የብዙ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት በተቃርኖ የተሞላ ይመስላል። ተቃርኗችንን የምናወሳስብባቸው ማጠንጠኛዎች ደግሞ ቁጥራቸውና ዘውጋቸው ዝንጉርጉር ነው። ሲያሻን ራሳችንን “ባለ ብዙ የመልካም ባህሎች ቱባ ባለጠጎች” እያደረግን “ልዩ ማንነታችንን” ስንሰብክ አፋችንን አይዘንም። “ቱባ ባህሎች እያለን ለምን ቱባ ኑሮ መኖር ተሳነን?” ብለን መጠያየቁን “ባህላችን” ስላላደረግነው በግልጽ መነጋገሩ የመርግ ያህል ከብዶን ሺህ ዘመናት በከንቱ አፍስሰናል።
ለመወያየት ሙከራ ተደርጓል ብለን ሙግት ብንገጥም እንኳ ስንለማመድ የኖርነው የመሸሻ ማምለጫችንን (Scape Mechanisms) እየቀየስን እንጂ ቁስላችንን ለማፍረጥ አቅም አልነበረንም። “አይቅርብኝ” ይሉት ዓይነት ጨዋታ ለመጫወት ግን ብዙ ዓይነት መድረኮችን መድርከን የኮሜዲና የትራዠዲ ተውኔቶችን ተውነንባቸዋል። “ቱባ ባህሎቻችንን” የሀገራዊ ፀጋ መገለጫ ከማድረግ ይልቅ የአፍ ማበሻ ኩራት ማድረጋችን ሳይቆጨን የሚቀር አይመስለኝም።
“ኢትዮጵያ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ይህን ያህል ጊዜ ስለተጠቀሰች የቃል ኪዳን ምድር ነች” እያልን እንጽናናለን። በመሠረቱ ሀገራችን በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የመጠቀሷ እውነትነት ባይካድም “በቅድስና ተለይታ የብፅእና ካባ ካልተደረበላት” እያልን ሰይፍ እስከ መሞሻለቅ መድረስ ግን ተገቢነቱ አይታየኝም። “ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ መጥፋታቸውን” የምናረጋግጠው ከመጻሕፍት ንባብ ብቻ ሳይሆን በተግባር ጭምር ነው። “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፀባዖት ማንሳቷን” በእውነት አምነን የምንቀበል ከሆነ የእኛን ሰብዓዊ እጆች ለሰላምና ለመደናነቅ ለምን ዝቅ ማድረግ ተሳነን? ራሳችንን መመርመሩ አይከፋም።
“ሕዝባችን ጨዋ፣ ኩሩና እንግዳ ተቀባይ ነው” እያልን በመፎከርም ከተግባር ርቀንና ከመሆን አንሰን “ጨዋነታችንን” በማርከስ ለብዙ እኩይ ድርጊቶች በሽፋንነት ስንገለገልበት ይስተዋላል። የሕዝባችንን ደግነትና ርሁሩህነት ማን ይስታል? ማንስ ሊክድ ይችላል? ችግሩ በታሪካችን ውስጥ መራራ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የኖሩና እየፈጸሙ ያሉ በርካታ ቡድኖችና ግለሰቦች የወጡት እኮ ከዚሁ ሕዝብ መካከል ነው። በጨካኝነትና በርህራሄ አልባነት ግብራቸው ያንገፈገፈን ወገኖች ለምን የሕዝቡን ጨዋነት አልወረሱም? ለምንስ የመልካም ዜጎችን ባህርይ አልተካኑም? ደጋግመን ጠይቀን ደጋግመን መልስ ያጣንባቸውን ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እየደጋገምን ብንጠይቅ አይፈረድብንም። ይህንን ግዙፍ የመንደርደሪያ ሃሳብ እስከ መዳረሻዬ እያጣቀስኩ እቀጥላለሁ።
ማድነቅና መደናነቅ ለምን ይተናነቀናል?
መልካም ሥራ የሠራ የውጤት ሰው መሞገሱ ባህል ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊ የስብዕናችን ቅመም ጭምር ነው። ጥሩ የሠራ ሰው ይሞካሻል። አስፈላጊ ሲሆንም እየተጨበጨበለት አድናቆት ይዥጎደጎድለታል። የሚጨበጨብለት የተሻለ ሥራ እንዲሠራና ዳግም ወደ ከፍታ እንዲወጣ እንጂ ሙገሳውና አድናቆቱ ናላውን አዙሮ እርሾ እንደበዛበት ሊጥ ያለልክ በአጉል ትምክህት ኩፍ ብሎ በመቡካት ራሱን እንዲያገዝፍ አይደለም።
እርግጥ ነው በሽንገላ የተሸፈኑ፣ በሤራ የተውጠነጠኑ ጭብጨባዎች የምድራችንን ዓየር እየሰነፈጡ ስለመሆናቸው የሚካድ አይደለም። አንዲት ኢምንት የምታህል ተናዳፊ ቢምቢ (ትንኝ) ከእናቷ ጋር ተጨዋውታለች ብሎ ተረታችን የሚተርክልን አንድ ወግ ለዚህ ሃሳብ ማጎልበቻነት ቢጠቀስ መልካም መስሎ ታይቶኛል። ሕፃኗ ቢምቢ ከእናቷ ጉያ አምልጣ የአካባቢውን ዓለም ስትቃኝ ውላ ቤቷ እንደተመለሰች ለእናቷ እንዲህ ስትል ሪፖርት አቀረበችላት ይባላል። “እናቴ ቢምቢ ሆይ! ዛሬ በትልቅ ጉባዔ ውስጥ ድንገት ዘው ብዬ ስገባ ሰዎች ሁሉ በአጠገባቸው ሳልፍ እንኳን ደህና መጣሽ እያሉ በማጨብጨብ አድናቆታቸውን ሲገልጡልኝ ዋሉ።” አለቻት። እናትም የሕፃን ቢምቢን በደስታ የተፍለቀለቀ ሪፖርት በኀዘን ካዳመጠች በኋላ “አዬ ልጄ! ያጨበጨቡልሽ መቼ ሊያደንቁሽ ሆነና በሁለት መዳፋቸው መካከል አስገብተው ሊጨፈልቁሽ እንጂ።” አለቻት ይባላል። ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ እያልኩ ነገሬን እቀጥላለሁ።
ተገቢ የሆነ የአድናቆት ንፉግነት የከፋ ስስት ነው። ክፉ ሤራ እያውጠነጠኑና ጥርስ እየነከሱ የለበጣ ጭብጨባ ማዋጣትም ሰይጣናዊ ባህርይ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ የማስመሰል የሕይወት ጠገግ ዳርቻዎች ላይ ቆመው ሕይወትን የሚመሩ በርካታ ዜጎች ስለመኖራቸው ምሳሌ መጥቀስ አይሳነንም። ለምሳሌ፤ መልካም ውጤት አስመዝግቦ በመምህሩ “ጎበዝ!” በሚባል ተማሪ ጓደኛው ተናዶ የራሱን ደብተር በመቀዳደድ ቅንዓቱን የሚገልጽ ተማሪ ስለመኖሩ የመምህርነትን ሙያ በጥቂቱም ቢሆን የቀመስን ዜጎች እናውቀዋለን። ከጎበዙ ተማሪ ተጠግቶ የጉብዝናውን ፍሬ ከመጋራት ይልቅ በማግለልና ፊት በመንሳት ማስደንገጥ የተለመደ የተማሪ ቤት ክስተት ነው። ምን ይደረግ አስተዳደጋችን ነዋ!
ሌላም ላክል፤ ንግዱ ሰምሮለት የተሳካለትን ባለ ኪዮስክ (ባለ ቡቲክ) ያየ ቀናተኛ ነጋዴ የራሱን የእንጀራ መሶብ በመድፋት እንደምንም ተንፏቆ ወደ ተሳካለት ነጋዴ ሱቅ ቀረብ በማለት በተመሳሳይ የንግድ ዘርፍ ግፊያ መፍጠር የንግድ ሥርዓታችን አንዱ የእኩይነት መገለጫ ባህርይ ነው። የኖርንበት ነዋ ምን ይደረግ!
ምሳሌዬን ልሠልስ፤ የፖለቲከኞች ጭካኔማ የከፋ ነው። “የፖለቲካችንን ክፋት ማወቅ ከፈለግህ የእኛን ተሞክሮ ብቻ ማየት ይበቃል።” ያለኝ አንድ የኢህአዴግ ቤተኛ የነበረ ሰው ነው። ይህ ሰው በፖለቲካው ባህር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተዘፍቆ ሲዋኝ ከኖረ በኋላ በአንድ ወቅት ብንን ሲል በግምገማ እርቃኑን እንዳቆሙት ያስተውላል። ምክንያቱ ደግሞ “እነ እከሌ የሠሩትን መልካም ተግባር በይፋ በመገናኛ ብዙኃን ለምን አበሰርክ” በሚል ክስ ተወንጅሎ ነበር። ወንጃዮቹ የተበሳጩት “አድናቆቱ ከእኛ አልፎ ለምን ለሌላ ተሰጠ” በሚል ቁጭትና ስግብግብነት እንደሆነ የኋላ የኋላ ምክንያቱ በግልጽ ተነግሮታል።
ግምገማ በሚባል “ሠይጣናዊ ሤራ” ኢህአዴግ ምን ያህሉን ልጆቹን አኮላሽቶ የአመለካከትና የቀናነት ድሃ እንዳደረጋቸው ተጎጂዎቹ ራሳቸው ይፋ ወጥተው ቢመሰክሩ ብዙ ጉድ ይዝረጠረጥ ነበር። በዚሁ ክፉ የግምገማ ተብዬ አባዜ ብዙዎች መንፈሳቸው ተሰነጣጥሮ እንክትክት እንዳሉ ያለፉበት ያውቁታል።
በአንድ ወቅት አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበረ ሰው የሆነ ያልሆነው ተወርቶበት በግምገማ ሤራ በተባረረ ማግሥት የኃጢያቱ ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ በመሸማቀቁ ሀገሩን ጥሎ ለስደት መዳረጉን በአፀደ ሥጋ ከተለየችን የወቅቱ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ጋር ስንጨዋወት እንዲህ ብላኝ ነበር። “ያንን የመሰለ ግፍ መፈጸም ፖለቲካችን ተክኖበታል። የኢህአዴግ አባል ከመሆን ከሰይጣን ጋር ጽዋ መጠጣት ይሻላል።” የወዳጄ ንግግር እውነትነቱ የተረጋገጠልኝ የገማው ሥርዓት መፈራረስ ከጀመረ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ነው።
“ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም” እንዲሉ የኢህአዴግ መንፈስ ያሳበዳቸው ወበከንቱዎች ዛሬም በሀገሪቱ ውስጥ የሚስተዋሉት የመልካም ሥራ ጅምሮች አልዋጥላችሁ እያለ ሲያጥወለውላቸው እያስተዋልን ነው። በተለይም የሥርዓቱን መዘውር በእጃቸው ጨብጠው ሲያስሩና ሲገርፉ፣ ሲዘርፉና ሲያዘርፉ፣ ሲቀብጡና ሲያቃብጡ፣ ሲጥሉና ሲያነሱ የነበሩት ፊታውራሪዎች እነርሱ ያልሠሯቸው ግዙፍ ሥራዎች እንኳ በዓይናቸው ፊት እየተሠሩ ማድነቅና ማመስገን አልቻሉም። ማመስገኑ እንኳ ቢቀር ቅንዓታቸውን ዋጥ አድርገው ዝምታን ለመምረጥ አቅም አላገኙም።
የቀድሞውን ኢህአዴግ የሙጥኝ ብለው ሙጭጭ ያሉት ብቻም ሳይሆኑ የአዲሱ ትውልድ አንዳንድ የፓርቲ ሹመኞችም ቢሆኑ በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ የትስስር መረቦች የሚያወናጭፏቸው የቃላት አረሮች በእጅጉ እያስደነገጡን እንዳሉ ባንገልጽላቸው ከህሊናችን ጋር እንኳረፋለን። በዚያም ሆነ በዚህ ወገን ያሉት ተፋላሚዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ኩሩነት፣ መልካምነትና የባህላችንን ጨዋነት ነጋ ጠባ እየተረኩ እነርሱ ግን ከሌላ ዓለማት እንደመጡ ፍጡራን ራሳቸውን ስድ ለቀው አሳፋሪ ሃሳቦችን ሲለዋወጡ ስናስተውል “ይብላኝላችሁ!” እያልን እንደምንፈርድባቸው የገባቸው አይመስለኝም፤ ወይንም “በኬሬዳሽ እብሪት” ጠምብዘው የ“ምን ይሉኝ” ይሉኝታ መክኖባቸው ታውረዋል።
ሌላውን በማዋረድ መጀገን ለማንም አይበጅ፤
“ስድብሽና ስድቤ እኩል ነው፤ ትርፉ ሰው መስማቱ ነው” አለች አሉ በድርጊቷ የተፀፀተች “ሥራ ቤት”። የሕዝብን ጨዋነት፣ የመልካም ባህሎቻችንን “ቱባነት” ቀን ከሌት የሚዘምሩ የቅድመና የድህረ ኢህአዴግ ቤትኞች ዛሬም በጆሯችን በሚያንቆረቁሯቸው የእብሪት ዲስኩሮች ብዙኃኑ እየታዘባቸው እንደሆነ ወይ አልገባቸውም፤ አለያም ገብቷቸው እንደለመዱት “ምን እንዳይኮን” በሚል ግትርነት የፀኑ ይመስላል።
ጥቂት ፈታ እናድርገው። “እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳል!” እንዲሉ ቡሄ ጨፋሪ ታዳጊዎች፤ እዚያ ማዶ ያሉ “ሸበቶዎች” በቤታቸው የተዳፈነው የፍም እሳት ሊቀጣጠል የጭስ ምልክት ማሳየቱን በመካድ ከእነርሱ ውጪ የሆነን ሕዝብና ባህል ሲያዋርዱ መስማት ማሳዘን ብቻም ሳይሆን ልብን አቁስሎ ያደማል። እነርሱ ተገን ያደረጉት ሕዝብ በእንግዳ ተቀባይነቱ፣ እድፍ ባልሸፈነው እውነተኛ አፍቃሪነቱ፣ አኩሪ ታሪክ በተለበጠ ባህሉ የተከበረና የተወደደ ስለመሆኑ ከእነርሱ ይልቅ ሌላው ሕዝብና ታሪክ ቢመሰክር ይሻላል። እነርሱ ተወለዱበት እንጂ አያውቁትማ። የሀገር ውበትና ጌጥ ከሆነው ከዚህ ሕዝብ መካከል መውጣታቸው እስኪያጠራጥረን ድረስ ምሽግተኞቹ ፖለቲከኞች በነጋ በጠባ የሚሰጡት የጦርነት መግለጫ ዛቻና የስድብ ዓይነት እንዴት እያሳቀቀን እንደምናፍር ምነው በገባቸው።
ለመሆኑ ለበርካታ ዐሠርት ዓመታት የተጠመቁበት ኢህአዴጋዊ የፖለቲካ ጠበል ሲያስለፈልፋቸው የኖረው ስድብና ሌላውን ማዋረድን ብቻ ነውን? እስከ ማለት ደርሰናል። የፖለቲካ ልዩነታቸው ግቡ “ጨዋ ለሚሉት ሕዝብ” ትሩፋት ያስገኛል ብለው ካመኑ ለምን በሰላማዊ ቋንቋና ውይይት አይነጋገሩም። ለምንስ ለሕዝብ ሁሉ ተደራሽ በሆኑ መገናኛ ብዙኃን ሕዝብ እንዲያደምጣቸው አይከራከሩም!? የፖለቲካ ልዩነትን ቢያንስ “ጨዋ ነው” እያሉ ለሚሸነግሉት ሕዝብ ጥቅም ከሆነ ተነጋግሮ ችግርን ለመፍታት ለምን አልተቻለም?
አንድ የሀገር መሪ አንድ ሰው ብቻ አይደለም። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚወክል ፊት መሪ አንጂ። “ጓድ እና ጓዲት” እየተባባሉ በመሸነጋገል ሥልጣናቸውን ሲያጣጥሙ ኖረው ዛሬ ላይ “ፈላጭ ቆራጭነቱ” ሲቀር በጠላትነት ተፈራርጆ ለፍልሚያ “ይዋጣልን” እያሉ ከበሮ መደለቅ ምን ይሉት አባዜ ነው። ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ መፎከሩና ማስፎከሩስ ግብዝነት እንጂ ምን ማለት ይቻላል። “የዋህ፣ ቅን፣ ትሁት” እየተባለ በስሙ እየተማለ የሚሸነገለው ሕዝብ ይጠየቅና እስቲ ምን እንደሚመልስ እንስማ? ለካንስ “ቀጥ ለጥ ብለን” ለዓመታት ስንገዛ የኖርነው እነዚህን መሰል ግለሰቦች በሚመሩት ድርጅትና ስብዕና ነበርን? እያሉና እያልን ለመጠየቅ ተገደናል።
አንደበታቸውን የማይገሩ፣ ሕዝብን “እናከብራለን” እያሉ የሚያዋርዱ፣ “ቱባ የሚባል ባህል” እየናዱና እየናቁ ራስን ብቻ እንደ ምሥራች አብሳሪ “መሲህ” መቁጠር ከብዙኃን ጋር ብቻ ሳይሆን ከራስ ጋር ጭምር የመጣላት ምልክት እንጂ ምን ስም ይሰጠዋል። በጸሐፊው የግል እምነት ብዙዎቹ የሀገሬ ፖለቲከኞች ከወዲያም ሆነ ከየትኛውም ወገን “ግራ አጋቢ” የፖለቲካ አቋማቸውን እንድንቀበል ከሚያስገድዱን ይልቅ በቅድሚያ ለአንደበታቸው “ለከት” ቢያበጁለት ይሻል ይመስለኛል። እንደ አለሌ የገጠር ጎረምሶች በየሚዲያ ማማቸው ላይ ተሰቅለው አንዱ አንዱን አያዋረደ ሲበሻሸቁ ባንሰማ ደስታችን ነው።
በየጎሬያቸው እየተሰባሰቡ በግብዣና በፌሽታ “በሕዝብ ስም እየማሉ” ጊዜያቸውን ከሚያጠፉ ይልቅ የኮሚዩኒኬሽን መሠረታዊ ጥበብንና የሕዝብ አክብሮትን ሥነ ምግባር በመማር ራሳቸውን ቢለውጡ ይበጃቸዋል። በግልጽ እንነጋገር ከተባልም በሰሜናዊ የሀገራችን ጫፍ ላይ ምሽግ ገንብተው የተቀመጡትም ሆኑ እዚህ አፍንጫችን ሥር የአሸናፊነትን ክብር ተጎናጽፈናል እያሉ “ዱታ ነን” የሚሉት ፖለቲከኞች ጭምር ራሳቸውን ፈትሸው ነፃ ቢወጡ ይበጃቸዋል።
ለየትኞቹም “አንደበተ ንክ” ፖለቲከኞች ለሥነ ምግባራቸው ማንቂያ ይጠቅማቸው ከሆነ ጸሐፊው እጅግ የሚወደውን አንድ ብርቱ ጥቅስ ከታላቁ መጽሐፍ ውስጥ ልብ እንዲሉት እነሆ ተጠቅሶላቸዋል።
“አንደበት እሳት ነው። ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና። የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል። የአራዊትና የወፎች፣ የተንቀሳቃሽና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፤ ደግሞም ተገርቷል። አንደበትን መግራት ጥበብ ነው። መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነውና። መራራ ቅንዓትና አድመኝነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ሥፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አለና” (የያዕቆብ መልዕክት ምዕ. 3)። ለማድነቅ ኮስምነን፣ ለማዋረድ ብንፈጥን ውድቀታችንም የዚያንው ያህል ስለሚፈጥን ልብ ያለው ልብ ይበል። ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)