እርግጥ ነው ቀለሞች በየዲሲፕሊኑ የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም። ከሃይማኖት እስከ ባህል፤ ከጥበብ እስከ ሥነ-ልቦና፣ ከሰው ሠራሽ እስከ ተፈጥሮ ወዘተ ሁሉ ድርሻቸውና አስተዋፅኦአቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በዚህ መሀል ችግር ወዳለበት ፖለቲካና አያያዙ ስንመጣ ቀለማትን የምናገኛቸው ቅጥ አጥተው ነው።
በዓለማችን በ”የቀለም አብዮት” ስም ብዙ ህይወት ረግፏል፤ በተከፋፈለ የቀለም ስያሜ (ቀይ/ነጭ) ከስታሊን ጀምሮ እዚህ እኛ ድረስ የዘለቀ የእርስ በእርስ መተላለቅ ተስተውሏል። ችግሩ የከፋው የአዳም ልጁ ሰው የጥቁር/ነጭ ቀለማት ሰለባ መሆኑ ዘላለም አለሙን አለመላቀቁ ነው። ይህን ጉዳይ በአንድ ብጣሽ ጽሑፍ ፉት የምንለው ባለመሆኑ ወደ ወቅታዊው ቀለም ተኮር ሟች-ገዳይ ትራጀዲ እንሂድ።
ባለፈው ሳምንት በምድረ አሜሪካ ተጀምሮ ከግማሽ በላይ ክፍላተ-ዓለምን እያጥለቀለቀ ያለውን ቀለም-ወለድ አሳዛኝ ክስተትን በተመለከተ ያልተባለ ነገር ባይኖርም፤ እየተባለ በሄደ ቁጥር ግን ያልተባለ እየተባለ መገኘቱና የማናውቃቸው መብዛታቸው ነው።
የህግ የበላይነትን ያስከብራሉ፣ የዜጎችን መብትና ደህንነት ይጠብቃሉ ወዘተ የተባሉና ቁልፍ የህግ አካል የሆኑ ነጭ ፖሊሶች ጥቁሩን ጆርጅ ፍሎይድ በብረት ካቴና ከጠፈሩትና በቁጥጥር ስር ካዋሉት፣ ከአንድም አራት ሆነው ከከበቡት በኋላ መኪናቸው ስር ቀርቅረውት፣ አስፓልት ላይ አስተኝተውት፣ በማን አለብኝ ባዩ ነጭ ፖሊስ እግር ክርን ጉሮሮው ላይ ተረግጦ (ዕድሜ ለወጣቷ ዳርኔላ ፍሬዘር ቪዲዮውን ለቀረፀችው) ህይወቱ ተቀጥፏል። በዚሁ ቁጭትም በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ነገር እሳት በእሳት ሆኗል።
ድርጊቱ አዲስ አይደለም። ዕድሜ ጠገብ ነው። ልዩነቱ የአሁኑ የግፉ ብዛትና የጭካኔው ከጣራ በላይ በመሆን ከጥቁሮች ባለፈ ነጮቹንም ማስገንፈሉ ለጋራ ተቃውሞ አሰልፏቸዋል።
የ46 ዓመቱ ሟች ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ከሁለት ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን እናቱን ጠርቶ ገዳዩን “እባክህ መተንፈስ አልቻልኩም፤ ተነሳልኝ (I can’t breathe.)” እባክህ ጌታዬ (Sir)” ቢማፀንም፤ ጆሮ ዳባ ያለው ነጭ ምንም ዓይነት የሚራራ ሰብዓዊ አንጀት አልነበረውምና በወታደር እግሩ ክርን ጉሮሮው ላይ ቆሞ ገድሎታል፤ ግዳይ እንደ ጣለ ሁሉ ሲንጎማለል ታይቷል።
የ44 ዓመቱ ነጭ ፖሊስ በጆርጅ ፍሎይድ ጉሮሮ ላይ እጁን በኪስ አድርጎ በጉልበቱ ክርን (8 ደቂቃ ከ46 ሰኮንድ) ቆመበት፣ ሟች ትንፋሽ አጥሮት ህይወቱ እያለፈች መሆኑን የተገነዘበ፤ ነፍሱ እስክትወጣ ድረስ በዚያው ክርኑ ረግጦት መቆየቱ ለነጩ ገዳይ የጭካኔ ጥግ ማሳያ መሆኑን ምስሉን እያገላበጡ በማሳየት የሚያብራሩ ብዙዎች ናቸው።
እነዚህን ወገኖች ይበልጥ እርር፤ ድብን እያደረጋቸው ያለው ሌላው ጉዳይ የተዛባው “ሦስተኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል” ፍርድ ሲሆን፤ እንደነዚህ ወገኖች አስተያየት ገዳይ በዚህ ደረጃ ሳይሆን መሆን ያለበት “አንደኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል” ነው።
እንደ እነሱ አስተያየት የሚኒያፖሊስ የፖሊስ መኮንን የሆነው ገዳይ ተከሳሽ ዴሪክ ቾቪን 3ኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል በሚል ክስ የተመሰረተበት መሆኑ እጅግ አሳፋሪና የፈራጆቹን የለየለት የዘረኝነት አስተሳሰብ አመላካች ነው፤ ገዳይ በምንም ዓይነት የፍትህና ርትእ መመዘኛ ከ25 ዓመት እስራት የማይበልጥ ቅጣትን በሚያስከትለው የ3ኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል (Third degree murder) ፈፃሚ ተብሎ ሊፈረጅ አይገባም። ምክንያቱም “ከዚህ የበለጠ አሰቃቂ፣ የከፋና በጭካኔ የተሞላ አረመኔያዊ የግድያ ወንጀል ከወደየት ሊመጣ ነው?” ባይ ናቸው።
በምድረ አሜሪካ እንደ ሰደድ እሳት በደቂቃዎች ልዩነት እየተዛመተ ያለውን ተቃውሞ ያስነሳው የፍሎይድ አሰቃቂ ግድያና የነጭ ዕድሜ ጠገብ ዘረኝነት ጉዳይ ምንም እንኳን አዲስ ይምሰል እንጂ 400 ዓመታትን የዘለለ፤ በተለይ በዚህ ሁሉ የዘመን ሂደት ውስጥ ጭቆናውን፣ አድልዎን፣ መድልውንና የነጭ የበላይነትን ከሚዋጉት ወገኖች ጎን ላፍታም ሳትለይ እዚህ የደረሰችው ኪ(ሥ)ነ-ጥበብ ጉዳዩንና ዘረኝነቱን ዓይን ከያለበት እያገላበጠች በማሳየት ኃላፊነቷን ስትወጣ የቆየች ሲሆን፤ ይህም ፍሬ ማፍራቱ ቢታወቅም በዘመነ ምርጫ ኦባማ አለቀ፤ ደቀቀ። ሞቶም ተቀበረ። እንዳልተባለለት ሁሉ፤ ቀን እየቆጠረ የሚያገረሽበት ዘረኝነት ግን ሰንኮፉ አልተነቀለ ኖሮ በድርጊቱ፤ ጭካኔውና ስቃቄው እየጨመረ መጥቶ እዚህ ደርሷል።
ከጥንት፤ በተለይም ከ1800 ጀምሮ በነጭ የበላይነት ስትመራና ስትተራመስ የኖረችው ዓለማችን፤ የትርምሱም ሆነ የበላይነቱ ጡጫ የሚያርፈው እዚሁ የፈረደበት ጥቁር ላይ ሆኖ ምዕተ ዓመታትን ሲያስቆጥር ኖሯል። ይህን መታገል፤ ታግሎም መጣል አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የግድ ስለነበር ለጥቁር ህዝቦች ከሁሉም ቀዳሚ መታገያቸው ጥበብ ነበረች።
ይህ ከነጭ የበላይነት ሳይሆን አስቀድሞ ከነበረው የበታችነት ስሜት የተፈጠረ የጨቋኝነት ባህርይ በሂደት በአንዳንድ ጉዳዮች ቀድሞ የመገኘት አጋጣሚን ተጠቅሞ (ለዛውም እኮ በጥቁር ትከሻ) ሙዚቃ (በተለይ ጃዝ፣ ሬጌ እና ብሉዝ)፣ ሥነ-ጽሑፍ (ሥነ-ግጥም፣ አጭር/ረጅም ልቦለድ፣ ትረካው)፣ ሥነ-ቃል ወዘተ ሁሉ አስከፊውን ዘረኝነትና ቅኝ አገዛዙን ለመገርሰስ የተጫወቱት ሚና ከዚህ መለስ ሊባል የሚችል አይደለም።
ጎልተው ከወጡት (emblematic) ቦብ ማርሌይ፣ ሴዳን ሴንጎር፣ ሙጋብ፣ ፀጋዬ ገብረ መድህን፣ ቹና አቼቤ፣ ዎሌ ሶይንካ (ትራምፕ ሲመረጡ የመኖሪያ ፈቃዱን የቀደደው)፣ የአፍሪካን ከሁለት መሰንጠቅ ያተረፉት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ኮፊ አናን፣ ማንዴላ፣ ላጉማ፣ ፒተር አብረሃስ (በትውልድ ኢትዮጵያዊ)፣ ኤለን ጆንሰን፣ ዴዝሞን ቱቱ፣ ኔሬሬ፣ አንድሪያስ እሸቴ እና ሌሎች በርካቶችን ሳይጠቅሱ፤ ታሪክና ሥራዎቻቸውን ሳያገላብጡ ስለ ነጭ የበላይነት፤ የጥቁር ህዝቦች የከፋ ጭቆና፤ ጭቆናውንም ለመገርሰስ ሲደረግ የቆየውን መሪር ትግል፤ እንዲሁም ስለ አፍሪካ ጥበብ፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ባህል፣ ማንነት ወዘተ ለመፃፍም ሆነ ለመናገር፤ በተለይም በምድረ አሜሪካ ከከንፈር ያላለፈ ዴሞክራሲና የሰው ልጆች እኩልነትና አሁን እየታየ ያለውን ለመናገር የሚቸግር የቀለም ልዩነት የወለደው (የከፋና የከረፋ) የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአግባቡ ለመረዳትም ሆነ ለማሄስ ቸገር ይላል።
በተለይ በተለይ፤ የእነዚህ ሁሉ መክፈቻ ቁልፍና አንቀሳቃሽ ሞተር የሆነውን መታገያ ፍልስፍና-ማለትም “ኢትዮጵዊነት/Ethiopianism”ን (ለምሳሌ የግራሀም ኤ. ዱንቻንን “Ethiopianism in Pan-African Perspec¬tive, 1880 – 1920” ይመለከቷል።) ሳይቃኙ ወደ የትም መራመድ አይቻልምና የነጭ/ጥቁር ቀለማትን የዘረኝነት ከ–እስከ ለመረዳት ሁሉም እዚሁ ውስጥ መኖሩን ተናግረን ከመሰናበታችን በፊት “ይህ የተቀጣጠለ የጥቁር ህዝቦች ትግል ለዘመናት ስር ሰዶ የኖረውን የነጭ የበላይነት ርእዮተ ዓለም ወዴት ያደርሰው ይሆን?” የሚለውን ወደፊት የምናየው መሆኑን መግለጥ አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2012
ግርማ መንግሥቴ