የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ ላሊበላ ከተማ ለሚያደርጉት ጉዞ ዋነኛ ማሳለጫ ሆኖ ያገለግላል፤ የአማራን ክልል በማቋረጥ እስከ ትግራይ ክልል ድረስ ያዘልቃል::ግንባታው በልዩ ልዩ ምክንያቶች በመዘግየቱም የሚጠበቅበትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እየሰጠ አይደለም- የጋሸና ቢልባላ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት::
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የጋሸና ቢልባላ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ተጠሪ መሀንዲስ አቶ ደረጄ ዳንዱ እንደሚገልፁት፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ ከጋሸና አስከ ቢልባላ ያለውን 90 ኪሎ ሜትርና የላሊበላ ማሳለጫን 15 ኪሎ ሜትር ጨምሮ 105 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው::ለግንባታውም 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የመንግስት በጀት ተይዞለት ነው እ.ኤ.አ በየካቲት ወር 2014 ግንባታው በይፋ የተጀመረው::
የቻይናው ሬልዌይ ነምበር ስሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በተቋራጭነት እንዲሁም መታፈሪያና ስፓይስ አማካሪ ስራዎች ማህበር በአማካሪነት ፕሮጀክቱን እያከናወኑት ይገኛሉ::የመንገዱ ስፋትም በገጠር አካባቢዎች በሰባት ሜትር በከተሞች አካባቢ ደግሞ እንደ የከተማዎቹ ስፋትና ሁኔታ 12፣ 19 እና 22 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል::
ተጠሪ መሃንዲሱ እንደሚገልፁት፤ እስካሁን ባለው ከግንባታው ስልሳ ኪሎ ሜትር የሚደርሰው የአስፓልት ኮንክሪት ስራ ተሰርቷል::ከአንድ ድልድይ፣ አምስት የቦክስና ስላቭ ካልቨርት እንዲሁም ሃያ ፓይፕ ካለቨርት ስራዎች በስተቀር አብዛኛዎቹ የስትራክቸር ስራዎችም ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል:: ከሰባት ድልድዮች ውስጥ ስድስቱ ተጠናቀዋል::ከሃያ ሁለት ቦክስ ካለቨርት ሃያ አንዱ ተጠናቀዋል::ከ320 ፓይፕ ካልቨርት ውስጥ ሶስት መቶ ያህሉ ተሰርተዋል::ከስልሳ ሰባት ስላቭ ካልቨርት ውስጥ ደግሞ 64 ያህሉ ተጠናቀዋል::
ሌሎች ከአስፋልት በፊት የሚሰሩ የሰብ ቤዝና ቤዝ ኮርስ ስራዎች ከ105 ኪሎ ሜትሩ ውስጥ 100 ኪሎ ሜትር ያህሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የመንገዱ አጠቃላይ የፊዚካል አፈፃፀም 90 ከመቶ ደርሷል::የፋይናንስ አፈፃፀሙም ከፊዚካል አፈፃፀሙ ጋር ተቀረራቢ ነው፤ 91 ከመቶ ደርሷል::
ተጠሪ መሃንዲሱ እንደሚሉት፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት በአርባ ስምንት ወራት ውስጥ ወይም በሶስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እ.ኤ.አ ነሃሴ ወር 2017 ድረስ መጠናቀቅ ነበረበት፤ ይሁንና ለስራ ተቋራጩ ተጨማሪ ስራ በመሰጠቱና ይህም ጊዜ በመውሰዱ ፕሮጀክቱ መራዘም የግድ ሆኖበታል::
በኮንትራት ውሉ መሰረት መንገዱ የሚሰራበት ደረጃ በደብል ሰርፌስ ትሪትመንት ነበር፤ ነገር ግን ከአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ያነሰ በመሆኑ የመንገድ ስራ ደረጃው ይቀየር በሚል የአካባቢው ህብረተሰብ ተቃውሞ አሰምቷል፤ አመጽ ተቀስቅሶም ነበር፤ በኮንትራክተሩና አማካሪው ካምፖች ላይም መጠነኛ ጥቃት ደርሰዋል::በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቱ ለስድስት ወር ቆሟል::ለሶስት ዓመት ያህል ጊዜም እስካሁን ድረስ ሊዘገይ ችሏል::
ፕሮጀክቱ አንድ ከተማ አስተዳደርና ሶስት ወረዳዎችን እንደሚነካም አስታውቀው፣ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ በከተማ አስተዳደሩ በኩልም ሆነ በወረዳዎቹ በተለይ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ሰፊ ችግሮች አጋጥመውታል ሲሉ ያብራራሉ::አሁንም ይኸው የወሰን ማስከበር ችግር አልፎ አልፎ እንደሚታይ ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመፍታት ከላሊበላ ከተማ አስተዳደርና ከሌሎች የወረዳ አስተዳደሮች ጋር በቅርበት ለመስራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ይላሉ::ፕሮጀክቱ እየተጠናቀቀ በመምጣቱ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታዩ የግንዛቤ ክፍተቶች እየቀሰኑ መምጣቸውን ያብራራሉ::
እንደ ተጠሪ መሃንዲሱ ገለፃ ፤ በቀጣይ ቀሪውን የፕሮጀክቱ 45 ኪሎ ሜትር መንገድ አስፓልት የማንጠፍ ስራ ይሰራል፤ ቀሪ አንድ ድልድይ እና የስላቭ ካልቨርት ስራዎችም ይጠናቀቃሉ፤ በመንገዱ ግራና ቀኝ ያሉ ዲቾች እና ቀሪ ወደ መንደር የሚያስገቡ መንገዶችን የማጠቃለል ስራዎችም ይሰራሉ፡፡
ተጠሪ መሃንዲሱ እንደሚናገሩት፤ ስራ ተቋራጩ ፕሮጀክቱን ከፍፃሜ ለማድረስ በሚቻለው መጠን ሁሉ እየሰራ ይገኛል::የአብዛኛው የመንገዱ ክፍል ግንባታም ተጠናቅቋል::መጪው የክረምት ወቅት እንደ ተገባደደም በቀሪዎቹ ሶስትና አራት የበጋ ወቅት ወራት ቀሪው የአስፓልት ስራ ተሰርቶ ይጠናቀቃል::አሁን ባለው የአፈፃፀም ደረጃ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ካልገጠሙት በስተቀር ፕሮጀክቱ እስከ መጪው ጥር ወር 2013 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ይደረጋል::
የላሊበላ ከተማ የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኗ መጠን መንገዱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን ለመጎብኘት ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የሚመጡ ቱሪስቶችን ፍሰት በመጨመር የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንደሚያነቃቃ ይጠበቃል::የላሊበላና አካባቢውን ህብረተሰብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ይገመታል::
ፕሮጀክቱ ከጋሸና አንስቶ ቢለባላን አልፎ ሰቆጣ የሚደርስ በመሆኑ የአማራ ክልልን ከትግራይ ክልል በማገናኘት የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ትስስር እንደሚያፋጥንና በተመሳሳይም አርሶ አደሩም ምርቱን በቀላሉ ወደ ከተሞች በመውጣትና ወደ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያስችልም ይጠበቃል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2012
አስናቀ ፀጋዬ