በዘመናት ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያን ሲፈታተኗት ከቆዩት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መካከል ድርቅን ያህል የፈተናት የለም ማለት ይቻላል፡፡ በተፈጥሮ መዛባት በአካባቢ ላይ በሚደርሰው አደጋ ምክንያት ኢትዮጵያን እርሃብና ድርቅ በየ10 ዓመቱ ሲጎበኛት የቆየ ከመሆኑም በሻገር ለበርካታ ዜጎች ህልፈትም ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድም የሀገሪቱ መለያም እስከመሆን ደርሷል።
ከዜጎች ህልፈትና ስቃይ አልፎ የሀገሪቱን ገጽታ ያበላሸውን ይህንን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድና ኢትዮጵያ እንደስሟ የአፍሪካ ውሃ ማማና የዳቦ ቅርጫት እንድትሆን የሀገሪቱ መንግስትና ዜጎች የጋራ ጥረት ማድረግ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡ ፡ በተለይም የዶክተር አብይ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ የሀገሪቱ የዘመናት ችግር ሆኖ የዘለቀውን ድርቅና የአካባቢ ማራቆት ለማስወገድ መጠነ ሰፊ የሆነ የችግኝ መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ባለፈው የክረምት ወራትም ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በሀገር አቀፍ ደረጃ በመትከል ስር የሰደደውን የአካባቢ መራቆት መታደግ የሚያስችል አይነ ግቡ ስራ ተከናውኗል፡፡ ከተተከሉት ችግኞች ውስጥም 84 በመቶ በመጽደቅ አዲስ ምዕራፍ ተጽፏል፡፡
ይህንኑ አርአያነት ያለውን ተግባር በማስፋትም ዘንድሮም አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ክረምቱን የሚዘልቅ አዲስ መርሃ ግብር ተዘርግቷል፡፡ በትናንትናው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና የስራ ባልደረቦቻቸው መርሃ ግብሩን አስጀምረዋል፡፡
የዘንድሮውን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከሌላው ጊዜ የተለየ የሚያደርገው ተከላው የሚካሄደው በዓለም ላይ ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀና በአገራችንም የስርጭት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ዘንድሮ ችግኝ ሲተከል በተለየ ሁኔታ የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋና የበለጠ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ በማድረግ ጭምር መሆን አለበት፡፡
በማንኛውም አጋጣሚ በዚህ ስራ ላይ የሚሳተፉ ዜጎችም የችግኝ ተከላውም ሆነ የኮሮና ቫይረሱን የመከላከል እንቅስቃሴው ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን በመገንዘብ እነዚህ ሁለት ወሳኝ ጉዳዮች በጥንቃቄ መካሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ህይወት ስንተክል ህይወታችንን በመጠበቅ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም፡፡
በተለይም በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየከፋ በመምጣቱና በአጠቃላይም በሀገሪቱ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 2000 እየገሰገሰ ባለበት ወቅት ማንኛውም እንቅስቃሴያችንን ይህንኑ ክፉ ደዌ ለመግታት የሚያስችል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ስራችንም በአንድ ጎን ልማትን በሌላ ጎን ደግሞ ጥንቃቄን መርሁ አድርጎ መከናወን ይገባዋል፡፡ ይህ ሲሆን ነው የትውልድን ቀጣይነት የምናረጋግጠውና ስራችንም በታሪክ ማህደር ውስጥ ሊታወስ የሚችለው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012