
አዲስ አበባ፡- በመጪው ክረምት በምሥራቅ አፍሪካ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚጥል ይህን ተከትሎ የሚፈጠረውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ከወዲሁ የተግባር ሥራ መጀመር እንዳለበት የኢጋድ አየር ትንበያ እና ምርምር ገለጸ።
በኢጋድ የአደጋ መከላከል ሥራ አስኪያጅ አሕመድ አምዲሁን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በቀጣናው ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት የክረምት ወራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሱዳን፣ በኤርትራ እና በደቡብ ሱዳን ከሚጠበቀው በላይ የዝናብ መጠን እንደሚኖራቸው የአየር ትንበያ መረጃ ያመላክታል። ምንም እንኳን ወቅቱ ለግጦሽ ፣ ውሃ እና ለመኸር ምርት ዘመን ጥሩ አጋጣሚ ቢሆንም የጎርፍ አደጋ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል።
አደጋውን ለመከላከል ከተቀመጡ አቅጣጫዎች መካከል የመጀመሪያው መረጃውን ማወቅ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ከእዚሁ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋዎች በተጓዳኝ ይዘው የሚመጡትን የወባ በሽታ እና ውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል ጤና ሚኒስቴር እና አደጋ ስጋት የግንዛቤ ማስጨበጥ እንዲሁም የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በመንግሥት እና በማህበረሰቡ አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ከወዲሁ የተሰጠው መረጃ ለሁሉም ተደራሽ መደረግ እንዳለበት አመልክተው፤ በመንግሥት በኩል አደጋውን ለመከላከል በጀት መመደብ እንደሚያስፈልግና ቀደም ተብሎ የሚደረግ የጥንቃቄ ርምጃ ወጪን የሚቀንስ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
በጎርፍ አደጋ ምክንያት ሰዎች ተፈናቅለው ከባድ ኪሳራ ከማስተናገድ እና ከመሯሯጥ በፊት የተጠቀሱት ሀገራት ቀድመው የጎርፍ መከላከል ሥራዎች ቢሠሩ አዋጪ እንደሚሆን አመላክተዋል።
መረጃ መስጠት ዋነኛ ጉዳይ ቢሆንም፤ በአተገባበር ላይ ክፍተቶች ይታያሉ ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በጀት መድቦ የተገኘውን መረጃ ከወዲሁ ወደ ድርጊት መቀየር ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም የጥንቃቄ ርምጃ በመውሰዱ ሂደት የቀጣናው ሀገራት የቅድመ ጥንቃቄ እቅድን ተከትለው ለመተግበር ግብረ ኃይል አቋቁመው ወደ ትግበራ መግባት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ከጎርፍ ጋር ተያይዞ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው ያሉት አቶ አሕመድ፤ ያደጉት ሀገራት በሚያደርጉት መጠን ባይሆንም በሀገራችንም ሆነ በቀጣናው ለእዚሁ ተብሎ የሚበጀት ገንዘብ ስለሚኖር አስቀድሞ ወደ ተግባር መግባት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ትንበያው በቀጣናው በዓመት ሦስት ጊዜ እንደሚለቀቅ በመግለፅ ፤ቀጣናው ከሳይንስ እና ዘመናዊነት ጋር ተያይዞ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ( ኤኣይ) በመጠቀም እንዴት መሥራት እንደሚቻል በመገምገም እና በማሻሻል ሂደት ላይ ከኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ ጋር የሚስተካከል ጠንካራ ተቋም መመስረቱን አቶ አህመድ ገልጸዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም