
– ኮሚቴው ምርጫው ፍትሐዊ እና አሳታፊ ነው ብሏል
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሦስት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የሥራ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ መልማይ ኮሚቴው ስድስት እጩዎችን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ እጩ አባላት መልማይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ በኮሚቴው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ የተመረጡ ስድስት ዕጩ አባላትን ትናንት ይፋ አድርገዋል።
ቀሲስ ታጋይ ዕጩዎችን ይፋ ሲያደርጉ እንደገለጹት፤ ኮሚቴው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ተቋቁሞ የቀረቡ ዕጩዎችን በአዋጁ መሠረት ለቀረቡ ክፍት ቦታዎች የመለየት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
ማህበረሰቡ ከሚያዝያ 1 ቀን 2017 ጀምሮ ለተከታታይ 21 ቀናት በአካል በመቅረብ፣ በስልክ፣ በፖስታ፣ በዋትስአፕ እና በኢሜል ጥቆማዎችን ሲሰጥ መቆየቱን የተናገሩት የኮሚቴው ሰብሳቢ፤ በድግግሞሽ የቀረቡ ከአንድ ሺህ በላይ ጥቆማዎች ውስጥ 168 ተጠቋሚ እጩዎች ተለይተዋል።
ከ168 እጩ ተጠቋሚዎች ውስጥ በ3 የማጣሪያ ምዕራፎች 6ቱን ዕጩ አባላት በመምረጥ እንዲያልፉ ተደርጓል። በእዚህም መሠረት፤ አቶ ተስፋዬ ንዋይ፣ አቶ ተክሊት ይመስል፣ ዶ/ር ያሬድ ሀብተማርያም፣ ወይዘሮ ነሲ አሊ፣ ወ/ሮ ዳሮ ጀማል እና ወ/ሮ ፍሬህይወት ግርማ በአዋጁ መሠረት መስፈርቱን በማሟላታቸው ሦስት የማጣሪያ ሂደቶችን አልፈው ተመርጠዋል ብለዋል።
የተመረጡት ዕጩዎች፤ ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ እንደሚሠሩ እና ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ነጻ መሆናቸውን ቀሲስ ታጋይ ተናግረዋል። በሥራ ሂደትም፤ የብሔር እና የፆታ እኩልነት እንዲኖር፤ እንዲሁም ሁሉንም አሳታፊ ለማድረግ መሠራቱን ጠቁመዋል።
በቀጣይ የተመረጡት ስድስት ዕጩዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ሲሆን፤ እርሳቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ከስድስቱ የመጨረሻ ዕጩዎች ሦስቱ ጊዜያቸውን ባጠናቀቁ የምርጫ ቦርድ አባላት የሚተኩ መሆኑንም ሰብሳቢው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን መሠረት በማድረግ በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን፤ ማቋቋሚያ ሕጉም “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011” ተብሎ ይጠራል። አዋጁ የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ላይ የነበሩ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋሙን አመሠራረትና ኃላፊነቶች ድንጋጌዎችን በመሻር መጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ፀድቆ ሥራ ላይ ውሏል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ የተሻሻለበት ዓላማ የዜጎችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከማንኛውም አካል ነፃ በሆነ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም እንዲመራ፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላትን አመላመልና አሿሿም ግልጽ ለማድረግ እና በተወዳዳሪ ድርጅቶች እና በመራጮች ዘንድ ያለውን ተአማኒነት እና የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ እንዲረዳ መሆኑ ታውቋል። የማቋቋሚያ አዋጁ ስለቦርዱ ሥልጣንና ተግባር፣ ስለቦርድ አባላት አሰያየም እና ሥነ ምግባር የሚደነግጉ ዝርዝር ክፍሎችን ይዟል።
መልማይ ኮሚቴው፣ የእጩዎች ጥቆማም ከሚያዝያ 1 እስከ ሚያዚያ 30/2017 ዓ.ም ድረስ በኢሜል፣ በዋትስ አፕ ፣ በስልክ ፣ በፖስታና በአካል የ168 ሰዎችን ጥቆማ መቀበሉን ገልጿል። ከእነዚህም ውስጥ 103 ወንዶች ፣ 65 ሴቶች እና 6 አካል ጉዳተኞች መሆናቸው ተገልጿል።
መልማይ ኮሚቴው፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ሆነው ቢሾሙ ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሊያስተባብሩ እና ሊመሩ ይችላሉ ያሏቸውን ስድስት እጩዎች ይፋ አድርጓል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም