እ.ኤ.አ በህዳር 3 ቀን 1969 በአፄ ኃይለሥላሴ አማካይነት ተመርቆ የተከፈተው ሒልተን ሆቴል በኢትዮጵያ የተገነባ የመጀመሪያው ባለኮከብ ሆቴል እንደሆነ ይነገርለታል። ይህ ሆቴል 60 ሺህ ካሬ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ባለ 12 ወለልም ነው።
ሒልተን አዲስ አበባ በአሜሪካዊው ቻርለስ ዋርነር እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ዲዛይን የተደረገ እንደሆነም ይገለፃል። ዲዛይኑም የብሉይ ኪነ ሕንፃን ሥነ ውበት የያዘና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያንን መሠረት አድርጎ የተገነባ እንደሆነም ነው የሚገለፀው። ዋናው የሆቴሉ መግቢያም ሆነ መዋኛው በመስቀል ቅርጽ የተሠሩ ናቸው፤ በውጭ ገጽታው ላይ የሚታዩ ትንንሽ የጌጥ መስኮቶች ደግሞ በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚገኙ ማጮለቂያዎችን እንደሚወክሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአፄ ሃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሥራውን የጀመረውን ይህን ሆቴል ለማስተዳደር መንግሥት ከሒልተን ወልድዋይድ (ዓለም አቀፍ) ኩባንያ ጋር የ50 ዓመት ስምምነት እንደነበረው ይነገራል። ይኸው ስምምነት በየአስር ዓመቱም ሲታደስ መቆየቱም ነው የሚገለፀው። 400 የመኝታ ክፍሎች እንዳሉም ይገለፃል።
መሠረቱን አሜሪካ ያደረገው የሒልተን ሆቴሎችና ሪዞርቶች ድርጅት አንድ ክፍለ ዘመን ታሪክ ያለው ሲሆን፣ ሒልተን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ዓለማት የሚያስተዳድራቸው ሆቴሎች ብዛት 585 ያህል እንደሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የ96 ዓመት እድሜ ያስቆጠረው ይህ የሒልተን፤ የሆቴሎችና ሪዞርቶች አገልግሎት በ82 አገራት በሚገኙ ሆቴሎቹ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ወደ አፍሪካ ከገባም ግማሽ ክፍለ ዘመን (50 ዓመት) ማስቆጠሩም ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012
አስቴር ኤልያስ