ከጨለማ ወደ ብርሃን

ቤተሰቦቹ እሱን ሲወልዱ፤ ልክ እንደሌሎች ጥንዶች “ወግ ማዕረግ አየን” ሲሉ ወግአየሁ ብለው ስም አወጡለት። ወግአየሁ ግን ለወግ ለማዕረግ ሳይበቃ ገና በጨቅላ ዕድሜው ቀኑ መሸበት። ቀኑም፣ ሌሊቱም አንድ ሆነበት።

ወጣት ወግአየሁ ፈጠነ ትውልዱና እድገቱ ሀረር ነው:: ወጣቱ የዓይን ብርሃኑን ያጣው ገና በሕፃንነቱ በኩፍኝ በሽታ ምክንያት ነው ። በሽታ የዓይን ብሌን ላይ ጠባሳ በመፍጠሩ ለአይነስውርነት ተዳርጓል::

በዚህ የተነሳ ወግአየሁ ልክ እንደ እድሜ አቻዎቹ እንደልቡ መንቀሳቀስ፣ መቦረቅ፣ መጫወትና ትምህርቱን በአግባቡ መከታተል አልቻለም:: ጀንበሯን ልክ እንደእኩዮቹ ሳይቦርቅባት ገና በጠዋት የቀን ጨለማ ውጦት ቆይቷል::

በ2000 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ባመቻቸለት የዓይን ብሌን ልገሳ ዕድል፤ አንደኛውን ዓይኑን የብሌን ንቅለ ተከላ በማድረግ የዓይን ብርሃኑ ተመልሷል:: ከስድስት ዓመት በኋላ ደግሞ ሁለተኛውን ዓይኑን የብሌን ንቅለ ተከላ በማድረግ ሁለቱም ዓይኖቹ ከድቅድቅ ጨለማ ተላቀው በብርሃን ተሞሉ።

የዓይን ብርሃኑ መመለሱን ተከትሎ ትምህርቱን የጀመረው ወጣት ወግአየሁ ፤ በትምህርቱም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ አሁን ላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ በማርኬቲንግና ማኔጅመንት የዲግሪ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል::

ወግአየሁ የዓይን ብርሃኑ ሊመለስለት የቻለው በጎ ፍቃደኞች ከህልፈት በኋላ በለገሱት የዓይን ብሌን መሆኑን በማመልከት ፤ ልክ እንደርሱ ሌሎች የጨለመባቸው ዜጎች ብርሃን እንዲፈነጥቅላቸው ሰዎች በሕይወት እያሉ ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንዲገቡ ጥሪውን አስተላልፏል።

የዕይታ ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ህዳር ወር በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል። ይህንን በማስመልከት በዚህ ወር በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ “ብርሃን አይቅበሩ፤ በብሌን ጠባሳ የተነሳ ዓይነስውር የሆኑ ወገኖችዎ ብርሃን እንዲያገኙ ምክንያት ይሁኑ!” በሚል መሪ ሃሳብ የዓይን ብሌን ልገሳ ወር እየተከበረ ይገኛል።

በዓይን ብሌን ልገሳ ዘመቻ ወር ኅብረተሰቡ ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌኑን እንዲለግስ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ሰፊና ልዩ የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ይናገራሉ።

ዓይን ባንኩ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ማየት የተሳናቸው ዜጎች መልሰው ብርሃን እንዲያገኙ ማስቻል ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባንኩ ከህልፈት በኋላ ከለጋሽ ወገኖች ብሌን በማሰባሰብ ጥራቱንና ደህንነቱን ጠብቆ ለንቅለ ተከላ ሕክምና እንደሚያሰራጭ ያስረዳሉ።

በዚህ መሠረት ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም ድረስ ከ3ሺ 500 በላይ ወገኖች በተለያዩ የሕክምና ማዕከላት የብሌን ንቅለ ተከላ ተደርጎላቸው የዓይን ብርሃን ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ ከ15 ሺ በላይ ወገኖች ደግሞ ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ የቃል ኪዳን ሰነድ ፈርመዋል ብለዋል::

በአህጉራችን ከኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የዓይን ባንኮች ውጭ ከ21 ዓመታት በላይ ቋሚ የዓይን ብሌን  ንቅለ ተከላ አገልግሎት እየሰጠ የቀጠለና እድገት እያሳየ የመጣ የለም የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባንኩ የሚሰጠው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በርካታ ወገኖች የዓይን ብርሃናቸውን እንዲያገኙ ቢያስችልም፤ አሁንም አገልግሎቱን ከሚፈልጉ ዜጎች አኳያ ብዙ የቤት ሥራ እንደሚቀር ይናገራሉ::

ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቀደም ሲል በጤና ሚኒስቴር በኩል በተደረገ ጥናት መሠረት ከ300 ሺ በላይ የሚሆኑ በዓይን ብሌን ጠባሳ ዓይነ ስውራን ዜጎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ። ተቋሙ በሠራው ሥራ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ የሚያከናውኑ ባለሙያዎችና አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት ቁጥር እያደገ ቢመጣም፤ አሁንም ባለሙያዎቹና ተቋማቱ በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በዓይን ብሌን ጠባሳ ብርሃናቸውን ያጡ ዜጎች ብርሃን እንዲያገኙ ብዙ መሥራት ይጠይቃል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ ህብረተሰቡና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጭምር ይህን የሕዝብ ዓይን ባንክ በተለያየ መልኩ እንዲደግፉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አስተላልፈዋል::

የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ባለሙያዎችን እንዲሁም የዓይን ባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ቁጥር ለመጨመር ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አመላክተው፤ በተያዘው በጀት ዓመት አንድ የዓይን ባንክ ክልል ላይ እንደሚከፈት ጠቁመዋል። የዓይን ብሌን ልገሳ የሚከናወንበት ወጥ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የዓይን ባንክ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አምሳለ ጌታቸው በበኩላቸው ፤ የዓይን ብሌን ከዓይናችን ትንሹ ክፍል ሲሆን፤ ጥቁሩ የዓይናችን ክፍል ላይ ያለው እንደ መስታወት የሚያንፀባርቀው ስሱ ክፍል እንደሆነ ያስረዳሉ::

የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡ ሰዎች ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ፤ ይህ የዓይናቸው ክፍል በሚነሳበት ጊዜ ፊታቸው ላይ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ገልጸው፤ የዓይን ብሌን ለመውሰድም የሚፈጀው ጊዜ ከ20 ደቂቃ በታች እንደሆነም ጠቁመዋል። ይህም የቀብር ሥነ ሥርዓትን እንደማያስተጓጉል አስታውቀዋል::

ቤተሰብ ይህንን ተገንዝቦ ለጋሹ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ወደ ዓይን ባንክ ደውሎ ብሌኑ እንዲወሰድ በማድረግ፤ ብርሃናቸውን ያጡ ወገኖች ብርሃን እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ ለጋሹ በሕይወት እያለ የገባው ቃል ተፈጻሚ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You