ለአንድ አገር እድገት ባህልና አርክቴክቸር ወሳኝ ናቸው:: የሰው ልጆች ባህል ለተከታዩ ዘመን ካበረከታቸው መካከል አርክቴክቸር በዋነኝነት ይጠቀሳል:: በታሪክ የሚጠቀሱት ሕንፃዎች የሁለቱ ድምር ውጤት መሆናቸው እሙን ነው:: ከፍተኛ ራእይ ያላቸው የጥንት መሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር በቅርስነት የተመዘገቡ ሕንፃዎች፣ ድልድዮች፣ ወዘተ አስገንብተዋል:: በምሳሌነትም በግብፅ የሚገኘውን ፒራሚድ እንዲሁም የቀድሞ ሮማን ኢምፓየር ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች የሚገኙትን ሕንፃዎች መጥቀስ ይቻላል::
እነዚህ የጥንት ግንባታዎች አሁንም ድረስ ታሪካዊነታቸውን ጠብቀው ይገኛሉ:: ከዚህ ውስጥ የእንግሊዙ የሀርድያን ግንብ፣ታላቁ የቻይና ግንብ እና በኮንስታንቲኖፖል የሚገኘው ቲዎዶሳን ግንብ ይጠቀሳሉ:: በተጨማሪም በዚህ ዘመን ከሰሜን አፍሪካ እስከ ደቡባዊ ቱርክ ድረስ የተገኑበትን ትያትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶችና ስታድየሞችንም መጥቀስ ይቻላል:: ሁሉም የስነ ሕንፃ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ናቸው::
የአርክቴክቸር ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወሰደው ከግብፅያውያን እንደሆነ ይነገራል:: ለመጀመሪያ ጊዜ አርክቴክቸር ሥራ ላይ የዋለውም በግሪክ እንደሆነ ይነገራል:: በመቀጠል ወደ ሮማን ኢምፓየር በመዛመት ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ እንደመጣ ይገለጻል:: ከዚያም በተለያዩ ሀገሮች ከተሞች የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን፣ የኦፔራ ቤቶች እና የህዝብ ቤተ መፅሐፍት ቤቶችን በአስደናቂ መንገድ መገንባት ተጀመረ:: የህንድ አርክቴክት ሥራ የተለያዩ ቀመሮችና ህጎች ሲኖሩት፣ በሀገሪቱ የተሠሩት ቤተ እምነቶች በአጠቃላይ በዚህ መንገድ በመገንባታቸው አሁንም ድረስ ተፅዕኖ ፈጥሪ ሆነው ይገኛሉ::
የመጀመሪያው አርክቴክት ከብዙ ሺ ዓመት በፊት የኖረ ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: ይህ አርክቴክት ግንባታዎችን በማቀድና ንድፍ በማውጣት የአርክቴክት ሙያን እንዳስተዋወቀ ይነገራል:: የእጅ መሳሪያዎች በዘመናዊ መሳሪያዎች ከመተካታቸው በፊት የሰው ልጅ በጭቃ ወይም በሌሎች ቁሳቀስ ቤት ይሠራ ነበር:: የአሁኑ ዘመናዊ የሚባለው ሰው የመጀመሪያው አርክቴክት አስትሮኖሚካል እንደሚሆን ግምት ይሰጣል:: በታሪክ ተመዝግቦ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም የመጀመሪያዎቹ አርክቴክቶች የተለያዩ ሰዎች ናቸው ተብሎ ይታመናል::
የመጀመሪው የታወቀ አርክቴክት
የታሪክ አጥኚዎች ኢምሆቶፕን ያውቁታል:: ከክርስቶስ ልደት በፊት 2600 ላይ እንደኖረም ይነገርለታል:: ኢምሆቶፕ በግብፅ የፈርኦናውያን መቃብር የሆነውን ፒራሚድ ንድፍ የሥራ ሲሆን፤ የመጀመሪያው አርክቴክት ተደርጎም ይወሰዳል:: የእሱ ሥራ ቀጥሎ ቅንጡ ፔራዶች እንዲሠሩ መንገድ ከፍቷል:: ኢምሆቶፕ ከመቶ ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ ግብፃውያን ለእዚሁ አርክቴክት እውቅና ሰጥተውታል::
የመጀመሪያው የግሪክ አርክቴክት
የግሪክ አርክቴክቸር የተወሰደው ከማይሳንያን ባህል ሲሆን፣ ይህ ባህል በሮማን፣ ፕርሽያንና ሌሎች የቅርብ ስልጣኔዎች ላይ አሻራውን እንዳሳረፈ ይነገራል:: የፕሌቶራን ግንባታ የሠራው ሰው የግሪክን ስታይል የያዘ በመሆኑ እስከአሁን ድረስ ሥራው እየተወደሰ ይገኛል:: ነገር ግን የመጀመሪያውን አርክቴክትና የፕሌቶራ ዶሪክ ግንባታን የነደፈውን ሰው ታሪክ ረስቶት ይገኛል::
የቻይና ግንብ ንድፍ ሠሪ
የቀድሞዎቹን የታላቁ የቻይና ግንብ የጀመሪያ ዲዛይነር ታሪክ ረስቷቸዋል:: አርኪዮሎጂስቶች እንደሚናገሩት በሦስተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ይህ የቻይና ግንብ ሃንግቱ በሚባል የግንባታ መስሪያ የተሠራ ሲሆን፣ መገንቢያውም በጥርብ ድንጋይና በእንጨት መሰል ነገር የሚዘጋጅ ነው::
በአሜሪካ የመጀመሪያው አርክቴክት
የመጀመሪው የአሜሪካ አርክቴክት በመባል የሚታወቀው ቤንጃን ሄነሪ ላትሮብ ነው፤ይህ ሰው እ.አ.አ 1764 በእንግሊዝ ነው የተወለደው:: የቤንጃሚን የመጀመሪያው የሕንፃ ንድፍ ሥራ የነበረውና በቶማስ ጄፈርሰን እገዛ የተሠራው የቨርጂንያ ከተማ ሕንፃ ሥራ ነው:: በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ ደቡባዊ ክንፍ ቦታንን ንድፍ ሠርቷል:: በሌላ በኩል በሜሪላንድ ባልቲሞር የሚገኘውን ካቴድራል ሕንፃ ንድፍ፣ በዋንሽንግተን ዲሲ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስትያን እና በፊላደልፊያ የፔንስቪልኖያ ባንክን ንድፍ መሠራቱ ይነገራል:: የነጩ ቤተ መንግሥትን መግቢያ ሥራ ማከናወኑም ይጠቀሳል::
የመጀመሪያዋ ሴት አርክቴክት
እ.አ.አ 1873 በሊልኖኢሰ ኡርባና ቻማፓኝ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የተመረቀችው ሜሪ ሊ ፔጅ በአሜሪካ የመጀመሪያዋ ሴት አርክቴክት እንደሆነች ይነገራል:: በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ልዊስ ብላንቸርድ ቤቴሁን የመጀመሪያው የአርክቴክት ባለሙያ አድርጎ ይጠቅሳል:: ጆን ኤች ሊንሀርድ በፃፈው አርቲክል ሶፊ ሀይድን የመጀመሪያዋ በኮሌጅ ደረጃ የሰለጠነች አርክቴክት ናት ብሎ ገልጿል:: ሀይድን ከማስቹስቴስ ኢኒስትቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ በ1890 እንደተመረቀች በአርቲክሉ ጠቅሷል::
አርክቴክቸር በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ የአርክቴክቸር ሥራ ከክልል ክልል የተለያየ ሲሆን፣ በዚህም በየጊዜው የተለያዩ የሕንፃ ንድፎችና አሠራሮች እንደነበሩ ይገለጻል:: የኢትዮጵያ የሕንፃ ንድፍ ሥራዎች ብዛት ያላቸው ባህሎችና ታሪኮች አሻራ ያረፈባቸው መሆናቸውም ይገለጻል:: በአክሱም ዘመነ መንግሥት፣ ከአረብ፣ ኢንድያ፣ ቱርክ፣ ፖርቱጋል እንዲሁም ጣሊያን ወረራ ጋር በተያያዘ የተለያየ የከተማ አሠራር ተጽእኖ ያረፈባቸው የሕንፃ ንድፎች ሥራ እንዳለ ይነገራል:: እነዚህ የንድፍ ሥራዎች በታሪካዊነታቸው የተመዘገቡና የሚጎበኙ ናቸው:: ለምሳሌነትም የላሊበላ ውቅር አብያተክርስትያናትን፣ የአጼ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥትና የንጉሣውያን መኖሪያ ሕንፃዎችን መጥቀስ ይቻላል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2012
መርድ ክፍሉ