የጋሸና-ቢልባላ-ሰቆጣ የመንገድ ፕሮጀክት አካልና ሰቆጣን አልፎ ከትግራይ ክልል ጋር የሚያገናኝ ነው።የሰሜን ወሎና ዋግህምራ ዞኖችንም በማገናኘት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ያረጋግጣል ተብሎም ተገምቷል፡፡በልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት ከተያዘለት የኮንትራት ስምምነት ተጨማሪ አመታትንም ፈጅቷል- የቢልባላ -ሰቆጣ የመንገድ ፕሮጀክት።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የጋሸና ላሊበላ ሰቆጣ ኮንትራት ሁለት ቢልባላ ሰቆጣ- ፕሮጀክት ተጠሪ መሐንዲስ አቶ ሞላ አድማሱ እንደሚገልፁት ፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ በይፋ የተጀመረው እ.ኤ.አ ሰኔ 12 ቀን 2015 ሲሆን፣ የቻይናው ፈርስት ሃይዌዬ በስራ ተቋራጭነት እንዲሁም ቤስት ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ሀገር በቀል አማካሪ ድርጅት የማማከሩን ስራ እያከናወኑት ይገኛሉ።
99 ነጥብ 75 ኪሎሜትር ርዝማኔ ያለው የመንገድ ፕሮጀክቱ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ በሙሉ የሚሸፈን ነው፤2 ነጥብ 04 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት በሶስት አመት የኮንትራት ጊዜ ውስጥ እስከ መስከረም 9 ቀን 2018 እንዲጠናቀቀ ታቅዶ ግንባታው ሲከናወን ቆይቷል።
ይሁንና በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት፣ተጨማሪ ስራ በመካተቱ፣ ጎርፍና መሬት መንሸራተትን በመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችና በህብረተሰቡ ጥያቄዎች ሳቢያ ለመጓተት ተዳርጓል፤ተጨማሪ የአደባባይና የመንገድ ማስፋትና ማርዘም ስራዎች በመካተታቸው እና በወሰን ማስከበር ችግሮች ምክንያት የኮንትራክተሩ የማቴሪያል አቅርቦት ችግር እንዳለ ሆኖ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ሁለት ዓመት ተኩል ፈጅቷል።ከሁለት ዓመት በፊት በአካባቢው የነበረው አለመረጋጋት የመንገዱን ግንባታ በማቋረጡ ለፕሮጀክቱ መዘግየት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
እንደ ተጠሪ መሃንዲሱ ገለፃ ፤የመንገዱ ስፋት በገጠር በአብዛኛው ተራራማ አካባቢዎች ላይ የትከሻ ስፋቱ በዲዛይኑ መሰረት 50 ሳንቲ ሜትር ሲሆን፣ ሜዳ ላይ ደግሞ 1 ነጥብ 5 ሳንቲም ነው። የኬሬጅ ዌይ አስፓልት ስፋቱ ደግሞ 7 ሜትር ነው፤ በዚሁ መሰረት የመንገዱ ስፋት ተራራማ አካባቢዎች ላይ 8 ሜትር ሲሆን፣ በሜዳማ አካባቢዎች ላይ ደግሞ 10 ሜትር ይሆናል ነው።
በከተሞች አካባቢ የመንገድ ፕሮጀክቱ ሁለት ዞኖችን፣ ሶስት ወረዳዎችንና ስምንት ከተሞችን እንደሚያቋርጥ ተጠሪ መሀንዲሱ ጠቅሰው፣ በሰቆጣ ከተማ በህብረተሰቡ ጥያቄ መሰረት የመንገዱ ስፋት ከ20 ወደ 27 ሜትር አድጓል ይላሉ።ግንባታው 2 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው የእግረኛ መንገድንም እንደሚያካትት ተናግረው፣በቀሪዎቹ ሰባቱ ከተሞች ደግሞ መንገዱ 20 ሜትር ስፋት አለው ይላሉ።
ፕሮጀክቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አስካሁን ድረስ በሰቆጣ ከተማ ከገጠመው የወሰን ማስከበር ችግር በስተቀር የቁፋሮ፣ ሙሌት፣ የስትራክቸርና የአፈር ስራዎች ሙሉ በሙሉ እንደተጠናቀቀም ያመለክታሉ፡፡‹‹42 ኪሎሜትር የአስፓልት ስራም ተጠናቋል። በአጠቃላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ አፈፃፀም 77 ነጥብ 72 ከመቶ ደርሷል፡፡››ሲሉም ያብራራሉ።
ተጠሪ መሀንዲሱ እንደሚሉት ፤የመንገድ ፕሮጀክቱ በቀጣይ የሚቀረው 68 ኪሎ ሜትር አስፓልት የማልበስ ስራ ነው፤መንገዱ በአብዛኛው በተራራማ አካባቢዎች ላይ የሚሰራ ከመሆኑ አኳያ በሁለቱም ጎን የውሃ መፋሰሻ ቦዮች ወይም ኮንክሪት ሳይት ዲች ስራዎችም ይሰራሉ።አስካሁንም 50 ከመቶ ያህል ስራው ተጠናቋል።በመሆኑም ዋናው የፕሮጀክቱ ስራ በሰቆጣ ከተማ የአስፓልት ቤዝ ኮርስ ስራ ይሆናል።የፊዚካል አፈፃፀሙም በተመሳሳይ 77 ነጥብ 72 ከመቶ ደርሷል። የዝግጅትና የአቅርቦት ስራዎች ወደ ፕሮጀክቱ አፈፃፀም ውስጥ የሚካተቱ ከሆነ ግን አፈፃፀሙ 83 ከመቶ ሊጠጋ ይችላል።ይሁንና ይህ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ውስጥ ታሳቢ አይደረግም።
በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት የመንገድ ፕሮጀከቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት መሆን የነበረበት በመጪው ሃምሌ ወር እ.ኤ.አ በ2020 ቢሆንም ስራ ተቋራጩ ፕሮጀክቱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ግዜያቶችን በመጠየቁ በአማካሪ ድርጅቱ በኩል ጉዳዩ እየታየ ይገኛል፡፡የሚሉት ተጠሪ መሀንዲሱ፣ በዚህም ምክንያት የመንገድ ፕሮጀክቱ በትክክል መቼ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን አይታወቅም ሲሉ ያመለክታሉ።
ኮንትራክተሩ ያቀረበው ጥያቄ ከተገመገመና ለአሰሪው አካል /የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን/ እንዲቀርብ ከተደረገ በኋላ ፍቃድ አግኝቶ ተገምግሞ ሲያፀድቅ የመንገድ ፕሮጀክቱ መቼ እንደሚጠናቀቅ የሚታወቅ ይሆናል።
ተጠሪ መሃንዲሱ እንደሚገልፁት፤የመንገድ ፕሮጀክቱ እስካሁን በነበሩት ችግሮች ከመጓተቱ ውጪ ችግሮቹ ተቀርፈው በአሁኑ ወቅት በተሻለ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል። የወሰን ማስከበር ችግር በሰቆጣ ከተማ ላይ ያለ ቢሆንም በሌሎች አካባቢዎች ላይ የተቀረፈ በመሆኑ ስራው በተሻለ ፍጥነት እየሄደ ይገኛል።በፕሮጀክቱ ላይ መጪው የክረምት ወቅት መጠነኛ ስጋት ከመፍጠሩ ውጪ የፕሮጀክቱን ከፍጥነትና ጥራት ጋር በማጣጣም ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ከጋሸና ተከትሎ እስከ ሰቆጣ የሚደርስ ከመሆኑ አኳያ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም እጅግ ሰፊ ነው።በዋናነትም መንገዱ ከጋሸና ተነስቶ ሁለቱን የሰሜን ወሎና የዋግህምራ ዞኖችን ያገናኛል።ከዚህ በኋላም መንገዱ የአማራ ክልልን በመሻገር የትግራይ ክልልንም ጭምር ያገናኛል።ወደ ላሊበላ የሚደረገውን የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ጎብኚዎች ፍሰት በከፍተኛ ደረጃም ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012
አስናቀ ፀጋዬ