የሀገራችን ረጅም ዘመን የጦርነት ታሪክ ነው። በነገሥታቱ ዘመን የአካባቢ ገዢዎች ገብሩ ሲባሉ አልገብርም ካሉ ግጭት ይነሳል። በነበረው የግብርና ሥራ እያረሰ እየገበረ ግጭት ሲመጣ ደግሞ ተነሳና ተዋጋ ይባላል፤ ሳይወድ በግድ ይዘምታል ይዋጋል። በሰላም ቀን ግብርናውን እየሠራ በግጭት ቀን ደግሞ ወደ ውትድርናው ይሄዳል። በወቅቱ አርሶአደርም አርብቶአደርም ሁለቱንም የሆኑት ገበሬዎቻችን በክፉ ጊዜ ደግሞ ወታደሮቻችን ነበሩ። ሀገራችን በማንም ፉከራ አትደናበርም ወታደሮቻችን ሁሌም ዝግጁዎች ናቸው።
በነገሥታቱ ዘመን ለዘማቾቹ ደመወዝ የሚባል ነገር አልነበረም፤ ዘማቹ ከሄደበት አካባቢ ስንቅ ካለቀ አምጡ ይላል። አልያም ዘርፎ ይበላል። በግብርናም በውትድርናም የሚያገለግሉ ሰዎች እንጂ ዘላቂ ወታደር አልነበረም። ከላይ እንደጠቀስነው የአካባቢ ገዢዎች ተገዢነታቸውን የሚያረጋግጡት ለበላዮቻቸው በመገበር ነበር። እንደ ዘመናችን የሚሠሩ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የህክምና ቦታዎችና ትምህርት ቤቶች አልነበሩም። ግፋ ቢል ደግሰው ለአካባቢው ሰዎች እና ለባለሟሎቻቸው ያበላሉ ያጠጣሉ። ለዚህም በወቅቱ አባባል “ግብር አበሉ” ተብሎ ይነገርላቸዋል።
ይህ ሁሉ የሚሆነው በገባሪና አስገባሪ ሽኩቻ ነው። የውጭ ጠላት ሲመጣ ግን ሁሉም ልዩነቱን ወደ ጎን ትቶ፣ መሣሪያውን አንግቶ፣ ወራሪውን ለማባረር በአንድነት ከትቶ ይረባረባል። በዚህም ከሀገር በላይ ማንም እንደሌለ ለእኛ የእናት ሀገር ፍቅርና ውሉ ለጠፋብንና በድንግርግር ለምንሄድ ትምህርት የሚሆነን ይመስለኛል።
በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የታሰበው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ነው፤ በ1950ዎቹ መጨረሻ ንጉሡ በወቅቱ ታዋቂ በነበሩ የውጭ ባለሙያዎች ጥናት አስጠንተው ጨርሰው ለግድብ ግንባታ ቢዘጋጁም አልተሳካላቸውም። የዓለም ባንክ ለግንባታው ብድር ለመስጠት አሻፈረኝ አለ፤ ለዚህ ደግሞ የግብፅ ዲፕሎማቶች ጫና ነበረበት። ንጉሡም ፕላኑ ይቀመጥና አንድ ቀን የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረትና ዕውቀት ሲያገኝ ይገነባዋል አሉ ይባላል።
ዘውዳዊው መንግሥት ተገርስሶ ወታደራዊው ደርግ ቢተካ በመሃል ሀገር የነበረው የነኢህአፓ ሽኩቻ በሰሜንና በምዕራብ የነበረው የነፃ አውጪ ግንባሮች ንቅናቄ ፋታ ሊሰጠው አልቻለም። በዚሁ ላይ የሶማሊያ መንግሥት ውጊያም ሌላው ራስ ምታት ነበረ።
በምዕራብና በሰሜን ሲያደረጉ የነበሩ ውጊያዎች ቀጥለው በኢህአዴግ ተጋዳላዮች ደርግ ሥልጣኑን ተቀምቶና ጦሩን በትኖ ተደመሰሰ። ኢህአዴግ ደግሞ ጊዜ ሲያገኝ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድርና ርዳታ ለግድቡ ግንባታ እንደማይሰጡ አስተውሎ ህዝቡን አስተባብሮ የአባይን ግድብ አስጀመረ። ለጅማሬው አድናቆታችንን እየገለጽን እንቀጥል።
ግብፅ አሁንም 1929 እና 1959 ስምምነት እየጠቀሰች አይገነባም እያለች በሰመመን ሆና ትባንናለች። ግብፅ መጀመሪያ የወንዙ ባለቤት እኔ ስለሆንኩ ወንዙ መገደብ ቀርቶ አንዲት ጠብታ አይነካም ስትል ነበረ። መገደብ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ ግድቡ በ20 ዓመታት መሞላት አለበት ማለት ጀመረች። አይገነባም ከሚለው ግትር አቋም በተወሰነ ዓመት ግድቡ ይሞላ ወደ ሚለው አፈገፈገች፤ ሃሳቡን ባንቀበለውም ይሄ በራሱ ለኔ ራሱን የቻለ ድል ነው።
ባለፈው የካቲት ወር አሜሪካና የዓለም ባንክ ኢትዮጵያን ሱዳንና ግብፅ አደራድራለሁ ብላ ስብሰባ ጠራች። አደራዳሪ መስላ የቀረበችው አሜሪካ ጭብሏን አውልቃ ተደራዳሪ ሆና ብቅ አለች። በድርድሩ ሥፍራ የግብፅ ቃል አቀባይ ሆና ተገኘች። ይግረማችሁ ብላም በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካይነት ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር መግለጫ አወጣች። ኢትዮጵያ ረቂቅ ስምምነቱን እንድትፈርም፣ ስምነነቱ ከመፈረሙ በፊት ምንም ዓይነት በግድቡ ሙሌት ሙከራና እንቅስቃሴ እንዳታደርግ፣ ስምምነቱን ከመፈረሟ እና ግድቡን መሙላቷን ከመጀመሯ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃዎች መሠረት ሁሉንም አስፈላጊ የደህንነት መስፈርቶች የመተግበር አስፋላጊነትና ዕውቅና እንድትሰጥ የሚል እንደነበር ሰነዶች ያስረዳሉ።
ወደ ጣሊያንም ሄዳ ሳሊኒ የሚያካሂደውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲያቆም ግብፅ ሞክራ ነበር፤ ለግድቡ የሚወጣውን ወጪ እንክፍላችሁና አቁሙ ስትል ለምና እንደነበርም ይነገራል። የጣሊያን መንግሥት ግን ጆሮ ደባ ልበሽ አላት። የአረብ ሊግንም ሰብስባ ግድቡን እንዲቃወሙ አደረገች፤ በቅርቡም የግብፅ ባለሥልጣናት ግድቡን አስመልክቶ ቻይናን አነጋግረዋል።
ግብፅ በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 11ኛው ሰዓት ላይ አጀንዳው በተባበሩት መንግሥታት ድምፅን በድምፅ መሻር ላለባቸው አምስቱ ሀገሮች አቀረበች፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም የግድቡን አስፈላጊነት እና ለኢትዮጵያውያን የህልውናና የብልጽግና ጉዳይ መሆኑን የሚገልጽ ምላሽ ሰጥቷል። ይህ ሁሉ ሙከራ ግድቡ ፍሬውን እንዳያፈራ የታለመ ነበር። በሀገራችን የምትፈለፍላቸው ተቃዋሚ ነኝ ባይ ባንዶችን ጨምሮ ይህ ሁሉ የዲፕሎማሲ ጥረት ግን ለግብፅ “ዘጠኝ ገዝቶ ዘጠኝ መሸጥ ትርፉ ዘጥዘጥ” እንዲሉ ሆነባት። ያራገፈችው ገንዘብ ግድቡን ከመገደብ ሊገታው አልቻለም። ግድቡን ሊገታው ቢችል ኖሮ የነፃ አውጪ ግንባሮች ሽኩቻ ሊያቆመው በቻለ ነበር፤ ግን አልሆነም።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን እንደ አክሱም ሀውልት የምናደንቀውና መኩሪያችን የሚሆን፣ እንደ ጎንደር አብያተ መንግሥት የምንጎበኘው፣ እንደ ሐረር ጀጎል ቅርሳችንና መኖሪያችን የሚሆን ነው ማለት እንችላለን። ከግድቡ በስኬት መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸው ይቀየራል። በቅጠል እና በኩበት ጭስ ዓይናቸው የሚጨነባበስ ወገኖቻችን እፎይ ይላሉ። ግድቡ ከሱዳን ድንበር እስከ 50 ኪሎ ሜትር የሚርቅ በመሆኑ ሱዳን እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ብዙ ፋብሪካዎች ሊመሠረቱ የሚችሉበት ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል፤ ግድቡ ለእኛ ራትና መብራት በመሆን የሚያገለግል የህልውናና የብልጽግና ምንጭ ነው። በእንቦጭ ወረራ እየታመመና እየታከመ ላለው ጣና ሀይቅ አቻ ሀይቅ ፈጠርንለት ማለት ነው። “አባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” ያልነውን አባይ ማደሪያ አለው ፋና ይዞ ይዞራል በሚልም እንቀይረዋለን።
ሀገራችን ያለችው በክረምት ውሃውን እንሞላለን ነው። ገብጋባ እና እኛ ብቻ ይድላን የምንል ብንሆን ኖሮ ዓመቱን ሙሉ ግድቡን መሙላት እንችል ነበር። ክረምት እንዲሞላ የተፈለገው ወንዞች ከወሰናቸው አልፈው ስለሚፈሱ እና በታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ጉዳት ስለሚያደርሱ ነው።
በጣና ሐይቅ ላይ የተስፋፋው እንቦጭ ለማጥፋት ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ግብፅ ምንም ድምፅ አልነበራትም። የኢትዮጵያ መንግሥት እንቦጭ እየተስፋፋ ከሄደ ጣና ሊጠፋ ይችላል። የዚህ ጉዳት ደግሞ ዞሮ ዞሮ ወደ ግብፅም ጓሮ ይደርሳል። ጣና ጠፍ ሆነ ማለት የሀገራችን ህይወት ብቻ ሳይሆን የእነሱም ህይወት ተናጋ ማለት ነው።
ለዚህ ዕውን መሆን ግን ዜጎች ሁሉ ከመንግሥት ጎን ሊሆኑ ይገባል፤ ባለንበት የኮረናና ወረራ ምክንያት አደባባይ ወጥቶ ሃሳብን መግለጽ ባይቻልም በአውሮፓና በአሜሪካ ያሉ ምሁራን ዜጎች ለመንግሥት ያላቸውን አጋርነት የአሜሪካንን አድሏዊነት በመንቀፍ ጭምር ሊያሳዩ ይገባል። ለማጠቃለል ያህል የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውናና የብልጽግናችን መሠረት ነው። የአባይ ግድብ መገንባት በባንዳነት የሚንቀሳቀሱ ጥቃቅንና አነስተኛ ፓርቲዎች የገቢ ምንጭ የሚያደርቅ ለዜጎች ለገቢ ምንጭ ህልውናና ብልጽግና መሠረት የሚሆን ነው እላለሁ። ሰላም ሁኑልኝ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 1,2012
ይቤ ከደጃች.ውቤ