እንስት እህቶቻችን በማህበረሰብ ውስጥ ከተፈጠረ የተሳሳተ ግንዛቤ የተነሳ ከቤት ውስጥ ሥራ ባለፈ ውጤታማ መሆን ስለመቻላቸው ብዙም ጎልቶ ሲነገርላቸው አይሰማም። አብዛኞቹ የስኬት ትርክቶች ወደ ወንዶች ያመዘኑ ስለመሆናቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ይህም ሆኖ በተለያዩ አጋጣሚዎች ብዙ ተግዳሮቶችን በጽናት ተሻግረው የስኬት ባለቤት የሚሆኑ እንስቶች ቁጥር እለት እለት እየጨመረ ስለመሆኑ በተለያዩ የመገናና ብዙሃን እንሰማለን። እነዚህ እንስት እህቶቻችን የተጓዙባቸው የስኬት መንገዶች የሚጎረባብጡ ቢሆኑም፤ መንገዱን በጽናት ተሻግረው መገኘታቸው ለብዙዎች ተምሳሌት ያደርጋቸዋል።
ዛሬም በሥራ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ለመትረፍ መሻት ላላቸው እህቶቻችን ተምሳሌት ይሆናሉ ያልናቸውን ተጨባጭ የጥንካሬ ተምሳሌቶችን ይዘን ቀርበናል ወይዘሮ ሙሉየ ካሳ ይባላሉ:: የሙሉ ጤና ባልትና ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ናቸው:: ድርጅታቸው ከ50 ሺህ ብር ካፒታል ተነስቶ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ካፒታሉን ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ደርሷል::
ሥራ ካፒታል ስላለ ብቻ አይጀመርም የሚሉት ወይዘሮ ሙሉየ፤ የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው መሥራት የጀመሩት ከ55 ዓመታቸው በኋላ መሆኑን በመግለጽም፤ ሥራን ለመጀመር ፍላጎት እና ችሎታ ወሳኝ መሆንን ይመክራሉ። እድሜ፣ ጾታ፣ ገንዘብ እና ሌሎችም ወደ ሥራ ላለመግባት ምክንያት አይሆኑም ይላሉ::
ድርጅታቸው የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን በማዘጋጀት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ሶስት ባለሙያዎችን ይዞ መጀመሩን አመልክተው:: ድርጅቱ አሁን ላይ ካፒታሉን ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር መድረሱን ፤ ለ12 ቋሚ እና ለ12 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ያስረዳሉ::
በኮቪድ ወቅት የውጭ ሀገር ገበያው ሙሉ በሙሉ ቆሞ ነበር የሚሉት ሥራ አስኪያጇ፤ የሚያዘጋጁትን የባልትና ውጤት በሀገር ውስጥ ገበያው በስፋት በማቅረብ ድርጅቱን ከመዘጋት ታድገናል ይላሉ:: በቀጣይ ለድርጅታቸው እህት ኩባንያ እና የማሠልጠኛ ማዕከላትን ለመክፈት ማቀዳቸውን ይገልጻሉ::
ሌላኛዋ የጥንካሬ ተምሳሌት እምሻው ብርቄ ትባላለች:: ነዋሪነቷ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ነው ፤ ካለፉት 12 ዓመታት ጀምራ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን በማዘጋጀት ሥራ ላይ ተሠማርታለች:: ህልሟ አረብ ሀገር ሠርታ ባመጣችው ገንዘብ የባህል ምግብ ቤት መክፈት ቢሆንም ለምግብ ቤት የሚሆን ቦታ ስትፈልግ ከባድ የመኪና አደጋ እንደደረሳባት ታስታውሳለች::
ምግብ ቤት እከፍትበታለሁ ያለችውን ገንዘብ ለህክምና ለማዋል የተገደደችው እምሻ :: ለሰዎች ከማገዝ ወጥታ ወደተረጅነት እየሄደች መሆኗ ሲገባት በክራንች እየሄደች ሥራ ጀመረች:: ሥራ የጀመረችው ደግሞ ለእሷ ማስታመሚያ በተዘጋጀው የአጥሚት እህል እንደሆነ ትናገራለች::
በክራንች እየተራመደች በጀርባዋ ደግሞ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን ይዛ በተለያዩ ጎዳናዎች በመዞር ከአንድ ዓመት ለላነሰ ጊዜ ሠራች:: በቀጣይም ሥራዋን በማሳደግ እና ንግድ ፈቃድ በማውጣት በቤቷ እና በተለያዩ ባዛሮች ላይ እየዞረች መሥራቷን ቀጥላበታለች::
ሃሳቧ ሥራዋን በማሳደግ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የሥራ እድል መፍጠር በመሆኑ፤ ሥራውን ከፍ ባለ የዓላማ ቁርጠኝነት መሥራት በሚያስችል መነቃቃት በትጋት መስራቷን ቀጥላለች:: እምሻው ትዕዛዝ ሲመጣ የለኝም ማላት አታቅም:: የታዘዘችውን የቅመማ ቅመም ዓይነት ታዘጋጃለች:: አሁን ላይ 68 ዓይነት ቅመማ ቅመሞችን ታዘጋጃለች ፤ 800 ሺህ ብር ካፒታል ላይም ደርሳለች:: በዚህም ቤተሰቧን በአግባቡ ማስተዳደር ችላለች::
ሀጉሽ ተክላይ ትባላለች:: የባልትና ውጤቶችን እና ጣፋጭ ምግቦችን በማዘጋጀት ለሽያጭ ታቀርባለች:: ሥራውን ለመሥራት ካላት ከፍተኛ ፍላጎት በተጨማሪ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስዳለች::
የባልትና ውጤቶች እና ጣፋጭ ምግቦች ማዘጋጀት የጀመረችው ኑሮዋን ለመደጎም በማሰብ በቤት ውስጥ በምትጠቀምበት የአስቤዛ ገንዘብ ነው:: አሁን ላይ ከራሷ አልፎ ለሌሎች ሰዎችም እንጀራ መሆን እንደቻለ ታስረዳለች::
በአሁኑ ሰዓት ሁለት የሽያጭ ማዕከላትን ከፍታለች:: ከተለያዩ አካባቢዎች ትዕዛዝ ተቀብላም ታስተናግዳለች:: ከራሷና ከቤተሰቧ አልፋ ለሰባት ቋሚ እና ለሶስት ጊዜያዊ ደግሞ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችላለች:: እስከ 2018 ዓ.ም ሥራዋን ወደ ማሠልጠኛ ማዕከል ለማሳደግ ማቀዷንም ትናገራለች::
ሀጉሽ ሰዎች የኑሮ ችግር ባይኖራቸውም ሥራ መሥራት የግድ ነው የሚል እምነት አላት ፤ ቤት የሚውሉ ሰዎች የተለያዩ የሥራ መረጃዎችን በማሰባሰብ ጊዜያቸውን በሥራ እንዲያሳልፉ ትመክራለች:: ሥራን በጥራት ማከናወን ከተቻለ ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል እራሷን ምስክር አድርጋ ትናገራለች::
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም