ባለፈው ሳምንት ዝግጅታችን ስለስትረስ(ውጥረት) ምንነት፣ መንስኤዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ጥቂት መረጃዎችን እንዳካፈልናችሁ ይታወሳል። ዛሬም በዚሁ ዙሪያ ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል።
የበሽታው የመላመድ ሂደት / Adaptation Syn¬drome/
የስትረስ ጥናት ጀማሪ የሚባለው ዶ/ር ሀንሰ ሴሊዬ ውጥረት በማንኛውም የሰውነታችን ስርዓተ አካል እና ስነ ህይወታዊ አሠራር ስርዓት ላይ የሚታይ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ምላሽ ነው በማለት ይተረጉመዋል። እንደ ዶ/ር ሀንሰ ሴሊዬ አባባል የተለያዩ ውጥረት አምጭ (Stress¬or) መንስኤዎች ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። ለምሳሌ ለተለያዩ ውጥረት አምጪ መንስኤዎች የምንሰጣቸው ምላሾች የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡- ለዓለም ነባራዊ ሁኔታ ያለን ፍላጎት/ተነሳሽነት/ትጋት/ጉጉት መቀነስ፣ የጡንቻ መዳከም፣ የሰውነት ዝለት፣ ንጭንጭ፣ ንዴት፣ ድብርት…ወዘተ።
ይህ ጠቅላላ የመላመድ ሂደት/The General Adap¬tation Syndrome/ ፅንሰ ሃሳብ ሰውነታችን ውጥረት ሲያጋጥመው ሦስት ደረጃዎችን እንደሚያልፍ ያሳያል።
እነዚህም፡- የመነቃቂያ/ማስጠንቀቂያ ደረጃ /Alarm Stage/
i. የመቋቋሚያ/መከላከያ ደረጃ /Resistance Stage/ iii. የመዳከሚያ/ዝለት ደረጃ /Exhaustion Stage/ ናቸው።
i. የማስጠንቀቂያ ደረጃ /Alarm Stage/
በዚህ ደረጃ ሰውነታችን ጊዜያዊ ንዝረት ያጋጥመዋል። በዚህም ምክኒያት አካል በውጥረት ውስጥ በመሆኑ የደም ዝውውራችን ግፊት፣ የሰውነት ሙቀት፣ የልብ ምት ይጨምራል። በዚህ ደረጃ የውጥረት አምጪ መንስኤዎችን ምላሽ መስጠት ካልቻልን ወደ ውጥረትን የመቋቋሚያ/ መከላከያ ደረጃ ይሸጋገራል።
የመቋቋሚያ ደረጃ /Resistance Stage/
ይህ ደረጃ የውጥረት አምጭ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች (ሆርሞኖች) በከፍተኛ ሁኔታ መመረት የሚጀምሩበት ሲሆን፤ ሰውነታችንም ያለውን ሙሉ አቅም በመጠቀም ወደ ቀድሞ መደበኛ ስርዓቱ ለመመለስ ወይም ውጥረትን ለመቋቋም በሚሞክርበት ወቅት የሰውነታችን የደም ግፊት፣ የልብ ምት፣ የሰውነት ሙቀት እና የአተነፋፈስ ስርዓት ጣራ የሚነካበት ወቅት ነው። በዚህ የአፀፋ ምላሸ ምክኒያት ውጥረትን መቀነስ የሚቻልበትን ሁኔታ ሰውነት ያመቻቻል። ሆኖም ግን በዚህ ሁኔታ ሰውነት ስትረስን መቀነስ ካልቻለ ወደ መጨረሻው የመዳከሚያ/ዝለት ደረጃ ይሸጋገራል።
iii. የመዳከሚያ ወይም የዝለት ደረጃ /Exhaus¬tion Stage/
ይህ ደረጃ የሚከሰተው ለውጥረት አምጪ መንስኤዎች ለረጅም ጊዜ ወይም በተደጋጋሚ በምንጋለጥበት ወቅት ነው። በዚህም ምክኒያት ሰውነታችን ውጥረትን መቋቋም አቅቶት ይዳከማል፣ ለተለያዩ አካላዊና አዕምሯዊ ህመሞች ልንጋለጥበት የምንችልበትም አጋጣሚ የሚፈጠርበት ወቅት ነው።
በሽታና የሰውነት በሽታ መከላከያ ስርዓት /Ill¬ness and the Immune System/
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሰውነታችን ስርዓተ ነርቭ፣ የሰውነት በሽታ መከላከያ ስርዓት እና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታዎች (ህሳቤያዊ፣ ስሜታዊና ድርጊታዊ ባህሪ) መካከል ጥብቅ ግንኙነት እንዳለ ያሳያሉ። ለምሳሌ፡- ሌቪ የተባለ የስነ ልቦና ምሁር እ.ኤ.አ በ1985 ባደረገው ጥናት በካንሰር ህመም ከተጠቁ ህሙማን መካከል በጣም የሚናደዱ እና ስለበሽታው የሚያብሰለስሉ የሰውነት በሽታ መከላከያ ስርዓታቸው ተዳክሞ የታየ ሲሆን፤ በተቃራኒው ህመሙን በለዘብተኛነት የተቀበሉት እና ራሳቸውን ከህመሙ ጋር አስማምተው የሚኖሩት ደግሞ የሰውነት በሽታ መከላከያ ስርዓታቸው ጠንካራ ሆኖ ተገኝቷል።
ስትረስ በአካላዊና በአዕምሯዊ ጤና ስርዓት ላይ ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ የሆነ ጫና ሊያመጣ ይችላል። ስትረስ በጤና ላይ የሚያደርሰው ቀጥተኛ ጫና የሰውነት ስርዓታችንን በማዛባት ጤናን በቀጥታ መጉዳቱ ነው። ለምሳሌ ኮርቲሶል የተባለው የስትረስ ሆርሞን ለረጅም ጊዜ በሰውነት ውስጥ በሚበዛበት ወቅት በሽታ የመከላከል አቅምን ይቀንሳል፣ የበሽታ ተከላካይ ነጭ የደም ሴሎችን ምርት ያስተጓጉላል፣ አድሪናሊን የሚባለው ሆርሞን ደግሞ በጨጓራ ሥራ ላይ ጫና ይፈጥራል። በሂደትም የጨጓራ ግድግዳ ቁስለትን ያስከትላል። ከዚህ በተጨማሪም ስትረስ ተደጋጋሚ የሆነ ጉንፋን እና ራስ ምታት፣ ልብ እና ከልብ ጋር ተያያዥ ከሆኑ ህመሞች፣ ከስኳር ህመም እና ከአስም ጋር ግንኙነት እንዳለው የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ።
በስትረስ ምክኒያት የሚከሰተው ተዘዋዋሪ የምንለው ጫና በጤና ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያላቸውን ባህሪያት በመፍጠር ለምሳሌ፡- መጠጥ አብዝቶ መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ በአግባቡ እና በስዓቱ ምግብ አለመመገብ እና ለአካል እንቅስቃሴ ያለንን ፍላጎት በማሳጣት ጤናን ማቃወሱ ነው።
1. ስሜታዊ የውጥረት መንስዔዎች /Emotional Fac¬tors in Stress/
ስሜት ማለት ከውስጣዊ ስነ-አካል የሚነሳ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ምላሽ ነው። ለምሳሌ፡- ደስታ፣ ኀዘን፣ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ …. ወዘተ። ስሜት የሰውነትን አሠራር ስርዓት፣ ስርዓተ አካል እና ባህሪ ላይ ለውጥ ያስከትላል። በመሆኑም አሉታዊ ስሜቶች ለምሳሌ፡- ኀዘን፣ ጥላቻ፣ ንዴት፣ ጭንቀት፣ ድብርት፣ …ወዘተ ሲደጋገሙ ውጥረትን ያስከትላሉ። በዚያው መጠን ደግሞ ደስታ፣ እርካታ፣ ሀሴት፣….ወዘተ ሲደጋገሙ ደግሞ አዎንታዊ የሆኑ ስሜቶችን ሊፈጥር ይችላል።
2. ስብዕና ነክ የውጥረት መንስዔዎች /Person¬ality Factors in Stress/
ሰዎች የተለያየ ዓይነት ስብዕና እንዳላቸው ግልጽ ነው። እነዚህም ስብዕናዎች እንደልዩነታቸው ሁሉ ውጥረትን የማምጣት እና የመቋቋም ባህሪያቸው ይለያያል።
ለምሳሌ፡- ዓይነት A እና ዓይነት C የተባሉት የስብዕና ዓይነቶች ውጥረትን በማምጣት የሚታወቁ ሲሆን፤ ሌሎች የስብዕና ዓይነቶች ደግሞ ውጥረትን በመቋቋም ይታወቃሉ።
ዓይነት A ስብዕና
እንዲህ ዓይነት ስብዕና ያላቸው ሰዎች ከመጠን በላይ የመፎካከር፣ አስቸጋሪ፣ እብሪተኛ፣ ኃይለኛ፣ ትዕግስት ያጣ እንዲሁም ከመጠላላትና ከቅራኔ ጋር የተያያዘ ባህሪ ሲኖራቸው፣ ይህም ለተለያዩ አካላዊ ህመሞች እና ከልብ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በሽታዎች ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
ዓይነት C ስብዕና
እንዲህ ዓይነት ስብዕና ያላቸው ሰዎች ስሜትን ለሌላ ሰው ማካፈል ያለመቻል እንዲሁም የመረበሽና የፍርሐትን ስሜት መግለጽ ባለመቻል መናደድ፣ መሸበር እና ከልክ ያለፈ ቁጥብ የመሆን ባህሪ ሲኖራቸው ይህ ስብዕናቸውም ለተለያዩ አካላዊና አዕምሯዊ ህመሞች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2012
ወርቅነህ ከበደ እና ሲሳይ የማነ (ዶ/ር)
(ሳይኮሎጂ ት/ቤት – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)