀን 2012 ዓ.ም «ደህና ቆዪ ኢትዮጵያ» የ5ኪ.ሜ የሩጫ ውድድር የመጀመሪያው አልነበረም ።ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ቨርቿል ሩጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. መካሄዱ ይታወሳል።የሩጫ ውድድሩን የታላቁ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ አስተባባሪነት በአንጋፋና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መሪነት የተካሄደም ነበር። የቨርቹዋል ሩጫውም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያሳደረውን ተፅዕኖ መቀነስና መቀየር ይቻል መካሄዱን የውድድሩ አዘጋጅ አካል አስታውቆም ነበር።በኢንተርኔት በመታገዝ ከግንቦት 14 እስከ 29 ቀን 2012ዓ.ም ለሰባት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው «ደህና ቆዪ ኢትዮጵያ»የ5ኪሜ ሩጫ ከዚሁ ተመሳሳይ አላማና ድምቀት በመላበስ የተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012
ዳንኤል ዘነበ