ዕለቱ ብዙዎች የረፋዷን ደማቅ ፀሐይ መውጣት ከመኝታቸው ሳይነሱ ለመጠባበቅ እንደሚሹት ዓይነት ነው፡፡ ማልጄ ከተገኘሁበት የሥራ ቦታዬ ስደርስ ዕድሜ የጠገበና ያደፈ ነጭ ጃኬታቸው እጅጌ ስር በርከት ያሉ ወረቀቶችን የሸጎጡ አንድ አባት ተመለከትኩ፡፡ ሁኔታቸው ቀልቤን ሳበኝና ዓይኖቼን ከእርሳቸው ላይ ተከልኩ፡፡ ጥቁር ባርኔጣ ከአናታቸው ጣል አድርገዋል፡፡ በመካከላችን ያለው ርቀት እየጠበበ ዕርምጃቸው ወደእኔ እየቀረበ ሲመጣ ከሁለት ዓመታት በፊት ወደተቋማችን ቅሬታቸውን አቅርበው የተስተናገዱት አቶ አደመ ገብረፃዲቅ መሆናቸውን ለመረዳት ቻልኩ፡፡ እኛም ዳግም ፍረዱኝ ያስባላቸውን ጉዳይ ከሚመለከተው አካል ምላሽ እና የሰነድ ማስረጃዎችን ፈትሸን እንዲህ ይዘንላችሁ ቀረብን፡፡
ለመነሻ
በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በማጀንግ ብሔረሰብ ዞን መንገሺ ወረዳ የሪ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አደመ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በጥቅም የተሳሰሩ አንዳንድ የክልሉ አስተዳድር አካላት ለሕገወጦች ባደረጉት ድጋፍ 200 ሔክታር የቡና ማሳቸውን በጠራራ ፀሐይ ተነጥቀው ለእስር ተዳርገው ነበር።ከማረሚያ ከወጡ በኋላም የነበራቸውን ሁሉ በቀማኞች ተዘርፈው ልጆቻቸውንና የሞቀ ትዳራቸውን ለመበተን ተገድደዋል።ፍትሕን ፍለጋም የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን በር ሲያንኳኩ ደጅ ጠንተዋል።ይህም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ወድቀው ማጉረስ የለመደ እጃቸው የሌሎችን እጅ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡
200 ሔክታር የቡና ማሳቸው ላይ ባልታወቀ መልኩ ለሌሎች ግለሰቦች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሠርቶ መሰጠቱ ሳያንስ ከ2004 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም ጥብቅ ደን በማውደም ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።ጉዳዩን የመረመሩ አካላት ሕጋዊ መሆናቸውንና በንብረቱ ላይም ሕጋዊ ባለመብት እንደሆኑ ቢያስተላልፉም፤ በዞኑ በግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ውስጥ የሚሠሩ አካላት ሥልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም በደል እንዳደረሱባቸው ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።ይህም ሕገመንግሥቱ ያጎናፀፋቸው ሁሉም ሠው በሕግ ፊት እኩል ነው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ተሽሮ በደል በመድረሱ ከልማት ተፈናቅለው ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንደተጋለጡ አብራርተዋል።
ትከሻቸውን የሰበረ የበዛ ቁጥር ያለው ማስረጃቸው ዘብጥያ ከመወርወር ያላዳናቸው አቶ አደመ፤ ረጅም ቀጠሮ እየተጠየቀ ባልፈፀሙት ወንጀል በተደጋጋሚ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ እንደተደረጉ ይናገራሉ።አቤቱታቸውን ለተቋማችን አቅርበው ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓ.ም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅሬታቸውን፣ የሰነድ ማስረጃዎቻቸውንና የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር በማነጋገር በሠራው ዘገባ ጉዳያቸው ለመንግሥትና ለሕዝብ ጆሮና ዓይን ደርሷል።በዚህም ዳግም በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዲታይ ተደርጎ ያለአግባብ በግለሰቦች እጅ የሚገኘው ንብረታቸው እንዲመለስ በመወሰኑ የተስፋ ብርሃን ለማየት ችለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በድብቅ የተሠራው ካርታ እንዲመክንና ንብረታቸው ተመላሽ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ወደ ሥራ እንዲገቡ ለዞኑ ቢያሳውቁም በአሁኑ ወቅት ውሳኔው ተፈፃሚ ባለመሆኑ በንብረታቸው ባይተዋር ሆነው ሕገወጦች ዕለት ተዕለት በሀብታቸው ምርታማነታቸው እየተረጋገጠላቸው ይገኛል።ክልሉ የወሰነውን ውሳኔ ግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቢያስገቡም ምላሽ ግን ሊያገኙ አለመቻላቸውን ያስረዳሉ።
ምንም እንኳ ክልሉ የተፈጠረባቸውን ችግር አምኖ መፍትሔ እንዲሰጣቸው በደብዳቤ ጭምር ቢያሳውቅም ውሳኔውን የሚያስፈጽምላቸው በሕግ ኃላፊነት የተጣለበት የመንግሥት አካል በማጣታቸው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በሌሊት ውርጭ ከመመታት ሊድኑ አልቻሉም።በመሆኑም የሚመለከተው አካል የሕግ ውሳኔ ዋጋ አጥቶ የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን ይዘው ለእንግልት መዳረጋቸውን ተመልክቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡
ከአንደበታቸው
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቀድሞ ኢሉባቦር መቱ ክፍለ ሀገር በሞቻ አውራጃ በጎደሬ ወረዳ የካቦ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ አደመ፤ የእርሳቸውና መሠል የአካባቢው የሸካና ከፋ ተወላጅ ነዋሪዎች ይዞታቸው አያቶቻቸውና አባቶቻቸው ከምንሊክ ዘመነ መንግሥት አስቀድሞ የያዙት እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህም እንዲኖሩበት ያወረሷቸውን ውርስ በአዲሱ መዋቅር በጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስር እንዲተዳደሩ በመወሰኑ ሕጉ በሚያዝዘው መሰረት በቀበሌ ደረጃ በማስመዝገብ ዕውቅና ማግኘታቸውን ይገልጻሉ።ቡና ሲያለሙ የሚጠበቅባቸውን የመንግሥት የመሬት ኪራይ ግብር በማህበራቸው ሥም በመክፈል በማልማት ላይ እያሉ ግን ድንገት ያላሰቡትና መላ ሕይወታቸውን ዝብርቅርቅ ያደረገ ክስተት እንዳጋጠማቸው ያስታውሳሉ፡፡
በማህበር ደረጃ ኩታገጠም የሆነውን የቡና እርሻ ይዞታቸውን ከኋላ ቀር አምራችነት ወደዘመናዊ አሠራር ለመቀየር በዚህም ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለመቀላቀል ደፋ ቀና እያሉ ባሉበት ሁኔታ ያጋጠማቸውን ዱብ ዕዳ ሲቃ እየተናነቃቸው ያስታውሱን ጀመር።ነጋቸውን የተሻለ ለማድረግ መንግሥትም በፖሊሲና ስትራቴጂው ያስቀመጠው ነውና ግብርናቸውን ለማዘመን እቅድ በማውጣት 1999 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2004 ዓ.ም ቡና ሲያለሙ ይቆያሉ።በዚህ ሁሉ መሀል ይዞታውን ያገኙትም በሕጋዊ መንገድ ነውና ቡና እርሻ ይዞታቸው ላይ ሲሠሩ ተከራካሪ ሌላ አካል አልነበረም፡፡
የተተከለው ቡና ምርት መስጠት የሚጀምረው ከአራት ዓመት በኋላ በመሆኑ በ200 ሔክታር ስፋት መሬት ላይ ለችግኝ ዝግጅት፣ ለምንጣሮና ለጉድጓድ ቁፋሮ፣ ከመደብ ችግኝ ወደ እርሻ ማሳ ለማዛወር እና ለመትከል፣ የተተከለውን ቡና ችግኝ ለማረም እና ለመንከባከብ፣ ለሠራተኛ አስቤዛ እና የቀን ደመወዝ ክፍያ የእርሻ መሳሪያ ግዥ ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብና መሠል ወጪዎችን ከቤተሰቦቻቸው የምግብ ዋስትና ተቀናሽ በማድረግና ወደ ሥራ በማዞር ሩቅ አልመው ይተጉ ነበር።ለሥራው ስኬትም የቤተሰቦቻቸውን ጉልበት በመጠቀም የተከሉትንና ለምርት ሲደርስ ከምርቱ አላባ ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ መልሰው ለመተካት በማሰብ ለልማቱ ሥራ ማፈጸሚያ በማዋል ከጨረሱ በኋላ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ሥራ ኃላፊዎች የማህበራቸውን የቡና እርሻ ይዞታ ሕጋዊ ሰውነት በማሳጣት ለባለሀብቶች እንደሰጡባቸው አቶ አደመ በኀዘን ይገልጻሉ።ተያይዞም ባለሀብቶቹ መጋቢት 25/07/2000 ዓ.ም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሠርቶ የተሰጣው ሲሆን፤ በተቃራኒው አቶ አደመ ግን ልማታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ በወንጀል ክስ ይመሰረትባቸዋል።
የማህበሩ የቡና እርሻ ይዞታ የሚገኘው በጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በማጃንግ ብሔረሰብ ዞን በመንገሺ ወረዳ በየሪ ቀበሌ ውስጥ ልዩ መጠሪያው ጋለቂቶ ተብሎ በሚታወቅ ስፍራ ሲሆን፤ እንደይዞታ አቀማመጥ በሰሜን የጎደሬ ወረዳ የካቦ ቀበሌ የቀድሞው አገር በቀል ኦርጋኒክ ቡና እና ቅመማ ቅመም አምራች አክሲዮን ማህበር የቡና እርሻ ይዞታ፣ በምሥራቅ የመንገሺ ወረዳ የየሪ ቀበሌ ልማት ቡድን ንዑስ ገበሬዎች የቡና እርሻ ይዞታ እና ሙሉ በሙሉ የሸሲ ወራጅ ወንዝ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።በደቡብ የሸሲ ወራጅ ወንዝና የአፋለች ወራጅ ወንዝ፣ በምዕራብ የመንገሺ ወረዳ የየሪ ቀበሌ ግሮባይ ንዑስ ገበሬዎች ቡና እርሻ ይዞታ፣ በደቡብ ምዕራብ ገበሬ መጫ አባዋጆ የቡና እርሻ ይዞታ፣ በሰሜን ምዕራብ ገበሬ ሀሰን ሱፍ የቡና እርሻ ይዞታ መልስ በወሰንተኞች በድንበር ታወቆ የሚገኝ ይዞታ መሆኑን የሚያብራሩት አቶ አደመ፤ በቡና እርሻ ይዞታቸው ዙሪያ በተነሳ ክርክር በመንገሺ ወረዳ በየሪ ቀበሌ ልዩ መጠሪያ ጋሊቂቶ አድራሻ ስም ተጠቅሶ የግል ተበዳይ የማህበሩ ሥራ አስኪጅ በሆኑት አቶ አደመ ሥም በወንጀልና በፍትሐብሔር ክስ ይመሰርታል፡፡
ለዘጠኝ ዓመታት ጉዳያቸው ተገቢ ምላሽ ሳያገኝ አንዴ በእስር፤ ቀጥሎ ደግሞ በጎዳና ሕይወትን እየገፉ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አደመ፤ የችግራቸው ምንጭ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሙስና እንደሆነ በኀዘን ያስረዳሉ።የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የማጃንግ ብሔረሰብ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ሥራ ኃላፊዎች በጥቅም በመተሳሰር የማህበራቸውን የቡና እርሻ ይዞታ ለባለሀብቶች እንዳስተላለፉባቸው ነገሩን የኋሊት በትዝታ ተጉዘው ያስታውሳሉ።በዚህም ባላወቁት ሁኔታ መጋቢት 25/07/2000 ዓ.ም ለኢንቨስትመንት የሚሆን የገጠር መሬት መረከቢያ ባለሙያ በይዞታቸው ላይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ሠርቶ ለባለሀብቶቹ ያስረክባል፡፡
በይዞታቸው ላይ ሕገወጦች ባለቤት ሲደረጉ ሕጋዊ የሆኑት አቶ አደመ ደግሞ በመንግሥት ጥብቅ ደን ማውደም ወንጀል በሐሰት ክስ ተመስርቶባቸው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 40 መሠረት ከተደነገገው ስርዓት ውጪ ጉልበተኞቹና ሕገወጦቹ ሕጋዊ ባለመብት እንደተደረጉ ነው የሚያስረዱት።በዚህም ባለሙት ሀብትና ንብረት ላይ የማይታወቁትን ግለሰቦች ወራሽ በማድረግ በጥቅም የተሳሰሩት የክልሉ አስተዳደር አካላት መሆናቸውን ያስቀምጣሉ።የግል ተበዳይ የሆኑት እነ አቶ አደመም የገዛ ንብረታቸው በአደባባይ ተነጥቆ የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37 የተደነገገው ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን ተነፍገው ለዘጠኝ ዓመታት ሲንከራተቱ ቆይተዋል፡፡
የማህበሩ የቡና እርሻ ይዞታ አስመልክቶ የየሪ ቀበሌ አስተዳደር ምክር ቤት ባለቤትነታቸውን አረጋግጦ ለሚመለከተው ለበላይ አካል በመሸኛ ደብዳቤ ድጋፍ ቢያደርግላቸውም፤ በመቀጠልም የቀበሌው የበላይ ተጠሪ የመንገሺ ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት፣የማጃንግ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር ምክር ቤት ለአራተኛ ዙር ለአቤቱታቸው ምላሽ የሰጡበት ይዞታ ቢሆንም መፍትሔ ሊያገኙ አልቻሉም።በጉዳዩ ላይ የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት ለአቤቱታቸው በተመሳሳይ አስተዳደራዊ ውሳኔውን ለአራተኛ ዙር በመስጠት ይዞታው እንደሚገባቸው ቢያረጋግጥም በተለ ያዩ ጊዜያት የተላለፉት ውሳኔዎች ተግባራዊ አለመደ ረጋቸው ችግሩ ምን ያክል ስር የሰደደ እንደሆነ አመላካች ነው ባይ ናቸው፡፡
በቀድሞ አጠራሩ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር የክልሉ መንግሥት ለቅሬታቸው ውሳኔ እንዲሰጥ የውሳኔ ትዕዛዝ መስጠቱንም አቶ አደመ ያስታውሳሉ፡፡
በይዞታው ላይ ሕጋዊ መሆናቸው ቢታወቅም በሐሰት ክስ ከተጠያቂነት ያላመለጡት አቶ አደመ የማህበሩን የቡና እርሻ ይዞታ በማስመልከት በወንጀል እንዲጠየቁና ከአካባቢው ለማራቅ በአሻጥር ብዙ ሥራ እንደተሠራባቸው ያብራራሉ።በዚህም ጥብቅ የመንግሥት ደን በማውደም ወንጀል እና በግለሰቦች በፍትሐብሔር በሥማቸው ክስ ተመስርቶ በጊዜ ቀጠሮ በዞን ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም በፌዴራል ፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ባልሠሩት ወንጀል ማረሚያ ቤት ሲማቅቁ ቆይተዋል።በአሁኑ ወቅትም ጉዳያቸው እልባት አግኝቶ ይዞታቸው ተመላሽ እንዲደረግላቸው ተጠያቂ የሚደረጉ የእኩይ ተግባሩ ተሳታፊዎችም እንዲጠየቁ ትዕዛዝ ቢተላለፍም ለእርሳቸው ግን ጠብ ያለ የሚታይ መፍትሔ አለማግኘታውን ነው የሚናገሩት።ጉዳዩን ያጠናክራል ያሉትን መረጃም ተራ በተራ በማውጣት አሳይተውናል።
ቆየት ያሉ ሰነዶች
የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የማዥንግር ዞን የጎደሬ ወረዳ መስተዳደር ምክር ቤት መዝገብ ቁጥር 2022/6/5 በቀን 28/6/2003 ዓ.ም የካቦ ቀበሌ አስተዳደር ጽ/ቤት በላከው ደብዳቤ የኢንቨስትመን እርሻ ይዞታን አስመልክቶ ጽፏል።በዚህ ክልል በዞኑ ለሚደረገው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ በተጠና ቦታ የቡና እርሻ ይዞታ በሀውተቺ ንዑስ መንደር ከወረዳው ኢንቨስትመንት ጋር በመሆን አቅጣጫውን በመለየት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይላል።በመቀጠልም ለጎደሬ ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት በመዝገብ ቁጥር መሰ 00/99/01 በቀን 24/06/2003 እና በቀን 15/07/2003 ዓ.ም በካቦ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሀውተቺ ንዑስ መንደር የርክክብ ጥናት የኢንቨስትመንት የእርሻ ቦታ አስመልክቶ ደብዳቤ እንደተፃፈ ቆየት ያሉ ሰነዶች እንደሚያመላክቱ አቶ አደመ ያሳያሉ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለም የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ለማዥንግር ዞን ጎደሬ ወረዳ መስተዳድር ምክር ቤት በመዝገብ ቁጥር ኢንቨ/858/የ/3/1 በቀን 02/9/2003 ዓ.ም ደብዳቤ ልኳል።በዚህም ቀደም ሲል በቁጥር ኢንቨ 238/9/3/1/ባን በቀን 19/02/2003 ዓ.ም
ስለተጠናው የመሬት መረከቢያ ሰነድ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ የእርሻ መሬቱን የተረከቡ መሆኑ መረጋገጡን ያትታል። ስለሆነም የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ወይም ካርታ እስከሚዘጋጅላቸው ድረስ ሥራ እንዲጀምሩ መባሉን ያመለክታል።በዚህ መልኩ ለግለሰቦቹ አለአግባብ ይዞታቸው እንደተላለፈ የሚናገሩት አቶ አደመ የማህተም ማጭበርበር እንደተደረገም ይጠቁማሉ፡፡
መሬት ኪራይ ወይንም ሊዝ ሥምምነት ሰነድ መዝገብ ቁጥር 1331/0-1/2 በቀን 26/4/2004 እና በቀን 25/04/2004 ዓ.ም ዘላቂ አካባቢ ተፈጥሮ ሀብት ልማት እና አጠቃቀም ሥራ ሂደት ባለቤት የነበሩት ግለሰብ ለዘጠኝ ዓመት በሥራ ላይ ያልዋለ በጋምቤላ ሕዝቦች ክልላዊ መስተዳድር በዞን ሁለት መስተዳድር የጎደሬ ወረዳ የካ ቀበሌ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት በሚል ስልጣናቸው የወረዳ ሆኖ ሳለ የቀበሌ ማህተም በመጠቀም ተግባሩን እንደፈፀሙም ማስረጃዎቹን አሳይተውናል።
የውሳኔ ሰነዶች
በቀን 20/07/ 2011 ዓ.ም የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት በመዝገብ ቁጥር መ2/3859/መ1/10 ወጪ አድርጎ ለማጃንግ ብሔረሰብ ዞን መስተዳድር ምክር ቤት የላከው ደብዳቤ ከሰነዶች መካከል በቀዳሚነት የተመለከትነው መረጃ ነው።የክልሉ ፕሬዚዳንት በደብዳቤው በማህበሩ ላይ የተፈፀሙ ሕገወጥ ድርጊቶችን አውግዘዋል።ማህበሩ በማጃንግ ብሔረሰብ ዞን መንገሺ ወረዳ የሪ ቀበሌ ውስጥ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የቡና ልማት ሲያካሂድ ቢቆይም በ2004 ዓ.ም ግን በተወሰኑ ግለሰቦች በቀረበው ሕገወጥ ጥያቄ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር በደብዳቤው ሰፍሯል።አቶ አደመ ማረሚያ ከቆዩ በኋላ ፋይሉን የያዘው የማጃንግ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከወንጀል ነፃ እና የንብረት ባለመብት መሆናቸውን በመወሰኑ ከእስር ከወጡ በኋላ ማህበሩ የጀመረውን ልማት መቀጠል ሲገባው በሕገወጥ እና በጥቅም በተሳሰረ መንገድ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ዋጋ በማሳጣት በ2007 ዓ.ም በድጋሚ መታገዱን ያብራራል፡፡
በዚህም ከመንገሺ ወረዳ መስተዳድር ምክር ቤት ጀምሮ በሁሉም የአስተዳድር እርከኖች አቶ አደመ ለመንግሥት ጥያቄ ቢያቀርቡም ይህን በኪራይ ሰብሳቢዎች ድጋፍ የተፈፀመውን ሕገወጥ ድርጊት ማስተካከል የሚችል አካል ባለመኖሩ በማህበሩ ላይ የተፈፀመው የአስተዳደር በደል ከክልሉ አልፎ በተለያዩ የፌዴራል ተቋማት እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መድረሱን ደብዳቤው ያትታል።በዚህም ጥያቄያቸው በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅጣጫ መሰጠቱንም ያመለክታል፡፡
በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሳታፊ በመሆን ለክልሉና ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ልማታዊ ባለሀብቶችንና ማህበራትን ድጋፍ መስጠትና ማበረታታት ሲገባ፤ ሕዝብን የመምራት ኃላፊነት ተቀብሎ እያስተዳደረ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲከሰቱም በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በኃላፊነትና ተጠያቂነት ስሜት ዕርምጃ ወስዶ ማስተካከል የሚችል መንግሥት /ተቋም/ አለ ተብሎ በሚታሰብበት ወቅት በልማት ለተሰማራው ማህበር አቤቱታ ምላሽ የሚሰጥ ኃላፊነት የሚሰማው አካል ባለመኖሩ ማህበሩ ልማቱን ለማቆም መገደዱንም ደብዳቤው አስፍሯል።በዚህም በሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በእንጭጩ መፍታት ተገቢነቱ ባያጠያይቅም ማህበሩ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ አለመሰጠቱ ግን ወረዳውና ዞኑ ፍትሕንና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የነበረባቸውን ከፍተኛ ችግር አጉልቶ ያሳየ እንደሆነም የክልሉ ፕሬዚዳንት ለዞኑ በላኩት ደብዳቤ ገልጸዋል።የተፈፀመው ሕገወጥ ድርጊት አገሪቱ የተያያዘችውን የለውጥ ጉዞ የሚፃረር በመሆኑ ተጠያቂነት እንደሚያስከትልም አክለው ጠቁመዋል፡፡
የሸሲ ቡና ተክል አምራች ገበሬዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የጀመረውን ልማት እንዲቀጥ ልም በይዞታው ላይ የገባ ሌላ ድርጅት ካለ በአስቸኳይ እንዲለቅ ብሎም የተሠራ የይዞታ ማረጋገጫ የባለቤትነት ካርታ ካለም በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ፕሬዚዳንቱ በደብዳቤው አዝዘዋል።በዚህም ማህበሩ በመታገዱ ምክንያት ያልከፈለውን የመንግሥት ግብር እንዲከፍልና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የኢንቨስትመንት ፍቃዳቸው እንዲታደስ ድጋፍ ተደርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ልማት እንዲገቡ መታዘዙን ከደብዳቤ ግልባጩ ተመልክተናል።ይህን መነሻ በማድረግ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ግልጽ መመሪያ መሰጠቱን ገልፆ ለዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ደብዳቤ ጽፏል።በዚህም በማህበሩ ጣልቃ የገባ አካል ወጥቶ የተሠራ ካርታ ካለም ተሰርዞ ማህበሩ በአጭር ጊዜ ወደ ሕጋዊ የልማት ሥራው እንዲመለስ እንዲደርግ ማሳሰባቸው ሰፍሯል።
የዞኑ አስተዳደር ምክር ቤት ለማጃንግ ብሔራዊ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ በቀን 03/08/2011 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 4452/ማዞን/005 ወጪ አድርጎ በላከው ደብዳቤ፤ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተዋረድም ከጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት በተሰጠው ግልጽ መመሪያ መሠረት በማህበሩ ይዞታ ጣልቃ የገባ አካል ወጥቶ፤ ካርታም ተሠርቶ ከሆነ በአስቸኳይ ተሰርዞ ማህበሩ ወደ ሕጋዊ የልማ ሥራው ተመልሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚነቱ በሪፖርት እንዲገለጽ መምሪያው ከዞኑ ጥብቅ ማሳሰቢያ እንደተሰጠው ደብዳቤው ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ግንቦት 03 ቀን 2012 ዓ.ም በቁጥር ER3-M41/18/20 ወጪ አድርጎ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የላከው ደብዳቤ ከመረጃዎች መካከል የተመለከትነው ሰነድ ነው።ተቋሙ ዓላማውን ለማሳካት የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትልና ምርመራ እንዲሁም ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንደሚሰጥ በደብዳቤው ሰፍሯል።በዚህም መሠረት አቶ አደመ የቡና እርሻው ባለመብትነታቸው በሕግ አግባብ ቢረጋገጥም ውሳኔዎች በመፈፀማቸው ምክንያት በክልሉ በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ተቋማት የመብት ጥሰት እንደደረሰባቸው አቤቱታ ማቅረባቸውን ደብዳቤው ያትታል፡፡
በደረሰባቸው ችግር ቤተሰባቸው ተበትኖ ጎዳና ላይ መውደቃቸውንና ለእንግልት መዳረጋቸውን ለድርጅቱ የሕግ ድጋፍ መጠየቃቸውን ሰነዱ ያሳያል።አቶ አደመ ተቋሙን የጠየቁትን የሕግ ድጋፍ ለመስጠት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ምላሽ ማግኘት አስፈላጊ በመሆኑ በጽሑፍ እንዲገለጽለት ጥያቄ ማቅረቡንም ከደብዳቤው ለመረዳት ችለናል፡፡
እኛም የቀድሞ መረጃዎቻቸውን እንዲሁም እንደ አዲስ የተደራጁ መረጃዎቻቸውን ተመልክተናል። ክልሉም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያሳለፈለትን ትዕዛዝ ተቀብሎ ባደረገው ማጥራት የአቶ አደመ ቅሬታ ትክክለኛና ተገቢ እንደሆነ አምኖ ችግሩ የተፈጠረው ኃላፊነታቸውን ወደጎን በማለት ምዝበራ ላይ ባተኮሩ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች መሆኑን ገልጹዋል።በመሆኑም እርሳቸው ወደ ልማታቸው እንዲመለሱ በድርጊቱ የተሳተፉ ደግሞ ተጠያቂ እንዲሆኑ ቢያዝም ውሳኔው ግን ተፈፃሚ ሊሆን አልቻለም።ስለምን ጉዳዩ እልባት ካገኘ በኋላ የቡና ማሳቸው ሊመለስላቸው አልቻለም? በጽሕፈት ቤቱስ በኩል ያለው መረጃ ምን ይመስላል? ስንል ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቀናን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
በጉዳዩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመልካም አስተዳደር ፍትሕና አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ምላሽ እንዲሰጠን ደብዳቤ ጽፈን ነበር።በአሁኑ ወቅት ደብዳቤዎች በፖስታ ቤት እንጂ በአካል መስጠት እንደማይቻል የጽሕፈት ቤቱ መዝገብ ቤት በገለጸልን መሠረት በተባለው መልኩ ልከናል።ይሁን እንጂ መረጃውን ለማግኘት አልተቻለም።በቀጣይም ጽሕፈት ቤቱ ምላሹን እንደሰጠ የምናስተናግድ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2012
ፍዮሪ ተወልደ