አንዳንድ ጊዜ ሳስበው መላው የሰው ልጅ ታሪክ የፍርሐት ታሪክ ይመስለኛል።ምክንያቱም ሰው በኖረባቸው ዘመናት ሁሉ ራሱን ሲፈራ ኖሯል።ማለትም “ከራሴ ወገን ጥቃት ሊሰነዘርብኝና ልጠፋም እችላለሁ” በሚል የራስ ፍርሐት ከመሰሉ ሊሰነዘርበት የሚችለውን ጥቃት ለመመከትና ከሚያስበው ጥፋት ለመዳን ካልቻለ ከ“ጠላቱ” ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ከቻለ ደግሞ የበላይ ለመሆን የሚያስችለውን ኃይል ይዞ ለመገኘት ነው ዘመኑን ሙሉ ሲለፋ የኖረው።
የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር ዋነኛው ዓላማው አድርጎ ሲሠራበት የኖረው ቢያንስ ራሱን ማዳን አለያም መሰሉን በኃይል አንበርክኮ በአቻው ላይ የበላይነትን ማግኘትን ይመስላል።ለዚህም ይረዳው ዘንድ በየጊዜው አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን በመፈልሰፍና በመጠቀም አብዛኛውን የታሪኩን ክፍል ከመሰሉ ጋር በእኔ እበልጥ፤ እኔ እበልጥ የእርስ በእርስ ሽኩቻና በጦርነት ያሳለፈ ሲሆን፤ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ጀምሮ ባለፉት ስድሳ አምስት ዓመታት ደግሞ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ ለመሆን የሚያስችለውን ኃይል ለመቀዳጀት እንቅልፍ አልባ ሆኖ ሲሠራ አሁን ላይ ደርሷል።
እናም ትኩረቱን ሁሉ ይህንን የበላይነት ኃይል ለመቀዳጀት ያስችለኛል ያለውን የመጨረሻውን ኃይለኛውን የጦር መሳሪያ ማለትም የኑክሊየር አረር ማምረትና ማከማቸት ላይ አድርጎ ቆይቷል።እንደ እነ አሜሪካና ሩስያ የመሳሰሉ አገራትም ያላቸውን ሀብትና ዕውቀት ሁሉ አፍስሰው ጥረታቸው ተሳክቶ ቀድመው የዚህ አውዳሚ የጦር መሳሪያ የኑክሊየር ኃይል ባለቤት በመሆናቸው እነሆ በ“ኃያላንነት” ዓለምን በበላይነት እየመሩ ይገኛሉ።ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ብሪታንያ፣ እሥራኤል፣ ህንድና ፓኪስታንም በብዙ ጥረት መሳሪያውን በመታጠቅ የ“ኃያላኑን” ጎዳና ተከትለዋል።እንደ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ የመሳሰሉት አገራት ደግሞ መሳሪያን ለመታጠቅ ለዓመታት ወገባቸውን አስረው ባለ በሌለ አቅማቸው እየደከሙ ቢሆንም ቀድመው ባየሉት የእነ አሜሪካ የ“እንጠፋለን” ፍርሐት ምክንያት በሚፈጠር ሳንካ እስከአሁን አልተሳካላቸውም።ኒዩክሊየሩን ማምረታቸው የማይቀር ከሆነም ለሠላማዊ የኃይል ምንጭነት እንዲያውሉት ከኃያላኑ አንዴ ማባበያ ሌላ ጊዜ ማስፈራሪያ እየቀረበላቸው ጊዜው ደርሶ እነርሱም በእሳት ወንጭፋቸው እስኪፈሩ ድረስ ኑክሊየራቸውን በጣቢያቸው፤ ቂማቸውን በልባቸው እያብላሉ በከፍተኛ ትኩረት አሁንም ጥረታቸውን አጠንክረው ቀጥለዋል።
ዳሩ ምን ያደርጋል ይህ ሁሉ ትኩረትና ጥረት ሰውን ከሰው ጥቃትና ጥፋት ለመጠበቅ የተደረገ ሆነ እንጅ! ታላቅ ሲባል አንሶ፣ ክቡር ሲባል ወርዶ፣ መአምር ሲባል መሃይም ሆኖ የተገኘው ክፉውና ስግብግቡ የሰው ልጅ ላለመበለጥና ለመብለጥ፣ ከሆነለትም አሸናፊና የበላይ ሆኖ ለመገኘት ከእርሱ ውጪ ያሉ ሌሎች የህልውና ስጋቶችንና የሕይወት ጠላቶችን ሁሉ ትቶ፣ በራስ ፍርሐት ተሸብቦ፣ ከራሱ ጥቃት ለማምለጥ ዘመኑን ሁሉ ራሱን መከላከያና ማጥቂያ መሳሪያ ፍለጋ ላይ ተቸንክሮ ባዝኖ ቀረ እንጅ! ምናለ የሰው ልጅ ከፍጡር ሁሉ በልጦ የተሰጠውን ይህን ሁሉ ዕውቀቱንና ኃይሉን ሁሉ ከፈጣሪው ጥበቃ በታች ከራሱ ሳይሆን ከሌሎች ፀረ ሰውና ፀረ ህይወት ፍጡራን ሊደርስበት የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል ተጠቀምቦት ቢሆን ኖሮ?
ግና አልሆነም።ገና ሲፈጠር፣ ከቃየልና አቤል ዘመን ጀምሮ በ“ይበልጠኛል ፍርሐት” ሰው በቅናት ወንድሙን ሲገድል፣ እርስ በእርሱ በጠላትነት ተፈራርጆ ሲጠፋፋ፣ ሲፈራ፣ ከራሱ ሲሸሽ ነው የኖረው።ምክንያቱ ደግሞ የሰው ልጅ ራስ ወዳድና ስግብግብ በመሆኑ፤ ጠላትና ስጋት አድርጎ የሚቆጥረው በብቸኝነት ማድረግና ማግኘት የሚፈልገውን ሁሉ “ያጓድልብኛል” ብሎ የሚያስበውን የስንፍናውና የባህርይው ተጋሪ የሆነውን የራሱን ፍጥረት ነው።ከሌላው ይልቅ መሰሉን ነው ያጠቃኛል ብሎ የሚፈራው።የስግብግብነትና የአልጠግብ ባይነት ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰደው ጅብ እንኳን ከመሰሎቹ በልጦ ለመገኘት ሲል እርስ በእርሱ አይጠፋፋም፤ ፉክክሩ ከሌሎች ሥጋ በል እንስሳት ጋር እንጅ ከጅቦች ጋር አይደለም፤ ተሰባስቦ በሕብረት ያጠቃል እንጅ ተከፋፍሎና ተቧድኖ እርስ በእርስ አይጠቃቃም።ያጠቃኛል ብሎ በስጋትነትና በጠላትነት ቆጥሮ የሚጠነቀቀውም ከአንበሳ እንጅ ከራሱ ፍጥረት ከጅብ አይደለም፡፡
የሰው ልጅ ግን ሁሉንም ፍጥረታት ይገለገልባቸውና ይገዛቸው ዘንድ ከፈጣሪው ስልጣን ተሰጥቶት ሳለ ሁሉን መግዛት አልበቃ ብሎት አንዱ አንዱን ለማሸነፍና ወንድም ወንድሙን በበላይነት ለመግዛት ሌላውን የውጭ ጠላቱን ትቶ እርስ በእርሱ በጠላትነት እየተያየ፣ ከራሱ ጥቃት ለማምለጥ ዘመኑን ሙሉ በስጋት የሚኖር ብቸኛ ፍጡር ሳይሆን አይቀርም! አዲዮስ ሰው ታላቁ ፍጡር።
እናማ ሰው ሆይ ራስህን ጠላት አድርገህ ከራስህ ዝርያ የሚደርስብህን ጥቃትና ጥፋት ለመመከት መከላከያና ማጥቂያ መሳሪያ ለመፍጠር ዘመንህን ሁሉ ስትደክም ስትኖር ሌላ የሚያጠቃ ጠላት መጣብህ።ከሰው ዘር የሚሰነዘርብህን ጥቃትና ጥፋት ለመመከትና በወገንህ መካከል የበላይ ለመሆንስ ዘመንህን ሁሉ ለፍተህ አሸናፊ የሚያደርግህን የመጨረሻውን ኃይለኛውን መሳሪያ ታጠቅክ፤ እንደ ቫይረስና ባክቴሪያ ዓይነት ከአንተ ውጪ የሆነ ኃያል ተዋጊ ጠላት የሚያደርስብህን ጥቃት ለመመከትስ ምን አደረክ? ጠላትህ ሞት ከማድረሱ በፊት ጥፋቱን አስቀድሞ ለመከላከል የምትችልበት መሳሪያስ ታጥቀሃልን?
በጦርነት ወይንም በተራ ጸብ ወገንህን ሰው ገድሎብህ ቢሆን ኑሮ በብዙ ሺህ እጥፍ ጠላቶቹን በመግደል ደሙን የምትበቀልለትን ወገንህን በገፍ ሲገድልብህስ ጠላትህ ላይ ምን ዓይነት የአጸፋ ዕርምጃ ወሰድክ? ምናልባትም በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለውብኛል በሚል በእንደነ “ታላቋ አሜሪካ” ዓይነት “ኃያላን” ሃገራት የተወሰደውን ሃገርን እስከ ማፈራረስ የደረሰ ዕርምጃ ያየን እንደሆነ “ከሰው ለሰው ጥቃቶች” ውጪ በሆኑ እንደነ ኮቪድ-19 በመሳሰሉ ሰው ልጅ ጠላቶች ላይ የሚወሰደው የመከላከልና የማጥቃት ዕርምጃ የከፋ ነው ማለት አይቻልም።ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቶቹን የሰው ልጅ ጠላቶች ለመከላከልና የሚያደርሱትን ጥፋት ለመመከት በጥቅሉ የሰው ልጅ እንደ ሰው ልጅ፣ ዓለም እንደ ዓለም፣ አሜሪካም እንደ አሜሪካ ያደረጉት ጥረት ያን ያህል አልነበረምና ነው።
እናስ? እናማ የሰው ልጅ እንደ ሰው ልጅ ብዙዎቻችን ትኩረት ማድረግና መሥራት በሚገባን ጉዳዮች ላይ ሳይሆን ብዙውን ዘመናችንን ያሳለፍነው የሚያሳስበውን ትተን በማያስጨንቀው እየተጨነቅን ነው ቢባል የራሳችንን እውነታ በሚገባ ተገንዝበናል ለማለት የሚያስችል ሚዛናዊ ግለ ሂስ ይሆንልናል።እስኪ አንዳንዶቹን ወቅታዊ እውነታዎች እያነሳን ራሳችንን እንመልከትባቸው።መላ ዓለም ኮቪድ-19 በሚባል ክፉ ወረርሽኝ እየተጨነቀች ባለችበት በዚህ ሰዓት እንኳን ከሃገራችን ጀምሮ በየክፍለ ዓለሙ ብንዟዟር አሁን ላይ የሰው ልጅ ከገባበት አሳሳቢ የህልውና ስጋት አኳያ ቅድሚያ ሊሰጣቸውና በፍጹም ሊያስጨንቁ የማይገባቸው ጉዳዮች አሳሳቢ ሆነው ብዙዎች ሲጨነቁባቸው ይስተዋላል።
ለምሳሌ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወረርሽኙ በአፍሪካ ሃገራት የገባው ከሌላው ዓለም ዘግይቶ በመሆኑ የስርጭት መጠኑንና አድማሱን ለማወቅ ባልተቻለበትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣበት አስጨናቂ ሰዓት በእኛ አቆጣጠር ከጥር 2012 መጨረሻ አንስቶ መላ ዓለምን እያስጨነቀ ካለው የኮሮና ወረርሽኝ በላይ የምርጫ 2012 ጉዳይ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።መምረጥና መመረጥ፣ ስልጣንና መንገሥት፣ ምርጫና ህገ መንግሥት ሊኖር የሚችለው ከሁሉም በፊት ሕዝብ ሲኖር መሆኑ እየታወቀ የሕዝብን ህልውና አደጋ ውስጥ ሊጥል በሚችል አኳኋን የግዴታ ምርጫው ካልተደረገ በሚሉ ወገኖች ከጭንቀቷ በላይ በማያስጨንቀው ነገር ሃገር ስትጨነቅ ሰንብታለች።“ምርጫ ካልተደረገ ሃገር ትፈርሳለች” ከሚለው ግርግር ባሻገር ከሰሞኑ በሃገራችን ከተፈጠሩ የማያስጨንቁ ጭንቀቶች መካከል የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ሰፋ ያለውን አየር ይዞ እዚህና እዚያ እየነፈሰ በክረምቱ ምድር አቧራ ለማስነሳት ሲሞክር ተስተውሏል፡፡
ወረርሽኙ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ ታስቦ ሕዝብና መንግሥት ተስማምቶበት በሃገሪቱ ውስጥ የተጣለውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የሕዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ ህይወታቸውን ሳይቀር አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል ተጋላጭ ሁኔታ ውስጥ ሆነው አዋጁን ለማስፈጸም መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚገኙ የፀጥታና የህግ አስከባሪ አካላት ላይ አዎንታዊም አሉታዊም ድምፆች ጎላ ብለው ተሰምተዋል።
የተቃውሞ ድምፆቹ ለወረርሽኙ መስፋፋት መንስኤ በሆኑ ድርጊቶችና ፈጻሚዎች ላይ በአዋጁ አስፈጻሚና በህግ አስከባሪ አካላት የሚወሰዱ ህጋዊ ዕርምጃዎችን ‹‹ከማረም ይልቅ ቅጣት ላይ የሚያተኩሩና የአንዳንድ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጥሱ ሊሆኑ ይችላሉ” ከሚል አላስፈላጊ ጭንቀት የመነጩ ይመስላሉ።ምክንያቱም ከቅጣቱ ይልቅ በሽታው በሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ መሆኑንና ይበልጥ አስጨናቂው ጉዳይ የወረርሽኙ መስፋፋት መሆኑን ግምት ውስጥ አላስገቡምና።ደግሞም እንኳንስ መተኪያ የሌለውን ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወትን ለማዳን ታስቦ የወጣን ህግ በሚጥሱ የህልውና ስጋቶች ላይ ይቅርና ቢጠፋም ነገ ተመልሶ የሚገኝ ንብረትን በሚሰርቁና “ያልሠራ አይብላ” የሚለውን ድህረ ሰዋዊ ትዕዛዝን በሚተላለፉ ደረቅ ወንጀለኞች ላይም እኮ የእርምት ዕርምጃ ይወሰዳል፣ በጥፋታቸው ልክ ይቀጣሉ።
የራሷ አስጨናቂዎች ያነሱባት ይመስል የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ “ተምሳሌት” በሆኑት እዚያው በተወለደበት በምዕራባውያኑ ሰፈር በጠራራ ፀሐይ ያውም የህግ አስከባሪ አካላት አንገቱን እየተረገጠ የሰው ያለህ እያለ የሚያስጥለው አጥቶ በአደባባይ በግፍ በሚገደልበት ወቅት የሰብዓዊ መብት “ተሟጋቹ” አምነስቲ ኢንተርናሽናልም እንደዚሁ በኢትዮጵያ በማያስጨንቀው እየተጨነቀ አላስፈላጊውን ጭንቀት ለማባባስ ሞክሯል።ይህም የበርካቶችን ህይወት ለማዳን ሲባል ህግን ለማስከበር የሚወሰዱ ዕርምጃዎችን በሰብዓዊ መብት ጥሰትነት በመፈረጅ የሃገርና የሕዝብን ደህንነትና ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረገውን ሂደት የሚያደናቅፍ ቢሆንም ሊታረም የሚገባው በመሆኑ በመንግሥት አካላት ምላሽ ተሰጥቶበታል።
የድርጅቱ መግለጫ ከዚህ ቀደምም ሲደጋገም የቆየ ቢሆንም የአሁኑ ግን በዓለም ላይና በሃገሪቱ ውስጥ ካለው አሳሳቢ የወረርሽኝ የደህንነት ስጋት አኳያ ወቅቱን ያላገናዘበና ሕዝቡ በሽታውን መከላከል ትቶ ትኩረቱን ሌላ አጀንዳ ላይ እንዲያውል የሚገፋፋ በመሆኑ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ “በማያስጨንቀው የሚጨነቅ” ያሰኘዋል፡፡
ከሃገር ቤት ጉዳዮች ወጣ ብለን እዚሁ በአህጉራችን አፍሪካ ያለውን ሁኔታ ስንመለከትም ድንበር የማንጋራት ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ብሩንዲ በአሁኑ ሰዓት የመላ የሰው ልጆች ስጋት የሆነው የኮሮና ወረርሽኝ በእርሷ ግዛት ውስጥም በመኖሩ ከሕዝቧ ደህንነት ይልቅ በማያስጨንቀው የምርጫ ጉዳይ አብዝታ ስትጨነቅ ተስተውላለች።ታዲያ ከእኛም ሆነ ከሌላው ዓለም የብሩንዲውን ለየት የሚያደርገው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ወረርሽኙን የመከላከልና በሕይወት ላይ ሊደርስ የሚችልን ጥፋት የመቀነስ ጉዳይን ችላ ብላ ሙሉ ትኩረቷን በማያስጨንቀው ላይ አድርጋ ስትባክን መታየቷ ብቻ አይደለም።
በዓለም ላይ ከአርባ ስምንት በላይ የሚሆኑ አገራት ለዜጎቻቸው ህይወት ቅድሚያ በመስጠትና ለሕዝባቸው ደህንነት በማሰብ ሊያደርጉት የነበረውን ምርጫ ባራዘሙበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት “ምርጫ ወይም ሞት” በሚለው አቋሟ እስከመጨረሻው ፀንታ አንድ ቀን ሳታዛንፍ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዋን “በወቅቱ” ማካሄዷ ነው ብሩንዲን ለየት የሚያደርጋት።ለዴሞክራሲ ተገዥነት እንዳይባል ሁለት ዙር ረግጦ ገዝቶ ለሦስተኛ ጊዜ ስልጣን ለመያዝ ፕሬዚዳንቱ የምርጫ ህጉን በሚያሻሽልባት በሃገረ ቡሩንዲ ብዙሃኑ የዓለም ሕዝብ ቤቱን ዘግቶ በተቀመጠበት በዚህ አደገኛ ወቅት ህይወትን አስይዞ ከሞት እየተጋፉ ምርጫ ማካሄድ ምን የሚሉት ነው?
ከአህጉረ አፍሪካ ተሻግረን ወደ ደቡብ አሜሪካ ስናማትር ከብሩንዲውም የከፋ የሰው ልጅን ቂልነት እንታዘባለን።ሦስት መቶ ሚሊዮን ሕዝብን የማስተዳደር ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በታላቁ የመሪነት ቦታ ተቀምጠው በቀጠናው ከፍተኛ ተሰሚነት ያላትንና የክፍለ አህጉሩ ተጠሪ የሆነችውን ትልቅ ሃገር ብራዚልን እየመሩ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ቦልሶራኖ አሳሳቢውን ጉዳይ የማያስቡ ከመሆናቸውም ባለፈ ሌሎችንም እንዳያስቡ የሚያበረታቱ ሰው ሆነው መገኘታቸው ዓለምን ጉድ እያስባለ የሚገኝ የሰውነት እንቆቅልሽ ሆኗል።
ፕሬዚዳንቱ በሃገረ ብራዚል የሺዎችን ህይወት እየቀጠፈ፣ ኢኮኖሚውን እያሽመደመደ የአያሌ ዜጎችን ኑሮ እያመሰቃቀለ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጥቃት ለመመከት ተገቢውን የመከላከያና የጥንቃቄ ዕርምጃ በመውሰድና በማስወሰድ ፋንታ በአላዋቂ አድናቂዎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ታጅበው በዋና ከተማዋ ብራዚሊያ ህዝብ በተሰበሰበባቸው ጎዳናዎች ላይ እያሳሉ በነፍሳቸው እያፌዙ ከግብዝ መሰሎቻቸው ጋር ሲስቁና ሲሳለቁ በአደባባይ ታይተዋል።
እንደ Just Security ድረ ገጽ ዘገባ ፕሬዚዳንት ቦልሶራኖ ይህንን የሚያደርጉትም ከኮሮና በፊትም ቀውስ ውስጥ ገብቶ የነበረ በመሆኑ በሃገሪቱ በተንሰራፋው ድህነትና ሥራ አጥነት ምክንያት ብራዚልን በተደጋጋሚ ሲንጣት ከቆየው የዜጎች ተቃውሞና አመጽ እርሳቸውንና መንበራቸውንም እንዳይነቀንቅ የሕዝብ ብሶትንና ደካማ ጎንን ተጠቅሞ ወንበርን ማደላደልን ታሳቢ ያደረገ ፖለቲካዊ ስሌት ነው።ይኸውም ኢኮኖሚው ላይ ትኩረት ያደረጉ በማስመሰልና በሃገሪቱ ውስጥ በተንሰራፋው አስከፊ የድህነት ኑሮ የተማረሩና የዘወትር ህልማቸው ከዚህ ችግር መውጣት የሆኑ የብዙሃኑን ብራዚላውያን ልብ በማሸነፍ ለራሳቸው ፖለቲካዊ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ነው።
ታዲያ ሕዝብን መምራትን የሚያክል እንደ እግዚአብሔር ዙፋን የሚከብደውን ታላቅ ኃላፊነት የተሸከመ ሰው ለስልጣንና ለግል ፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል አምኖ ስልጣን ላይ ባወጣ ሕዝብ ህልውና ላይ አደጋን መጋበዝ ከማንም ተራ ሰው እንኳን የማይጠበቅ ተግባር ሲፈጽም ምን ይባላል? ድርጊቱ የሰው ልጅ ስንፍና ክብደት የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው።የከንቱነት ጥግ መገለጫ የአልቦነት ተምሳሌት ይሉሃል እንደ ቦርሶራኖ ዓይነቶቹ ሰዎች ናቸው።የሰው ልጅ ምን ያህል ከራሱ ጋር የተጣላ ለእግዜር የማይመች መሆኑን ለመገንዘብስ ከዚህ የበለጠ ማሳያ ከወዴት ይገኛል?
አሜሪካና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለማችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ኃይሏን እያሳረፈች የመጣችው ቻይና ክንዳቸውን አስተባብረው የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ጠላት በሆነው አሳሳቢው ቫይረስ ላይ መዝመት ሲገባቸው አሁንም እርስ በእርስ ለመጠቃቃት ሲያኮበኩቡ ይስተዋላሉ።ዛሬም የሚያስጨንቃቸው የሰው ልጆችን የጋራ ጠላት እንዴት እንከላከለውና ከዓለማያችን ላይ እናስወግደው የሚለው ሳይሆን ከጥፋቱ ባሻገር ያለው የማያስጨንቀው ሁለተኛ ጉዳይ ነው።እንዲያውም የልዕለ ኃያሏ ሃገር አሜሪካ መሪ የሆኑት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰው ልጆችን ሁሉ ወክሎ የጋራ ጠላትን በመከላከል እና በመቆጣጠር ላይ ለተሰማራው ተቋም የሚያዋጡትን የገንዘብ መዋጮ ማቋረጣቸውና ከድርጅቱ አባልነት መውጣታቸውን ያለ ሃፍረት በይፋ አሳውቀዋል።በትልቁ ክፍለ ዓለም በእስያ ደግሞ ከኃያላኑ ተርታ የሚሰለፉት (እርስ በእርስ የሚጠቃቁበትን የጥፋት ኃይል ስለታጠቁ) እንደዚሁ በአስጨናቂው የሰው ልጆች ጠላት ላይ ሳይሆን ድንበር ዘልላ ያረፈች እርግብ ጉዳይ እጅጉን አሳስቧቸዋል።እንዲያውም ከገዳዩ ወረርሽኝ ይልቅ እርግቧ ምን አስባ ድንበር እንዳቋረጠች ከመጠን በላይ ስላስጨነቃቸው እንደተለመደው ከውጫው ጠላት ይልቅ ከራስ የሚመጣው ጥቃት ይበልጥ አስፈርቷቸው በጋራ ድንበራቸው ላይ ከአምስት ሺህ በላይ ጦር አስፍረዋል።ታዲያ ከዚህ በላይ የራስ ፍርሐትና በማያስጨንቀው መጨነቅ በሰው ልጆች ዘንድ ካልሆነ በስተቀር በወዴት አለ? በማያስጨንቀው እንዳንጨነቅ ፈጣሪ ማስተዋሉን ይስጠን፤ የሚያስጨንቀውን ደግሞ በምህረቱ ያስወግድልን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2012
ይበል ካሳ