
የየትኛውም ሀገር እድገት የሚወሰነው እንደ ሀገር ያለን አቅም በአግባቡ አውቆ ስትራቴጂክ በሆነ ዕይታ ፤ ሀገር እና ሕዝብን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ መልማት ሲቻል ነው። የአደጉ እና የበለጸጉ የሚባሉ ሀገራትም አሁናዊ እውነታ የሚያሳየው ይህንኑ ተጨባጭ ሀቅ ነው። ከዚህ ውጭ ብልፅግናን/ ልማትን በተለየ ሌላ አማራጭ ያመጣ ሀገር እና ሕዝብ የለም።
ሀገራት ለመልማትም ሆነ ልማቶቻቸውን ለማስቀጠል የልማት አቅሞቻቸውን አሟጥጦ ከመጠቀም ባለፈ የውጭ ኢንቨስትመንትን የማልማት ዋነኛ አቅም አድርጎ መንቀሳቀስ ከጀመሩም ረጅም ዓመታት ተቆጥረዋል። ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የቀደመ ታሪካቸውን በፈጣን ልማት መቀየር የቻሉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው።
ቻይናን ጨምሮ በፈጣን ሁኔታ በልማት የተስፈነጠሩ የእስያ ሀገራት፤ የውጭ ኢንቨስትመንት ለዕድገታቸው ዋነኛ አቅም አድርገው በመውሰድ፤ ራሳቸውን በሁሉም መንገድ በማዘጋጀት ስትራቴጂክ ተጠቃሚዎች ሆነዋል። አሁንም በስፋት እየተጠቀሙ ናቸው። የልማት ትርክታቸው አንድ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል።
ቀደም ባሉት ዘመናት ልማትን አጣጥመው አንቱ የተባሉ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ሀገራትም ቢሆኑ፤ አሁን ላይ ያለውን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት በአሸናፊነት ለመወጣት በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው። እንደ ሀገር ያላቸውን የቀደመ የኢኮኖሚ ባሕል በመግራት የተፎካካሪነት አቅማቸውን እያሳደጉ ነው።
ከዚህ ተጨባጭ እውነት የተነሳም ሀገራት የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ናቸው። በፉክክሩ አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት ሁሌም በተሻለ ዝግጁነት ላይ ይገኛሉ። ወቅቱ በሚጠይቀው መሠረት የሕግ እና የቢሮክራቲክ አሠራራቸውን እየገሩ የተጠቃሚነት እድላቸውን ያሰፋሉ።
እኛም እንደ ሀገር የጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጥረት በብዙ ያደሩ፣ አሁናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው። በተለይም እንደ ሀገር ያሉንን የተፈጥሮ ፀጋዎች አልምቶ ወደሚጨበጥ ልማት/ብልፅግና ለመቀየር ከፍ ያለ ሀብት ያስፈልጋል። ይህን ሀብት አሁናዊ በሆነው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ውስጥ አግኝቶ ለመጠቀም ያለው ፈተና ከባድ ሆኗል።
የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ ዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ የበለጸጉ የሚባሉ ሀገራት ጭምር ተፎካካሪ ሆነው የመገኘታቸው እውነታ፣ ሁኔታውን እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ለዘመናት በሮቻችውን ዘግተው ለኖሩ፤ ደግሞ ከትናንቶቻቸው ተምረው ነገዎቻችውን በብዙ ተስፋ ለሚጠብቁ ሀገራት ጥልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል።
ሀገራዊ በሮችን በመዝጋት የተሻለ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል የሚሉ ከአሁናዊ ዓለም አቀፍ እውነታዎች የሚቃረኑ አስተሳሰቦች እና አስተሳሰቦቹ የወለዷቸው ሥጋቶች። ሥጋቶቹ የፈጠሯቸው ፖሊሲዎች፣ ሕጎች እና መመሪያዎች ሀገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ለምታደርጋቸው ጥረቶች ተጨባጭ ፈተና ሆነው ቆይተዋል።
በርግጥ እንደ ሀገር ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ ለልማት የሚውል ወጣት ትውልድ አለን፣ ይህንን ወደሚጨበጥ ልማት ለመቀየር በቂ ሀብት የለንም። ለዘመናት የመጣንበት መንገድ ለዚህ የሚሆን ሀገራዊ ሀብት ማፍራት የሚያስችል እድል አልሰጠንም። ከዚህ ይልቅ ለተመጽዋችነት የዳረገን ነው።
የቱንም ያህል የተፈጥሮ ሀብት ሆነ የልማት ኃይል የሚሆነን ወጣት ትውልድ ቢኖረንም፣ እነዚህን ሀገራዊ አቅሞች አቀናጅቶ ወደ ዘላቂ ልማት ለመቀየር የውጭ ኢንቨስትመንት ወሳኝ አቅም ነው። ይህንን አቅም በአግባቡ ለመጠቀም አጠቃላይ የሆነውን የሀገር ኢኮኖሚ ሊብራላይዝድ ማድረግ፣ ለዚህ የሚሆን ከዝግጅት ያለፈ ቁርጠኝነት ይጠይቃል።
ከዚህ አንፃር መንግሥት በሄደበት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊበራላይዝድ ለማድረግ የመጣበት መንገድ የሚበረታታ፤ በተጨባጭም ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየተመዘገቡበት ያለ ነው። ሰሞኑን የውጭ ባለሀብቶች በሀገሪቱ ቋሚ ሀብት እንዲያፈሩ የሚያስችላቸውን ረቂቅ ሕግ ማዘጋጀቱ የእዚሁ እውነታ አንድ ማሳያ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከውጭ ኢንቨስትመንትን ጋር በተያያዘ ያለውን ውድድር አሸንፎ ፣ እንደ ሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ትግል ስኬት የሚያስፈልገንን ሀብት ለማሰባሰብ እና ሀገራዊ አቅሞችን ወደ ልማት ለመቀየር ረቂቅ ሕጉ ትልቅ ስትራቴጂክ አቅም ነው!
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም