የ2012 የትምህርት ዘመን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ሞቅ ደመቅ ብሎ ነበር የተጀመረው። በተለይም የከተማ አስተዳደሩ በመንግስት ትምህርት ቤት ለሚማሩ ተማሪዎች የደንብ ልብስ አሰፍቶ ሁሉን ተማሪ አንድ አይነት በማልበስ፣ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ በማሟላት ፣ የቁርስና የምሳ አገልግሎትን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተደራሽ በማድረግ አብዛኛው ተማሪ ትኩረቱን ትምህርቱ ላይ እንዲያደርግ ለማስቻል ተሞክሮ ነበር።
በዚሁ ሁኔታ ተማሪዎች የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ትምህርታቸውን በሚገባ የተማሩና ያጠናቀቁ ሲሆን፤ የሁለተኛው መንፈቅ ዓመት ትምህርት ተጀምሮ ብዙም ሳይኬድ የኮሮና ቫይረስ በሽታ በመምጣቱ ትምህርቱ ተቋርጧል።
ቫይረሱ መምህራንንም ሆነ ተማሪዎችን ቤት ያዋለ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም ተማሪዎች ከትምህርት ዓለም እንዳይርቁ ለማድረግ በትምህርት ቢሮውም ይሁን በትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ተማሪዎች በቤታቸው ሆነው የመማሪያ መጽሀፋቸውን ከማንበብ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ከትምህርት ቢሮውና ከትምህርት ቤቶቻቸው የሚሰራጩላቸውን ትምህርቶች በአግባቡ በመከታተል መጪውን ጊዜ በተስፋ እንዲጠብቁም አድርጓቸዋል፡፡
በተለይም ትምህርት ቢሮው “ትምህርት በቤቴ” የሚል መርሃ ግብርን በመጀመርና ተማሪዎች በቤታቸው ሆነው የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን እየተጠቀሙ ትምህርታቸውን እንዲማሩ በማድረግ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን ትምህርት ለማካካስ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በማህበራዊ ትስስር ገጾች በመታገዝ ትምህርቶቹ እየተሰራጩ መሆናቸው ይታወቃል። ይህም ለብዙዎች ተደራሽ ይሆናል የሚል እምነትም ተይዟል።
ካለፈው ሚያዚያ 07 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪሄልዝ ቲቪ ከ 7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ላሉ ተማሪዎች ትምህርት ሙሉ በሙሉ መሰጠት የጀመረ ሲሆን፤ በኤፍ ኤም 94 ነጥብ 7 ፣ በቴሌግራም እና ዋትስአፕ በመሳሰሉት ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በሁሉም የትምህርት ክፍሎች የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን ቀጥታ የማስተማር ስራ በመከናወን ላይ ነው።በሌላ በኩልም በአዲስ አበባና በዙሪያ ለሚገኙ ተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ከአማርኛና ከእንግሊዝኛ ቋንቋዎች በተጨማሪ በአፋን ኦሮሞ ትምህርት በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ የቢሮው መረጃ ያመለክታል፡፡
ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አማካኝነት በቴሌቪዥን እየተሰጠ ባለው “ትምህርት በቤቴ“ መርሃግብር በአጭር የፅሁፍ መልእክት ለተሳተፉና ጥሩ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መደበኛ የመማር ማስተማሩ ሂደት ቢስተጓጎልም ቴክኖሎጂን በተከተለና ተማሪዎችንም ባሳተፈ መልኩ የመማር ማስተማሩ መቀጠል እንዳለበት ነበር የተናገሩት።
በተማሪዎች ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ትውልድ መገንባት እንደመሆኑ ከጥቅሙ አንፃር ወጪው አነስተኛ ነው ፤ በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት የሚሰጠው ትኩረት በተጠናከረ መንገድ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በተያዘው ዓመት ለተማሪዎች የተሰጡት የደንብ ልብስ ፣ የደብተር፣ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁሶችና የምገባ መርሃግብሩ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን በጥራትና በመጠን ጨምሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
እኛም በተለይም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠው የመማር ማስተማር ስራ በዚህ መልኩ መቀጠሉ ያለው ውጤትና እንደ ተግዳሮት የሚነሱ ነገሮችን ይዘን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ከአቶ ዳኜ ገብሩ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የትምህርት ሥርዓቱን ረብሾታልና አሁን ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ዳኜ፦ እንደሚታወቀው የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ በኢትዮጵያ ከተገኘበት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በኋላ መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎች በቤታቸው ውስጥ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲያጠኑ በተመሳሳይ መምህራንና ሰራተኞችም በቤታቸው ሆነው ስራቸውን እንዲሰሩ በመንግስት በኩል በተላለፈው መመሪያ መሰረት ተማሪዎቻችን እስከ አሁን ያሉት በቤታቸው ነው።ተማሪዎች በቤታቸው ቢሆኑም ሁሉም የሚማሩባቸው መጽሀፍት አሏቸው፤ በመሆኑም በቤታቸው ተቀምጠው መጽሀፍቶቻቸውን ያነባሉ ብለን እናስባለን፤ እያነበቡም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ተማሪዎች በእጃቸው ያሉትን የመማሪያ መጽሀፍት ብቻ አንብበው የዓመቱን የትምህርት መርሃ ግብር ማጠናቀቅ ይቻላል?
አቶ ዳኜ፦ በእርግጥ ተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፋቸውን በማንበብ ብቻ የዓመቱን መርሃ ግብር ሊሸፍኑት አይችሉም።በመሆኑም ትምህርት ቢሮው ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን አድርጓል። “ትምህርት በቤቴ “ የሚለው መርሃ ግብር ደግሞ ከዝግጅቶቹ መካከል ተጠቃሹ ነው።በመርሃ ግብሩም መጀመሪያ ኤፍ ኤም 94 ነጥብ 7 በተባለው የራሳችን ሬዲዮ ጣቢያ ጠዋት በአማርኛ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ትምህርት እየሰጠ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከ 7 እስከ 12 ክፍል ያሉ ተማሪዎች የመም ህራን እርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያ ስፈልጋቸው በመሆኑ የተወሰኑ ትምህር ቶችን በመምረጥ 7 እና 8 ክፍልን በእንግ ሊዝኛና በአፋን ኦሮሞ እንዲሁም ከ 9 እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ሙሉ በሙሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርቶች በአፍሪ ሔልዝ የቴሌቨዥን ጣቢያ እንዲሰጥ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡
አዲስ ዘመን ፦ የእነዚህ የትምህርት ማሰራጫ መንገዶች ተደራሽነትና ውጤታማነታቸውስ ተመዝኗል?
አቶ ዳኜ፦ እነዚህ በሬዲዮ በድምጽ በቴሌቭዥን ደግሞ በምስል የተቀረጸው ትምህርት እንደገና በቴሌግራም፣ በዩቱብ፣ በማህበራዊ ድረ ገጽ (ፌስቡክ)ና የተወሰኑት ደግሞ በቲውተር ገጾቻችን ላይ ይጫናሉ። ተማሪዎች ይህንን እያወረዱ እንዲጠቀሙ አስፈላጊው ቅስቀሳ ተደርጓል፤ በመሆኑም በዚህ መሰረት ተማሪዎች ጋ ለመድረስና ትምህርቱን ለመስጠት እየተሞከረ ነው።በእነዚህ መንገዶች በተለይም በማህበራዊ ድረ ገጾቹ ላይ አጫጭር ማስታዎሻዎችን (ኖቶችን) በማውጣት እንጭናለን፤ ከዚህም በተጨማሪ የመምህሩ መምሪያ የተማሪው መጽሀፍ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች በሙሉ ይጫናሉ።
በመሆኑም ተማሪዎች ከቻሉ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው እንዲማሩ ካልሆነ ደግሞ የሚቻላቸውን መርጠው እንዲጠቀሙ እያደረግን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ትምህርቱን እየሰጣችሁ ነው ግን ተማሪዎቻችሁ ጋ መድረስ አለመድረሱን ገምግማችኋል ወይ? ከሆነስ ያገኛችሁት መረጃ ምን ይመስላል?
አቶ ዳኜ፦ በቀጥታ እንኳን በራሳችን ማህበራዊ ድረ ገጾች ያለውን ብንመለከት በቴሌግራም እስከ አሁን ከ 78ሺ በላይ ተጠቃሚዎች አሉን፤ በኤፍኤም 94 ነጥብ 7 ላይም እንዲሁ የተለያየ አስተያየት የሚሰጡን ከ1 ሺ በላይ አድማጮች አግኝተናል፤ ቴሌግራም ላይም 3ሺ 600 ተማሪዎች ሃሳብ ያቀርባሉ፤ ሃሳብ ይሰጣቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ብሎም እንደ አገር በመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ አቅማቸው የሚታወቅ ነው፤ ይህንንም አስመልክቶ ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ አድርጓል፤ አሁን ደግሞ ይህ ወረርሽኝ ተከስቷል ምን ለማለት ፈልጌ ነው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እናንተ ለመማር ማስተማሩ ያግዛሉ ብላችሁ ያስቀመጣችኋቸውን አማራጮች ምን ያህል ያገኟቸዋል?
አቶ ዳኜ፦ የመጀመሪያው ከዚህ ውጪ ምንም አማራጭ የለም፤ በበጎ ፈቃደኞች እንዲሁም እኛም እራሳችን ወረቀቶችን እያባዛን ትምህርቶቹን ተደራሽ ማድረግ እንችል ነበር ፤ ግን ሁሉም አማራጮች ንክኪ አላቸው።የመጀመሪያው ጤና ነው፤ ሌላው ነገር ቀስ ተብሎ የሚደረስበትም ጉዳይ በመሆኑ ንክኪ ያላቸውን አማራጮች አንጠቀምም።
በነገራችን ላይ የግል ትምህርት ቤቶችም በዚህ መልኩ ወረቀቶችን (worksheet) እያባዙ መስጠት ጀምረው ነበር ግን በዚህ መልኩ ንክኪ መፈጠር ስለሌለበት አግደናቸዋል፡፡
የመጨረሻው ትንሹ አማራጭ ተማሪዎች በእጃቸው ላይ መጽሀፍ አለ፡፡ በመጥፎ አጋጣሚ የተገኘ ጥሩ አጋጣሚ ደግሞ ወላጆች፣ ታላላቅ አህትና ወንድሞች ቤታቸው ናቸው፤ እነሱ ደግሞ መጻህፍቱን ይዘው ያግዟቸዋል ብለን እናስባለን፡፡ ይህ እንግዲህ የመጨረሻውና በእጅ ያለው አማራጭ ነው፡፡
ሌላውና ቀላሉ አማራጭ ሬዲዮ ነው፤ ሁሉም ሰው እጅ ላይ ያለችው ትንሿ የእጅ ስልክ (ሞባይል) ሬዲዮ ትስባለች።እዚህ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖር ነዋሪ ደግሞ በትንሹ ይህች የእጅ ስልክ አለቻቸው፤ በመሆኑም ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ ካለ ያዳምጣሉ ብለን እናስባለን።ቴሌቪዥንም እንደዛው።ሌሎቹ ምናልባት ቴክኒካል ጉዳይ ሊፈልጉ ይችላሉ።ዞሮ ዞሮ ግን ወላጆች በዚህ ጊዜ ላይ ተጨማሪ መስዋዕትነት መክፈል ሊኖርባቸው ይችላል ግን አማራጭ የለውም፡፡
እዚህ ላይ በደንብ እንዲያዝልኝ የምፈልገው ነገር ትምህርቱ በምንም ተሰጠ በምንም ሃሳቡ በእጃቸው ላይ ያለው መጽሀፍ ውስጥ ያለ ነው።እነዚህ መንገዶች የበለጠ ትምህርቱን ለማስረጽ የምንጠቀምባቸው ናቸው እንጂ ሌላ ምንም የተለየ ነገር ያላቸው አይደሉም።አንዳንድ ጊዜ ሁሉም ነገር ተሟልቶላቸው የማይከታተሉ ተማሪዎች የመኖራቸውን ያህል ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለትምህርታቸው ትኩረት የሚሰጡ በአግባቡ የሚከታተሉ እንዳሉ ይታወቃል ይህ በትምህርት ቤት ውስጥም ባሉበት ወቅት የሚያጋጥም ነው፤ ስለዚህ በአንደኛው አማራጭ ጎበዝ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ ሁሉም አማራጮች ቀርበውላቸውም ያን ያህል ውጤታማ የማይሆኑ አሉ፤ በመሆኑም እንደ ትምህርት ቢሮ ያለውን አማራጭ ተጠቅመን መድረስ ያለብን ድረስ እንደርሳለን ብለን እናስባለን እንጂ መቶ በመቶ ውጤታማ እንሆናለን ብለን አንገምትም።
አዲስ ዘመን፦ ከሳምንታት በፊት ትምህርት ቢሮው ያዘጋጀው የሽልማት መርሃ ግብር ምን ይመስላል ስራችሁንስ ለማየት አስችሏችኋል?
አቶ ዳኜ፦ ከላይ እንደገለጽኩት እንግዲህ ሁሉም ነገር ተሟልቶላቸው ትምህርታቸውን የማይከታተሉ እንዳሉ ሁሉ ባገኟት አጋጣሚ ተጠቅመው ደግሞ ጥሩ ውጤትን የሚያስመዘግቡ ብዙ ተማሪዎች እንዳሉን አይተንበታል። ተሸላሚዎቹ የተሟላላቸው ተማሪዎች አይደሉም፤ ቤተሰቦቻቸው በጣም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ናቸው።ከዚህ የምንረዳው ደግሞ አሁን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቢቋረጥም ነገ የተሻለ ይሆናል ብሎ ጥርሱን ነክሶ የሰራ ሰው እንደሚወጣ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ባለፉት ሳምንታት የ8ኛና የ12 ክፍል ክልላዊና ብሔራዊ ፈተና ምክንያት ሞዴል ፈተናዎች ወጥተው ተማሪዎች እንዲሰሩ ሆኗል፤ በዚህስ በኩል ያያችሁት ጠንካራና ደካማ ጎን ምንድን ነው?
አቶ ዳኜ፦ በተሰጡት ፈተናዎች ተማሪዎች በሚገባ ራሳቸውን አይተዋል ብለን እናስባለን፤ ይህ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች እንደሚጠቀሙባቸው ቴክኖሎጂው ያሳያል፤ ፈተናውንም የክልል ተማሪዎች ሁሉ ወስደውታል።ለምሳሌ በአዲስ አበባ ደረጃ 2 ሺ 445 በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ለመፈተን የተመዘገቡ ተማሪዎች ቢኖሩም ፈተናውን የወሰዱት ግን በአንድ የትምህርት ዓይነት ብቻ እንኳን ከ 26 ሺ የሚበልጡ ተማሪዎች እየተፈተኑ እንዳሉ ነው የሚያሳየው ይህ ደግሞ የአዲስ አበባ ዙሪያንም ማዳረስ አስችሏል ማለት ነው።
በ12ኛ ክፍል በኩልም 24ሺ ተፈታኝ ተማሪዎች ናቸው አዲስ አበባ ላይ ያሉን ግን ፈተናውን የወሰዱት ከ 30ሺ በላይ ናቸው፤ ይህም የሚያሳየው ተደራሽነቱ ጥሩ እንደነበርና ተማሪዎችም እየተከታተሉን እንዳሉ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ በመንግስት ትምህርት ቤት በኩል ተማሪዎችን ለማግኘት እየተሄደበት ያለው መንገድና የግል ትምህትርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን
እየተከታተሉበት ካለው መንገድ አንጻር እንዴት ይገልጹታል? በተማሪዎች መካከልስ ልዩነት አይፈጥርም? እኩል መወዳደር ያስችላቸዋል?
አቶ ዳኜ፦ የመጀመሪያው እኛ ሁሉንም የትምህርት ማሰራጫ ዘዴዎቻችን የቀየስነው ለግሉም ለመንግስቱም ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነው።የግልና የመንግስት የሚባለወም የይዞታ ጉዳይ ነው።ቀደም ሲል አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የሚፈጽሙት የሥርዓተ ትምህርት ጥሰት ተስተውሎ እንዲታረሙ የማድረግ ስራ ሰርተናል።እዚህ ላይ ግን የግልም ይሁን የመንግስት ትምህርት ቤቶች ትምህርቶቻቸውን ሊሰጡ የሚገባው በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት መሰረት ነው። በዚህ ወቅትም አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ፈተናዎችን በብዛት የመላክ ነገር ታይቶ ይህ ትክክለኛ አካሄድ አለመሆኑን ነግረን እንዲታረሙ አድርገናል፡፡
በመሆኑም አሁንም ቢሆን ሰው የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ቤት መማሩ ብቻውን ውጤታማ አያደርግም ዋናው ነገር የራስ ጥረት ነው።በእርግጥ የግል ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸውም በኢኮኖሚ አቅማቸው ሻል ያሉ በመሆናቸው የግል አስጠኝ እስከመቅጠር ድረስ ሊደግፏቸው ይችላሉ ፤ አሁን ላይ ግን ወሳኙ ነገር ፈተና አይደለም፤ ቁም ነገሩ ለዓመቱ ያስቀመጥነው የትምህርት መርሃ ግብር ተሸፍኗል ወይ የሚለው ነው፤ አሁን እየተሯሯጥን ያለነውም ይህንን ለማጠናቀቅ ነው፡፡
ሌላው ልጆቹ ትምህርቱን በደንብ ጨብጠው አልፈው ለሚቀጥለው ዓመት ምንም ዓይነት ችግር እንዳይገጥማቸው ማድረግ ነው።ብሔራዊ ፈተና ካልሆነ የክፍል ፈተና ያን ያህል አሳሳቢም አይደለም፤ ወደፊትም ውሳኔ የሚያገኝ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፦ ኮሮና ቫይረስ ሙሉ በሙሉ መቼ ከአገራችን እንደሚወጣ ይምናውቀው ነገር የለም፤ ምናልባት ደግሞ ይህ በሽታ አብሮን የሚዘልቅ ከሆነ በተለይም በመማር ማስተማሩ ስራ ላይ ጫና ያሳድራልና ትምህርት ቢሮው ከወዲሁ እየተዘጋጀበት ያለ ነገር አለ?
አቶ ዳኜ፦ ይህንን ፈጣሪ ነው የሚያውቀው፤ በእቅድና በመደበኛ ስራችን መሰረት አይደለም እየሄድን ያለነው፤ እኛ ያቀድነው የዘንድሮውን ዓመት ትምህርት እንዴት እንሸፍነው የሚል ነው፤ ቀጣይ የሚመጣውን ነገር አይተን ዝግጅት እናደርጋለን።ነገር ግን በእኛ ግምት የዚህ ዓመት ትምህርት በምን መልኩ እንደሚያልቅ እያሰብን ነው።ምናልባት የበሽታውን ስርጭት በቶሎ በቁጥጥር ስር ማዋል ቢቻል ኖሮ የማካካሻ ትምህርትንም ለመስጠት ዝግጁዎች ነበርን።አሁንም ቢሆን የበሽታውን ስርጭት በቶሎ በቁጥጥር ስር ማዋል ከተቻለ ክፍተቱን የሚሞላና ተማሪዎችን እኩል የሚያመጣ ስራ እንሰራለን። ዋናው ነገር ግን በሽታው ከአገራችን መውጣቱ ነው፡፡
አሁን በተደጋጋሚ እየተናገርን ያለነው መጠበቅ ያለበት የሰዎች ህይወት የልጆች ጤና ነው፤ ትምህርቱን ሁሉንም መንገዶችን ተጠቅመን እንደርስበታለን የሰውን ህይወት ግን ዳግም ማግኘት ስለማይቻል ሁሉም ራሱን ሊጠብቅ በተለይም ልጆች ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ እንዲደረግላቸው ያስፈልጋል፡፡
“ልጆች እባካችሁ ከትምህርት ውጪ ሆናችሁ እቤት እንድትቀመጡ የተደረው በምክንያት ነውና ወደውጭ አትውጡ፤ ሰው ወደበዛበት አካባቢ አትሂዱ፤ ጤንነታችሁን ጠብቁ ከዚህ ውጪ ግን የቀረባችሁን የትምህርት መርሃ ግብር በሽታው ከአገራችን ሲወጣ ከልሰን ወደቀጣዩ የትምህርት እርከናችሁ ትሄዳላችሁ” የሚለው መልዕክት ይተላለፍልኝ፡፡
አዲስ ዘመን፦ በሁሉም አማራጮች ተጠቅ ማችሁ የዘንድሮው ዓመት ትምህርት እስካለንበት የግንቦት ወር ድረስ ምን ያህል ሸፈናችሁ?
አቶ ዳኜ፦ አንደኛው መንፈቅ ዓመት ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ገብተን ብዙም ሳንርቅ ነው የኮሮና ቫይረስ የመጣው ፤ ትምህርት ቢሮውም በሬዲዮ በቴሌቪዥን እንዲሁም በማህበራዊ ድረ ገጾች ትምህርቱን ማሰራጨት የጀመረው ሁለተኛው መንፈቅ ዓመት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ነው፤ እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ ያለውን ትምህርት አገባደናል፤ በቀጣይም በተለመደው ሰኔ ላይ ትምህርቱን ሳናበቃ አንድ ወር ወደፊት ገፋ የምናደርግ ይሆናል፤ በዚህም በመሸፈን ደረጃ እኛ ሁሉንም እንሸፍናለን ግን የተማሪዎች ሚና ከፍተኛ ሊሆን ይገባል።
ተማሪዎች የትምህርት መርጃ መጻህፍቶቻቸውን እስከመጨረሻ ማንበብ በትምህርት ቢሮው የሚሰጠውን ትምህርትም በአግባቡ መከታተል አለባቸው።እኛ ደግሞ ለሚከታተሉን ተማሪዎች በቅደም ተከተል ይዘን አንድ ወር ወደፊት ጨምረን ትምህርቱን እንሰጣለን ብለን ተዘጋጅተናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ አሁን ባለው ሁኔታ መምህራን ከስራ ውጪ ናቸው ፤ ትምህርት ቢሮውን የሚያግዙበት ምቹ ሁኔታስ ተመቻችቶላቸዋል?
አቶ ዳኜ፦ ሁሉም መምህራን እቤታቸው ናቸው የተነገራቸውም በቤታቸው እራሳቸውን እየጠበቁ ተማሪዎቻቸውን በሚያገኙበት ወቅት በቀላሉ ትምህርትን የሚያሰርጹበትን ዝግጅት እንዲያደርጉ ነው።ይህንንም እያከናወኑ እንዳሉ ነው የምናስበው።በሌላ በኩል ግን በቴሌቪዥንና በሌሎች መንገዶች የምናሰራጨውን ትምህርት የሚመሩልን፣ የሚያስተምሩልን፣ በምልክት ቋንቋ አስተርጓሚነትም የሚረዱን የራሳችን መምህራን ናቸው።ከዚህ አንጻር የጠራናቸው በሙሉ በመልካም ፍቃደኝነት እያገዙን ነው።ሌሎቹ ደግሞ የቴሌግራም ቡድን በመመስረት ለሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ጥያቄ በመስጠት ያልገባቸው ነገሮች ላይ ውይይት በማድረግም የሚሳተፉ መምህራን አሉን።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የተጀመሩና ተማሪዎችንም ሆነ ወላጆችን በከፍተኛ ሁኔታ የጠቀሙ ስራዎች ተሰርተዋል፤ እነዚህን ስራዎች በመመልከት በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደመንግሰት ትምህርት ቤት ልከዋል፤ በዚህም ሽፍት እስከመጀመር አድርሷል፤ ቀጣዩ ጊዜ ከዚህ የባሰ ስለሚሆን ቢሮው ከወዲሁ እያሰባቸው ያሉ ነገሮች ይኖሩ ይሆን ?
አቶ ዳኜ፦ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ከማስፈለጉ ጋር ተያይዞ በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ ደረጃ በርካታ ስራዎችን የሰራንበት ጊዜ ነው፤ በዚህም ደረጃቸውን ከፍ በማድረግ ተመራጭ እንዲሆኑም ማድረግ ተችሏል፤ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ተማሪዎች ስለምንም ነገር እንዳያስቡና ከእኩዮቻቸው ጋር ተመሳሳይ ስነ ልቦና እንዲኖራቸው ለማድረግ በጋራ እንዲመገቡ፣ ተመሳሳይ የደንብ ልብስ እንዲለብሱ፣ በምገባ መርሃ ግብሩም ሁሉም እንዲሳተፉ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ አሁን ደግሞ ኮሮና ቫይረስ መጥቶ ምገባውን ቢያቋርጥብንም በየወረዳው በተቋቋሙ የምግብ ባንኮች አማካይነት ችግረኞቹ እንዲረዱ እየሆነ ነው፡፡
እንግዲህ በቀጣዩ የትምህርት ዘመንም መንግስት አዲስ የደንብ ልብስ አሰፍቶ የትምህርት ቁሳቁሶችን ዘንድሮ ከነበረው በተሻለ ሁኔታ እንደሚቀርብና የምገባ መርሃ ግብሩም ሰፋ ተደርጎ እንደሚሰራበት ክቡር ከንቲባው ተናግረዋል ቢሮውም ዝግጅት ያደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን፦ በአንድ ክፍል ውስጥ ያለውን የተማሪ ብዛት በተመለከተ የጠየኮትን አልመለሱልኝም?
አቶ ዳኜ፦ በርካታ ትምህርት ቤቶች በማስፋፊያ ስራ ላይ ሲሆኑ አብዛኞቹም ተጠናቀዋል።ይህ የመጨናነቅ ሁኔታ ከፍቶ የሚታየው በየካ ክፍለ ከተማ ነው ኮልፌ ላይ በአንጻሩ ብዙ ትምህርት ቤቶች ተጠናቀዋል።የተጀመሩ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ያለምንም መዘግየት እንዲጠናቀቁ እየተሰራ ነው።በሚቀጥለው ዓመትም ወደመንግስት ትምህርት ቤት የሚመጡ ተማሪዎች ቁጥር በእጥፍ እንደሚጨምር ይታሰባል፤ በዛ ልክ ለመዘጋጀት ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፤ ይህ ብቻም ሳይሆን በትምህርት ቤት ጊቢ ውስጥ ያሉ እንደ መጸዳጃ ቤትና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተሻለ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ርዕሳነ መምህራን በስራ ላይ ስለሆኑ ያልተጠናቀቁትንና ያልታደሱትን በማሰራት ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ ትምህርት ቢሮ የመምህራንን ጥቅማ ጥቅም በማስከበር በኩል የጀመረው ስራ ነበር፤ በዚህም ቤት ሰጥቷል ግን ደግሞ ይህ ስራ በአንድ ዙር ብቻ ቀርቷል የሚሉም ቅሬታዎች አሉና እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ዳኜ፦ በየጊዜው ጥያቄዎች ይቀርባሉ ፤ እንደተባለውም የመምህራንን ጥቅማ ጥቅም በሚፈለገው ልክ ወደፊት መግፋት አልተቻለም እንግዲህ ወደፊት እየታየ እንደሁኔታው ጥያቄያቸው ምላሽ ሊያገኝ ይችላል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለትምህርት ዘርፉ ተዋንያን የተላለፉ መመሪያዎች ነበሩና ተፈጻሚነታቸው ምን ያህል ነው ?
አቶ ዳኜ፦ አሁን ያለው ነገር ትምህርት ቤቶችን መቆጣጠር ሳይሆን መደገፍ ላይ ነው ትኩረት አድርገን እየሰራን ያለነው፤ ሆኖም ከክፍያ ጋር በተያያዘ የወጡ መመሪያዎች ምን ያህል ተፈጻሚ እንደሆኑ ደግሞ በየጊዜው እያየን መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች እንዲያሻሽሉ እናደርጋለን።በመመሪያው መሰረት ተፈጻሚ እያደረጉ ስለመሆኑም በየጊዜው ቁጥጥር ይደረጋል።
ባለፉት ጊዜያትም ከክፍያ ጋር በተያያዘ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የተጻፈባቸው ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ አሻሽለው በመመሪያው መሰረት ስራቸውን እያከናወኑ እንደሆነ መረጃው አለን፤ የተወሰኑት ከአቅም ጋር ይታይ ብለው እያቅማሙ ነው፤ ግን ይህ ምንም ጥያቄና መልስ የሌለው በመሆኑ ሁሉም በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ያስተካክላሉ፡፡
አሁን እየገጠመን ያለው ችግር ወላጆችም ክፍያውን መመሪያው በሚያዘው መሰረት በወቅቱ እየከፈሉ አለመሆኑ ነው።በዚህ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ችግር እየገጠማቸው በመሆኑ ወላጆቸም ክፍያውን መክፈል አለባቸው።የግል ባለሀብቶችም ከ 50 እስከ 75 በመቶ ነው የተፈቀደላቸው ከዛ በላይ መሄድ አይቻልም፤ በመሆኑም ሁለቱም ተጣጥመው በመሄድ መምህራንም ችግር ላይ እንዳይወድቁና ደመወዛቸውን እንዳያጡ ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ወትሮም ቢሆን የትምህርት ጥራቱ ብዙ መሰናክሎች ያሉበት ነበር፤ አሁን ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ችግሩን የበለጠ አወሳስቦታል እርስዎ እንደባለሙያ ምን ይላሉ?
አቶ ዳኜ፦ ኮቪድ 19 በዓለም ላይ በትምህርት ዘርፉ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚውና በፖለቲካውም ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ነው እያደረሰ ያለው፤ በሌሎቹ ሴክተሮች ላይ ጉዳት እንደደረሰው ሁሉ እኛም ጉዳት ደርሶብናል።ተማሪና መምህራን በትምህርት ቤታቸው ተገናኝተው ፊት ለፊት የሚያደርጉትን የእውቀት ልውውጥ ማጣት ቀላል ነገር አይደለም፤ ተማሪዎችም በትምህርት ቤት መገኘትና ቤት መዋል እኩል የስነ አእምሮ እድገት የለውም ሁላችንም በየቤታችን እናውቀዋለን፤ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሲውሉ ነው ንቁና ብዙ ነገሮችን የማሳካት አቅም የሚኖራቸው፤ አሁን እቤት ሲውሉ ያለው ጫና ከባድ ነው፤ ግን ይህንን ለመቋቋም እየተፍጨረጨርን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻም ለወላጆች ለመምህራን እንዲሁም ለተማሪዎች ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
አቶ ዳኜ፦ ኮሮና ቫይረስ አደገኛ ነው ስለዚህ ህብረተሰቡ ራሱን በተገቢው ሁኔታ መጠበቅ አለበት።በጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችንም ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።ህዝብ ሲኖር ነው ለአንድ አገር ሀብት የሚሆነው በመሆኑም ተማሪዎች በቤት በመቀመጥ ከቤት መዋል የማይችሉት ደግሞ አስፈለጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እንዲንቀሳቀሱ ያስፈልጋል፡፡
ወላጆች ከትምህርት ቢሮው የሚተላለፉ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎቸን በመጠቀም ልጆቻቸው መስራት አለመስራታቸውን የከፈሉትን መስዋዕትነት ከፍለው እንዲከታተሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ዳኜ ፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2012
እፀገነት አክሊሉ