አዲስ አበባ፡- የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ከ100 ቀናት ዕቅዱ ውስጥ ወጣቶችን የተመለከቱ እቅዶቹን አለመተግበሩ ተገለጸ፡፡
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ረዳት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ማሞ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ በ100 ቀናት እቅዱ ካካተታቸው መካከል ወጣቶችን የተመለከቱ ዕቅዶችን ተግባራዊ አላደረገም። ለዚህም ዋናው ምክንያት በአዲስ መልክ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተቀላቀለውን የወጣቶችን ጉዳይ የማቀናጀት ሥራ እስካሁን ባለመጠናቀቁ ነው፡፡ በመሆኑም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ100 ቀናት ዕቅድ ውስጥ በአብዛኛው የተተገበረው ንቅናቄ እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሥራ ፈጠራ ተቋማት ለወጣቶች ትኩረት እንዲሰጡ ግንዛቤ መስጠት፣ የወጣቶች ፖሊሲ ለማሻሻል ምክረ ሀሳብ ማቅረብ፣ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ በሴክተር መሥሪያ ቤቶች በእቅድ ውስጥ መካተቱን ማረጋገጥ እና የወጣቶች የውሳኔ ሰጪነት ድርሻን በተመለከተ መረጃ ማሰባሰብ ወጣቶችን የተመለከቱና ያልተከናወኑ እቅዶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጀግኒት ንቅናቄ ለማካሄድ፣ የከፍተኛ ሴት አመራሮች ፎረም መመስረት፣ የሴቶች የልማት ቡድንን ሥራ የሚደግፍ ኮሚቴ የማቋቋም፣ ሥራ አጥ ወጣት ሴቶችን በመለየት ማደራጀትና ማሰልጠን፣ የዕደ ጥበብ ባለሙያ ሴቶችን ገበያ ትስስር መፍጠር እና ለሴቶች ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ከዕቅዱ ውስጥ ያልተተገበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሴቶች የሰላም ኮንፈረንስ ንቅናቄ፣ የሴቶችን ጥምረት መፍጠር እና በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ የንቅናቄ መድረኮች ማካሄድ በእቅድ ተይዞ እንደነበር አቶ አለማየሁ ጠቅሰው፣ በዚሁ መሰረት ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡና 800 ሴቶች የተሳተፉበት ‹‹እኛ ሴቶች ዘረኝነትን በመጠየፍ ሰላማችንን እንጠብቅ›› በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል። የጎሳና የሃይማኖት መሪዎች፣ አባገዳዎች፣ የሴቶች እና የሌሎች አደረጃጀት ተወካዮች በአጠቃላይ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች የነበሩት የንቅናቄ መድረክ መካሄዱን አስታውቀዋል፡፡
ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የተዘጋጀውን የአምስት ዓመት ረቂቅ ፍኖተ ካርታ በማፅደቅ ወደ ሥራ እንዲገባ የማጠናቀቂያ ሥራ መሰራቱንም አቶ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የሴቶችና ህፃናት የፍትህ ፎረም ለማቋቋም ባቀደው መሰረት በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የሚመራ ሌሎች የፍትህ አካላትን በአባልነት የያዘ የሴቶችና ህፃናት የፍትህ ፎረም እንዲቋቋም መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ በሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዙሪያ ግንዛቤዎችን ለመስጠት የሚዲያ ፎረም እንዲቋቋም መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 12/2011
ሰላማዊት ንጉሴ