እንኳን ለ79ኛ ዓመት የልደት በዓልህ አደረሰህ። በመልካም ልደት የጀመርኩበት ምክንያት የብዙ ጋዜጠኞችና ደራሲያን ባለውለታና ፈር ቀዳጅ በመሆንህ ጭምር ነው። በአንተ ምክንያት ብዙዎች የመረጃ ጥማታቸውን አርክተዋል። አያሌ ሰዎች የማንበብ ባህላቸውን አዳብረዋል። ተመራማሪዎችና ፀሐፍት እጃቸውን አፍታተዋል።
ለዚህ ውለታህ ደግሜ ደጋግሜ እንኳን አደረሰህ እላለሁ። ከውልደትህ ጀምሮ አሁን ላይ እስከደረስክበት ጊዜ ያጋጠመህን የህይወት ውጣ ውረድ ሳታወጋኝ ግን በቀላሉ አለቅህም። ለዚህም ነው አንተን የዛሬ ‹‹ የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳዬ ለማድረግ መፍቀዴ፡፡
ውልደት
ጊዜው 1933 ዓ.ም ግንቦት 30 ነው። ፋሺስት ጣሊያን ከወረራት የጀግኖች ምድር ዳግም የሀፍረት ካባውን ተከናንቦ የተባረረበት። ‹‹ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ ዘመን ተጀመረ›› የሚለው የንጉሱ ንግግር ለአንተ ውልደት መሰረት ሆኗል። እናም 42 ሴንቲሜትር በሆነው አርበ ጠባብ ቁመትህ እና 31 ሴንቲሜትር ስፋት ነበር የተወለድከው ። አምዶችህ በሶስት የተከፈሉ ፤ ስምህ የግዕዙን ሥርዓት በጠበቀ መልኩ የተጻፈና በስርዓተ ነጥብ የታጀበ መሆኑን የነበረህ ገጽታ ይመሰክራል።
በተፈጠርክ ማግስት ጉልበትህ እየጠነከረ ሲመጣ ‹‹አዲስ ዘመን ›› ለሚለው መጠሪያ ስምህ ድርብ ጽሑፍ ትጠቀም ጀመር። ድርብ ጽሁፉን ከአምዶችህ መሃል እንደምታደርጋቸውም አይቻለሁ። በልጅነትህ ደግሞ አንዳንድ ነገሮች አልነበሩህም። ለአብነት ርዕሰ አንቀጽና የዋና አዘጋጅ ስም አይጻፍም ነበር። መቼም በበላይነት እየቆነጠጠ ያስተዳድርህ የነበረውን የጋዜጣና ማስታወቂያ ጽህፈት ቤት አትረሳውም። ለነገሩ ከአስተዳደሪህ ጋር ‹‹እውነት፣ አገልግሎትና ረዳትነት›› የሚሉ ዓላማዎች ስለነበሩህ ብዙም አትጋጩም ነበር።
የተፈጠርክ ሰሞን ወዳጆችህ ለማንበብ የሚገዙህ በሦስት ‹‹ሊሬ›› ወይም በሶስት የጣሊያን ሳንቲም ነበር። ለጊዜው በራስህ ጋዜጣ ባወጅከው መሰረት አንድ ሊሬ አንድ ሳንቲም ነበር። በዚያ ዋጋ ገዝተው ለሚያነቡህ በቂ መረጃና ትምህርት ትሰጥ ነበር። ይህንን መረጃ ያገኘሁት ከማን እንደሆነ ታውቃለህ? ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ አዳሙ ስለአንተ በ2006 ዓ.ም ከሰራው ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ ነው። ከዚህ ጥናት ብዙ ነገሮችህን ተረድቻለሁ። ከዚህ የሚቀጥለው የህይወት ታሪክህ አብዛኛው ክፍል ከዚህ ጥናት ላይ የተወሰደ ነው።
ለአንተ እድገትና እስካሁን መኖር ብዙዎች ለፍተዋል። ዋጋ ከፍለዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ስትወለድ አንተን የተንከባከቡህና መረጃ ሰጪነትህ እንዲቀጥል ያደረጉት ዋና አዘጋጅ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ናቸው። እርሳቸው የቤተክህነት ሰው ሲሆኑ፤ ለረጅም ዓመታት አንተን ጠብቀዋል። ከተወለድህ ጀምሮ አምስት ዓመት እስኪሞላህ አርበ ጠባብነትህን ይዘህ የቀጠልህ ሲሆን፤ አምስተኛውን የነጻነት በዓል ምክንያት በማድረግ ደግሞ ራስህን አስተካክለሃል። ያው መቼስ አደግህ አይደል የሚባለው። አርበ ሰፊ ሆነህ የገጽ መጠንህን ወደ ስምንት ከፍ አለ።
እንደ ስምህ አዲስ ሊያደርጉህ ሲፈልጉ ደግሞ ዳግም ወደነበረህ ማንነት በ1940 ዓ.ም መለሱህ። በዚህም አርበ ጠባብ ሆነህ ወደ ፈላጊዎችህ መድረሱን ቀጠልክ። ይህም እንደ አዲስ ተፈላጊነት ጨምሮት እንደነበር ይነገራል። የመሸጫ ዋጋህ ደግሞ ከነበረው ከፍ ብሎ በዓመት 2 ብር ከ60 ሳንቲም ሆነ። ለውጭ አገር ሰዎች ደግሞ በእጥፍ ነበር የምትሸጠው።
እድገት ወደ እለታዊ ጋዜጣ
በ1933 ዓ.ም እስከ 18 ዓመት ድረስ በሳምንት አንድ ቀን ጠብቀህ ነበር ለወዳጆችህ የምትደርሰው። ከዚያ ከ18 ዓመት በላይ ከሆንክ ተፈላጊነትህና ራስህ በራስህን መምራት ስለምትችል በየዕለቱ መውጣቱንና ከወዳጆችህ ጋር መገናኘቱን አጠነከርከው። ስለዚህም ሳምንት ጠብቀህ ሳይሆን በየቀኑ በመውጣት ነጻነትህን አወጅህ። ዕለታዊ የመሆንህ ጉዳይ ሲነሳ አንዱ ወላጅህ የሆነው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹ከ18 ዓመት የሳምንት አገልግሎት በኋላ ወደ ዕለታዊ ጋዜጣነት የተለወጥከው ዕድለኛው አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንኳን ይህን ለመሰለ መሻሻል አበቃህ በማለት ደስታዬን ከደስታህ ጋር አስተባብራለሁ›› ነበር ያለህ ። አሁንም ግን ወላጆችህ አልፈቀዱምና በሳምንት አንድ ቀን ገደብ ተጣለብህ። ሰኞ ዕለት መታተም ክልክል ነው የሚል። ጊዜ ጠብቆ ደግሞ በ1993 ዓ.ም ሰኞ ዕለትህ ሆኖ ተፈቀደ። ከዚህ በኋላማ ማን ይቻልህ። ሳምንቱን ሙሉ ለወዳጆችህ መረጃን ታቀብል ቀጠልክ።
ወርቃማ ጊዜያት
ለአንተ ከብዙ አዳዲስ ዘመኖችህም በላይ ወርቃማ ጊዜያት ነበረህ። ይህ ወቅት ዋና አዘጋጅ ነጋሽ ገብረማርያም በነበሩበት ወቅት ነው። ይህ ዘመን ጋዜጠኝነት መልክ የያዘበት ነው፤ እነጋዜጠኛና ደራሲ አሀዱ ሳብሬ፣ ብርሃኑ ዘሪሁንን የመሳሰሉ ሳተና ጋዜጠኖችም የፈሩበትና ላንተ ውጤታማነት የተጉበት ጊዜ ነበር። ተነባቢነትህ በእጅጉ ጨምሯል። እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ ተፈላጊና ተወዳጅነትህ ወደር አልነበረውም ።
የዜና፣ የአስተያየት፣ የርዕሰ አንቀጽና ሌሎች ሐተታዎች በቋሚነት አምድ እንዲኖራቸው የተደረ ገበትና የተማሩ ጋዜጠኞች የተሳተፉት በዚህ ወቅት ነበር። እንዳውም በዋና አዘጋጁ አማካኝነት ርዕሰ አንቀጽ የተጻፈ ሲሆን ‹‹ውበት ብቻውን አይበቃም›› ይል እንደነበረ ጋዜጠኛና ደራሲ አበረ ያጠናው ጥናት ይናገራል፡፡
ሌላው ደግሞ ይህ ጊዜህ ወርቅ እንደነበር የሚነግረኝ ወኔህን ሰብስበህ በይፋ መተቸትና ጠንካራ ሂሶችን በባለስልጣናት ላይ ማድረግ መቻልህ ነበር። ለዚህ መሰረት ደግሞ ዋና አዘጋጅህ አንጋፋው ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን እንደነበርም አንብቢያለሁ። በዚህ ቢያንስ ለሦስት ዓመታት ነጻነትህ ተጠብቆልህ ቆይተሃል። የህዝብ አገልጋይነትም በእጅጉ ታይቷል። ባለቤትነትህ ‹‹የህዝብ›› ነበርና እውነትም ህዝቡን አድምጠህ ነበር።
ፈተናህ
ከውልደተህ ጀምሮ እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ የነበረው ጊዜ በመጠኑ የተደላደለ ቢመስልም በእጅጉ አድካሚ እንደነበርም አትዘነጋውም። ፈጣሪዎችህ የመጻፍ ፍቅር ያላቸው ቢሆኑም ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር ብዙም አልተዋወቁም ነበር። በዚህም ሙያውን አውቆ ለመጣው ዋና አዘጋጅ እጅግ ከባድ መከራን አስተናግዷል። በተለይም የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ከጋዜጠኝነት ጋር የተዛመደ አለመሆኑ ካንተ ጋር የሚጋጩ ብዙዎች ነበሩ። ከሁሉም በላይ ‹‹የጋዜጣና ማስታወቂያ ጽህፈት ቤት›› በኋላም ‹‹የማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር›› ይመሩህ ነበርና በሚያደርጉት እንቅስቃሴና ግራ በሚያጋባ ጽሑፍ ያወዛግቡ ሀል። በተጻፈ ብቻ ሳይሆን በቃል ሕጋቸው ጭምር የፈለጉት በአንተ ላይ እንዲሆን ያስገድዳሉ። ይህ ደግሞ ለጋዜጣው አዘጋጆች ደስ የማይል ጊዜ እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡
የገጽ ቅንብር፤ የፊደል ለቀማና የፊደል መጠንህ በሚፈለገው መልኩ አለመሆኑም ለአንተ ተመራጭነት ፈተና ደቅኖ እንደነበር አትረሳውም። ከዚያ አልፈህ ማተሚያ ቤት ስትገባም የቱ ሥራ የትኛው ገጽ ላይ እንደሚወጣ ግልፅ ባለመሆኑ፣ ርዝማኔና እጥረትህን ያለትውውቅ በመሆኑ ለገጽህ የታሰበው ጽሑፍ ግራ ያጋባህ እንደነበርም አይረሳህም ። በማተሚያ ቤት የነበረህ ፈተና የፊደላት በአግባቡ አለመግባትም ጭምር
ነበር። ይህ ደግሞ የአንተን ህልውና ከመፈታተኑም በላይ ጋዜጠኞች ዋጋ እንዲከፍሉም አድርጓቸው እንደነበር ይረሳሃል ብዬ አላስብም።
ሌላው ፈተናህ የየስርዓቱ የፖለቲካው ጣጣ ነው፤ የአንተ ፍላጎት እንዳይሟላ አድርጎታል። ምክንያቱም ለአንተ ህልውና የሚሰሩት ጋዜጠኞች ከደመወዝ ቅጣት እስከ ህይወት ማጣት ደርሶባቸዋል። ለአብነት እንደ እነ የተሻወርቅ፣ በዓሉ ግርማና ወርቁ ተገኝ የመሳሰሉት እንደወጡ የቀሩት ለአንተ ህልውና እንጂ የማንንም ስልጣን ፈልገው እንዳልነበር አበረ አዳሙ ባጠናው ጥናት ተመላክቷል።
የፖለቲካ ኃይሎች ፍትጊያ እየናረ ሲሄድ የአሸናፊውን አካል ፕሮፓጋንዳ ማውራት ግዴታህ ሆነና ሁሉም ገሸሽ ያደርግህ ጀመር። ‹‹ቀይ ሽብር ይፋፋም! ቀኝ መንገደኞች ይመንጠሩ! ገንጣይ አስገንጣዮች ከምድረገጽ ይጥፉ! ለአረንጓዴው የባህልና የምርት ዕድገት ዘመቻ ወደፊት! እያልክም የመንግሥት አፋሽ አጎንባሽነትህን ተያያዝከው። ይህ ደግሞ ዛሬም ድረስ ተአማኒነትህን ጥርጣሬ ውስጥ ከተተው። ምን ጥሩ መረጃና አስተማሪ ጉዳይ ይዘህ ብትወጣ ማንም ሊያይህ አልወደደም ከመጤፍ ሊቆጥርህ አልቻለም።
ዘመነ-ደርግ
በንጉሱ ጊዜ የተጓዝክበትን ጎዳና በተለያየ መልኩ ስላነሳሁት ዋና ትኩረቴን በቀጣዮቹ ላይ አደርጋለሁ። የመጀመሪያው አንተም እንደምታውቀው ደርግ ነው። ለመሆኑ ይህ ጊዜ እንዴት ነበር? አሁንም የአበረ አዳሙ ጥናት መሰረቴን አድርጌ እነግርሃለሁ። መስከረም ሁለት 1967 ማለት አይደል። ለተወሰኑ ወራት ነጻነትህ ታውጆልህ ነበር። በዚህም ወላጆችህ የፈለከውን ያደርጋሉ። የተመሰረትክበትን አላማም ያስፈጽማሉ። ለዘመናት ታፍኖ የቆየውን ማንነትህን በፋና ወጊ ብዕራቸው እየከተቡ ህዝብ በደንብ እንዲያደምጥህና እንዲወድህ አደረጉ።
ለስልጣን ይፋለሙ የነበሩ ልዩ ልዩ ኃይሎች በአንተ ገፅ ላይ ይሟገቱ ነበር፡፡በዚህ ሰፊ የውይይት መድረክ እንደነበርክም አትረሳውም። በጊዜው ተከፍተው የነበሩ የውይይት መድረኮች የተለያዩ አመለካከቶች የሚንጸባረቁባቸው ስለሆኑ ተስፋህን ብሩህ ያደረጉም ናቸው። ጋዜጠኞችህ ግልጽ በመሆን መንግሥትንም መተቸት ስለቻሉ በአንተ የሚማር በዝቶ እንደነበርም አንብቤያለሁ። ይህ እድል ለአንተ ብቻ አልነበረም ፡፡አንተ በምታቀርበው መረጃ ላይ ተመስርቶ ህዝቡም የወደፊቱን እንዲያስተካክል ረድቶታል። ምክንያቱም በወቅቱ በብዛት የሚነሳው ብሔራዊ ጉዳይ ነበር። እንደ ዴሞክራሲ፣ የመሬት ይዞታ፣ የመንግሥት ሥርዓት …።
ይህንን በማድረግህ የተፈላጊነትና የመሸጫ ዋጋህ ከፍ ብሎ እንደነበርም ታስታውሳለህ። በስምንት ሳንቲም ለአዟዋሪዎች ትሸጥ እንዳልነበር ሦስትና አራት ብር ተቸብችበሀል። ህዝቡም አንተን ለማግኘት ይጋፋ ነበር። አንተም ብትሆን ህዝቡ ማስተዋል እንዳለበት፣ ወደ ብጥብጥና ግርግር እንዳይገባ ትመክራለህ። ስለዚህም ለሁለታችሁም ጥሩ ጊዜ ነበር። ግን ሌሎች ሊተኩ ሲሉ አሁንም አደጋ ውስጥ መግባትህ አልቀረም። ወላጆችህም ብዙ ገደቦች ተጣሉባቸው። ስለዚህም የፈለከው የደስታ ጊዜ በማክተሙ እጅጉን አዝነህ እንደነበርም አይረሳም።
ዘመነ ኢህአዴግ
ዘመኑ 1983 ዓ.ም ነው። በዚህ ወቅት አንድ እድል አግኝተሃል። እርሱም የቅድሚያ ምርመራ ወይም ሳንሱር መታገዱ ነበር። ሆኖም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ስለነበር ያልተፈቱ ብዙ ነገሮች ቀጥለው ነበር። ጋዜጠኞችህ በፍርሃትና በፖለቲካ ቀጥታ ደጋፊነት እራሳቸውን ሳንሱር ማድረጉን ተያያዙት። መንግሥት በሚፈልገው መልኩ ይጽፉም ጀመር። እንዳውም ‹‹አቅጣጫ ›› በሚባለው አባዜ ከመንግሥት አቋም ውጪ የህዝብ ወገንተኝነታቸው ጥያቄ ውስጥ ገባ።
ወቅቱ በተለይ የግል ጋዜጦች እንዲበራከቱ የፈቀደበት በመሆኑ አንተን ባላንጣ የሚያደርጉ በርካቶች ነበሩ። ይህ ደግሞ የህዝብ አመኔታህን እስከመነጠቅ አድርሶሃል። በዚያ ላይ መረጃ የሚሰጥህ አካል ብዙም አልነበረም። ስለዚህም ሥራህ ሌሎችን ተከታይ ማድረግ ሳይሆን የእነርሱን ማረጋገጥ ብቻ ሆኖ ቆይቷል። እንዳውም የመንግሥት መመሪያዎችና ፖሊሲዎች የእግዚአብሔር ትዕዛዛት እስኪመስሉ ድረስ ትተገብራቸው እንደነበርም ማስረጃው ራስህ ነህ። ‹‹መንግሥት የማይሰራ ተቋም ይልሃል፤ ህዝብም የመንግሥት አቀንቃኝ ነው ››ሲል ይፈርጅሃል። ስለዚህም ይህ ጊዜ ለአንተ ከሁለት ያጣ እንደነበር ብዙ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።
በእነዚህ ጊዜያት የተሻለ ሥራ ሰርተሃል የተባለበት ጊዜ ምርጫ 97 ነበር። በተቻለ መጠን በሚዛናዊነት እንደቆየህ ይነገራል። የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሀሳብ በማምጣት እርስ በርሳቸው የሚሟገቱበት ነፃ ሜዳ በመሆን ምስጋና ይቸርህ ነበር። ሆኖም ሳይውል ሳያድር በመንግሥት እግር በመረገጥ ብዙ እድሎችህን በራስህ ላይ ዘግተሃል። ይሄ ግን እንደምን ይቀጥላል?
ስለዚህ ከ2000 እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ በአዲስ መልክ ለማምጣት በማሰብ ጥናት ተደረገ። የአንባብያን አስተያየትም ተሰበሰበ። ግን በዚህም ላይ የታየው ለውጥ እምብዛም አልነበረም። ለአብነት የስርጭት ጉዳይ ተነስቶ ነበር። ሲለወጥና ብዙዎች በእጃቸው ሲገባ አላየንም። የቅጅ ብዛታቸው እንደውም ወደታች ወርዶ እንደነበር ጥናቱ ይናገራል። የህዝብ ወገንተኝነት በመቅረቱ ሳቢያ ገጽህን ባለቀለም ብቻ አድርገህ እድሜህ ሳያንጸባርቅና ሌሎችን ሳይስብም በከንቱ ቀጨኸው።
የምትመራው በ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኛ›› በሚለው ርእዮት ዓለም ስለነበር ልማቱ ህዝብ ሳይሆን ወቅታዊ ፖለቲካ ብቻ ሆኖ ቀረ። የምርመራ ዘገባዎች ዳዴ ብለው ቀሩ። ወቅቱ መልካም እድሎችን ሰጥቶህ ነበር። ሃሳብ በነፃነት እንዲንሸራሸር የውጭ ጸሐፊዎችን ተሳትፎ ነበር። በዚህም በአደረጃጀት ጭምር የምትሻሻልበት መንገድ ተመቻችቶልሃል። ቀጣዩን ጉዞህን ብሩህ እንድታደርግ እድል ፈጥሮልሃል። ግን እንዳልተጠቀምክበት ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። አንተም ታስታውሳለህና አልድገመው።
ዛሬስ
ለመነሳት እያኮበኮብክ ትመስላለህ። ብዙዎች አንተን አብነት አድርገው ውሳኔ ሲሰጡ ይስተዋላል። አንተን እያነሱ ዜናውን፣ ሐተታውን አምዱን ለህዝብ ማስተማሪያ እያደረጉት ይገኛል። መንግሥትም ቢሆን ስህተቱን የሚያምንባቸው መንገዶችን እየፈጠርክ ነው። ለዚህ ያበቃህ ደግሞ ነጻ ሆኖ መጻፍ መጀመሩ ይመስለኛል። የመረጃ ምንጮችም ሳይፈሩ የሚሰጡበት እድል በመመቻቸቱ ተስፋህ ብሩህ እየሆነ ነው። በተለይ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረልህ ዘመኑ ይመስላል። ቴክኖሎጂውን ተገን በማድረግ የህትመት ጋዜጣውን ጥሬ ጽሁፉን በማህበራዊ ድህረ ገፅ ማድረስ መቻልህ ጥሩ የተመልካች ቀልብ መሳቢያ ሳያደርግህ አልቀረም። ይህ ሂደት ለሁሉም አንባቢ እንዲደርስ የእድል በር ከፍቷል። ሆኖም አሁንም የሚቀሩህ ብዙ ነገሮች አሉ። ድክመቶች ይታዩብሃል። መፈራራትና አቋም መያዝህ በራስህ መሆን አለበት። አሁንም ይቀርሀል ነጻ መውጣት።
ይዘት በዘመናት
በጅማሮህ አብዛኛውን ጊዜ ወገንተኝነት ይታይብህ ነበር። እንደውም ብዙ ሽፋኖችህ ስለ ንጉሰ ነገስቱ ክብር ነበር የምትዘግበው። በአገር ፍቅር ወዳድነትህም ተወዳዳሪ አይገኝልህም። ከዚያ በተለይ ከግሪክ ፈላስፎችን ሥራ በስፋት እያተምክ ህዝቡ እንዲያውቅ፣ እንዲመራመር ወደማድረጉ ገባህ። ግን ይህንን ሁሉ ስታደርግ የዜና፣ የርዕሰ አንቀጽና የአስተያየት ገጽ አልነበረህም። ስለዚህም ወሬዎችህ ሁሉ ከቤተመንግሥቱ አይርቁም። እንደውም ፊት ገጽ ላይ የሚወጣው ስድስቱም አምዶች የቤተመንግሥቱ ተራ ወሬ ነበሩ። አለፍ አለ ከተባለ የንጉሱ ህይወት ሥራ ናቸው። እንደውም አበረ አዳሙ በጥናቱ እንዳስቀመጠው ‹‹ዊልያም ኤች ሲድ›› የተባለ የጋርድያን ጋዜጠኛ ‹የጃንሆይ ስም ጠቅሶ የሚጻፍ ማናቸውም ጽሑፎች ተውላጠስሙ ሳይቀር ካፒታል ፊደል መሆን አለበት። በማንኛውም ጽሑፍ የጃንሆይ ስም መጥቀስ ካለበት ከእርሳቸው በፊት የሌላ ሰው ስም እንዳይወጣ፤ በሕይወት የሚገኝ ሰው ፎቶግራፍ ከሞተ ሰው ፎቶ ግራፍ ጋር መታተምና መውጣት እንደማይኖርበት፤ በጅምላ ብዙ ሰዎች የያዘ ፎቶግራፍ በጋዜጣው ሲወጣ በመካከላቸው በሞት የተለየ ሰው ካለ ፎቶግራፉ መታተም እንደሌለበት ተደንግጓል›› ይላል። ስለዚህም አንተም በዚህ ዘመን ይዘቶችህ ይቃኙ የነበሩት በዚህ መንገድ እንደነበር ማረጋገጥ ይቻላል።
ደርግ ሲገባ ብዙ ነገሮችህ ተቀይረዋል። በተለይም የአምዶችህ ሁኔታ ቢያንስ ለሦስት ዓመታት ነጻነት የታከለባቸው ስለነበሩ ይዘቶችህ ይማርካሉ። ህዝቡም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በተለያየ መንገድ ያካፍሉ ነበር። እንደውም ከንቲባው ጭምር ይጽፉብህ እንደነበር አንተን ገለጥ አድርጎ ያነበበ መረዳት ይችላል። ፍቅር፤ የአገር ጉዳይ፣ ማህበራዊ መስተጋብሮች ልዩ ዋጋ የሚሰጥበትና በይዘቶችህ እነዚህን ነገሮች ሳታነሳ የማታልፍበት ጊዜ ነበር። ትምህርትም ሆነ ጤናም ልዩ ትኩረት በመስጠት በይዘቶችህ አካተህ ታሳያለህ። ስለዚህ ይህ ዘመን የይዘት ለውጥ የመጣበት እንደነበር ያመላክታል። ወደ ዘመነ ኢህአዴግ ስንገባ ደግሞ ከቃላት ምርጫ ጀምሮ ብዙ የማያስደስቱ አምዶች የሚወጡበት ነበር። ይህ ደግሞ ለማንበብ እንኳን አይጋብዝም። ዋናው ጉዳይ የመንግሥት አቋም በመሆኑ ማንም አይወደውም።
ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮችም ይዘቶችህ ነበሩ። ግን ብዙውን ሽፋን የምትሰጠው ወቅታዊ ለሆነው የመንግሥት አቋም ስለነበርና በባለስ ልጣናት የተጻፉ አቋም መሳይ ዘገባዎች ስለሚስተናገዱ ለአንባቢያን ሳቢ እንዳልነበረ አትረሳውም። የካድሬዎች ስብሰባ የአንተ መነሻ ዘገባም መሆኑ ይዘቶችህ ተወዳጅ እንዳይሆኑ ካደረጉት መካከል አንዱ ነበር። ሚዛናዊ ዜናዎችን ለመስራት ብዙ የማትደፍርበት በመሆኑም ዜናዎቹ በአንባቢዎች ተመራጭ አልነበሩም።
ብልጽግና ወይም ለውጡ ግን አንተን የለወጠህ ይመስላል። የፈለከውን መከተብ ጀምረሃል፤ ይዘቶችህ የሀሳብ ነጻነት የሰጡ ናቸው። ለዚህ ማረጋገጫው ሌሎች የሙያ አጋሮችህ አንተን አብነት እያደረጉ ነው። ተመራጭ ተጠቃሽ በመሆን ላይ ነህ። ለዚህ ያበቃህ ደግሞ በእቅድ መመራትህ ይመስለኛል።
መሪዎችህ ሳምንት ሙሉ አስበውና ተጨን ቀው ለአንተ እድገት መስራት መጀመራቸው ተመራ ጭነትህንም እያሰፋው ይመስለኛል። ግን አሁንም ብዙ የሚጎሉህ እንዳለ አስብ።
ለኢትዮጵያ ሥነጽሁፍ መዳበር ወደር የሌለው ተግባር የሰራህ አንጋፋ ጋዜጣ ነህ። በንጉሱ ዘመን ከ1937 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ስነ ፅሁፍ ለአንባብያን እንዲጎርፉ ፈር ቀደሃል። ከ1970 እስከ 1971 ዓ.ም ደግሞ ‹‹ የባህል መድረክ›› የሚል ገጽ በመክፈት ባህልን ለህዝብ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ያስተዋወቅክ ባለውለታ ነህ። ከዚያ አለፍ ሲልም በርካታ መጽሐፍት፣ ተውኔቶች እንዲተቹ አድርገሃል። አንባቢያና ደራሲያንም ከትችቶች እንዲማሩ ያደረገ ማንም አልነበረም አንተው ነህ።
የልምዣት፣ አንድ ለአምስት፣ ግርዶሽ፣ ወገግታ፣ ጉንጉን፣ እንጉዝ፣ ከጣሪያው ሥር፣ አደፍርስን የመሳሰሉ መጽሐፍት አንተ በፈጠርከው አምድ ተተችተው ህዝቡ እንዲማርባቸው ሆነዋል። ይህ ደግሞ በአንተ መሰረትነት የተገነባው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ‹‹ የክፍለዘመኑ የኢትዮጵያ ሥነጽሁፍ ጀግና›› ለመባል በቅቷል። ከዚያም አልፎ በ1994 ዓ.ም የአገሪቱ ደራሲያን ማህበር የእድሜ ልክ የክብር አባልነትን ሰጥቶታል።
የአንተ ውለታ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይመስለኝም። በኪነጥበቡ ቢባል በፖለቲካው የአንተ ሥራ በሁሉም ልብ ውስጥ አሻራውን አኑሯል። ስለዚህም ውለታህ የበዛላቸውን አሁንም አትቀንስባቸው።
ከዋና አዘጋጆች
ምንም ያህል ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ቢዘረጋም፣ ምንም ያህል ወቀሳና ክስ ቢቀርብብህም ከአንተ ጋር ያሳለፉትን ጊዜ መቼም አይረሱትም። እንደውም አንተ ‹‹ተስፋዬ ነበርክ›› የማይልህ እንዳልነበር የተለያዩ መረጃዎችን ሳገላብጥ ተመልክቻለሁ። ዛሬ በህይወት ያሉ ሁለት ዋና አዘጋጅ የነበሩ ሰዎችን አነጋግሬያለሁ ። እናም እነርሱ እንዲህ ነበር ያሉት። መጀመሪያ ያናገርኩት በ1990ዎቹ አንተን በዋና አዘጋጅነት የተወዳጀው አቶ ወንድምኩን አላዩ ነበር። ስለአንተ ውለታ አውርቶ አይዘልቀውም።
‹‹በእኛ ዘመን መንግሥት ጫና ያደርግ ነበር፤ ባለስልጣናትም የሚፈልጉት ጽሁፍ ካልወጣ ብለው ይሞግታሉ። ግን ጋዜጠኛው በጣም ስለሚወድህና ሙያውን ስለሚያከብር ማንነቱ ሊከበር ይገባል በማለት ይሟገትልሃል። በዚህም የተሻሉ መንገዶችንም ፈጥሮልህ አልፏል። ለአብነት‹‹ ባለጉዳይ›› የሚል አምድ በመክፈት የህዝብ መሆንህን ለማሳየት ተጥሯል። ውበትህ ከተፈላጊነትህ ጋር እንዲጣጣም መሸ ሳይል እያደረ ሁሉ ያንተን ደህንነት ሲያስጠብቅ ቆይቷል። ግን የነበረው ጫና ከዚያ በላይ በመሆኑ በነበርክበት ቀጥለሃል›› ይላል።
ነገ ብትሆን የምመኘው በአገሪቱ ያሉ ፖለቲከኞች የሚጽፉብህ፣ መንግሥትም ጭምር የሚወድህና አለኸኝ የሚልህ፣ ህዝብም ከእኔ ውጪ የሚወግንለት የለም ባይነቱን የሚሰጥህ ብትሆን ነው። ለዚህ ደግሞ ባለስልጣናት ጭምር የሚያስቡትንና የሚያልሙትን ጽፈው ሲስተናገዱበት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር አንተን መርጠው ብቸኛው ስለሆንክ በርታ እያሉ ሥራቸውን የሚያበረክቱብህ መሆን አለብህም›› ብሏል።
ሌላኛው ዋና አዘጋጅ በ2000ዎቹ ውስጥ የመራህ አቶ ንጉስ ወዳጅነህ ነው። እርሱም እንደ አቶ ወንድምኩን አንተን ያመሰግንሃል፤ መምህሩ እንደነበርክም ያወሳል። ግን በእርሱ ጊዜ ብዙ ችግሮች እንደነበሩብህ ሳይገልፅ አላለፈም። ለአብነት የብሔር ፍረጃው፣ የፖለቲካው ጣልቃ ገብነት፣ የፓርቲ አቀንቃኝነትና በአቅጣጫ ላይ ብቻ ተመርኩዞ መስራትህን እርግፍ አድርገህ መተው አለብህ ይልሃል። ምክንያቱም ይህ ለአንተ ለውጥ የማይተካ ሚና አለውና።
ዋና አዘጋጁ አንተን ከመለየቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የተጀመሩትን ለውጦች ይደግፋቸው ነበር። ለምሳሌ ዕለታዊ ሆኖ ሳምንታዊ ሥራ ለጋዜጠኞች በመስጠት የተሻለ ሥራ ይዞ መውጣት፤ የሌሎች ተከታዮች ሳይሆኑ በእቅድ ሰርቶ መንግሥትን ጭምር አቅጣጫ ማሳየት ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ እንደነበር ያስረዳል። የህዝብ ወገንተኝነት ካለህ ስያሜ አኳያ ሊጎላ ይገባልም ብሎሃል።
መቋጠሪያ
እድሜ ጠገብ ጋዜጣ ስለሆንክ ልምዶችህ አስተማሪ ሊሆኑ ይገባል። ተወዳዳሪዎችህ ጠንካራ እንደሆኑ በማሰብ መስራት ያስፈልጋል። እንደቀደሙት ጊዜያት የግል አጋሮችህ እኩዮችህ ሳይሆኑ ተከታዮችህ፤ አስተማሪዎችህ ሳይሆኑ ተማሪዎችህ እንዲሆኑ ማድረግን ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ፈጣን፣ ተአማኒ፣ተመራጭ፣ ተደራሽ፣አስተማሪ … ለመሆን ትጋ። ተጽዕኖን ተጋፈጥ እንቢ ባይነትን አቀንቅን ። ቅድሚያ ለህዝብ፣ ለህዝብ… እያልክ ራስህን ቀይር አጠንክርም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው