ባለሥልጣኑ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡ ተገለፀ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን በመጀመሪያው ሩብ አመት በሁሉም መስክ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ገለፀ፡፡

ባለሥልጣኑ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ የሩብ ዓመት አፈፃፀሙ አበረታች እንደነበረ ገልፆ የምግብ ደህንነት ቁጥጥርን ከማጠናከር አኳያ 871 ለሚሆኑ የምግብ አይነቶች የምዝገባና የፍቃድ አገልግሎት መስጠቱን ጠቁሟል፡፡

በ130 አምራች እና በ472 አስመጪና አከፋፋይ ተቋማት የድህረ ፈቃድ ኦዲቲንግ ኢንስፔክሽን ተከናውኖ በ13 የምግብ ፋብሪካዎች በ24 የምግብ ላኪ አስመጪና አከፋፋይ ድርጅቶች የውስጥ ጥራት ማረጋገጥ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉም ተጠቅሷል፡፡

ሕገወጥ ምርቶችን ከመለየት፣ ከመከላከልና ምላሽ ከመስጠት አኳያም ባለፈው ሩብ ዓመት በተለያዩ የምግብ ምርቶች ላይ በምግብ ገበያ ማዕከላትና በምግብ ችርቻሮ ድርጅቶች እንዲሁም በተለዩ የምግብ ዓይነቶች ላይ በ10 ዙር ቁጥጥር ማድረግ መቻሉን ጠቁሟል፡፡

ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ ቁጥጥሩ የተካሄደባቸው አካባቢዎች ሲሆኑ የዱቄት ወተት፣ የምግብ ዘይት፣ የበቆሎ ዱቄት፣ የጤፍ ዱቄት፣ የለውዝ ቅቤና ፕላምፕኔት ደግሞ ቁጥጥር ከተደረገባቸው የምግብ አይነቶች ተጠቃሽ መሆናቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡

በተደረገው ቁጥጥርም ከ252 ሺ ኪግ በላይ የሚመዝኑ ወይም ከ54.9 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ምርቶች ላይ ርምጃ መወሰዱን መግለጫው አስታውሷል፡፡

የመድኃኒቶች ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነት እንዲሁም አግባባዊ አጠቃቀም ቁጥጥርን በማሻሻሉ ረገድም ለ138 መድሃኒቶች የገበያ ፈቃድ መስጠቱን ገልጾ ለ104 አስመጪና አከፋፋይ እንዲሁም ለ9 ጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ አምራች ተቋማት ፍቃድ መስጠቱ ተብራርቷል፡፡

በሩብ ዓመቱ ከ127 ተቋማት የተሰበሰቡ ከ168.3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶች ላይ ርምጃ እንደተወሰደም ተመላክቷል፡፡

የህክምና መሣሪያዎችን ጥራት፣ ደህንነት እና ውጤታማነት ቁጥጥር ማጠናከርን በተመለከተም ለ154 የህክምና መሣሪያዎች ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሶ 200ሺህ ብር የሚያወጡ ሕገወጥ የህክምና መሣሪያዎች ላይ ርምጃ መወሰዱ ተብራርቷል፡፡

የመዋቢያ ምርቶችን ደህንነትና ቁጥጥር በማሻሻል ረገድም በሩብ ዓመቱ ለ14 የውበት መጠበቂያ ምርቶች ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ 97ሺ ብር የሚያወጣ የተበላሸና ደረጃውን ያልጠበቀ ምርት ደግሞ እንዲወገድ መደረጉን መግለጫው አስታውሷል፡፡

የትንባሆ እና የትምባሆ ምርቶች ቁጥጥር ሥርዓትን ከማጠናከር አንፃር በክልሎች የተቋቋመውን የትምባሆ ቁጥጥር ኮሚቴ ማደራጀት፣ ማጠናከር፣ መከታተልና መደገፍ መቻሉ ተብራርቷል፡፡

መቶ በመቶ ከትምባሆ ጪስ ነፃ የሕዝብ ቦታዎችን ከመፍጠር አንፃር አዲስ አበባ፤ ድሬዳዋ፤ ሐረር፣ አርባ ምንጭ፤ ሃላባ፤ ወላይታ ሶዶ እና ሆሳዕና ከተሞች የቁጥጥር ሥራዎች መሠራቱን የጠቆመው መግለጫው በሩብ ዓመቱ በተሰሩ የገበያ ቅኝቶችና ኦፕሬሽኖች ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሕገወጥ የትንባሆ ምርቶች መሰብሰብ መቻሉንም አመላክቷል፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You