የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ለመዋጋት የስፖርት ቤተሰቡንና ባለድርሻ አካላት በማሳተፍና በማስተባበር ጠንካራ ሥራዎችን መስራቱን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶችና ወጣቶች ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከትናንነት በስቲያ የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን የ2012ዓ.ም በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻፀምን ሲገመግም ፤የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳዊት ትርፉ፤ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ለመዋጋት የስፖርት ቤተሰቡንና ባለድርሻ አካላት በማሳተፍና በማስተባበር ጠንካራ ሥራዎችን መስራቱን አስታውቀዋል። «ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ከመደበኛ ሥራው ትይዩ ቫይረሱ ከተከሰተ ጀምሮ በከተማ አቀፍ ደረጃ ወረርሽኙን ለመዋጋት እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን በበጀት ዓመቱ የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ለመዋጋት የስፖርት ቤተሰቡንና ባለድርሻ አካላት በማሳተፍና በማስተባበር ጠንካራ ሥራዎቹን አከናውኗል»ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩን ጥሪን መሰረት በማድረግ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በህብረተሰባችን ላይ የሚደርሰውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማቃለል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለወገኖች የገንዘብ ፣ ለምግብነት የሚውሉ ቁሳቁሶች ፣ ንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎች ፣የደም ልገሳና የበጎ ፈቃደኛ አገልግሎቶች በመሥጠት ትልቅ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል ።ከዚህ ባሻገር ራሳቸውን ከኮረና ቫይረስ ለመጠበቅ በቤታቸው ለሚገኙ የጋራ መኖሪያ ( ኮንዶሚኒየም) ነዋሪዎች በቤታቸው ሆነው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተደራሽ በማድረግ ኮሚሽኑ ወረርሽኙን ለመዋጋት እየተደረገ ባለው ርብርብ ላይ የጎላ ተሳትፎ ማድረጉን ተናግረዋል።
ስፖርት ኮሚሽኑ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ቁልፍና አበይት ዕቅዶችን ያወጣ እንደመሆኑ ወረርሽኙ ወደ በሀገራችን ከመከሰቱ ቀደም ብሎና በተከሰተበት ወቅት የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን የገለጹት አቶ ዳዊት፤በዋናነት በታዳጊ ወጣቶች ስልጠና መርሀ ግብር፣ በማስ ስፖርት (በማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ)፣በውድድርና ተሳትፎ፣ በተቋማዊ ለውጥ ሥራ፤ የስፖርት የልማት ስራዎችና ግንባታ ክትትል ላይ ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ለቋሚ ኮሚቴው የዘጠኝ ወራቱን እቅድ አፈጻፀምን ለቋሚ ኮሚቴው ከማቅረቡ በፊት በከተማ እየተገነቡ ከሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያዎች መካከል በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙትን ሶስት ማዘወተሪያ ስፍራዎች ላይ የመስክ ምልከታ አካሂዷል። ቋሚ ኮሚቴው የስፖርት ኮሚሽኑን የዘጠኝ ወራት ተግባርን በጽሁፍና በመስክ ምልከታው ያደረገውን ግምገማ መሰረት በማድረግ አስተያየት የሰጠ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸው ተግባራት እጅግ የሚያስደስቱና የሚበረታቱ መሆኑን አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ፣በመዲናዋ ያለውን የስፖርት ማዘውተሪያ እጥረት ለመቅረፍ ትኩረት በማድረግ የተሰሩ ስራዎችን አድንቋል።በዘጠኝ ወራት የታዩትን ጠንካራ ተግባራትን አስቀጥሎ የነበሩትን ጉድለቶችን አስወግዶ በቀጣይ ጊዜያት የተሻለና አመርቂ ሥራ መስራት ይገባል ሲል ቀጣይ የስራ አቅጣጫን አስቀምጧል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2012
ዳንኤል ዘነበ