ያለንበት ወቅት ኮሮና በተባለ ክፉ ወረርሺኝ ዓለማችን ቁምስቅሏን እያየችበት ያለ እና በስልጣኔ እና በኢኮኖሚ ዕድገት እጅግ መጥቀዋል የተባሉ ሃያላን አገራት እንኳን ሳይቀሩ ከችግሩ ለመውጣት እጅጉን የተፈተኑበት ነው። መነሻውን የቻይናዋን ሁዋን ያደረገው ይህ ወረርሺኝ ዕለት ዕለት የስርጭት አድማሱን እያሰፋ፣ የብዙዎችን ነፍስ እየነጠቀ፣ ሰዎችን ከእንቅስቃሴ እየገደበና ኢኮኖሚውን ክፉኛ እያሽመደመደ ይገኛል።
ወረርሺኙ ቀደም ብሎ ኤስያ፣ አውሮፓና አሜሪካን እጅግ አጥቅቶ አሁን ላይ ወደ አፍሪካ ፊቱን ያዞረ ይመስላል። ከሰሞኑ እየወጡ ያሉ መረጃዎች የሚያሳዩትም ይህነንኑ ነው፣ በወረርሺኙ መጀመሪያ ወቅት እጅግም ችግሩ ባልከፋባት አፍሪካ አሁን ላይ ከዕለት ዕለት በቫይረሱ ተጠቂዎችም ሆነ በዚሁ ጦስ የሚሞቱ ሰዎች ብዛት እየጨመረ መምጣት እየታየ ነው። በአፍሪካ ያለው የኢኮኖሚ ደካማነትና የዜጎች አኗኗር ዘዴ ከቫይረሱ የመስፋፋት ባህሪ ጋር ሲዛመድ የጥንቃቄ እርምጃዎች በጥብቅ ዲስፕሊን ተተግብረው ወረርሺኙ በቁጥጥር ስር ካልዋለ የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ይገመታል።
በአገራችን ኢትዮጵያም ወረርሺኙ ከተከሰተ ሶስት ወር እየተጠጋ ሲሆን በመጀመሪያ ሰሞን የነበረው ዝቅተኛ የመያዝ እና የሞት መጠን በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ትልቅ ስጋት ደቅኗል። በተለይም ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ በ300 % እያደገ መሄዱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ከችግሩ መከሰት አንስቶ መንግስትና የጤና ባለሙያዎች እንዲወስዱ የመከሯቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች በአግባቡ መተግበር ቢቻል ኖሮ አሁን የተፈጠረውን ሁኔታ መለወጥ ይቻል የነበረ ቢሆንም ያ ዕድል ያመለጠ ይመስላል። በህዝብ ዘንድ ይታይ የነበረው ቸልተኝነት እንዲስተካከል መገናኛ ብዙሃን ቢወተውቱምና የመንግሰት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የሃይማኖት አባቶች ቢማጸኑም ሰሚ ጆሮ ባለመገኘቱ ሰሞኑን ለምንሰማው አስደንጋጭ ዜና ዳርጎናል።
የኮሮና ቫይረስ በጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በላይ በኢኮኖሚው ላይ የደቀነው አደጋ እጅጉን የከፋ ነው። እንደሚታወቀው የኮሮና ወረርሺኝ የሰዎችን እንቅስቃሴ በመገደብ፣ ሥራ አጥነትን በማስፋፋትና ምርትና ምርታማነትን እንዲወድቅ በማድረግ የሰው ልጆችን ህይወት ክፉኛ በመፈታተን ላይ ነው። ይህ ደግሞ የአቅርቦት እጥረት በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲከሰትና የዜጎች የመግዛት አቅም እንዲዳከም ያደርጋል። ከላይ እንደተገለጸው ብዙ ሰዎች በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ሥራ ባጡበትና ገቢያቸው እንዲቀንስ በሆነበት ሁኔታ የዋጋ ንረት መከሰቱ ደግሞ የመኖር ህልውናን በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ላይ ይጥላል።
የኮሮና ወረርሺኝ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን አስከፊ ጉዳት በተመለከተ ለቢቢሲ ሃሳባቸውን ያጋሩት ታዋቂው ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ሮቢኒ “ይህ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ውሎ በዓመት ውስጥ ምጣኔ ሀብቱ ማንሰራራት ቢጀምርም ነቀርሳው ግን ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ይቆያል። እንዲያውም አንዳንድ የሥራ ዘርፎች ጨርሶውኑ ላያንሰራሩ ይችላሉ። ወረርሽኙ ከ2008ቱ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ጋር ሲወዳደርም ሆነ በ1930ዎቹ ከተከሰተው የዓለም ክፉው የምጣኔ ሀብት ድቀት ጋር ሲተያይ የአሁኑ የከፋ ነው። ያን ጊዜ ምርት በዓለም ላይ እንዲቀንስ ወይም የቀውሱን ምልክቶች በተግባር ለማየት ከችግሩ በኋላ ዓመታትን ወስዶ ነበር። ኮሮና ቫይረስ ግን ከእነዚህ ሁለቱ ቀውሶችም በላይ ነው። ያስከተለውን የምርት ማሽቆልቆልን በግላጭ ለማየት ዓመታት ወይም ወራት አልወሰደበትም። በሳምንታት ውስጥ በመላው ዓለም ምርት ተንኮታኩቷል። ይህ የሚነግረን መጪው ዘመን ፍጹም ጭጋጋማ መሆኑን ነው። በዚያ ዘመን 3 ዓመት የወሰደው የምርት መንኮታኮት በዚህ ዘመን 3 ሳምንት ነው የወሰደበት።” ሲሉ ገልጸውታል።
በአገራችንም የኮሮና ወረርሺኝ የሚያሰከትለውን የኢኮኖሚ ችግር ቀደም ብሎ በማሰብ ለመፍትሄው ብዙ መሰራቱ ብዙ ሰዎች ከስራ እንዳይፈናቀሉ አድርጓል። ይህም ዜጎች የመኖር ህልውና ፈተና ሳይገጥመው እንዲቀጥል የራሱን አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል። ከዚህም ጎን ለጎን ችግሩን እንደምቹ ሜዳ በመጠቀም የኑሮ ወድነትን በሚያባብሱ ኃይሎች ገበያው እንዳይናጋ የቁጥጥር እና ህግ የማስከበር ሥራዎች በመሰራታቸውም የከፋ ችግር እንዳይደርስ ለማድረግ ተችሏል።
ይሁንና ከሰሞኑ በዘይት፣ በፍራፍሬና አትክልት ዋጋዎች ላይ የዋጋ ጭማሪዎች በስፋት ተስተውለዋል። ጉዳዩን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተሰጡ መረጃዎች ለዚህ ችግር ምክንያቱ አንድም በአቅርቦት ላይ ያለ ችግር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሀገወጥ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል። ስለሆነም መንግስት ችግሩን በተረዳበት አግባብ የአቅርቦት ችግሩን አቅሙ በፈቀደ መጠን በማስተካከልና ከዚህ ለጎን ለጎንም ዋጋ በማናር ህገወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላትን አደብ በማስገዛት የገበያውን ሰላማዊነት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2012