
ባልተጠበቀ ወቅትና መጠን የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪዎች ላይ ጥቁር ጥላውና በማሳረፍ ዓለምአቀፉን ኢኮኖሚ ክፉኛ አንኮታኩቶታል። የንግድ ትስስር በመበጣጠስ ግዙፍ ኩባንያዎችን በማሽመድመድም ሚሊየኖችን ሥራ አልባ አድርጋል።
ወረርሽኙ በርካታ የንግድ ተቋማት ማዘጋቱና ዓለምአቀፍና አህጉራዊ ዝግጅቶችና የጉዞ መርሐ ግብሮች እንዲሰረዙ ማድረጉም በርካቶችን ለኪሳራ ዳርጓል። ይሕን ተከትሎም የኢንሹራንሶችን በር የሚያንኳኩ ደንበኞች ቁጥር በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በእጅጉ አሻቅባል።
በእርግጥ ዕድሜ ጠገቡ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ቀደም ባሉት ዓመታት የስፓኒሽ ፍሉና ኢቮላን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችን መታዘብ ችሏል። ማናቸውም ግን የወቅቱን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያሕል ህልውናውን እስከማሳጣት አልተፈ ታተኑትም።
የኢንዱስትሪው ተዋናዮች በመቶ ዓመት አንድ ጊዜ ሊከሰት እንደሚችል ለሚታመነው መሰል የጥፋት ወረርሽኝ ትላንት ብቁና አስፈላጊ ግብረመልስ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ መዘጋጀትና መደራጀት አለመቻላቸውም ዛሬ ላይ ሸክማቸውን አክብዶታል።
በጉዳዩ ላይ ሰፊ ትንታኔን በመስጠት ላይ የሚገኙ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃንም፣ የኮቪድ 19 የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይ ያሳረፈው ዱላ ከሃሪኬን ክትሪናም ሆነ ከሱናሚ እንዲሁም ዩናይትድ እስቴትስ ላይ ከተከሰተው የመስከረም 11 የሽብር ጥቃት ቀውስ በብዙ እጥፍ የገዘፈ ስለመሆኑ መስክረዋል። ‹‹የወረርሽኙን የቆይታ ዕድሜ ርዝመትም አጠቃላይ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን አስር ቢሊየን፣ ግማሽ ትሪሊየን አሊያም ከዚያ በላይ ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችል አመልክተዋል።
አንዳንዶች በአንፃሩ የተለያዩ ጥናቶችንና ስመጥር ካምፓኒዎችን ዋቢ በማድረግ ኢንዱስትሪው ከወዲሁ የተነጠቀውና በቀጣይ የሚነጠቀው ረብጣ ገንዘብ ምን ያሕል እንደሆነ ይፋ አድርገዋል። ሲ ኤን ቢሲ በቢዝነስ አምዱ ስመጥሩን የብሪታኒያ ኮሜርሻል ባንክ የሎይድስን ጥናት ዋቢ በማድረግ ‹‹በወረርሽኙ ምክንያት ዓለም አቀፉ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ እስከ 203 ቢሊየን ዶላር ሊነጥቅ ይችላል ሲልም›› አስነብቧል።
መቀመጫን ለንደን ያደረገው ድርጅት ወረርሽኙን ተከትሎ ለሚጎርፉ የደንበኞቹ የድረስልን ጥያቄዎችም በታሪክ ከፍተኛ የተባለለትን አራት ነጥብ ሦስት ቢሊየን ዶላር ገንዘብ ሊከፍል እንደሚችል ተጠቁማል። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚም ጆን ኒልም በዚህ ዓመት ኮቪድ 19 በተለያዩ ዘርፎች በተለይ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይ ያስከተለውን ቀውስ ተከትሎ ከተለያዩ ደንበኞች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች የሚከፈለው ክፍያ እጅጉን የገዘፈ መሆኑን መስክረዋል።
መቀመጫውን ሙኒክ ላይ ያደረገው የጀርመኑ ግዙፍ የፋይናንስ ካምፓኒ አሊያንዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኦሎቨር ቤትስ፣ ኮቪድ 19 ከአሁኑም በላይ በቀጣይ ጊዜያት የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ከባድ ኪሳራ እንደሚያጋጥመው መስክረዋል። ግለሰቡ ከብሉንበርግ ቴሊቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በርካታ ቢዝነሶች ከወረርሽኙ አንጎቨር ማግስትም ቢሆን ወደ ቀድሞ ተክለ ቁመና በቀላሉ መመለስ መቸገራቸው ይሕን እንዲሉ ምክንያት እንደሆናቸውም አስረድተዋል።
ሌላኛው በዓለምአቀፍ ደረጃ ስመጥር የኢንሹራንስ ካምፓኒ የሆነውና በዩናይትድ እስቴትስ የሚገኘው ግዙፍ ኮሜርሻል የኢንሹራንስ ድርጅት ‹‹ቹብ›› ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢቫን ግሪንበርግም፣ ቀውሱ እጅግ በከፋ መልኩ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን እንደሚያንኮታኩተው በተለይ በሁለተኛ ሩብ ዓመት ጭካኔው እንደሚያይል አመልክተዋል።
ታዋቂው የቢዝነስ ባለሙያ ስትቴቨን ብድገር በበኩሉ ኮቪድ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን በኃይል በማንገጫገጭ ለከፍተኛ ኪሣራ ሊዳርገው እንደሚችል አስረድተዋል።
ይህን እሳቤ የሚያጠናክረው ታዋቂው የኤን ኤስ ኢንሸራንስ ፀሐፊ ፓትሪክ ብሩሳናህ፣ በወረርሽኙ ምክንያት የዓለማችን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ 100 ቢሊየን ዶላር የብራንድ ዋጋ ኪሳራን ሊታቀፍ እንደሚችል አስረድቷል። ‹‹ኢንዱስትሪው ከመቶው ስመጥር ካምፓኒዎች ብቻ ሃያ በመቶ ዋጋውን ያጣል›› ብላል። የብራንድ ፋይናንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴቪድ ሃይ ኮቪድ 19 የኢንሹራንስ ዘርፉን ክፉኛ እንደሚያናጋው ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍለው አስረድተዋል።
ወረርሽኙ የኢንዱስትሪው ህልውና ላይ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ግዙፍ አደጋ ቢደቅንም፣ ድርጅቶች ከደንበኞቻቸው ጎን መቆም ምርጫቸው እንዲያደርጉና ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ እንዲሰጡ ተጠይቋል። ይህ ጥያቄ ግን እንደመናገር ቀላል ሆኖ አልታየም።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በበለፀጉት አገራት ዜጎች የሚፈልጉትን ዓይነትና የኢኮኖሚውን ደረጃ ታሳቢ ያደረጉ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች ይገኛሉ። ከጠቅላላው የኢንዱስትሪው ሽፋን የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የላቀ ድርሻ እንዳለው በግልጽ ይስተዋላል።
ይህ በሆነበት ባልተጠበቀና ባልታሰበ ጊዜ የተከሰተው የወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ከሁሉ በላይ ያለ ምንም ርህራሄ የሰዎችን ሕይወት መንጠቁ በተለይ ለህይወት ኢንሹራንስ ሽፋን አቅራቢዎች ከባድ ራስ ምታት ሆኗል።
በርካቶቹ ድርጅቶችም ምንም እንኳን ይህ ይመጣል ብለው ባይዘጋጁም በተለይ ጤናና ሕይወት ነክ ሽፋን ላላቸው ደንበኞች ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ የሕይወትም ሆነ የጤና ዕክል ወጪዎች ሽፋን እንደሚሰጡ አሳውቀዋል።
አንዳንዶቹ በአንፃሩ በቀውሱ ከፍታና ሚዛን እኩል መጠን የሚቀርቡ እጅጉን ከፍተኛና የተለዩ የድጋፍ ጥያቄዎችን በቀላሉ መመለስ የተቻላቸው አይመስልም። ከየአቅጣጫው ከተለያዩ ደንበኞቻቸው የሚቀርባላቸውን የደግፉን ጥያቄ ለመመለስ እርምጃቸውን ሲያዘገዩም ታይተዋል።
የኢንሹራንሶቹን ለድጋፍ መንቀራፈፍና ዝምታ ያስተዋሉ በርካታ የንግድ አንቀሳቃሾችና ደንበኞቻቸውም ከመገረምና ከመደናገጥ ባሻገር ስጋት ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል። አንዳንዶቹም ‹‹በመሰል ወቅት የደህንነት ዋስትና መከታ ሆኖ እስካላገለገለና ፈጣን የአጋርነት ምላሽ መስጠት እስካልቻለ የኢንሹራንስ ፋይዳ ምንድ ነው?›› የሚል የተጠያቂነትና የተእማኒነት ጥያቄን ማንሳት ጀምረዋል።
የዚህ ትችት ተፃራሪ አስተያየት ሰጪዎችም ሆኑ ድርጅቶች በሌላ በኩል፣ ደንበኞች ቀደም ሲል የገዙት የጤናና የሕይወት መድን ፖሊሲ በእንደዚህ ዓይነት ከባድ ወረርሽኞች ምክንያት ለሚከሰቱ አደጋዎች ሽፋን እንዲሰጡ እንደማያስገድዳቸው እየሞገቱ ነው። በርካቶቹም ‹‹ኮቪድ-19ን በመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ምክንያት ለሚከሰቱ ጉዳቶች ሽፋን ለማግኘት ተጨማሪ ውል መግዛት ግድ ይላል›› የሚል ሙግት ገጥመዋል።
አንዳንድ ኢንሹራንስ ድርጅቶችም ከወዲሁ በቂ ሠራተኞች እንደሌላቸው በማሳወቅ በጊዜ ስጡን ሰበብ አስባብ ለደንበኞቻቸው ጀርባቸውን ለመስጠት እየዳዱ ስለመሆኑ ተጠቁማል። የምጣኔ ሀብት ምሁራን በሌላ በኩል በአሁን ወቅት ከኢንሹራንስ ፖሊሲ ውጪ መራመድና ከድጎማ መሸሽ ለድርጅቶቹ የሚያዋጣ መንገድ እንዳልሆነ ማስመዝገብን ምርጫቸው አድርገዋል። ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት የሚያመራ ከሆነም ድርጅቶቹ ለከፋ ቀውስ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።
ከግብግቡ ባሻገር የኮሮና ወረርሽኝ ክስተት ሰዎች ስለ ኢንሹራንስ አገልግሎት ሽፋን በቂ እውቀት እንደሌላቸው ማሳየቱን የሚጠቁሙና ስለ ኢንዱስትሪው አጠቃላይ ተግባር የሚያስረዱ ባለሙያዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳ ሁኔታዎች መኖራቸውን ችግሩ አደባባይ ይዞ ወጥቷል። ይህ የግንዛቤ ክፍተትም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የኢንሹራንስ ሰጪ ድርጅቶቹ ውስብስብና ግልጸኝነት ችግር የወለደው ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል።
ጉዳዩን በተለየ መንፅር የተመለከቱ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን በሌላ በኩል፣ ክስተቱ ኢንሹራስ ድርጅቶች ከፍተኛ መጠን ያለው የደንበኞች ጥያቄና መብት በሚመጣበት ወቅት በአሠራርም በተለይም በቴክኖሎጂ ረገድ ብቁ እንዳልሆኑ ቁልጭ አድርጎ ማሳየቱን አብራርተዋል።
‹‹በቴክኖሎጂ ረገድ እርስ በእርስ በልጦ ለመታየት እሽቅድድም ከማድረግ ባለፈ በመሰል ቀውስ ወቅት ለሚቀርቡ የደንበኞቻቸው ጥያቄዎች ዘመናዊና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ረገድ ከጥንካሬ ይልቅ ድክመታቸው ቀድሞና ጎልቶ ይታያልም›› ብለዋል።
ወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተለይ በበለፀጉት አገራት የኢንሸራንስ ኢንዱስትሪ ላይ መሰል ቀውስና ውዝግብ ማስከተሉን ከመዳሰስ ባሻገር ወላፈኑ በማደግ ላይ በሚገኙና በደሃ አገራት ላይ ያስከተለውን ጠባሳ የሚዳስሱ መገናኛ ብዙሃንና ምሁራንም አልታጡም። ‹‹በአፍሪካ ምድር ዜጎች የሚፈልጉት ዓይነትና የኢኮኖሚውን ደረጃ የሚመጥኑ የኢንሹራንስ ፖሊሲዎች አለመኖራቸውም የቀውሱ ጉዳት የጎላ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል›› ተብሏል።
በበለፀጉት አገራት የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ከጠቅላላው የኢንሹራንስ ሽፋን ውስጥ የላቀ ድርሻ ቢኖረውም፣ በአህጉራችን አፍሪካ ግን እጅግ የበዛውን ድርሻ የሚይዘው ሕይወት ነክ ያልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ስለመሆኑ አስረድተዋል። ‹‹ኩባንያዎቹ የሚሰጡት የመድን ሽፋን መጠን የተወሰነ መሆኑ ብቻም ሳይሆን፣ ከ70 በመቶ በላይ በተሽከርካሪ ኢንሹራስ ላይ የተንጠላጠለ ሆኖ መዝለቁም ከወቅቱ ቀውስ ሊታደጋቸው ይችላል›› ብለዋል።
ይህ ማለት ግን ወረርሽኙ በአፍሪካ ምድር በርካታ የንግድ ተቋማት አላዘጋም፣ ዓለምአቀፍና አህጉራዊ ዝግጅቶችና የጉዞ መርሃ ግብሮች እንዲሰረዙ አላደረገም፣ በርካቶችንም ለኪሳራ አልዳረገም ይህን ተከትሎም የኢንሹራንሶችን በር የሚያኳኩ ደንበኞች ቁጥር አልታየም ማለት አይደለም።
ምንም እንኳን ቁጥራቸው በርካታም ባይሆን አንዳንድ ድርጅቶች ጤናና ሕይወት ነክ ሽፋን ላላቸው ደንበኞቹ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ የሕይወትም ሆነ የጤና ዕክል ወጪዎች የመድን ሽፋን እንደሚሰጡ አሳውቀዋል።
ወቅታዊውን ቀውስ ከመመልከት ይልቅ በቀጣይ ምን ይደረግ የሚለውም በመገናኛ ብዙሃኑም በምጣኔ ሀብት ምሁራኑም በስፋት ተዳሷል። የኢንሹራንስ ድርጅቶች ከወትሮው በተለየ ይበልጥ ኃላፊነት መውሰድና የሽፋን አገልግሎታቸውንም ቢሆን ግልፅ ማድረግ እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።
‹‹በቀጣይ መሰል ዓለምአቀፍ ወረርሽኞች ቢከሰቱ አገልግሎታችን ምን ይሸፍናል አሊያም አይሸፍንም ከሚለው ጀምሮ ቀደም ሲል ይራመዱበት የነበረውን የቢዝነስ አሠራርና የአደጋ ግብረ መለስ አቅጣጫ መቃኘት አለባቸውም›› ተብሏል።
አፍሪካ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ፣ አቅማቸው እንዲያፈረጥምና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተፈለገም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው መሥራት እንደሚገባቸው ተመላክቷል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2012
ታምራት ተስፋዬ