መጥፎነት እና ስግብግብነት እንደ መልካምነት እና ቸርነት ይጋባሉ፤ከአንዱ ወደ ሌላው ይተላለፋሉ ።መልካምነት እና ቸርነት አብሮነትን አሳክተው የጋራ ህልም እንዲኖር በማገዝ የሰዎችን ህይወት የተሻለ በማድረግ ይቀይራሉ።ስግብግብነት እና መጥፎነት ደግሞ አንዱን ከሌላው የማያስማሙ የጋራ ህልም ቀርቶ፤ አንዱ ሌላው ላይ የሚያሴርበት፤ አንዱ ሌላውን የሚነጥቅበት መነጣጠል የገዘፈበት እና በመጨረሻም ሁሉም ለጉስቁልና የሚዳረጉበትን ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡
እነዚህ ባህሪያት በተለያየ መልኩ ይዳብራሉ።በአገር ደረጃ ስግብግብነት እና መጥፎነት መንሰራፋቱ ሲነሳ የትምህርት ሥርዓቱ ተወቃሽ ይደረጋል። በቤተሰብ ደረጃ ሲጠቀስ ደግሞ የአስተዳደግ ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ይገባል።ብዙ ጊዜ ባለማስተዋል ውስጥ ጊዜ እና ቦታ ሳይሰጣቸው ያደጉ ህፃናት እንዲሁም ታላላቆቻቸው በጥሩ ሆነው ሞዴል ያልሆኗቸው ልጆች ሲያድጉ መልካም እና ቸር ከመሆን ይልቅ ስግብግብ እና መጥፎ ሆነው ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ይበድላሉ፡፡
ገና በ14 ዓመት ዕድሜዋ አባቷን ያጣችው ማረፊያሽ አበበ፤ በተንደላቀቀ ኑሮ ውስጥ የነበረው ህይወቷ የአባቷን ሞት ተከትሎ በመምዘግዘግ በከፋ ድህነት እና ልትሸከመው በማትችለው ኃላፊነት ውስጥ ዘፈቃት።አባቷ እሷን ጨምሮ የ15 ዓመት እና የ16 ዓመት ሁለት ታላላቅ ወንድሞች፤ ከታች የ11 ዓመት አንድ ወንድም እና የ8፣ የ 5 እና የ3 ዓመት ታናናሽ ሶስት እህቶችን ትተው ነው በድንገተኛ ሞት ይህችን ዓለም የተሰናበቱት፤አቶ አበበ ሲሞቱ ነፍሰጡር የነበሩት ባለቤታቸው ወይዘሮ ማስረሻ ጉልማ በሁለተኛው ወር ሁለት መንታ ሴት ልጆችን ተገላገሉ።
አባት ትተው የሞቱት ሀብት የሚያስተውል ቢኖር ቤተሰቡን በብቃት የማስተዳደር አቅም እንደነበረው የምትናገረው ማረፊያሽ፤አባት 45 እና 60 ሰዎችን የሚጭኑ ሁለት የአገር አቋራጭ አውቶቡሶች እና አንድ የቤት መኪና ነበራቸው።ከ545 ካሬ ሜትር መሬት ግቢ 100 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የመኖሪያ ቤትም ባለቤት ነበሩ።
የዚህ ሁሉ ባለጸጋው የእነ ማረፊያሽ ቤተሰብ በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ አጣ።የዘጠነኛ ክፍሏ ማረፊያሽ ትምህርቷን መቀጠል ብትችልም፣ታላላቅ ወንድሞቿ ግን ማቋረጥ ግድ ሆነባቸው፡፡
ታላላቅ ወንድሞቿ የአውቶቡሶቻቸው ረዳት ሆነው መስራት ጀመሩ።ማረፊያሽ እንደምትገልፀው፤ወንድሞቿ መስራታቸው ባልከፋ፤ነገር ግን ገንዘቡን በአግባቡ ይዘው ቤተሰባቸውን ከመርዳት ይልቅ ማባከን፤ አልፈው ተርፈው ከዕድሜያቸው በላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመሆን እየሰከሩ እናታቸውን እና መላ ቤተሰቡን ማሳዘን ጀመሩ፡፡
የአውቶቡሱን ገቢ ለቤተሰብ ‹‹አንሰጥም›› እስከ ማለት ደርሰው፣ቤተሰቡን ለምስቅልቅል ህይወት ይዳርጉት ጀመር።ይህን ሁሉ ያስተዋሉት ወይዘሮ ማስረሻ ግራ ተጋቡ።ልጆቹን በዘመድ አዝማድ በጎረቤት ሳይቀር አስመከሩ፤በዚህም የተወሰነ ገንዘብ ያገኙ ጀመር፡፡
ይሁንና የመጠጥ ሱስ እየተጣባቸው ይመጣል፤ ለአውቶቡሶቹ ማንቀሳቀሻ የሚሆን ገንዘብ እስከማጣት ይደርሳሉ፤ ቀስ በቀስ አውቶቡሶቹ ከገቢ ይልቅ ለወጪ የሚዳርጉ ሆኑ፡፡ ጎማ ሲተነፍስ እና የቴክኒክ ብልሽት ጎማ መቀየርም ሆነ የቴክኒክ ብልሽትን ማስጠገን አቃታቸው፡፡አውቶቡሱቹ ለመቆም ተገደዱ፡፡
የቤት መኪናውን በማከራየት የሚያገኙት ገቢ በቂ እንዳ ልነበር የምትናገረው ማረፊያሽ፣ትምህርቷን አቋርጣ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ፅዳት እየሰራች ደመወዟን ለእናቷ እየሰጠች የማታ መማር መጀመሯን ታስታውሳለች፡፡
ማረፊያሽ እንደምትገልፀው፤የአውቶቡሶቹ የጥገና ወጪ እየበዛ መምጣቱ መላ ቤተሰቡን ለችግር ዳረገው።በእንዲህ አይነት የስቃይ ውጣ ውረድ ማረፊያሽ 12ኛ ክፍል ብትደርስም ብሔራዊ ፈተናውን ማለፍ አልቻለችም፡፡
‹‹ታላላቅ ወንድሞቼ ላይ ተስፋ ቆርጬ ባለኝ አቅም ታናናሾቼን ለመርዳት ብታትርም፤ ለተወሰነ ጊዜ መኪናዎቹ በመቆማቸው ጎረምሶቹ ገቢያቸው ቆሞ እንደሌሎቹ የቤተሰብ አባላት የሚበሉት በማጣት ስለተቀጡ ‹ይመለሳሉ› የሚል ተስፋ ያድርባታል፤ይህን ተስፋዋን ለማለምለምም ከእናቴ ጋር ተመካክሬ የቤት መኪናውን በመሸጥ ለአውቶቡሶቹ ጥገና እንዲውል ይደረጋል፤በዚህ አይነት ሁኔታ ወደ ስራ የተመለሱት ወንድሞቿ ግን ቤተሰቡን ሊታደጉት አልቻሉም፡፡
‹‹ጎረምሶቹ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረጌ ትልቅ ጥፋት ነበር፡፡›› የምትለው ማረፊያሽ፣ ሁለቱም በፉክክር ለቤተሰብ የሚተርፍ ገንዘብ ለመስጠትም ሆነ ለማስቀመጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም››ትላለች፡፡የእነርሱ ኃላፊነት አለመሰማት የተቀሩትን ልጆች የከፋ የእርስ በእርስ ጥላቻ ውስጥ እንደከተታቸውም ትናገራለች፡፡
ማረፊያሽ ‹‹እናቴን ረዳለሁ፤ የታናናሾቼን ርሃብ አስታ ግሳለሁ፤ ህይወታቸውንም እቀይራለሁ ›› ብላ በቤት ሰራተኝነት ለመቀጠር ወደ ቤሩት አመራች።የማረፊያሽ ታናሽ ደግሞ ትምህርቱን አቋረጠ።ታናናሾቿ ግን በወንድሞቻቸው ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት እየተንገበገቡ ጥላቻን በማዳበር እንደምንም አባታቸው በተውላቸው ቤት ውስጥ እያደሩ አደጉ።
የማረፊያሽ ታናሽ ወንድምም የጠጪ ወንድሞቹን ጎራ ተቀላቀለ፡፡ ይህ ወንድሟ በጣም እየጠጣ መላ ቤተሰቡን በዋነኛነት እናታቸውን ማሰቃየት ጀመረ፡፡ በቤሩት ደህና የሚረዷት ሰዎች አጋጥመዋት እየሰራች በተሻለ ሁኔታ እየኖረች ለእናቷ ገንዘብ መላክ ብትችልም፤ ስልክ በደወለች ቁጥር እናትየው ያለእርሷ የሃሳብ እርዳታ ልጆቹን ማሳደግ እና ቤተሰቡን ማስተዳደር እንደከበዳቸው ይገልጹላት ጀመር፡፡ ብዙም ሳትቆይ ይህን የተመቻቸ ሕይወት ትታ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች፡፡
ሁለቱም መኪናዎች ከአገልግሎት ውጪ ሆነው ተሸጡ። ማረፊያሽ እንደምንም ብላ ታላላቅ ወንድሟቿ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ስለሆነ መንጃ ፍቃድ እንዲወጣላቸው አድርጋ በሹፌርነት ተቀጠሩ።ሌሎቹም ልጆች አደጉ።
እንዲያም ሆኖ ቤተሰቡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ባጣው ፍቅር የተነሳ መኪናዎቹ ተሸጠው ሲያልቁ የመኖሪያ ቤቱም ላይ የሽያጭ ሃሳብ ቀረበበት፡፡በተለይ የማረፊያሽ ታናሽ ወንድም የቤት ዕቃ እያወጣ መሸጡ አልበቃ ብሎት ፣‹‹ቤቱን ሸጣችሁ ድርሻዬን ስጡኝ›› እያለ ይወተውት ጀመር።
በቤተሰቡ ውስጥ አስተዋይነት፣ መልካም አሳቢነት እና ደግነት ጠፋ፤ ሴቶቹም እርስ በራሳቸው መስማማት ተሳናቸው፤ቤት ለማፅዳት አቅም እያላቸው ስንፍና እና ዳተኝነት የተጠናወታቸው ክፉዎች ሆኑ፡፡
ወንድሞቿ የቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ጉዳይ ሲነሳ የሚታሰባቸው የጋራ ሀብትን፤ የቤተሰብ ንብረትን ስለማ ቆየት አይደለም፤ሸጠው ስለሚያገኙት ገንዘብ ብቻ ሆነ፤ስለእናታቸውና እህቶቻቸው ህይወት መቀየርም አልተ ጨነቁም።
ለደላሎች ነግረው ቤቱን እንዲሸጡላቸው ቢያስጎበ ኙዋቸውም፣ ቤቱ በፈለጉት ፍጥነት ሊሸጥ አልቻለም፡፡አንዴ እነርሱ ‹‹በዚህ ዋጋ አንሸጥም›› ሲሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጎብኚ እንጂ እውነተኛ ገዢዎችን ማግኘት ሳይችሉ ቀሩ፤ያንንም ያንንም እያሳዩ በዋጋ ሳይስማሙ እየቀሩ ፣አንዴ ደግሞ አንዱ በሰጣቸው ዋጋ ሲቆጩ ብዙ ቆዩ፡፡
ከዋጋ ጋር በተያያዘ ሲጨቃጨቁ እና ሲጣሉ ዓመታት ተቆጠሩ። ቤቱ ሰላም እየራቀው መጣ።ምንም እንኳ ሁሉም ውጪ እየዋለ ማታ ገብቶ ቢተኛም፤ በአኗኗሩ እርካታ እየጠፋ ጠዋትና ማታ ጭቅጭቅ ሆነ፡፡
‹‹እንሸጣለን›› ብለው ገዢ ማፈላለግ በጀመሩ በሶስተኛው ዓመት ደፍሮ የሚገዛ መጣ።ሰውየው ለመግዛት አሰፍስፎ፤ ወዲያው ሁሉም በተገኙበት በውል እና ማስረጃ 545 ካሬሜትር መሬት ከ100 ካሬሜትር ያላነሰ ቤት ያረፈበትን ግቢ በአንድ ነጥብ አራት ሚሊየን ብር ገዛ።የማረፊያሽ እናት የሚስት ድርሻ በሚል ከሽያጭ ዋጋው ከወጪ ቀሪ ተቀንሶ እኩል ተካፍሎ 650ሺህ ብር አካባቢ ፣ልጆች ደግሞ እያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር ደረሳቸው፡፡
እናት በደረሳቸው ገንዘብ አነስተኛ ቤት ያረፈበት ህጋዊ መሬት አዲስ አበባ ውስጥ ለመግዛት ቢፈልጉም፣ አልተሳካላቸውም፡፡50 ካሬ ሜትር ቤት ያረፈበት 100 ካሬ ሜትር ቦታ ግቢ ያለው መሬት ቀርቶ፤20 ካሬ ሜትር ቤት ያረፈበት 75 ካሬ ሜትር ቦታ መግዛት ተሳናቸው፡፡
ቦታና ቤት ማግኘት ሲያቅታቸው በቤቱ ሽያጭ መጎዳ ታቸው እየገባቸው መጣ። የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ሲያጣሩ ቤቱን መሸጣቸው ይቆጫቸው ጀመር። በወረደ ዋጋ መሸጣቸው የገባቸው ቆይቶ ነው። ለካ ገዢው አጣድፎ፣ እነርሱም ባለማስተዋል የሸጡት ቤት በወቅቱ ገበያ ላይ ከእጥፍ በላይ በሚያወጣ ገንዘብ መሸጥ የነበረበት ነው፡፡
ወይዘሮ ማስረሻ ገንዘባቸው በኪራይ ቤት እየተመናመነ መጣ፤ እንደምንም ብለው ባለ46 ካሬ ሜትር አንድ የጋራ መኖሪያ ቤት ገዙ፤ልጆቹ ግን ሁሉም 50ሺህ ብሩን ለስድስት ወር እንኳ አልተጠቀሙበትም፤አንዳንዶቹ የቤት ቁሳቁስ፣ልብስ፣ ጌጣ ጌጥ ሲገዙበት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ለሱሳቸው አውለው ጨረሱት።
በሱስ የተጠመዱት ልጆች በእጃቸው የነበረውን ያን የመሰለውን ትልቅ ሀብት፤ ማረፊያቸውን፤ የአባታቸውን ቅርስ፤የወደፊት ተስፋቸውን እንደ ጠላት ገንዘብ አባከኑት፡፡መላ ቤተሰቡ ለጉስቁልና ተዳረገ፡፡
ከእናትየው ውጪ በቤታቸው በፈለጉበት ሰዓት ገብተው የሚያርፉት ልጆች ሁሉም የግለሰብ ቤት ተከራይ ሆኑ፡፡ሰርተው ያገኙትን ገንዘብ ለቤት ኪራይ ማዋላቸውን የህይወት ጉዟቸው አካል በማድረግ የጉስቁልናን ህይወት ቀጠሉ። ሰላም !
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012
ምህረት ሞገስ