በወንዞች እና በገደላገደሎች ላይ የሚገነቡ ድልድዮች ሰዎችን ፣መንግሥታትን ፣ወዘተ ከብዙ ውጣ ውረዶችና እና ችግሮች መታደግ ይችላሉ:: የምንፈልገው በታ በአጭሩ እና ያለብዙ ድካም እንድንደርስ ያስችሉናል:: ድልድዮች በጥንቱ ግንዛቤ በአብዛኛው የሚያገለግሉት የውሃ አካላትን ያለስጋት ለመሻገር ነበር:: ድልድዮች ይህን አገልግሎታቸውን አሁንም በስፋት ይሰጣሉ::
የድልድዮች አገልግሎት ከዚህም እያለፈ ነው:: በባህር ላይ ጭምር ድልድይ እየተገነባ ይገኛል፤ ምንም የውሃ አካል እንዲሁም አስቸገሪ የመሬት አቀማመጥ በሌለባቸው ከተሞች በስፋት እየተገነቡ ይገኛሉ:: እነዚህ ድልድዮች የከተሞችን የትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ:: ከባህር ወዲህና ወዲያ ያለውን ህዝብ ግንኙነትም ያሳልጣሉ::
ድልድዮቹ እንደ የዘመኑ ስልጣኔና አስተሳሰብ በተለያዩ ግብአቶችና እውቀቶች የተገነቡ ሲሆን፣በርዝማኔያቸው በተሠሩበት ግብአት ፣በከፍታቸው፣ ወዘተ.ይለያሉ:: በዓለማችን በአስደናቂነታቸው ከሚታወቁ ድልድዮች አንዳንዶቹን እናስተዋውቃችሁ::
ዲያንግኩንስሀን ግራንድ ድልድይ
ይህ ድልድይ በቻይና ሻንጋይ ናንይጂን ከተማ ይገኛል:: 102 ማይል ርዝመት በመያዝ በዓለም የአንደኛነትን ደረጃም ተቆናጧል:: ድልድዩ ተሠርቶ ለህዝብ ክፍት የተደረገው እ.አ.አ 2011 ነው፤ በድልድዩ ግንባታም አስር ሺህ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ለግንባታው ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበት በአራት ዓመታት ውስጥ ነው የተጠናቀቀው::
ሚላሉ ቪአዱክት
ይህ ድልድይ በፈረንሳይ ነው የሚገኘው:: ከመሬት በላይ ባለው 343 ሜትር ከፍታም በዓለም የመጀመሪያውን ደረጃ ይዟል:: በክሌርሞንት-ፈርሬጅ እና በቤዚርስ – ናርቦን መካከል ያለውን ትልቅ ሸለቆ ያገናኛል:: በሥነ-ሐውልት አወቃቀር በተለየ እይታ የተሠራው ይህ ድልድይ፣ እ.አ.አ 2004 ላይ ነው አገልግሎት መስጠት የጀመረው::
ድልድዩ ከውሃ በላይ የተገነባ ሳይሆን አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥን ለመሻገር በሚል የተገነባ ነው:: ጭጋግ ባለ ጊዜ በዚህ ድልድይ መሻገር ሰማይን ሰንጥቆ የማለፍ ያህል እንዲሰማ ያደርጋል:: ድልድዩ ሦስት የዓለም ሪኮርዶች የተሰበሩበት እንደሆነም የሲኤንኤን መረጃ ያመለክታል::
ሪብልሄድ ቪያዱት
ከሙርላንድ በታች 32 ሜትር ከፍታ ያለው ድልድይ የተገነባው 24 የድንጋይ ቅርፅ ባላቸው ምሰሶዎች ነው:: ሪብልሄድ ቪያዱት በእንግሊዝ ከሚገኙ ድልድዮች የቪክቶሪያ ኢንጅነሪንግ ምሳሌ ተደርጎ ይወሰዳል:: ድልድዩ እ.አ.አ ከ1870 እስከ 1874 መካከል የተገነባ ሲሆን፤ የድልድዩ ሁለተኛ ክፍል እ.አ.አ 1988 ተገንብቷል:: የድልድዩ ዋነኛ ክፍል ለባቡር መንገድነት የሚያገለግል ሲሆን፤ በሦስት ተራሮች መካከል ይገኛል:: ድልድዩ ኩምባራና የዮርክሼር ድንበርን ያዋስናል::
ቫስኮ ደጋማ ድልድይ
በፖርቱጋል የሚገኘው ይህ ድልድይ አስር ማይል ይረዝማል:: ድልድዩ ሰሜኑንና ደቡባዊውን ፖርቱጋል ይገኛል:: ከአውሮፓ በርዝመት ቀዳሚውን ደረጃ የሚይዝ ሲሆን፣ አገልግሎት መስጠት የጀመረው እ.አ.አ 1998 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ:: ስያሜው የተሰጠውም በ15ኛው ክፍለ ዘመን ዓለምን በማሰስ በሚታወቀውና ህንድን ካገኘው ቫስኮ ደጋማ በመነሳት ነው:: በታጉስ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድዩ፣ በአካባቢው ያለው ከፍተኛ ንፋስ ድልድዩን በእግር ማቋረጥ አዳጋች ያደርገዋል::
ቢፓንጃንግ ድልድይ
ከ560 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ቢፓንጃንግ ድልድይ ወይም ዱግ ድልድይ በቻይና ሊፓምሹ እና ኪውንጃንግ ከተሞች መካከል ይገኛል:: የድልድዩ መገንባት የጉዞ ሰዓትን የቀነሰ ሲሆን፤ ለመገንባት 88 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል::
ጎልደን ድልድይ
እ.አ.አ 2017 ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው በቪየትናም የሚገኘው ጎልደን ድልድይ 150 ሜትር ርዝማኔ አለው:: ድልድዩ የተሠራበት የንድፍ ሁኔታ ልዩ በመሆኑ የቱሪስቶችን ቀልብ ይስባል:: በዳናንግ አቅራቢያ ከሚገኝ ተራራ ላይ የተገነባው ጎልደን ድልድይ ትላልቅ እጅ በሚመስሉ ድንጋዮች ላይ የተሠራ ነው::
ፖንት ዱ ጋርድ አኳዱት
በድሮ ጊዜ ከተገነቡ ድልድዮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ይህ የፖንት ዱ ጋርድ አኳዱት ድልድይ የተገነባው በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት እንደሆነ ይገመታል:: ድልድዩ የተገነባው ለኒምስ ከተማ ውሃ ማመላለሻነት እንዲያገለግል ታስቦ ነው:: 50 ሜትር ከፍታ እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ሲሆን፣ ግንባታው በለስላሳና በቢጫ የኖራ ድንጋይ የተከናወነ ነው:: እ.አ.አ 1840 በፈረንሳይ መንግሥት ጥንታዊ ድልድይ ተብሎ እንዲመዘገብ ተደርጓል::
ጎልደን ጌት ድልድይ
በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ይህ ድልድይ፣ የሳን ፍራንሲስኮ ከተማ መለያ ተደርጎ ይታያል:: ድልድዩ አገልግሎት መስጠት የጀመረው እ.አ.አ 1937 ነው:: ብርቲካናማ ቀለም ያለው ይህ ድልድይ ለአገልግሎት ክፍት ሲደረግ ሳምንት የቆየ ፌስቲቫል ተከናውኖበታል:: ድልድዩ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘው በንድፍ ሥራው ሳይሆን፣ ከእ.አ.አ 1937 ጀምሮ አንድ ሺህ 700 ሰዎች ከድልድዩ ዘለው ራሳቸውን ያጠፉ በመሆናቸው ነው:: እ.አ.አ 2017 ላይ ሰዎች ከድልድዩ ዘለው ራሳቸውን እንዳያጠፉ የሚያደርግ ግንባታ ተከናውኖበታል::
ኸርትላንድ ወይም ኒው ቡርነስዊኪ ድልድይ
ኸርትላንድ ወይም ኒው ቡርነስዊኪ ድልድይ በካናዳ ይገኛል:: እ.አ.አ 1901 ነው ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው:: ድልድዩ ብዙ ከተሞችን በማዳረስና ጥንታዊ ድልድይ በሚል እ.አ.አ 1980 እውቅና ተሰጥቶታል:: ድልድዩ 390 ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች በሚኖሩባቸው መንደሮች መካከል የሚገኝም ነው:: ነዋሪዎች ድልድዩ ከብዙ ነገር ጋርዶኖል የሚል ቅሬት በግንባታው ላይ እንደሚያሰሙ ይነገራል::
ኢሺማ ኦሃሺ ድልድይ
የዚህን ዝነኛ ድልድይ ምስል ሲመለከቱ መኪና በፍጥነት ማሽከርከር ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ይረዳሉ:: የመጽሐፍን ሽፋን በማየት ብቻ ስለመጽሐፉ ይዘት መናገር እንደማይችል ሁሉ የድልድዩን ስፋት በማየት የፍጥነት መንገድ ነው ተብሎ መገመት አይቻልም:: ይህ ድልድይ በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታ ጠባብ የሞተር-መንገድ የሚመስል ሲሆን፤ አንድ ተኩል ማይሎች ያህል ርቀት አለው:: ማሱሴን እና ሳካሚቲንቶን የሚያገናኘው ኢሺማ ኦሃሺ ድልድይ በጃፓን ትልቅ የሚባለው ድልድይ ነው::
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2012
መርድ ክፍሉ