አርክቴክት ዳዊት በንቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1987 ዓ.ም በአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከኢትዮጵያ መንግስት ባገኙት ስኮላርሽፕ በሕንድ አገር በኢንዲያን ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ሩርኪ መንግሥት በኪነ ሕንጻ ተምረው ተመርቀዋል። የመጀመሪያው ዲግሪያቸውን ካገኙ አንስቶ እስከ አሁን ለ24 ዓመታት በአዳማ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞ ስሙ ሕንጻ ኮሌጅ ተብሎ በሚጠራው በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ከተማ ልማትና ህንጻ ኮንስተራክሽን ኢንስቲትዩት እያስተማሩ ናቸው።
የአዲስ አበባን የትናንት ማንነት፤ የከተማዋን አነሳስ፤ እነማን ከጎጆ መንደርነት እንዳወጧት፤ እድገቷ ትናንትና ዛሬ ምን እንደሚመስል፤ አርክቴክቸር (ኪነሕንጻ) እንዴት ከፖለቲካ፤ ከኢኮኖሚና ከታሪክ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው፤ እየሞተም እንዴት እንደሚነሳ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ያጋሩንን በዛሬው እትማችን ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ከኪነ ሕንጻ (አርክቴክቸር) መምህርነትዎ ጋር በተያያዘ የሰሩባቸውን ቦታዎች ቢገልጹልን ?
አርክቴክት ዳዊት፡- በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አስተምሬአለሁ። በኢትዮጵያ ኪነ ሕንጻ ላይ ጠለቅ ያሉ ስራዎች ከዚህ ቀደም ተሰርተው አያውቁም። በጽሁፍ የተቀመጠ የተላለፈልን ማስረጃ የለንም።
የራሳችን የሆነውን ከጥንት ጀምሮ የነበረውን እንዲሁም አሁናዊውን ኪነ-ህንጻ ለማወቅ ሰፊ የምርምር ስራዎችን እሰራለሁ። የኢትዮጵያንን አሁናዊ (ኮንቴምፖራሪ) ኪነ ሕንጻ በተመለከተ በአዲስ አበባ በጎተ ኢንስቲትዩት እና በአሜሪካ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ኤግዚቢሽን አሳይቼአለሁ። በተለይ በኪነ ሕንጻና በአካባቢ ጉዳዮች ላይ ሶሻል ሚዲያውን በመጠቀም የአክቲቪዝም ስራዎች እሰራለሁ።
ኢትዮጵያን አርክቴክቸር ኤንድ አርባኒዝም የሚባል ቡድን አለን። በዚህም እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሳታፊ አለን። ዋናው ነጥብ ትውልዱ የሀገሩን ኪነ ሕንጻ ታሪክ እንዲያውቅ፣ በከተማው በሚሰሩ ዲዛይኖች እና ከተማ ፕላኖች ላይ የያገባኛል ስሜት እንዲኖረው፣ እንዲሁም በራሱ የሚኮራ እንዲሆን ለማድረግ እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጥንቱና የአሁኑ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር እንዴት ይገለጻሉ?
አርክቴክት ዳዊት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ጥንታዊ የሆኑ የላስታ ላሊበላን፤ የሀረሩን ጀጎል፤ የጎንደሩ ፋሲለደስን፤ የአክሱም ሐውልትን ብቻ ሳይሆን አሁንም አለን የምንለው አይነተኛ አርክቴክቸር ይታያል።
አዲስ ዘመን፡- የኋላ ታሪኩን በዝርዝር ቢገልጹልን ?
አርክቴክት ዳዊት፡- የኢትዮጵያ ኪነ ሕንጻ እጅግ በጣም ከሩቅ ነው የሚጀምረው። ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረ ኪነ ሕንጻ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ። በአክሱማውያን ጊዜ የነበሩ አብያተ ክርስትያናትና የሙስሊሙም ሥልጣኔዎች አሉ። የአርጎባ ፤ የሸዋ ፤የሀረር ጀጎል ስልጣኔ፤ የድሬ ሼክ ሁሴን ኪነ ሕንጻዎች አሉ።
ይህንን ዝርዝር መረጃና አሰራሩን አልመዘገ ብነውም። የተጸፈ የተላለፈ ነገር የለንም። በጣም ሰነፎች ነን። ስለእኛ የፃፉት የራሳችንን ታሪክ የሚነግሩን ለጥናትም ሆነ ለምርምር የምናገኘው ከውጭ ጸሀፍትና ተመራማሪዎች ነው። እነዚህ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው የኖሩ ሀገር ጎብኚዎች ወይንም አጥኚና ተመራማሪዎች ወይንም በኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ የቅርብ ሰው ሁነው ሲሰሩ የነበሩ የተለያየ ሀገር ዜግነት የነበራቸው ናቸው። ከእነሱ መጻሕፍት ነው ስለእኛ ኪነ ሕንጻም ሆነ ስለሌላው ታሪካችን ብዙ መረጃ የሚገኘው።
በየዘመናቸው የነበሩት የእኛ ጸሀፊዎች ነገስታቱን የማወደስ የዜና መዋእል ስራ ነበር እየጻፉ የሚያስቀምጡት። የነገሥታቱ ታሪክና ሀተታ (ክሮኒክልስ) አንድን ወገን አድንቆ አወድሶ የሚጽፍ ስለነበር ብዙም ሀገራዊ ታሪክን ስልጣኔን ኪነ ሕንጻን የያዘ አልነበረም። ስለእኛ ታሪክ አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮችን ስናነሳ የግድ የነጮች ጽሁፎችና መጻሕፍትን በዋቢነት እንጠቅሳለን፤ በራሳችን ሰዎች የተጻፈ የለንማ፤ ያ ታሪክ አሁንም አልተቀየረም። የኪነ ሕንጻችን ታሪክ ተሰንዶ (ዶክመንትድ ሆኖ) አልተቀመጠም። ይህ ወደፊት ይለወጣል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ኪነ ሕንጻ ላይ ኤግዚቢሽን አዘጋጅተው እንደነበር አንስተዋል። የት እና እንዴት እንደተዘጋጁ ቢገልጹልን ?
አርክቴክት ዳዊት፡-2016 (እኤአ) በአሜሪካ አሁናዊው የኢትዮጵያ ኪነ ሕንጻ (ኮንቴምፖራሪ ኢትዮጵያን አርክቴክቸር) የሚል ትልቅ ኤግዚቢሽን ፍሎሪዳ ሚያሚ ውስጥ አዘጋጅቻለሁ። ኢግዚቢሽኑን በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የተለያዩ ሀገር ዜጎች ጎብኝተውታል፤ አስገራሚ ነበር። ይህም ሚያሚ ከተማ በሚታተሙ ጋዜጦች ላይ ወጣ። ጋዜጦቹ በአድናቆት ነው የጻፉት። የእኔ ዓላማ የሀገሬን አርክቴክቸር ማስተዋወቅ ስለነበር ተሳክቶልኛል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን አሁናዊ ኪነ ሕንጻ ፈረንጆቹ እንዴት ነው የሚረዱት?
አርክቴክት ዳዊት፡- አሁናዊውን የእኛን ኪነ ሕንጻ ስናነሳ የድህረ ምእተ ዓመቱ ኪነ ሕንጻ (ፖስት ሚሊኒየም አርክቴክቸር) ነው የሚሆነው። ከእ.ኤ.አ. 2000 አመት በፊት ወዲህ የተሰሩ አስገራሚ ሕንጻዎችን አሉን። እኛን የሚያደንቁን ስለእኛ የሚጽፉት የውጭ ሰዎች ናቸው። አለመታደል ሁኖ ከጥንት ጀምሮ የኖረውን የራሳችን የሆነውን የኪነ ሕንጻ እውቀታችንን አክብረን ጠብቀን ተንከባክበን አልያዝነውም። ስንትና ስንት ትውልድ አቆራርጦ ሲተላለፍ የመጣ ነው። በእጅ ያለ ወርቅ አያደምቅ እንደሚባለው መሆኑ ነው። አሁንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ያልጠፉ ጥቂት ቢሆኑም፣ ከኮንክሪት ጫካ መካከል አስገራሚ ህንጻዎች አሉን። ያሉትን መጠበቅ፤ መዘገብ፤ ለሕዝባችን ማስተዋወቅ፤ በሰነድ ሰፍረው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- በሀገራችን በኪነ ሕንጻ ወርቃማ የሚባሉት ዓመታት የትኞቹ ነበሩ ?
አርክቴክት ዳዊት፡-ኪነ ሕንጻ ከፖለቲካውና ከኢኮኖሚው ውጭ ተነጥሎ አያድግም። በእኛ 1950 ዓ.ም መጀመሪያዎቹ በፈረንጆቹ 1960ዎቹ (እኤአ) አካባቢ ወርቃማ ጊዜ ነበረን። ይህ ጊዜ በሙዚቃው፤ በስነ ጥበቡ፤ በኪነ ሕንጻው በብዙ መስክ አዳዲስ ለውጦች የጎመሩበት ነበር። የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንጻ ተአምር ነው። በ1960ዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ አርቱሮ ሚዜዴሚ፤ ሄንሪ ሾሜ፤ ዛልማን ኤናቭ የሚባሉ እውቅ አርክቴክቶች ነበሩ። ቤተመንግስቱን የሰራው ሀገራችን ውስጥ የቆየ ኢጣሊያናዊ ነው። ውጭ ጉዳይንና ኢሲኤን የሰራው ዛልማን ኤናቭ የሚባል የእስራኤል አርክቴክት ነው። የ1960ዎቹ ዘመን በራሱ በጥልቀት መጠናት ይኖርበታል።
በኪነሕንጻ ለመታወቅ ኢኮኖሚው መፈንዳት አለበት። ኢኮኖሚው ሳያድግ ኪነ ሕንጻ አያድግም። የእኛ ኢኮኖሚ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ቡም አደረገ (ጎመራ)። ሕንጻዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። ባሕርዳር ያለው የአማራ ክልላዊ መንግስት መቀመጫ ሕንጻ ያስገርማል፤ በግንባታው ሂደት የሀገር ውስጥ ቁስ ተጠቅመዋል። ኪነ ሕንጻዊ ፋይዳ ያላቸው ስራዎች ሰርተዋል። ኪነ ሕንጻን በተመለከተ የተለየ ውበት ሲኖረው ሌላ ጋ የማታየው አይነት ስራ ሲሆን ያስደንቅሀል፤ ያስደምምሀል። ምንድነው? የት ነው የገባሁት? ትላለህ ፤ጥበቡ እውቀቱ ያናግርሃል፤ በምን ሰሩት ያስብልሀል። ለምሳሌ ላሊበላ ለምንድነው የሚደንቀን? ይቺን ነገር ያዝልኝ።
ለስህተት ቦታ የለውም (ዜር ኢዝ ኖ ሩም ፎር ሚስቴክ)። ለስህተት ቦታ የሌለው አርክቴክቸር ነው ብለህ ብትደመድመው ትችላለህ። ላሊበላ ቢሳሳት ኖሮ በሲሚንቶ ነበር እንዴ የሚሰራው፤ ለምንድነው ላሊበላ የሚያስደንቅህ ለስህተት ቦታ የለውም። ከአንድ ድንጋይ ነው የተሰራው። ግንባታ ቢሆን ትነቅለዋለህ፤ ቁፋሮ ነው። በቁፋሮው መደነቅ አለብህ። ይሄ እንግዲህ ከማቴርያል አንጻር ነው። የአክሱም ወጥ የድንጋይ ጥርቦቹ በምን ተሰሩ? እንዴት ወደላይ ቀጥ አድርገው አወጡት? ብለህ ስትጠይቅ አንድ ራሱን የቻለ ተአምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኪነ ሕንጻ እንደ ባሕልና ቋንቋ ይቀላቀላል የሚሉ አሉ ቢያስረዱን ?
አርክቴክት ዳዊት፡- በጣም ንጹህ ነው የምትለው ባሕል የለም። ይወራረሳል፤ ይጋባል፤ ይዳቀላል፤ ይዋለዳል።
በኪነ ሕንጻም ከወሰድነው ይሔው ነው፤ ንጹህ የሚባል የለም። ቅልቅሎች ነን (ሀይብሪድ)። ቋንቋችን አፍሮ ኤሽያቲክ ነው። እኛ የዓለም አቀፉ ቅልቅል በመሆናችን ልንኮራ ይገባል። ሙዚቃችንን ስታይ ለዓለም ምን አበረከትን ስንል አፍሮ ጃዝ፤ ፈንኪ ሙዚቃን (የተቀላቀለ) አበረከትን። አሁን ኪነ ሕንጻም እያበረከትን ነው። የድሮዎቹም የቅልቅል ውጤቶች ናቸው።
አማርኛን ስታየው 30 በመቶ ከኩሺቲክ ቋንቋ ተበድሮአል። ቀ፤ጨ፤ጰ፤ጠ፤የሚሉትን ፊደላት ግእዝ ውስጥ አታገኝም። ምሳሌ ለመስጠት ያህል ነው። ኪነ ሕንጻችንም ውስጥ ከሌሎች ወደ እኛ የመጡ ብዙ ነገሮች አሉ። የእኛን ደግሞ ካየህ የአክሱም ስልጣኔ በዝርዝሩ ሲታይ አይነተኛ (ቲፒካል) የኢትዮጵያ መገለጫ ነው። እንጨትና ድንጋይን ተጠቅሞ ኪነ ሕንጻ መስራት ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ከአክሱምም በኋላ ያልተደገመ ሚስጢራዊ ነገር ነው። ዛሬ ላይ ሆነን ስናይ ደግሞ ኪነ ሕንጻን ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የበለጠ ሊሰሩት ይችላሉ። ይጠበቡበታል። እንችላለን፤ ምናልባት የማንሰራው ታምነን ስለማይሠጠን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቀድሞው ዘመን የራሳችን አርክቴክቶች አልነበሩንም። የውጭ ዜጎች ናቸው መሰረት የጣሉትና የሠሩት። ዛሬ ኢትዮጵያ ብዙ አርክቴክቶች አሏት። ምኑን ነው የማይሰጧችሁ?
አርክቴክት ዳዊት፡- ስራው ሲሰጠን መስራት ይቻላል። በቀደመው ዘመናዊ ጊዜ ኢትዮጵያዊ አርክቴክት አልነበረንም። ዛሬ ኢትዮጵያ የተካኑ የበቁ የኪነሕንጻ ባለሙያዎች (አርክቴክቶች) አሏት። በቀድሞው ዘመናዊው ጊዜ የሰሩት ታዋቂ አርክቴክቶች የውጭ ዜጎች ነበሩ።
ሚዜዴሚ የንጉሱ አርክቴክት ተብሎ ይታወቅ ነበር። ማዘጋጃ ቤትን፤ኢሲኤን ሰራ። እሱን ኢጣሊያዊ ማለት አይቻልም። እድሜ ዘመኑን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያሳለፈው። በአብዮቱ ጊዜ የሚሰራው ስላጣ ነው ወደ ሀገሩ የሄደው። በኪነ ሕንጻ ስራው ላይ የኢትዮጵያ ተጽእኖ (ኢንፍሉወንስ) አለው፤ ጥበብ ይሰራል። ይጠበብበታል። የኢትዮጵያን ማንነት በኪነ ሕንጻ ሙያው ይገልጸዋል። ከአስር ዓመት በፊት ነው የሞተው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ግዙፍ አሻራ አለው። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የምታየውን የ1950ዎቹ አብዛኛዎቹን ማለት ይቻላል ብዙ ሕንጻ ገንብቷል። በዋነኛነት ማዘጋጃና ኢሲኤ የታወቁ ሕንጻዎቹ ሲሆኑ፣ ፒያሣ ላይ በርካታ የታወቁ ሕንጻዎች አሉት። ለእዚህም ራስ መኮንን ድልድይን ተሻግሮ የሚገኙት ሁለት የጥንት በጉልህ የሚታዩ ሕንጻዎች ይጠቀሳሉ።
አዲስ ዘመን፡- በውጭዎቹ ባለሙያዎች እግር ኢትዮጵያውያን ተተክተው ነበር ?
አርክቴክት ዳዊት፡-የኢትዮጵያን አርክቴክቸር ዘመናዊነትን (ሞደርኒዝምን) ስናየው በአጼ ምኒሊክ ጊዜ የተጀመረ ነው። አጼ ምኒሊክ ምን አደረጉ መሰለህ፤ የአራዳው ጊዮርጊስ ቤተክርስትያንን እየው። ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን የጣሊያን ኪነ ሕንጻ ተጽእኖ አለበት። ኦክታጎናል ቅርጽ ቢኖረውም ሙሉ በሙሉ ስራው ኢትዮጵያዊ አይደለም።
ማሕሌት፤ መቅደስ፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ተደርጎ የሚሰራው ደግሞ ኢትዮጵያዊ ኪነ ሕንጻ ነው። ቤተክርስትያኑ በአዲስ መልክ ከመሰራቱ በፊት በሳር ክዳን የተሰራች ትንሽ ቤተክርስትያን ነበረች። ጣሊያናዊ አርክቴክት መጣና ስራው ተሰጠው። በጣሊያን ኒዮ ክላሲካል በሚባል ዘይቤ ቤተክርስትያኑን ሰራው።
ይህን ተከትሎ የሚገራርሙ ስራዎች አዲስ አበባ በነበሩ አርመኖች መሰራት ጀመሩ። ሚናስ ኬርቤኪያን የተባሉ አርመናዊ ጣይቱ ሆቴልን ሰሩ፤ ከዛ በኋላ ኪነ ሕንጻ ፒያሣ ላይ በጣም መስፋፋት ጀመረ። ታዋቂው የህንዳዊ ነጋዴ መሀመድ አሊ ቤቶች ነበሯቸው። እነዚህን የመሰሉ ጥንታዊ ህንጻዎች ከመሀሙድ ሙዚቃ ቤት ወረድ ብሎ ቀጭኗ መንገድ ግራና ቀኝ ሶፋዎች የሚሰሩበት ቦታ ላይ ይገኛሉ፤ አስደማሚ ሕንጻዎች ናቸው። የሕንዶች ሰፈር ነው ያኛው።
በጠላት ወረራ ዋዜማ አፄ ኃይለስላሴ ከኢትዮጵያ ወጥተው ጣሊያን ሳይገባ ባሉት ሶስት ቀናት በ1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ በተፈጠረው የመንግስት አልባነት ዝርፍያ ነገሰባት፤ እብደት ነገሰባት፤ የዚህ ቪዲዮው አለ፤ ብዙ ሕንጻ ተቃጠለ።
ሲኒማ ኢትዮጵያ ተቃጥሎ እንደገና በጣልያን ጊዜ በአርማታ የተሰራ ህንፃ ነው። በድንጋይ ከተሰሩት ህንጻዎች የተረፉት እንደ ኬርኮፍ ሕንጻ ያሉት ናቸው። ያኔ ከእሳት የተረፉት ሕንጻዎች በጣም ጥቂት ናቸው።
ጣሊያን ሳይገባ በፊት የተሰሩ የኪነ ህንፃ ፋይዳ ያላቸው የእንጨት ቤቶች ነበሩ። አሁን ቀበሌ ወርሷቸው የኪራይ ቤት ሆነው እየወዳደቁ ያሉ በአርመኖችና በሕንዶች የተሰሩ ቤቶች አሉ። መጠበቅ ይገባቸው ነበር። ጣሊያን ከመጣ በኋላ የተቃጠሉትን ቤቶች የሚያሳዩ ብዙ ፎቶዎች አሉኝ።
አዲስ ዘመን፡- ጣሊያን ጥንታዊዋ አዲስ አበባ በእሳት ከጋየች በኋላ ምን ሰራ ?
አርክቴክት ዳዊት፡- በእሳት የወደመችውን ከተማ የአመድ ክምር ጠራርጎ አሁን ያለውን የኤሌክትሪክ ሕንጻ እንደገናም አየር መንገድ ያለበትን ሕንጻ ባወደሙት ምትክ ሰራ። ከሲኒማ ኢትዮጵያ ወደዚህ ፒያሣ ከርቩ ላይ ከዳርማር ሕንጻ አለፍ ስትል በጣሊያን ጊዜ ሳትቃጠል የቀረች ቤት አለች። ያ ሁሉ ቤት በግርግር ሲቃጠል ያቺ ቤት ብቻ ተርፋለች። ዛሬም አለች። ሄዶ ማየት ይቻላል።
በተረፈ ወደ ናዝሬት ት/ቤት አካባቢ ብትሄድ፤ ከስድስት ኪሎ ብትመጣ ታሪካዊና የተተው /የተውናቸው/ አሻራቸው ግን የማይደገም የአርመን የግሪክና የሕንዶች አሻራ ያለባቸው የእንጨት ቤቶች አሉ።
ከዚያ በኃላ ጣሊያን ሀገራችን ገብቶ አምስት አመት ሲቆይ በጣም ሰራ። ካሣንችስን ፤ ፖፑላሬን፤ጤና ጥበቃን አሁን እያረጁ እየፈረሱ ያሉ ቤቶችን ሰራ።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ጥንታውያን ባለብዙ ታሪክ ቤቶች ቅርስ ተደርገው ሊጠበቁ አይገባም ነበር ?
አርክቴክት ዳዊት፡- አዎን መጠበቅ ያለባቸው ትላልቅ ቅርሶች ናቸው። እንዳለመታደል ሆኖ ታሪክን በመጠበቅ ረገድ ድሀ ሀገሮች ጉዳያቸው አይደለም። ድህነት የሚያተኩረው እንጀራ ፍለጋ ላይ ብቻ ነው።ታሪኩን በአግባቡ አይጠብቅም። የውጭዎቹ በዚህ ረገድ ታሪካቸውን ይጠብቃሉ። ይንከባከባሉ። የቱሪስት መስህብ አድርገው በተደራጀ ሁኔታ ገቢ ያገኙባቸዋል። እኛም ታሪካችንን ለመጠበቅ መታገል አለብን።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ታሪካዊና ጥንታዊ ቤቶች በቅርስነት ተጠብቀው እየታደሱ እንዲኖሩ ለመንግስት ያሳወቃችሁት ነገር አለ ?
አርክቴክት ዳዊት፡- እጅግ በጣም ለታሪክ ለቅርስ ጥበቃ የሚቆረቆሩ ብዙ ዜጎች አሉ። ጉዳዩን እናነሳለን፤ እንነጋገራለን። አሁን ግን የኢትዮጵያን ታሪካዊና ጥንታዊ ኪነ ሕንጻን ለመጠበቅ በቀጣዩ ትውልድም እንዲታወቁ ለማድረግ፤ ከመንግስትም ጋር በዚህ ጉዳይ በቅርበት እየተነጋገሩ መፍትሄዎችን ለማስገኘት ጠንካራ ስራ መሰራት እንዳለበት ተስማምተናል።
የግድ የኢትዮጵያን አርክቴክቸር ታሪክ የሚጠብቅና የሚንከባከብ ማሕበር በሕጋዊነት መስርቶ መንቀሳቀስ የግድ አስፈላጊ ሁኖ ተገኝቷል። ማህበሩን እውን ለማድረግ እየሰራን ነው። እኔም ኪነ ሕንጻ ምንድነው፤ ታሪኬስ ምንድነው የሚለውን በጥልቀት ለማወቅ እየጣርኩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የራስን ታሪክ አለማወቅ ማንነትን አለማወቅ ነው የሚሉ አሉ። የራሱን ታሪክ በውል ሳያውቅ የውጭ ሀገር ታሪክ አድናቂ ሰው ይበዛል። ይህን ከኪነ ሕንጻው አንጻር ቢገልጹልን?
አርክቴክት ዳዊት፡- አሁን የእኛ ሰው የሚያደንቀው ዱባይ ፣ ሻንጋይ ወይ ሌላ ሀገር ሄዶ ሲመለስ ያየውን የተመለከተውን ነው። እኔ ውጭ ኖሬ አይቼዋለሁ፤ ምኑም አይናፍቀኝም፤ አይደንቀኝም። ዋናው ጥያቄ የውጭውን ሀገር የሚያደንቁት የእኛ ሰዎች የራሳቸውን ሀገር ታሪክ በቅጡ ያውቁታል ወይ የሚለው ነው። የራስን ታሪክና መሰረት ማወቅ የሚለው ነጥብ ትልቅ ነገር ነው። ከራሴ ጋር ለገጠምኩት ትግል መነሻው መሰረታዊ ምክንያት አለው።
ምንድነው መሰለህ ስዊዘርላንድ ሄጄ አንድ ዓመት ገስት ሌክቸረር ሆኜ አስተምሬአለሁ። የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ምንድነው ሲሉኝ የባህላዊውን እና የድሮውን ሳወራ የአሁኑስ አሉኝ። ስለአሁኑ አላውቅም። ለእኔ ትልቅ አሳፋሪ ጊዜ ነበር። ማነው ታሪኩን ለማወቅ ላሊበላና ጎንደርን ሄዶ የሚያየው ስትል ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ ሰው አይደለም። አሜሪካ ሄዶ ማንነቱ የጠዘጠዘውና ግራ የገባው ማንነቱን ለማወቅ የሚዳክር ሰው ነው ታሪካዊ ቦታዎችን ሄዶ የሚያየው። ተመልከት የራሱን ትቶ ሰው ወደ ዱባይ ይሄዳል እንጂ ድሬ ሼህ ሁሴን ሄጄ ልይ፤ ጀጎል አርፌ ልምጣ የሚል የለም።
ነጮቹ ናቸው ጀጎል መሄድ የሚፈልጉት። ይሄ የራሳችንን ታሪክና ማንነት ካለማወቅ የሚመነጭ ትልቅ ቀውስ ነው። ውጭ ስንሄድ ምንድነው የሚሆነው? የአንተን ሀገር ታሪክና አሁናዊ ጉዳይ ንገረን ሲባል ለመመለስ አለመቻል በጣም ያሳፍራል። በመጀመሪያው ቀን የሰጠሁት አሳፋሪ ሌክቸር ነበር። ሁለተኛው ላይ ትንሽ ሌላ አርእስት አስገብቼ ምናልባት እነሱ በማያውቁት ጉዳይ ታሪክ ሰርቼ ሰጠሁ። ከዛ በኋላ ግን ትኩረት አድርጌ የራሴን ሀገር የኪነ ሕንጻ ታሪክ ከመሰረቱ ማጥናት ጀመርኩ።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የተለያየ የስልጣኔ ብርሃን እንበለው የፈነጠቀበትን፣ የጎመራበትን የ1950ዓ.ም (የ1960 እ.ኤ.አ) የመጀመሪያው ጊዜ ቢጠቅሱልኝ ?
አርክቴክት ዳዊት፡- በብዙ መልኩ በሀገራችን ኪነ ሕንጻ፤ ስነጽሁፍ፤ ስነስእል፤ ሙዚቃ፣ወዘተ. ታላቅ ለውጦች የተካሄዱባቸው የ1960ዎቹ ዓመታት ናቸው። ጣሊያን በሀገራችን ለአምስት ዓመታት ሲቆይ በኪነ ህንጻው በኩል ብዙ ሰራና በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል አማካኝነት እንዲወጣ ተደረገ። ጣሊያን ከወጣ በኋላ ለረዥም ጊዜ እንቅልፍ ውስጥ ገባን። ከዚህ ጊዜ አንስቶ እስከ 1950ዎቹ ድረስ ለረዥም ጊዜ በሀገራችን ኪነ ሕንጻ አልነበረም። ሀገሪቷ በጦርነቱ ወድማ ነበር። አጼ ኃይለስላሴን ሁሉም ሰው ክዷቸው ነበር። ሕዝቡን አንድ ማድረግ ሕገመንግስት ማርቀቅ የመሳሰሉትን ስራዎች እየሰሩ ቆዩ።
ሀገር በሁለት እግሯ እንድትቆም የማድረግ ስራ ቀላል ሂደት አልነበረም። ኢኮኖሚው ሞቷል። እኛ ጣሊያንን ካባረርን በኋላ በአውሮፓ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተከፈተ በ1941 (እኤአ)። በዚህም የዓለም ኢኮኖሚ ተናጋ፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ሊያድግ አይችልም። የውጭ ባለሀብቶች መጥተው ኢንቨስት ካላደረጉ ማደግ አይታሰብም።
ከ1945(እኤአ) በኋላ ነቁና አሜሪካ በማርሻል ፕላን አውሮፓን ማሳደግ ጀመረች። ትግሉ በአውሮፓ ግንባር ነበር። ከዚህ በኋላ ብዙ ባለሀብቶች አርፍደው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ጀመሩ። በ1960 (እኤአ) አካባቢ እነመተሀራ ስኳር ፋብሪካ ተገነቡ። የአሜሪካ እርዳታ መጣ። ኢኮኖሚው መነቃቃት ሲጀምር ብር መፍሰስ ጀመረ። ያኔ ሙዚቃው ዘመነ። ስእል እና ስነጥበብም አደገ አዚህ ላይ እነ እስክንድር ቦጎስያን እዚህ ላይ ይጠቀሳሉ።
አጼ ኃይለስላሴ ወደ ሀገራቸው ሲገቡ የተማሩ ኢትዮጵያውያን አልነበሩም፤ ጣሊያን ሁሉንም ገሏቸዋል። ከድል በኋላ ንጉሱ ለትምህርት ወደ ውጭ የላኳቸው ኢትዮጵያውያን እየተማሩ ወደ ሀገራቸው መመለስ ጀመሩ። እነሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና ሌሎችም እዚህ ላይ ይጠቀሳሉ፤ ከዚያም አርቱ፤ ስነጽሁፉ፤ ሙዚቃው ፤ጃዙ ፤ ስእሉ፤ ኪነ ሕንጻው ጎመራ። አጼ ኃይለሥላሴ እያንዳንዱን ይደግፉ ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢሲኤ ሕንጻዎች ተሰሩ። ዛልማን ኤናቭ የሰራው ከአትክልት ተራ ወደ መስጊድ ስትሄድ ደረጃ ደረጃ ያለው ሕንጻ ያለው ቤት አለ። ይህን ህንጻ ንጉሱ በየቀኑ እየተመላለሱ ቆመው ነው ያሰሩት።
በ1955(እኤአ) ላይ የኢዮቤልዩ ቤተመንግስት ጊዜ መጣ። በዚህ ወቅት ቤተመንግስቱ ተሰራ፤ ብሔራዊ ትያትር ታደሰ። ሄንሪ ሾሜ የሚባል ፈረንሳዊ አርክቴክት ነው የሰራው። ቀጥሎ የጦር ኃይሎች ሕንጻ ተሰራ። ሕንዶች የጋንዲ ሆስፒታልን ሕንጻ አሰሩ።
ከተማይቱ አዲስ አበባ ከትናንሽ የሳር ጎጆ ቤቶችና አረመኖች ከሰሯቸው ቤቶች በስተቀር ምንም አልነበረባትም። እነዚህ የተሰሩት ኢዮቤልዩ ቤተመንግስት በተሰራበት በ1948 ዓ.ም አካባቢ ነው። ይህቺ ብቻ ነበረች የተሰራችው። የአርመኖችም ትንሽ ቤቶች ነበሩ። ኢኮኖሚው በጣም አዝጋሚ ነበረ። እንዳልኩህ በ1960 (እኤአ) አካባቢ ከውጭ ገንዘብ ወደ ሀገራችን መምጣት ጀመሩ። የአሜሪካ ዋነኛው እርዳታ ተቀባይ ሆንን። በሀገራችን ገንዘቡ ትንሽ መንቀሳቀስ ጀመረ። በዚያው ዓመት አካባቢ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ ወጡ።
ሶማሊያ መጀመሪያ ቀጥላ ጋና ነጻ ወጡ። በዚህን ጊዜ አጼ ኃይለሥላሴ እዚህ ሀገር ቶሎ ብለው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መክፈት ነበረባቸው። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ሕንጻ ቀንና ለሊት እያሰሩ አዲስ አበባ ላይ አስከፈቱ። ከዚያ በኋላ የ1953 ዓ.ም (1960እ.ኤ.አ) የታህሳስ ግርግር የሚባለው መፈንቅለ መንግስት በሀገራችን ተካሄደ። ይሄም ለቀጣዩ ሀገራዊ ሁኔታ ከፍተኛ ተጽእኖ ነበረው። ንጉሠ ነገሥቱ ኋላቀር ሳልሆን እኔ ተራማጅ ነኝ የሚለውን ሰርተው ማሳየት ነበረባቸው።
ዛሬም ድረስ የምንወዳቸው የምናከብራቸው ሕንጻዎች በ1960ዎቹ እንደ መአት በሩጫ በፍጥነት ዲዲዲ ተብሎ ተሰሩ፤ እንደ አሸን ፈሉ። ከፒያሳ ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር፤ ከብርሃንና ሰላም ጀምሮ ነው የተሰራው። በፒያሳ የሚገኙት ዘውዲቱ ሕንጻ፤ ገብረትንሳኤ ኬክ ያለበት ቤት አስደናቂ ሕንጻዎች ናቸው።
አርክቴክቶች ካልክ በዛ ዘመን ሶስት የውጭ ዜጎች ብቻ ነበሩ። ይሄን ሁሉ የሰራው አርትሮ ሜዜዴኒ ነው። የንጉሱ አርክቴክት ይባላል። አስመራ ገብቶ አዲስ አበባ የመጣ። ዛልማኒናፍ ዛልማን ኤናቭ የሚባል እስራኤላዊ ውጭ ጉዳይን ሰራ። ይህ ሰው እነሜዜዴኒን ገልብጦ ንጉሱ ዘንድ የገባ አርክቴክት ነው። ካርታ ስራ ድርጅትን ፤ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ያለውን የቋንቋዎች ጥናት ተቋም የሚባለውን ወይም /አይኤልኤስን/ ገነባ። እነዚህ ህንጻዎች ወርቃማ ሕንጻዎች ናቸው።
እነዚህ ሰዎች ለኢትዮጵያ ብዙ የለፉ ያገለገሉ ናቸው፤ ዘመናዊነትን የተከሉ ያልተዘመረላቸው ያልተነገረላቸው ጀግኖች ናቸው። ፒኤችዲ ማስተር ቴሲስ አልተሰራባቸውም። ዝም ብለን ሌሎች በለፉበት በደከሙበት እውቀታቸውን ባፈሰሱበት ሀብት ላይ ቁጭ ብለናል። እነሱ ናቸው ስለ እኛ ታሪክ የጻፉት። እኛ ምስጋና እንኳን አልሰጠናቸውም።
አዲስ ዘመን፡- ከኪነ ሕንጻ አሰራር አንጻር በጣም የሚያደንቁት ሕንጻ የቱ ነው ?
አርክቴክት ዳዊት፡- በድሮው ጊዜ የተሰሩ ብዙ የሚደነቁ የኪነ ሕንጻ ጥበብና እውቀት የፈሰሰባቸው ሕንጻዎች ነበሩ። እአአ በ1960ዎቹ ኢሲኤን እና ክቡን የብሄራዊ ባንክ ህንጻ (ሄንሪ ሾሜ የተባለው ፈረንሳዊ የሰራው)
አጼ ኃይለስላሴ ቤተመንግስቱ ውስጥ የተለያዩ እድገትና ለውጥ ያላቸውን ስራዎች መስራት አስበው ነበር። ውድድር ሲያደርጉ ሄንሪ ሾሜ መጣና የአዲስ አበባ አርክቴክት ሆነ። ሁሉን ነገር ያሰሩት ጀመር። ብሔራዊ ትያትር ውስጥ ስትገባ በብረት የተሰራውን ስታይ ድንቅ ተአምር ነው፤ ሌሎችንም።
ንጉሡ አዲስ ከተማን ማስፋፋት ስለፈለጉ እስጢፋኖስ ቤተክርስትያን አካባቢ የመስቀል ደመራ በ1950ዎቹ ላይ ነው ከጊዮርጊስ ወደ አሁኑ ቦታ ወርዶ እንዲከበር የተደረገው። አጼ ኃይለስላሴ አዲስ ነገር ፈለጉና የከተማውን እድገት ወዴት ወሰዱት መሰለህ ወደታች። የድሮውን አውሮፕላን ማረፊያ ከጦር ኃይሎች አካባቢ ነቀሉና በአዲስ መልክ እንዲሰራ ወደ ቦሌ አመጡት። ቀጥሎ አዲሱ የፊንፊኔ ሕንጻ ሬንዴቩ ያለበት፤ፖስታ ቤት ተሰራ። ቀጠሉና ቸርችል መንገድን ቀደዱት።
ንጉሱ ስልጣኔን ማስገባትና ማስፋፋት ስለነበረባቸው የሚደነቁ የኪነ ሕንጻ (አርክቴክቸር) ፓትሮን ነበሩ። ወደው ወይስ ተገደው ነው የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።
የደቡብ አፍሪካው ማንዴላ ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ቅኝ አገዛዝ ስር በወደቀችበት ዘመን ለትግሉ ሲል አዲስ አበባ መጣ። ሲያይ እኔ ኢትዮጵያ ሲባል ከእኛ ከደቡብ አፍሪካ የተሻለች ትመስለኝ ነበር፤ የገጠር መንደርና ከቤተመንግስቱና ከጦር መሣሪያ ውጭ ምንም የሌለባት በደሳሳ ጎጆ የተሞላች ነች አለ። ይሄ ዘ ማርች ቱ ፍሪ ደም በሚለው መጽሀፉ ላይ አለ። በአዲስ አበባ ጥቁር ፓይለት አይቶ ከመደነቁ ከቤተመንግስቱና ከአውሮፕላን ማረፊያው ውጪ ምንም ነገር የለም። በደሳሳ ጎጆ የተሞላች ነች ሲል ማንዴላ ጽፏል።
አዲስ ዘመን፡- በንጽጽር የዚያን ዘመን ደቡብ አፍሪካ በከተማነት ከእኛ ጋር ስትታይ እንዴት ነበረች ?
አርክቴክት ዳዊት፡- እንዴ—ያኔ የደቡብ አፍሪካዎቹ ኬፕታውን ደርባን እና ጆሀንስበርግ በከተማ እድገት ከለንደንና ከፓሪስ አይተናነሱም ነበር። እነዚህን በዛን ዘመን በጣም ያደጉትን ተዋቸው። ያኔ የጥቁሮቹ ከተማ የሚባሉት እንኳን እንደ እኛ የወደቁ አልነበሩም። እኛ ጋ ምንም አልነበረም። ጎጆ ቤት ብቻ ነው የነበረው። ለዚህ ነው በ1960ዎቹ (እኤአ) ላይ የአዲስ አበባ የከተማ ግንባታና መስፋፋት ተሟሟቀ ተሟሟቀና መጨረሻ ላይ አጼ ኃይለስላሴ ከስልጣን ሊወርዱ ሲሉ በሰሩት የሴቶች በጎ አድራጎት ሕንጻ ድርጅት ህንጻ እድገቱ ተገታ። አብዮቱ መጣ ማለት ነው።
ይህን ሕንጻ ስታየው ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ ነው። ከስር ጎጆ ቤቶች አሉት። ከላይ ወይ ቤተክርስትያንን ወይም ቤተመንግስትን ተክቶ እንደ ማእከል የሚሆን አካል ያለው ፎቅ አለ። ስትተረጉመው ማለት ነው። አርክቴክቱ ማን እንደሆነ አላወቅሁም። ስትገባ ውስጡ ጨለማ ነው።
ብሩታሊዝም ማለት በአርክቴክቸር ቋንቋ ጭካኔ ሳይሆን ምሰሶውን ውቅሩን (ኮለምኑን ስትራክቸሩን) ማሳየት ነው። የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስትያናት አሰራር ስታየው የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ለስላሳ (ሶፍት) አይደለም። እነዚህ ብሩታሊስት የሚባሉ ዓለም አቀፍ አርክቴክቶች ከውጭ መጡ። ትልቅ ጥናት አጠኑ። የጣና ሆቴልን ብታየው ነፍስህ ይነካል። ኢትዮጵያዊነትህን ታየዋለህ። ጎንደር ጎሀ ሆቴል ስትገባም እንደዚሁ። ሂልተን ሆቴል ስትገባም ከጨለማው ስትወጣ ታያለህ።
ሁሌ ያንን እንስራ ኢትዮጵያዊነት ጨለማ ነው ወይ ቢባል አይሆንም፤ ከ1960ዎቹና ንጉሡ ካሰሩት የሴቶች በጎ አድራጎት ሕንጻ በኋላ ጉልህ የኪነ ሕንጻ ስራ አልነበረም። ተመልሶ ኪነ ሕንጻ ተዳከመ፤ወደቀ።
በ1973 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ተሰራ። በደርግ ዘመን ቀድሞ በኢትዮጵያ ስር ሰዶ የነበረው የምእራቡ ዓለም ኪነ ሕንጻ ዘመን አበቃና የምስራቁ ዓለም የቡልጋሪያ፣ የሀንጋሪና የራሽያ አርክቴክቶች ደግሞ ወደ ሀገራችን ገቡ።
የደርግ ትልቁ ማህተም ማን ነው ብትለኝ መስቀል አደባባይ ነው። ከጋንዲ ሆስፒታል እና ከምኒሊክ መንገድ የመጣውን መንገድ አገናኝቶ እንዲሁም የቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤትንና የራስ ኃይሉን ቤት ቆረሰና ድንቅ ስራ ሰራ። ኮሚኒዝም ላይ ሕዝብን ሰብስቦ ማስጮህ የተለመደ ስለነበር የታወቀ የቡልጋሪያ አርክቴክት ያንን ትልቅ አደባባይ ሰራ።
በደርግ ጊዜ ከተሰሩት ድንቅ የአርክቴክት ስራዎች አንዱ የጣና ገበያ ሕንጻ ነው። የሚገርም ነው።የኢሰፓ አዳራሽ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ፤ለ10ኛው አብዮት በዓል ላይና የኢህድሪ/ ምስረታ ላይ ነው የተሰሩት።
የዚያን ጊዜ ሌላ ምንም የለም። አርክቴክቸር በጥራት አላደገም። የኢቲቪ ሕንጻ፤ የሠራተኞች ማሕበር ሕንጻ፤ አሁን ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መስሪያ ቤት የሆነው የግብርና ሚኒስቴር ሕንጻ በደርግ ዘመን የተሰሩ ናቸው። በዚህ ጊዜ የታወቀችዋን ሀንጋሪ አርክቴክት መጥቀስ ይገባል። ኪሮሽካ ጌሌንሰር ትባላለች። ዛሬም አዲስ አበባ ያለች ቀድሞ ብዙ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስተማረች ናት። በዚያን ጊዜም የውጭ ሰዎች ነበሩ የሚሰሩት።
በአንድ ወቅት ማይክል ቴዎድሮስ የሚባል ኢትዮጵያዊ ተዋቂ አርክቴት ታዋቂ ከሆነው ዛልማን ኤናቭ ጋራ አጼ ኃይለስላሴን ሊያነጋግር ገባ። ንጉሱ ሲያነጋግሩት አማርኛ አይችልም። ሁለተኛ ከእኔ ጋር እንዳትገናኝ አሉት። እንግሊዝ የተማረ አሜሪካ የኖረ ኤርትራዊ ደም ያለበት ነው። ዛልማን ኤናቭ ማይክል ቴዎድሮስን ገለል አድርጎ ንጉሱን መጠጋት ጀመረ። ይሄ ከአንድ የፒኤች ዲ መመረቂያ ጽሁፍ ላይ ያገኘሁት ነው። እነዚህ ታሪኮች አልተጻፉም። አናውቃቸውም። ያ ነው እንግዲህ የእኔ ስራና ፕሮጀክት። እንድናውቃቸው ጥናትና ምርምር አድርጎ መጻፍ። እውቀትን ገና እየቆፈርኩ ነው።
እነዚህን ታሪኮቻችንን በተመለከተ አዋቂ የለም። የምንማረው የሮማን፤ የግሪክን፤ የባይዛንታይንን፤ የፐርሽያን፤ የሕንድን፤ የግብጽን ፤የመካከለኛው ምስራቅን ፤የጃፓንን የቻይናን ኪነ ሕንጻ (አርክቴክቸር) ነው። የኢትዮጵያ ኪነ ሕንጻ በተለይ የዘመናዊው ጥናት የለም። የእኛን ኪነ ሕንጻ የሚቆፍሩት ምእራባውያን ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ከደርግ መውደቅ በኋላ ሀገራዊ ኪነ ሕንጻው ወዴት አመራ ?
አርክቴክት ዳዊት፡- ሀገራዊ ኪነ ሕንጻችን በደርግ ጊዜ ቀዝቅዞ በኢህአዴግ የመጀመሪያው አገዛዝ አካባቢ ሞተ። በዛው ቀጠለና ከምርጫ 1997ዓ.ም በኋላ ሀገራዊ ኢኮኖሚው ከሞተበት ተነስቶ ዳግም ማንሰራራት ጀመረ። የኢህአዴግ መንግስት ከተማ ተኮር መሆን ጀመረ።
ኪነ ሕንጻ ከፖለቲካ ከኢኮኖሚ ከታሪክ ከባህል ከብዙ ነገሮች ጋር በጽኑ ይተሳሰራል። የኪነ ሕንጻ ባለሙያ (አርክቴክት) ከሆንክ ሁሉንም ዘርፎች ለመረዳት በጣም በጥልቀት ማንበብ አለብህ። የሆነ ሀገር ስትሄድ የምትጎበኘው ኪነ ሕንጻውን ወይም ተፈጥሮን ነው። ሌላ የለም። ኪነ ሕንጻ በጣም መሰረታዊ ነው።
ምርጫ 1997ን ተከትሎ ወደ ሀገራችን ብር መጣ። ከተሞች ላይ ተበታተነ። ኢኮኖሚው ማደግ ጀመረ። ክርክሩን ለፖለቲከኞች እንተወው። ኢኮኖሚው በትክክል አድጓል። ሕንጻዎች መሰራት ሲጀምሩ ተደርጎ የማያውቅ ውድድር ተከሰተ። ኢትዮጵያውያን አርክቴክቶች ብቅ ማለት ጀመሩ።
በደርግ ጊዜ ቢዩልዲንግ ኢንተርፕራይዝ የሚባል ድርጅት ነበር። ስራው ዝም ብሎ ጸሐይን ተከላክለህ መገንባት ማምረት ብቻ ነበር። ለብዙሃን ማምረት ነው የሚፈለገው። ጥራት ብቃት ውበት ጥበብ አይታሰብም;።
ምስራቅ ጀርመን ሄጃለሁ። ምን አይነት ደካማ ኪነ ሕንጻ (አርክቴክቸር) እንዳላቸው አይቻለሁ። ፖላንድ ሄጃለሁ። ጭራሹን ኪነ ሕንጻቸው የሞተ ነው። ስሎቬንያን ጎብኝቼአለሁ። የደከመ አርክቴክቸር ነው ያላቸው። የኮሚኒስቱ ሥርዓት የሚከተለው የብዙሃን ኪነ ሕንጻን (ማስ አርክቴክቸር) ነው። ሞቷል፤አፈር የበላ ነው።
ወደ እኛ ስንመለስ በደርግ ጊዜ ሕንጻዎች አልተሰሩም ማለት አንችልም፤ ኪነ ሕንጻው (አርክቴክቸሩ) ግን ሞቶ ነበር።
በኢህአዴግ መንግስት ዘመንም ኢኮኖሚው ሲያድግ ኪነ ሕንጻው ዳግም አንሰራራ። በውድድር ሲባል ፉክክር ውስጥ ተገባና ደስ የሚሉ ሕንጻዎች በስፋት መሰራት ጀመሩ። ለምሳሌ የኦሮሚያ አባገዳ አዳራሽ፤ የኦሮሚያ ከፍተኛ ፍርድቤት ሕንጻ ነፍስህን በጣም ደስ የሚያሠኙ አስገራሚ ስራዎች ናቸው።
በስአሊያን በኩል እነ አፈወርቅ ተክሌ፣ ሰአሊው ከሞቱ በኋላ እነ መዝገቡ ተሰማ፤ እነ በቀለ መኮንን አሉ። ከጸሀፊዎች አለማየሁ ገላጋይና ሌሎችም አሉ። ከሙዚቀኛ ሙላቱ አስታጥቄ አለ። እንዲህ ከየሙያው ወደላይ ገዝፈው የሚታዩ የሚጠሩ አሉ።
እኔ አሁን እንደ አርክቴክት ማነው አርክቴክት ስትባል አፍህን ሞልተህ የምትናገረው ሰው አለ። ዘለቀ በላይ ፤በሙያው ስሙን ልትጠራው የምትችለው አርክቴክት ነው።
ከቄራ ወደ ሳር ቤት ስትሄድ በግራ በኩል ዘ ስቴር የምትባል ሕንጻ አለች። ያቺ ሕንጻ የአርክቴክት ዘለቀ በላይ ነች። በሀዋሳ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል። ብዙ ዓለም አቀፍ የአርክቴክት ፕሮፌሰሮችን ሀዋሳ ወስጄ እሱን ሕንጻ እንዲያዩ አድርጌአለሁ።
አንዳንድ ጊዜ አለመታደል ሆኖ አንዳንድ ሰው የሚገነባው አንድ ሕንጻ ብቻ ነው። ዘለቀ በላይ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገራርሙ የተማሪ ካፊቴሪያዎች ሰርቷል። አስተምሮኛል፤ አሁንም እየሰራ ነው።
አርክቴክቸሩ ከውድድሩ በኋላ እንደገና እስከ 2003ዓ.ም ድረስ እንቅልፍ ውስጥ ገብቶ ነበር። ኢህአዴግ ከገባበት ከ1983 ጀምሮ ፖለቲካውን ማረጋጋት ሀገር ማረጋጋት ሲል ለአስራ ምናምን ዓመታት ምንም አልገነባም ነበር።
ኪነ ሕንጻ የሚነሳው የሚያብበው ሁኔታው ሲሰክንና ሀገር ሲረጋጋ ነው። ኪነ ሕንጻ ብሩሽህን አውጥተህ የምትሞነጭረው አይደለም፤ ዳጎስ ያለ ብር ይፈልጋል። ብር አውጥተህ ነው በተጨባጭ ስራውን መሬት ላይ የምትሰራው። ግልጽነትና ተጠያቂነትን የተረጋጋ ሰላምን ይፈልጋል።
ኪነ ሕንጻን ‹‹ዘ አርት ኤንድ ሳይንስ ኦፍ ዲዛይኒንግ ኤንድ ኮንስትራክሽን ኦፍ ቢዩልዲንግ›› ይሉታል። የዲዛይንና የግንባታ ሳይንስና ስነጥበብ ነው የሚባለው። የተረጋጋ ኢኮኖሚና የበዛ ሰላም ይፈልጋል።
ከ1997 ዓ.ም በኋላ ፖለቲካና ኢኮኖሚውን ለባለሙያዎች ትተን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሀገሪቷ ማደግ ጀመረች። በወድድሩ ምክንያት በየቦታው ግሩም ሕንጻዎች በከተማውና በየኤምባሲዎችም መስራት ጀመሩ። አዲስ አበባ የተሰራውን የደች ኤምባሲን ሄደህ ብታየው ዓለም ላይ የታወቀና በየቀኑ ሊጎበኝ የሚችል ነው። የኢትዮጵያንና የደችን አርክቴክቸር አጋብቶ የተሰራ ነው። ላሊበላ የገባህ ነው የሚመስልህ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ቃለ ምልልስ በጣም እናመሰግናለን።
አርክቴክት ዳዊት በንቲ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2012
ወንድወሰን መኮንን