በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮረና ቫይረስ ምክንያት ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ በሚል የሰዎች እንቅስቃሴ መገደቡ ይታወቃል። ይሁንና በተለይ በታዳጊ አገራት ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ በመንቀሳቀስ የየዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ሲጥሩ ይስተዋላል። ስለዚህም የትናንቱ የመንገድ መጨናነቅ ዛሬም ቀጥሏል ማለት ነው። የትራፊክ መጨናነቁም በተወሰነ ደረጃ ጋብ ቢልም ሰው በፈለገው ሰዓት የፈለገውን ሸምቶ አሊያ ጉዳዩን ፈጽሞ ለመመለስ ጊዜ ሲወስድበት ይስተዋላል።
በኮሮና ምክንያት የትራፊክ መጨናነቁ ይቀንሳል ቢባልም የታሰበውን ያህል ግን አይደለም።የትራፊክ መጨናነቁ በደጉ ቀን ብቻ ሳይሆን አርፋችሁ ቤታችሁ ተቀመጡ በተባለበት በክፉውም ቀን እየታየ ነው።
በአጠቃላይ የትራፊክ መጨናነቅ የአዲስ አበባ ፈተና ሆኗል። ለትራፊክ መጨናነቁ ምክንያት ናቸው የተባሉትን ተግዳሮቶች ባለፈው ሳምንት ዕትም ማስነበባችን ይታወሳል። በዛሬው ዕትም ደግሞ መፍትሔ ናቸው የተባሉትን ነጥቦች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት የከተማ ልማት ኃላፊና መምህር የሆኑትን ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ብርሃኑ ወልደትንሳኤን አነጋግረን አቅርበነዋል።
እርሳቸው መፍትሔውን በሦስት መንገድ ይገልጹታል። ከእነዚህም መካከል አንዱና የመጀመሪያው የአቅርቦት አያያዝ (ሰፕላይ ማናጅመንት) ነው። ይህም ሲባል አቅርቦቱን በአግባቡ መጠቀም ማለት ነው። ለምሳሌ መንገዶችን እንዲሁም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን በአግባቡ መጠቀምና ማሻሻልን እንዲሁም ማሳለጥን ያስፈልጋል። ይህ የታራፊክ ፍሰቱን ያስተካክለዋል።
በተለይ ትራፊክን በተመለከተ አንዳንድ ዕርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ የከተማዋን አደባባዮች በአሁኑ ወቅት በማፍረስ ለመቀየር እየተሠራ ነው። በመሆኑም ለማሳለጥ ምቹ እንዲሆኑ እየተደረጉ ነው። ለአብነት ያህል ሳር ቤት አካባቢ ሰሞኑን እየተገነባ ያለውን ማየት ይቻላል። ይህ ልምድ ደግሞ ከጀሞና ለቡ መብራት ኃይል አከባቢ የተገኘ ነው። የቀድሞው አደባባይ ፈርሶ ፍሰቱን የሚያሳልጥ ተግባር ተከናውኗል። ይህ በመሆኑም ቀደም ሲል ይታይ የነበረው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ቀንሷል።
ሁለተኛው ደግሞ የፍላጎት አያያዝ (ዲማድ ማናጅመንት) እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ብርሃኑ፣ እዚህ ላይም ያለውን የትራንስፖርት ፍላጎት በአግባቡ ማረቅ እንደሚገባ ነው የሚያመለክቱት። ለዚህም አንድ ትልቅ ምሳሌ ነው የሚሉትን ሲጠቅሱ እንዳስረዱት፤ ሌሎች አገሮች የሚጠቀሙበት እዚህ አገር ግን የማይታይ አሠራር አለ። ይኸውም የሥራ እና የትምህርት ቤት መግቢያ ሰዓት በአብዛኛው አንድ ዓይነት ጊዜ ላይ መሆኑ ነው። ተማሪውም ሆነ ሠራተኛው የሚገባው ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ ነው። ስለዚህ ብዙ ጊዜ የትራፊክ መጨናነቁ ጫፍ የሚደርሰው በእዚህ ሰዓት ላይ ነው። ይህን በተለያየ ሰዓት ማስተናገድ ቢቻል የትራንስፖርት ፍላጎቱ ይቀንሳል፤ መጨናነቅ ደግሞ ይጠፋል። ይህ አንድ መፍትሔ ነው።
የሥራ ሰዓት ከትምህርት ቤት ሰዓት መለየት አንድ አማራጭ ነው። ለምሳሌ መስሪያ ቤቶች እስከ አንድ ሰዓት ተኩል ባለው ገብተው ቀደም ብለው እንዲወጡ ቢደረግ፤ ተማሪዎች ደግሞ እስከ ሁለት ሰዓት ተኩል እንዲገቡ ቢደረጉ ፍላጎቱ የሚመጣው በተለያየ ሰዓት ስለሚሆን የትራፊክ መጨናነቅ አይፈጠረም።
ሌላው ደግሞ ለህዝብ ትራንስፖርት ቅድሚያ መስጠትን ይመለከታል። ለምሳሌ በከተማችን በተወሰኑ ቦታዎች አካባቢዎች ለአውቶቡስ ብቻ የተፈቀደ መስመር ይታያል። ለምሳሌ ከመካኒሳ እስከ ሜክሲኮ ድረስ የባስ መስመር የሚል አለ። የዚህ ዓላማ ለህዝብ ትራንስፖርት ቅድሚያ መስጠት ነው። በዚህም የህዝብ ትራንስፓርት አገልግሎቱ ከትራፊክ መጨናነቅ ነፃ ሆኖ እንደልቡ እንዲቀሳቀስ ማድረግ ይቻላል።
ስለዚህ የትራፊክ መጨናነቅ የሚለካው በትራፊክ ፍጥነት ነው። መጨናነቅ ካለ መንቀሳቀስ የለም። ከዚህም የተነሳ አውቶቡሶች የሚሄዱት እንደልባቸው አይደለም። ፍጥነታቸው በጣም ዝቅተኛ ይሆናል። ነገር ግን ፍጥነት ቢጨምሩ ምልልሱ ይጨምራል፤ብዙ ሰው ማንቀሳቀስ ይችላሉ።
ዶክተር ብርሃኑ በምሳሌ ሲያስረዱ እንዳብራሩት፤ አንድ አውቶቡስ ከአንድ አካባቢ ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ ሲጓዝ በትራፊክ መጨናነቅ 30 ደቂቃ እና አንድ ሰዓት የሚፈጅበት ከሆነና ብዙ መመላለስ ካልቻለ በርካታ ህዝብ ማጓጓዝ አይችልም። ስለዚህ ለህዝብ ትራንስፖርት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ቢቻል ደግሞ የራሳቸው መስመር ላይ እንደልብ መጓዝ ቢችሉ ብዙ ሰዎችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ይችላሉ ማለት ነው። ለአብነትም ከመካኒሳ ወደ ሜክሲኮ የአውቶቡስ መስመር ቢኖርም እንደታሰበው ሲጠቀሙበት አይስተዋልም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ መኪና ቆሞበት ሲውል ይታያል። የትራፊክ ቁጥጥሩም ጥብቅ አይደለም። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በአግባቡ ቢሠራባቸው ፍላጎትን ማርካት ይቻላል።
ሦስተኛው መፍትሔ የመሬት አጠቃቀም አስተዳደር /ላንድ ዩዝ ማናጅመንት/ ነው። ለምሳሌ የከተማ የቆዳ ስፋት መለጠጥ አለ፤ የተጠቀጠቀው ከተማ ዘና እንዲል የማድረጉንም ጉዳይ ከግምት በማስገባት ሰዎች በቀላሉ ተንቀሳቅሰው የፈለጉትን ሸምተው አሊያም ተዝናንተው መመለስ እንዲችሉ ማድረግ ይቻላል። ስለዚህ ተራርቀው የሚታዩትን ቦታዎች መቀላቀል ያስፈልጋል።
ሌላው ደግሞ ትራንዚት ዲቨሎፕመንት ኦሬይንትድ (TDO) የሚባል በአዲስ አበባ እየተሞከረ ያለ ነገር አለ። ዋና የሚባለውን የከተማውን ቦታና ከፍ ያለ ልማት ያለበትን አካባቢ ማሳለጥ፤ ለምሳሌ በምዕራብ፣ ምሥራቅ፣ ሰሜንና ደቡብ ያለውን የባቡር እንቅስቃሴ በተለይ ዋና ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ ጥግግት ያለበትን ልማት ማበረታታት ነው። ለእዚህም ትራንዚት ኦሬይንትድ ዲቨሎፕመንትን መሞከር ያስፈልጋል። ይህን አሠራር የጀመሩት አሜሪካውያን ናቸው። አውሮፓውያኑም በሰፊው ሄደውበታል። ስለዚህ ትራንዚት ኦሬይንትድ ዲቨሎፕመንትን በመጠቀም ከተሞችን ማገናኘት ይቻላል። ይህን በማድረግ ሰዎች አስፈላጊውን ሁሉ በየአካባያቸው በቀላሉ እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል።
ዶክተር ብርሃኑ እንደሚገልጹት፤ በተለይ በላንድ ዩዝ ማጅመንት ላይ ቅይጥ ልማቱንም ማበረታታት የግድ ይላል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዓውድ አብዛኛው የሥራ ቦታ ያለው በከተማው መሃል ነው። ስለዚህ በየጊዜው ከተለያዩ የአምስቱም ኮሪደሮች ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ ፍሰት ወደመሃል ከተማ ይደረጋል። በሌላ በኩል ደግሞ የሚሆነው በተቃራኒው ነው። ስለዚህ ላንድ ዩዝን ለምንድን ነው የማንቀላቅለው? ለምሳሌ የመኖሪያ ልማቱን መሃል ከተማው ላይ ብናደርግ እንቅስቃሴውን እንቀንሰዋለን። አሁን ያለው እንቅስቃሴ ጤናማ አይደለም።
አዲስ አበባ ላይ በብዛት ከተስተዋለ ለምሳሌ ጠዋት ላይ ከሃያት አቅጣጫ ወደ መገናኛ ህዝቡ ይጎርፋል፤ ማታ ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ወደመጣበት ይመለሳል። በዚህ ላይ ያለው ጭንቅንቅ የሚነገር አይደለም። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ መኖሪያዎች ያሉት ከተማው ዳር ዳር ላይ መሆኑ ነው፤ የሥራ ቦታ ደግሞ ያለው መሃል ከተማ መሆኑ ነው። ስለዚህ እነዚህን ማጣጣም የግድ ይላል።
‹‹የትራፊክ መጨናነቁን ለመቀነስ በማሰብ ብስክሌት ቢታሰብ እንኳ ለመጠቀም ደግሞ የራሱ የሆነ እቅድ ይፈልጋል፤ የመሬት አቀማመጡም ምቹ መሆን አለበት። ለምሳሌ አዲስ አበባ ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚኬድ ከሆነ ብስክሌት አይታሰብም። ምክንያቱም የመሬቱ አቀማመጥ ተራራማ ነው። ስለዚህ እነርሱም እንደእግረኛው የተለየ መንገድ ተስጥቷቸው ሊሄዱ ይገባቸዋል። የራሳቸው የመሰረተ ልማት ሊኖራቸው ይገባል። አንዳንድ ቦታ የተሞከረ ነገር ቢኖርም ችግር እንዳለበት ይታየኛል›› ሲሉ ያብራራሉ።
በአዲስ አበባ አሁን እየተመከረ ያለው በርካታ ሰዎችን በአንዴ የሚያንቀሳቅስ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ነው። ለምሳሌ የሚናባስ ቁጥር በዝቷል፤ በመሆኑም የትራፊክ መጨናነቅን ይጨምራሉ። ስለዚህ አሁን አዲስ አበባ ላይ ብዙ ህዝብ ማንቀሳቀስ የሚችል ትራንስፖርትን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው። ነገር ግን የግል ባለሀብቱ ከሚኒባስ ወደ አውቶቡስ እንዲገባ የሚያስችል ሊገፋፋው የሚችል ማበረታቻ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም አትራፊ መሆን አለበት። ልክ አንበሳ አውቶቡስ ከመንግሥት ድጎማ ሊያገኝ እንደሚችል ሁሉ እነርሱም ደግሞ ድጎማ ካላገኙ ውጤታማ ሆነው መቀጠል አይችሉም።ከሚናባስ ወደ ብዙ ሰው የሚጭን አውቶቡስ መሄዱ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮችም መሞከሩን ነው ዶክተሩ የገለጹት።
በተመሳሳይ የባጃጆችም ነገር እንዲሁ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በተለይ በመካከለኛ ከተሞች ውስጥ በብዛት እንዳሉ ይጠቅሳሉ። በጣም በርካታ ናቸው፤ ከቦታ ቦታ የሚወስዱት ሰው ደግሞ አነስተኛ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ባጃጆቹ ለትራፊክ አደጋ እንደሚያጋልጡም ይጠቅሳሉ። ሰውም ቅሬታ ያቀርብባቸዋል። ስለዚህ ከባጃጅ ወደ ብዙ ሰው የሚጭን ትራንስፖርት መሄድ አዋጭም አማራጭም ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከህዝብ ትራንስፖርት ጀምሮ ብዙ ሰው ለሚጭን አውቶቡስ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል። 80 እና 100 ሰው ይዞ የሚሄድ አንበሳ አውቶቡስ ከቤት መኪና ጋር እኩል መጋፋት የለበትም፤ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
ሌላው ደግሞ ለምሳሌ በአራት አቅጣጫ በሚተላለፍ መንገድ ሁለቱ ላይ የትራፊክ ፍሰቱ አነስተኛ ቢሆንና ሁለቱ ላይ ደግሞ የተጨናነቀ ቢሆን የመቀያየር ነገር አለ። ሌላውን አግዶ ብዙ ህዝብ የያዘውን የመቀየር ጥበብን መጠቀም የሚቻል መሆኑንም ይናገራሉ። ይህ የሚሆነው ግን ረቀቅ ያለ ጥበብን ማለትም የመንገዶችን ሁኔታ በአግባቡ ሊያሳይ የሚችል እይታ ሲኖር እንደሆነ ነው ያስረዱት።
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2012
አስቴር ኤልያስ