ከተሞች በኢነርጂ ውስንንት ሲሰቃዩ ይስተዋላል። በየጊዜው መብራት ከመጥፋቱ ጋር ተያይዞም ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ኤሌክትሪክ ከአንድ ማዕከል የሚገኝና አቅርቦቱም ውስን በመሆኑ ሳቢያ እጥረት እየተከሰተ በፈረቃ እስከ ማቅረብ የሚደረስበት ሁኔታ ጥቂት አይደለም። ልማቱ የሚፈልገውን ያህል የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ ቢሞከርም ችግሩን ለሰሞነ ካልሆነ በቀር በዘላቂነት መፍታት አልተቻለም።
በኤሌክትሪክ መቆራረጥና አለመኖር ሳቢያ ብዙ ሥራዎች ሳይሰሩ ይቀራሉ፤ የሚበላሹ ብዙ ነገሮችም አሉ። ከተሞች አስተማማኝ ኢነርጂ እንዲያገኙ ለማስቻል ምን መሠራት አለበት? በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህንፃ ኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ኢንስቲትዩት የከተማ ዲዛይን መምህርና የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጥበቡ አሰፋ ከተሞች የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያመነጩ በማድረግ ራሳቸውን ማስቻል እንደሚቻል ይጠቁማሉ። ኢንቫይሮንመንት፣ ኢነርጂ እና ከተማ ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተም ጥናት ያካሄዱትና በሙያቸውም አርክቴክት የሆኑት ዶክተር ጥበቡ ከተሞች የፀሐይ ሃይልን በመጠቀም ኤሌክትሪክ እንዲያመርቱ ማድረግ ይቻላል ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የኢነርጂ ዋና ምንጭ ፀሐይ ናት። የፀሐይን አቅጣጫ ጠብቆ በተለያየ መንገድ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ብርሃኗንም ሆነ ሙቀቷን ማግኘትና ራስን በኢነርጂ በመቻል ነፃነትን ማወጅ ይቻላል። ለዚህም ህንፃ ከመገንባቱ አስቀድሞ አርክቴክቱ ከሌሎቹ ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት፣መሥራት ይኖርበታል።
ከሚመረተው ኢነርጂ የከተሞች ህንፃዎች ወደ 48 በመቶ የሚጠጋውን ሲጠቀሙ ወደ 25 በመቶውን ደግሞ ኢንዱስትሪዎች ይጠቀሙበታል። 27 በመቶው ለከተማው ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ይውላል። ትልቁን የኢነርጂ የሚወስዱት ህንፃዎች ናቸው ሲሉ ይናገራሉ።
ዶክተር ጥበቡ እንደሚሉት፤ ከ48 በመቶ ውስጥ 40 በመቶውን ህንፃው እንዲሠራ ማድረግ ይቻላል፤ በየቀኑ ለቴሌቪዥን፣ ለመብራት፣ ለማብሰልና ለተለያዩ ፍጆታዎች የምንጠቀመው አጠቃላይ 40 በመቶ ሲሆን፣ ቀሪው 8 በመቶ ግንባታውን ለመሥራት የሚውል ነው ማለት ነው።
ይህን ኢነርጂ በከተማ ውስጥ እንዴት ማመንጨት ይቻላል ለሚለው ሲመልሱ ‹‹ኢነርጂ ምንጭ ይፈልጋል፤ እንደማኛውም ነገር መመረት አለበት። የኢነርጂ ምንጮች ከሚሆኑት መካከል ደግሞ አንዷ ፀሐይ ናት።›› ሲሉ ይጠቁማሉ።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ የፀሐይ አወጣጥ ከአገር አገር ይለያያል። አንዱ ዘንድ እስከ ስድስት ወር ጨለማ የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ ወደ ምድር ወገብ ሲጠጋ ደግሞ ፀሐይን በቀን ለ12 ሰዓት ማግኘት ይቻላል። በምትወጣበት ጊዜ ህንፃውን የማሞቅ ኃይል ስላላት ቤት ይሞቃል። ይህም ኢነርጂ ብርሃን ለማግኘትም፣ ምግብ ለማብሰልም ይረዳል።
ጥሩ ቤቶች የሚባሉት የፀሐይን ኃይል መጠቀም የሚችሉ መሆናቸውን ዶክተር ጥበቡ ተናግረው፣ ያለምንም ቴክኖሎጂ የፀሐይን ኃይል በቀጥታ መስኮትን፣ በርን ወይም ደግሞ መንገዶችን እና አደባባዮችን መልክ በማስያዝና ከፀሐይ አንፃር በመቃኘት በቀን እንዲሞቁ ማድረግ እንደሚቻል ይጠቁማሉ።
የፀሐይን ኃይል እንዴት መጠቀም አለብን የምንል ከሆነ ፀሐይ ሙቀትም ብርሃንም አላት፤ ሙቀቷ ከብርሃኗ፤ እንዲሁም ብርሃኗ ከሙቀቷ አይለይም። ብርሃኑን ብቻ የምንጠቀምበት የራሱ የሆነ ቴክኖሎጂ ሲኖር፣ ብርሃን መቀበል የሚያስችል መሣሪያ ያስፈልጋል። እስካሁን ድረስም ዓለም እየተጠቀመበት ያለው ሲልከን የሚባለውን መሣሪያ ነው። ይህም መሣሪያ የፀሐይዋን ሙቀት ለመለወጥ የሚያስፈልጉት ግብዓቶች ይኖሩታል። ይህም የሚሆነው እንደ ፀሐይዋ አወጣጥና ሙቀት ነው። እንደ የሁኔታው ከፀሐይ በሙቀት የሚገኘውን ዋት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ወደ ኢነርጂ መለወጥ ይቻላል። በጣም የረቀቁ የፀሐይ ሙቀት መቀበያ ቴክኖሎጂዎችም እየተፈበረኩ ናቸው።
አንድ ኪሎዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት እንደ ፀሐይዋ ሁኔታ አስር ካሬ ሜትር ፓኔል ይፈልጋል የሚሉት ዶክተር ጥበቡ፣ እንደ ሰው ፍላጎት ማመንጨት እንደሚቻልም ያብራራሉ። አንድ ቤት የሚፈለገውን ያህል የኢነርጂ ፍጆታ ማለትም 40 በመቶውን ለማሟላት ምን ያህል ያስፈልገኛል የሚለውን ከጣራው ላይ በመስቀል አሊያም በግቢው ውስጥ በማድረግ ማመንጨት ይችላል፤ እያንዳንዱ ቤት የሚፈልገውን ኢንርጂ አስልቶ የሚጠቀምበት የኢነርጂ ነፃነት ማስፈን ነው የመጀመሪያው ነገር ራስን በኢነርጂ መቻል ማለት ነው። ለዚህም ቤቱ በሚገነባበት ወቅት እያንዳንዱ ባለሙያ ከአርክቴክቱ ጋር ተግባብቶ መሥራት ይኖርበታል።
የፀሐይን ሙቀት ወደ ኢነርጂ መቀየር ከሚችሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል አንዱ ቤታችን ጣራ ላይ የምንሰቅለው ዲሽ ነው። እሱ ሞለል ያለና የፀሐይን ሙቀት አንድ ቦታ መስብሰብ የሚችል ነውና ሙቀቱ አንድም የሚሰበሰበው በዲሽ አማካይነት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ገንዳ መሰል የሆነውና ልክ እንደ ‹‹ዲ›› ሁሉ ሞለል ያለ ቅርጽ ያለው ሲሆን፣ የፀሐይን አካሄድ እየተከተለ ሙቀቱ የሚሰበሰብበት ነው። አንዳንዶቹ ቴክኖሎጂዎች ልክ እንደ መስታወት በማፀባረቅ የፀሐይን ሙቀት የሚሰበስቡ እንደ መሆናቸው የፀሐይን ሙቀት ለመሰብሰብ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከቦታ አመራረጥ ጀምሮ ሰውን እንዳይጎዳ ተደርጎ ሊከናወን ይገባል። ጨረሩ ተሰብስቦ በአንድ ቦታ ላይ ስለሚሆን ከፍተኛ ሙቀት ይኖራል። ያንን ሙቀት የተለያዩ ቴክኖሎጂን መሠረት በማድረግ ወደኢነርጂ መቀየር ማለት ነው።
ብርሃኑን በመጠቀም በብሮድባንድ ማለትም ኢነርጂን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ የሚያስተላልፈውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነው ኢነርጂን ማሸጋገር እንደሚቻልም ይገልፃሉ። በዚህ መሠረት ምድር ቤትም ሌላ ቦታ በመውሰድ ብርሃኑን መጠቀም ይቻላል። በዚህ መልኩ መጠቀም አዋጭ ነው ይላሉ።
በሃይድሮፓወር ማለትም በውሃ ግድብ አማካይነት የሚገኘው ኢነርጂ በጣም ውድ በመሆኑ በቀላሉ ሊገኝ በሚችል ዘዴ መጠቀሙ አዋጭ መሆኑን ጠቁመው፣ በተመሳሳይ ብርሃን አቆይቶ አሊያም ልክ እንደ ውሃ ሁሉ አቁሮ መጠቀምም እንደሚቻልም ነው ዶክተር ጥበቡ ያመለክቱት። መሬት ውስጥ ኢነርጂ መኖሩን ጠቅሰው፤ መሬት ውስጥ ያለውን የሞቀ ውሃም እንዲሁ በቴክኖሎጂ አማካይነት ለኢነርጂ ፍጆታ መጠቀም እንደሚቻል ያመለክታሉ።
ኢነርጂ ፕላስ ህንፃዎች የሚባሉ እንዳሉም ተናግረው፣ እነዚህ ህንፃዎች የሚበቃቸውን ያህል የራሳቸውን ኢነርጂ አመንጭተው ለሌላም መትረፍ እንደሚችሉ ነው ያብራሩት። ይህም ማለት ከፀሐይ ያመርታሉ፤ ህንፃቸው ፀሐይን ተቀብሎ በሙሉ መለወጥ የሚችል ነው። ነፋስንም ተቀብሎ መለወጥ የሚችል ነው ሲሉ ይገልፃሉ።
ኢነርጂ ሲሰራ 8 በመቶው ኮንስትራክሽን ለመሥራት ነው ያሉት ዶክተር ጥበቡ፣ በተፈጥሮ ማለትም በፀሐይ የበሰሉ መሣሪያዎችን መጠቀም ሌላው ኢነርጂ መሆኑን ይናገራሉ። እንጨት፣ ድንጋይ፣ ጭቃ፣ ጡብ፣ ሴራሚክና መሰል ነገሮችን ለእዚህ በአብነት በመጥቀስ፣ ከእነዚህ የሚሠሩ ቤቶች በጣም ተመራጭ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በከተማችን ቤቶች በውጭ ምንዛሬ በመጡ እንደ አልሙኒየም በመሳሰሉ ነገሮች ከፍተኛ ኢነርጂ የሚወስዱ መሆናቸውንም ያመለክታሉ። እንደ እሳቸው ገለፃ፤ ይህ አይነቱ አሠራር ስህተት ነው፤ ከፍተኛ ኢነርጂ ይጠይቃል። ውጤታማ ኢነርጂን መጠቀም እንዲቻል ግንባታውን በተፈጥሮ ሀብት መሥራት ይገባል። ስለዚህ 8 በመቶውን በዚህ መልኩ አስበን ብንሠራ በተለይ መኖሪያ ቤቶች የከተማውን 60 በመቶ የሚፈጁ ናቸውና ብዙ ማትረፍ ይቻላል ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ ከባዮማስ ኢነርጂ ማምረት ይቻላል። ይህንንም የምናገኘው በተለያየ መልኩ ሲሆን፣ አንዱ ቀጥታ በመማገድ ነው። እሱ ከፍተኛ ካርበን ያመነጫል። ዓለምን ይበክላል። ባዮማስን በዘመናዊ መልኩ መቀየር ይቻላልና ወደዛ መሄዱ ተመራጭ ነው። ስለዚህ ያንን ለመጠቀም አንድ ዛፍ 20 ቶን ካርበን ይሰበስባል በሚል ስሌት፣ ለእያዳንዱ ቶን ስንት ዛፍ ያስፈልጋል የሚለውን ማስላት ያስፈልጋል። ያንን ካርበን እንዲመጥልን ከፈለግን በዛው ልክ ደግሞ የዛፍ ችግኞችን መትከል ይጠበቅብናል።
ከዛፍም ነዳጅ ማውጣት እንደሚቻል ዶክተር ጥበቡ ይጠቁማሉ። ማንኛውም ዛፍ ሃይድሮጂን አለው። ዓለም አሁን እየተጠቀመ ያለው ሶላር ሃይድሮጂን ሲሆን፣ ይህም የፀሐይ ሙቀቷን አሊያም ብርሃኗን በመውሰድ ሃይድሮጂን የሚገኝባቸውን መሣሪያዎች በመቀየር ሃይድሮጂኑ ነው የሚነደው። በአሁኑ ሰዓት በሃይድሮጂን ኢነርጂን ማጠራቀም ይቻላል።
እንደ ዶክተር ጥበቡ ገለፃ፤ ነፋስ ሌላው የአነርጂ ምንጭ ነው። አንድ ከተማ የራሱን ኢነርጂ ከነፋስ ማግኘት ይችላል። ነፋስን ለመጠቀም ሁለት አይነት ቴክኖሎጂዎች አሉ። አንደኛው በአግድመት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በቁመት የሚያመነጭ ነው። የአግድመቱ እንደ አዳማ እና አሸጎዳ አይነቶቹ ሲሆኑ፣ እነዚህ ሰፊ ቦታ ይፈልጋሉ።
ከዚህ የተሻለ በትንሽ ቦታ ከነፋስ ኢነርጂን ማምረት ይቻላል። ቦታ የሚይወስዱ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድ ይገባል። በግቢያችን አሊያም በጣሪያችን ላይ ከነፍስ ሃይል ኢነርጂ የሚያመነጩ መሣሪያዎችን በመትከል ኢነርጂን ማግኘት ይቻላል። እነዚህ በየህንፃዎቹ መካከልም በመትከል መጠቀም ይቻላል።
ከማንኛውም ወንዝ ከሚታየው ሞገድ ኢነርጂን ማምረት እንደሚቻልም ጠቁመው፣ ወንዙ ተንደርድሮ ሲወርድ ያንን ሃይል መቀየር የሚችል ቴክኖሎጂ በመጠቀም ኢነርጂ ሊመረት እንደሚችል ይገልፃሉ። ከሐይቅ ማዕበልም እንዲሁ ኢነርጂ ማምረት ይቻላል ይላሉ። በተመሳሳይ ከጽዋትም ኢነርጂን ማመንጨት እንደሚቻል ተናግረው፣ ከመብረቅም ሆነ ከአልጌ እንዲሁ ኢነርጂ ማግኘት እንደሚቻል ነው አርክቴክቱ የሚያስረዱት።
በአጠቃላይ የኢነርጂ አጠቃቀማችንን ማስተካከል አለብን የሚሉት ዶክተሩ፣ ይህን በማድረግም ከግድብ የሚመረተውን ለኢንዱስትሪዎች ማድረግና ለቤታችን ደግሞ እዛው በዛው ከተለያዩ ምንጮች ማምረት ይቻላል ሲሉ ነው የገለፁት። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ደንብ ማውጣት አለበትም ብለዋል።
‹‹ከውጭ የምናስገባቸው ቴክኖሎጂዎች በራሳቸው በጣም ጊዜ ያለፈባቸውና ኢነርጂን የሚያባክኑ አይነት ናቸው። ካደጉ አገሮች ስንገዛ ከካርበን ነፃ የሆነን ቴክኖሎጂ እንኳ አይሰጡንም። ስለሆነም ማሰብ ያለበን እኛ ራሳችንን መቻል እንጂ ቴክኖሎጂን በመግዛት አገርን እናስተዳድራለን ማለት ዘበት ነው።›› ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ ዶክተር ጥበቡ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በኢነርጂ ነፃነቷን ማወጅ እንድትችል በዋናነት በዘርፉ ምርምር ማድረግ አለባት። በነፍስ ወከፍ በቤት ደረጃ ያለውን ኢነርጂ አጥንተን መቀየር አለብን በማለት መነሳት ስንችል ነው ነፃነታችንን ማወጅ የምንችለው።
እርሳቸው እንደሚሉት ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሙሉ እና ሌሎችም ኢነርጂን ከታዳሽ ሃይል የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር አለባቸው። በከተሞች በአንዳቸውም መሥሪያ ቤቶች ላይ የተገጠመ ከፀሐይ ሃይል ለማግኘት የተደረገ ሙከራ አይስተዋልም። በሥራ ላይ እያለ መብራት ሲጠፋ የሚሠሩበት ኮምፒውተር ቀጥ ሲል ነው የሚታየው።
‹‹ለእዚህ ሁሉ መንግሥትም ሕግ ማውጣት አለበት፤ ኢነርጂም ሆነ ውሃ አቅርቤ አልችም፤ ላይህ ላይ የሚወድቀውን ኢነርጂ ሰብስብ፤ የሚፈሰውንም ውሃ ያዝ ሊል ይገባል።›› የሚሉት ዶክተሩ፣ ለዚህ ጉልበት እንዲኖር ደግሞ ጠቃሚ የሆኑ ቴክኖሊጂዎችን በማቅረብ ምርምሮች እንዲካሄዱ ማድረግ ይጠበቅበታል ይላሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012
አስቴር ኤልያስ