የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወደ ሀገራችን መግባቱ ከተሰማ ሶስት ወራት ሊሞላ የቀረው ሁለት ሳምንት የማይሆን ጊዜ ነው። መጋቢት 4/2012 የኮሮና ቫይረስ በአንድ ሰው ላይ ታየ ተብሎ የተጀመረው የመከላከል እርምጃ ስርጭቱን ሳይገታው አሁን ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎችን ማጥቃቱ በህክምና ምርመራ ተረጋግጧል። የሟቾች ቁጥርም ምንም ካልነበረበት ተነስቶ አሁን ስምንት ደርሷል። ይሄ ቁጥር የመቁጠር ጉዳይ አይደለም፤ የጠፋው የሰዎች ህይወት ነውና። ወረርሽኙ የብዙ ሰዎችን ኑሮ አናግቷል። የኢኮኖሚ፣የማህበራዊ እና የስነልቦና ቀውሶችንም አስከትሏል። በአጠቃላይ እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባላት ምን ያህል ተጎጂ እንደሆኑ ማሰብ ከባድ አይሆንም።
የኮሮና ቫይረስ ምን ያህል አሳሳቢና ሳይታሰብም ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ እንደሚችል የሌሎች ሀገሮችን ልምድ አይተናል። በዚሁ ወረርሽኝ የተነሳ ዛሬ በዓለም ላይ ከሶስት መቶ 67 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከስድስት ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። በአፍሪካም ከ135ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ አራት ሺህ አካባቢ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ይሄ በአጭር ጊዜ ውስጥ የታየ እውነታ ነው። በዓለም ላይ ትልቅ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ቀውስን ያስከተለ ክስተትም ሆኗል። የሟች ቤተሰቦች በቀብር ስነ ስርዓት ላይ የማይገኙበት ፣ ቤተሰቡ በሚፈልገው መንገድ አልቅሶ መቅበር የማይቻልበት እና የጅምላ መቃብሮች ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የታዩበት ክስተትንም ፈጥሯል።
ምንም እንኳን ስርጭቱ እጅግ አደገኛ በሚባል ሁኔታ በሀገራችን እየተስፋፋ ቢሆንም አሁን እየታየ ያለው የመከላከል እና የጥንቃቄ መንገድ እጅግ አስገራሚና አስደንጋጭ ነው። ቫይረሱ ወደ ሀገራችን መግባቱን የጤና ሚኒስቴር ባስታወቀበት ወቅት በህብረተሰቡ ዘንድ የነበረው መደናገጥና ለጥንቃቄ ይደረግ የነበረው ርብርብ ሁሉ አሁን ላይ ቆሟል ለማለት ያስደፍራል። በየመንገዱ ፣ በየንግድ ተቋማት፣ በትራንስፖርት አካባቢ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች የነበረው እጅን የመታጠብ እና የማስታጠብ እንቅስቃሴ ለዚህ በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
በሀገራችን የቫይረሱ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ በሆነ መልኩ ቢሆንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከመተግበር የጥንቃቄ እርምጃዎችን ከመተግበር አንጻር አሁንም የጎላ ክፍተት ይታያል። በተለይም በገበያ ስፍራዎች፣ በትራንስፖርት አካባቢ፣ በእምነት ተቋማት እና ባህላዊ ክዋኔ(ሰርግና ለቅሶ) በሚከናወንባቸው ስፍራዎች ከፍተኛ መዘናጋት አለ። ይሄ መዘናጋት አሁን እየተባባሰ ከመጣው የቫይረሱ ስርጭት ጋር ተዳምሮ የማንወጣው አደጋ ውስጥ ሊከተን እንደሚችል አያጠራጥርም። በእኛ የተዳከመ የኢኮኖሚ እና የጤና መሰረተ ልማት አቅም ታላላቅ የዓለም መንግስታት በማንኛውም መልኩ ያልተቋቋሙትን የቫይረስ ስርጭት እንቋቋመዋለን ብሎ ማሰብ የፈሰሰ ውሃን ለማንሳት እንደማለም መሆኑ እርግጥ ነው።
ዛሬም ድረስ በተለይም የአገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው በላይ ህዝብ በመጫን ላይ ናቸው። የአፍና የአፍንጫ ማስክ ሁሉም ሰው እንዲያደርግ፣ እርቀቱን ጠብቆ እንዲንቀሳቀስ እና አስገዳጅ ሁኔታ ካልገጠመው በስተቀር ከቤቱ አይውጣ የሚል ጥብቅ መመሪያ ከመንግስት ቢወጣም በተግባር የሚታየው ግን በተቃራኒ ነው። ይሄ ደግሞ አስፈሪውን ስርጭት እና ሞት ያስተናገዱ ሀገራት ከገጠማቸው በላይ አስከፊ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ግልጽ ነው።
አንድ ብሎ የጀመረው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ቁጥር ዛሬ አንድ ሺ ብሎ እስከ መቁጠር የተደረሰው ቀስ በቀስ ቫይረሱን የመከላከል የጥንቃቄ እርምጃዎችን በሚፈለገው ልክ ባለመተግበራችንና፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የመከላከያና የጥንቃቄ መንገዶችን በመሰላቸት እና በቸልተኝነት እየተዘናጋን በመምጣታችን ነው። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባህሪ ደግሞ ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚባለው የአበው ተረት አይነት እያዘናጋ ነው። ቀስ በቀስ ስርጭቱን በማህበረሰብ ውስጥ በማስፋፋት እና በማዘናጋት ለከፋ አደጋ ይዳርጋል። ስለዚህ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አክብሮ መተግበር እና ተገቢውን የመከላከል ጥንቃቄም ማድረግ አለበት። አዋጁን ለማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላትም ኃላፊነታቸውን ያለምንም ማወላወል በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2012