ዳግማዊው ሕዝብ ለሕዝብ ኪን ኢትዮጵያ

ዜና ሐተታ

በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ ድርቅ ተከሰተ። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገንዘብም የሃሳብም ድጋፍ አደረገ። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያበላሹ ትርክቶችም መነገር ጀመሩ። ይህን የተረዳው የወቅቱ መንግሥት የኢትዮጵያን ምንነት እና ማንነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት አለብኝ ብሎ ተነሳ።

‹‹ሕዝብ ለሕዝብ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ የኪነት ቡድን ተቋቁሞ በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተዘዋወሩ ኢትዮጵያን አሳዩ። በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችና ዓለም አቀፍ ጋዜጦች ሰፊ ሽፋን አገኘ። በወቅቱ የነበሩ የኪነት ሥራዎችም ዘመን ተሻጋሪ ሆነው ዛሬ ድረስ እየታወሱ ይገኛሉ።

እነሆ ከ40 ዓመታት በኋላ አምሳለ ሕዝብ ለሕዝብ ‹‹ኪን ኢትዮጵያ›› የተሰኘ የኪነ ጥበብ ቡድን በተለያዩ የዓለም ሀገራት የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ሊያሳይ ነው። ‹‹የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት›› በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ይህ የኪነት ጉዞ፤ ከ50 በላይ የሆኑ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተወከሉበትን የኢትዮጵያን ምንነት ለዓለም ሀገራት ያሳያል። የእዚህ ዓመት ጉዞውን የሚያደርገውም በብሪክስ አባል ሀገራት ነው።

ይህ ሃሳብ የታሰበው ከአራት ዓመታት በፊት መሆኑን በ2013 ዓ.ም የተሠራ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃ ያሳያል። የወቅቱ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ‹‹ሕዝብ ለሕዝብ›› ይባል የነበረውን ዓለም አቀፍ የኪነ ጥበብ ጉዞ ሊያስጀምር እንደሚችል ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ይህን ጉዞ ለማዘጋጀት የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ያወጣውን ጨረታ ያሸነፈው ሻኩራ ፕሮዳክሽን ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዝግጅቱን አጠናቆ ከትናንት በስቲያ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ለልዑካን ቡድኑ ሽኝት አድርጓል።

ኢትዮጵያን ወክላ የምትጓዘው ታዳጊ ያኔት ሰለሞን የሰርከስ ትርዒት ባለሙያ ናት። ታዳጊ ያኔት ሰለሞን በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጸችው፤ ለምታሳየው የሰርከስ ትርዒት በቂ ዝግጅት አድርጋለች። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት ባለሙያዎች መኖራቸውን ለዓለም ሀገራት ማሳየት ትፈልጋለች። እሷም በተለያዩ ሚዲያዎች በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚታዩ የሰርከስ ትርዒቶችን ታያለች። በምትጓዝባቸው ሀገራት ያሉ ባሕሎችንና ታሪኮችን ለማየትም ጓጉታለች።

ሌላኛዋ የሰርከስ ትርዒት ባለሙያ ታዳጊ አርሴማ አሰፋ በተመሳሳይ በቂ ዝግጅት እንዳደረገችና የሀገሯን የሰርከስ ትርዒት ለማሳየት እንደጓጓች ትናገራለች። በጉዞዋ ከተለያዩ ሀገራት አዳዲስ ልምዶች እንደምታገኝ እና ይህም ለሙያዋ እንደሚጠቅማት ትጠብቃለች።

በውዝዋዜ ኢትዮጵያን ወክላ የምትጓዘው ወጣት ሃና ነጋ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጸችው፤ የኢትዮጵያ የብዝሃ ባሕል ሀብቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መተዋወቅ ያለባቸውን ያህል አልተዋወቁም። የኢትዮጵያ ወጣቶች በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች የውጭ ሀገራትን ባሕሎችና ትርዒቶች ቢከታተሉም፤ የኢትዮጵያን ባሕልና ትርዒቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት ግን በእሷ ዕድሜ ሲሠራ አላየችም። ይህ ጉዞ ለእሷ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን የምትናገረው ሃና፤  የሀገሯን ባሕልና ወግ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት በቂ ዝግጅት እንዳደረገች ተናግራለች።

ከሥራዋ ጋር የሚመሳሰሉ የተለያዩ ሀገራት ውዝዋዜዎችን በሚዲያ አማራጮች የምትከታተል ቢሆንም፤ በአካል በቦታው ተገኝቶ ማየት ደግሞ የበለጠ ለልምድ እንደሚሆንም ተናግራለች።

የሻኩራ ፕሮዳክሽን መሥራችና ባለቤት የሙዚቃ አቀናባሪው ከሙዙ ካሳ በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጸው፤ የኪነ ጥበብ ልዑክ ጉዞ መዘጋጀቱ ልዩ እና ብዝሃ ውበት የሆነውን የኢትዮጵያን ምንነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት ዕድል የፈጠረ ነው። ሻኩራ ፕሮዳክሽን ጨረታውን አሸንፎ ዝግጅቱን ለመምራት ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ በቂ ዝግጅት አድርጓል ብሏል።

ሻኩራ ፕሮዳክሽን የኢትዮጵያን ብዝሃ ምንነት ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳየት ከኢትዮጵያ ሕዝብ አደራ የተረከበ መሆኑን የገለጸው ከሙዙ፤ ከእዚህ በፊት በቂ የመድረክ ዕድል ያላገኙ የኢትዮጵያ ባሕልና የጥበብ ሥራዎችን እንደሚያሳይ ተናግሯል።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ኪነ ጥበብ የአንዲት ሀገር ምንነት የሚገለጽበት የሕዝብ ነፀብራቅ ነው። የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለዓለም ሀገራት ማሳየት ሀገርን ማሳየት ማለት ነው። በተለይም ዓለም አቀፍ ጉዞው ደግሞ በሀገራት መካከል ያለውን አብሮነት ያጎለብታል። ሕዝቦችን ከሕዝቦች ጋር ያስተዋውቃል፤ ያቀራርባል። ሕዝቦችን ማስተዋወቅ እና ማስተሳሰር ለልማት እና ለሰላም ዕድገት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል።

ከ39 ዓመታት በፊት በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተደርጎ የነበረው የኢትዮጵያ የሕዝብ ለሕዝብ ጉዞ ሕዝቦችን በማቀራረቡ ለሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት ውሎ እንደነበርም ሚኒስትሯ አስታውሰዋል። የአሁኑ ኪን ኢትዮጵያ ጉዞ በተለይም ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች እና ያልተበረዘ ወጥ የራሷ ማንነት ያላት ሀገር መሆኗን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ በሽኝት መድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በዓለም ሀገራት ታሪክ የአንድን ሀገር ምንነት የሚያሳየው የባሕልና ጥበብ ሥራ ነው። ኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት ታሪክ እና የብዝሃ ባሕል ሀገር ስለሆነች ይህን ማንነቷን ለዓለም ሀገራት ማሳየት አለባት።

ይህ የኢትዮጵያ ብዝሃ ምንነት እና የረጅም ዘመን ታሪክ ለዓለም ጎልቶ እንዲታይ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል። በኪነ ጥበብ ሀብቶቿ የዓለምን ትኩረት በመሳብ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን አለባት ብለዋል።

‹‹ዛሬ ‹በልጽገዋል› እያልን የምንጠራቸው የዓለም ሀገራት ፊልሞቻቸው እና ሙዚቃዎቻቸውን በመጠቀም ዜጎቻቸውን በሚፈልጉት ሀገራዊ ሕልም ከመግለጻቸውም ባሻገር በዓለም ላይ ገናና እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው ለመታየት ችለዋል›› ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ይህ የሆነው በኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው የዓለምን ትኩረት በመሳባቸው ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ታገሰ ገለጻ፤ በኪነ ጥበብ ሥራዎች የሕዝቦችን አንድነት በመገንባት ጠንካራ ሀገር መገንባት እና ዘርፉን ለኢንቨስትመንት መጠቀም ይቻላል። መንግሥት ለኪነ ጥበብ ዘርፉ በሰጠው ትኩረት በርካታ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲሠሩበት አድርጓል። ዘርፉ ለገጽታ ግንባታ፣ ለትውልድ ቀረጻ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለዘላቂ ሰላም እንዲውል ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ አቶ ታገሰ ገለጻ፤ የኪነ ጥበብ የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያን ብዝሃ ማንነት ለዓለም አደባባይ በማሳየት፣ ዓለም አቀፋዊ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለመፍጠር፣ ዲፕሎማሲያዊ ልምድን ለማሳደግ፣ ቱሪዝምን በመሳብ ዜጎቿን ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ ሀገራዊ ተልዕኮ ነው። ኢትዮጵያ በውስጥ እና በውጭ የነበሩባትን ፈተና ተቋቁማ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በከተሞች ልማት፣ በኢትዮጵያ ታምርት እና በቱሪዝም ልማት ለብልፅግና መሠረት እየጣለች ባለችበት ወቅት የኪነ ጥበብ የልዑካን ቡድን ጉዞ መደረጉ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

ኪን ኢትዮጵያ የጥበብ ጉዞ አባላት በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተለያዩ የውጭ ሀገራት እንግዶች በተገኙበት የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችንና ትርዒቶችን አሳይተዋል። አባላቱ በቅርቡ ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን፤ የመጀመሪያ መዳረሻቸው ሩሲያ ትሆናለች ተብሏል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You