የብልፅግና ፓርቲን አምስተኛ ዓመት በዓል በማስመልከት የፓርቲው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል /
ለውጡና የለውጡ ፍሬዎች
በሕዝብ ግፊትና በፓርቲ ሳቢነት የመጣው ሀገራዊ ለውጥ፣ የመጀመሪያውን ምዕራፍ እየተሻገረ ነው። በዚህ የመጀመሪያ ምዕራፍ የለውጡ ሐሳቦች በቃልና በተግባር ተገልጠዋል። የለውጡ ፈተናዎችም አካል ገዝተው በሚገባ በመገለጣቸው ሕዝብ አውቆ እንዲታገላቸው ተደርጓል። ይሄም የለውጡን ፍሬዎች ለማጎምራት፣ የለውጡን ፈተናዎችንም ለመርታት ዕድል ሰጥቷል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎች ከቃል አልፈው ተግባራዊ ምላሽ አግኝተዋል። የፖሊሲ፣ የሕግ እና የአሠራር ብቻ ሳይሆን የባሕል ለውጥ አምጥተዋል። ለውጡ ያለፉት የሀገሪቱን ስብራቶች የሚጠግን፣ ዛሬን የሚዋጅና የነገውን የኢትዮጵያ ጉዞ የሚያቀና ነው። የለውጡ ዘመን መሪ ፓርቲ የሆነው ብልፅግና አምስተኛ ዓመቱን በሚያከብርበት በዚህ ወቅት የሚከተሉትን አንኳር የለውጥ ውጤቶች ማንሣቱ ተገቢ ነው።
የብልፅግና መመሥረት፡- የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ነው። እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ንቃት በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲፈጠር አድርገዋል። የፖለቲካ አደረጃጀቶችን አምጥተዋል። የሕዝብ ጥያቄዎችን ቅርጽና መልክ ሰጥተዋል። የፖለቲካ ትግል ስልቶችንም አስተዋውቀዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የትጥቅ ትግልና የፖለቲካ ትግል እንዲቀላቀል፤ የጥላቻ ፖለቲካ እንዲነግሥ፣ በብሔር፣ በርዕዮተ ዓለምና በትግል ስልት መፈራረጅ እንዲበረታ በማድረግ ለዘመናዊ የፖለቲካ ጉዟችን ሳንካዎችን አኑረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ነባሮቹን ፖለቲካዊ እሴቶች በሚያጎለብትና የፖለቲካ ስብራቶቻችንን በሚጠግን መልኩ ተመሥርቷል። ይሄም የለውጡ አንዱ ፍሬ ነው። የብልፅግና መመሥረት የዳርና የመሐል፤ ዋና እና አጋር፣ አርብቶ አደርና አርሶ አደር፤ ተራማጅና አድኃሪ፤ ጠላትና ወዳጅ፣ ወዘተ. የሚባሉትን ግንቦች በማፍረስ በሐሳብ ላይ ብቻ የተመሠረተ የፖለቲካ አደረጃጀትን ፈጥሯል።
የሃሳብ ልዩነቶችን እንደ ጌጥና እሴት በመውሰድ ተፎካካሪዎቹን በጠላትነት አይፈርጅም። በኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ላይ በመመሥረት፣ ከሌሎች ሐሳቦች በመማር፣ በገቢር ነበብ መንገድ ይጓዛል እንጂ የርዕዮተ ዓለም እሥረኛ አይደለም። ለአንድ አካባቢ ወይም ብሔር የቆመ ሳይሆን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያለው የሐሳብ ፓርቲ ነው። ይሄም የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዓ ምድር የለወጠ የለውጥ ፍሬ ነው።
የእምነት ተቋማት ልዕልና፡ የእምነት ተቋማት የመንግሥት ጥገኛነትና የሕልውና ፈተና ነበረባቸው። የሕልውና ፈተናውም በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተነሣ የሚፈጠር ፈተና ነው። ከለውጡ በኋላ የእምነት ተቋማት ልዕልና ተከብሯል። ይሄንን ልዕልና ለማስከበርም መንግሥት በተቋማቱ ላይ ሲያደርግ የኖረው ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ተደርጓል። ተቋማቱ ምንም እንኳን ነፃነትን የማስተዳደር ችግር ቢያጋጥማቸውም፣ ነገር ግን ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው ጉዳዮቻቸውን በሃይማኖታቸው ሕግ ብቻ እንዲያከናውኑ ዕድል ተሰጥቷቸዋል።
ልዕልናቸውን ይፈታተናቸው የነበረውን መለያየት ለማስቀረት ተለያይተው የነበሩ የሃይማኖት አመራሮችን ለማቀራረብ፣ ለማግባባትና ወደ አንድነት እንዲመጡ ለማድረግ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሚና ተጫውቷል። በዚህ ሚና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች መካከል የነበረው መለያየት ተወግዶ አንድነት ተፈጥሯል።
የሃይማኖት ተቋማቱ አንድነታቸውን በማጽናት ተልዕኳቸውን በሚፈልጉት ልክ ለመወጣት እንዲችሉ በሕግ በኩል የነበረባቸው ክፍተት ተሟልቷል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የሕጋዊነት ጥያቄ ሲያነሡ ነበር። ይሄንን የግማሽ ምዕተ ዓመት ጥያቄ ለመመለስ ሁለቱም በአዋጅ እንዲደራጁ ተደርጓል። ይሄም የለውጡ አንዱ ፍሬ ነው።
የሲቪክ ተቋማት፡ የአንድ ሀገር ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሕይወት እንዲሣለጥ የሲቪክ ማኅበረሰብ ወሳኝ ሚና አለው። ሲቪክ ተቋማት ማኅበረሰቡ በራሱ ፈቃድ በመደራጀት መብቱን የሚያስከብርባቸውና ሐሳቡን በተደራጀ መልኩ የሚያቀርብባቸው መንገዶች ናቸው። በእነዚህ ተቋማት ላይ የነበረውን የተንሸዋረረ አመለካከት በማስተካከል፣ የታሠሩበት ቀፍዳጅ ሕግ በለውጡ ተሻሽሏል። ለውጡ የሲቪክ ተቋማትን እንቅስቃሴ ለተቋማቱም ሆነ ለሀገር በሚበጅ መልኩ በአዲስ ሕግና አደረጃጀት እንዲዋቀሩ አድርጓል። ከለውጡ በፊት 1900 የሲቪክ ማኅበራት ብቻ ነበሩ። ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ግን 3300 አዳዲስ ሲቪክ ማኅበራት ተመዝግበዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማት፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚሳለጠው በዴሞክራሲ ተቋማት አማካኝነት ነው። የዴሞክራሲ ተቋማት ደግሞ ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ከለውጡ በፊት የነበረው የተቋማቱ ስብራትም ይሄንን ባሕሪይ ለመላበስ አለመቻል ነበር። ከለውጡ በኋላ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የዕንባ ጠባቂ ተቋም እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እንደገና እንዲደራጁ ተደርገዋል።
ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ እንዲሆኑ የሚያስችል የሕግና የአደረጃጀት ለውጦች ተደርጎባቸዋል። ከመንግሥት ጫና እና ጣልቃ ገብነት ውጭ በሕግና በሕሊናቸው ብቻ እንዲሠሩ የሚያስችል አካሄድን ይከተላሉ። እነዚህ ተቋማት ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ መንግሥትንም ሆነ ገዥውን ፓርቲ በሕጋቸው መሠረት የሚከታተሉ፣ አስፈላጊ ነው ባሉበት ጊዜ የሚቀጡ ተቋማት ሆነዋል።
የሚዲያ ነፃነትና ዕድገት፡ ሚዲያ የብዝኃ እና የዓይነተ ሐሳብ መድረክ ነው። የሐሳብ ነፃነት አንዱ መገለጫና የሥልጣኔ መንገድ መተለሚያ ነው። ለውጡ የሚዲያ ነፃነት እንዲከበር፤ ሚዲያዎች በሕግ ብቻ እንዲሠሩና እንዲተዳደሩ፣ የሁሉም ዓይነት ማኅበረሰብ የሐሳብ ገበታዎች እንዲሆኑ ለማድረግ አስችሏል። የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ሕግ ማሻሻል፣ የሚዲያን አሣሪ ሕጎች ማሻሻል፤ የሚዲያ ተደራሽነትን ማበረታታት፣ ሚዲያዎች እርስ በርስ ራሳቸውን የሚቆጣጠሩበትን ሥርዓት የመዘርጋት ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም የተነሣ ከለውጡ በፊት 122 የነበሩት መገናኛ ብዙኃን በአሁኑ ጊዜ 123፣ ዕድገት በማሳየት፣ 272 ደርሰዋል። የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከ25 ወደ 78፤ የሬዲዮ ጣቢያዎች ደግሞ ከ52 ወደ 73 አድገዋል። የእነዚህ መገናኛ ብዙኃን የቋንቋ ተደራሽነትም ከለውጡ በፊት ከነበረበት 39 ቋንቋ በመላቅ አሁን በ60 ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣሉ።
ኢትዮጵያን ማዘመን፤ የኢትዮጵያ አንዱ ስብራት የኋላ ቀርነት ፈተና ነው። በሁሉም ዓይነት ዘርፎች ኋላ ቀርነት በመንሰራፋቱ የተነሣ ኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት እድሜዋን ያህል አላደገችም። ለውጡ ከመጣባቸው ገፊ ምክንያቶች አንዱም ይሄው የኋላ ቀርነት ስብራት ነው። በለውጡ ዘመን ኋላ ቀርነትን ቀርፎ ኢትዮጵያን ለማዘመን አያሌ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለውጥም አምጥተዋል።
የግብርና ኋላ ቀርነትን ቀርፎ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተሠራው ሥራ የባሕልም የውጤትም ለውጥ መጥቷል። ከዚህ በፊት የዝናብ ወቅት ብቻ ይጠብቅ የነበረው የግብርና ባሕል መስኖን በመጠቀም፣ በኩታ ገጠም እርሻና መሬት ጦም እንዳያድር በተሠራው ሥራ፣ ዓመቱን ሙሉ የሚመረትበት ባሕል እያመጣ ነው። ስንዴን፣ ሩዝን፣ ገብስን፣ በቆሎንና የፍራፍሬ ምርቶችን ትኩረት አድርጎ በተሠራው ሥራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች። ስንዴን ከውጭ ማስመጣትም አቁማለች። በአትክልትና በፍራፍሬ ዘርፍም የወጪ ምርት መጠናችን ጨምሯል።
በሌማት ትሩፋት በተሠራው ሥራ የወተት፣ የዶሮና የማር ምርቶች በየቤተሰቡ ሌማት ላይ እንዲገኙ ጥረት ተጀምሯል። በዚህም የዶሮ ሥጋን ምርት ከነበረበት 70 ሺህ ቶን ወደ 208 ሺ ቶን፤ የወተት ምርት ከነበረበት 7.2 ቢሊዮን ሊትር ወደ 10 ቢሊዮን ሊትር ደርሷል። የማር ምርት ደግሞ ከ129 ሺህ ቶን ምርት ወደ 272 ሺህ ቶን ለማሳደግ ተችሏል።
ሌላው ኢትዮጵያን የማዘመን ተግባር ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማድረግ ተግባር ነው። ከመመናመን አልፎ እየጠፋ የነበረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልብስ፣ እየተመለሰ ነው። ኢትዮጵያ ከመራቆት ወደ አረንጓዴ ጋቢ እየተሻገረች ናት። ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊዮን የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል በቅተናል። ከእነዚህ ውስጥ 50.4 በመቶ የደን ዛፍ ችግኞች ሲሆኑ፣ 48.6 በመቶ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ፣ የፍራፍሬ፣ የመኖና የማገዶ የእንጨት ዛፎች ናቸው።
ኢትዮጵያን ለማዘመን በተሠራው የኢንዱስትሪ ምርታማነት ሥራ አያሌ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተቻለ ነው። ከዚህ በፊት ከውጪ የሚገቡትን የቢራ ብቅል፣ የምግብ ዘይት፣ ፓስታና አልሚ ምግቦች፣ የተማሪዎች ዩኒፎርም፣ የፀጥታ አባላት የደንብ ልብስ፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች (ፖል፣ ገመድና ትራንስፎርመር) በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሥራ ውጤት እያሳየ ይገኛል።
በዚህ ዘመን የሚደረግ ሀገርን የማዘመን ተግባር ያለ ዲጂታላይዜሽን ሊሳካ የሚችል አይደለም። በዚህም የተነሣ መንግሥት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚያደርገው ምርምር እና የሚያፈሰው ሙዓለ ንዋይ እየጨመረ መጥቷል። ለማሳያም ያህል የዲጂታል አካውንት ብዛት ከነበረበት 52.1 ሚሊዮን ዛሬ ወደ 205.4 ሚሊዮን ሆኗል። በዘመናዊ የክፍያ ዘዴ የተላለፈው የገንዘብ መጠን ደግሞ 9.6 ትሪሊዮን ብር በመሆን ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል።
ሌላው የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ በዘርፉ የተሠራው የዲጂታል ብድርና ቁጠባ አገልግሎት ነው። በአጠቃላይ 7.7 ቢሊዮን ብር በዲጂታል ቁጠባ ሂሳብ ተሰብስቧል። 8.4 ቢሊዮን ብር የሚያህሉ ጥቃቅን ብድሮች ደግሞ በተለመደው የባንክ ሥርዓት ብድር ሊያገኙ ለማይችሉ ዜጎች ተሰጥቷል።
ኢትዮጵያን ለማዘመን በአንድ በኩል ነባር አቅሞቿን አውጥቶ የመጠቀም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለዘመናዊነት በር የሚከፍቱ ተግባራትን የማከናወን ሥራ ተሠርቷል። በገበታ ለሸገር በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡት የቱሪስት መዳረሻዎች በተጨማሪ፣ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በጎርጎራ፣ በወንጪ፣ በሐላላ ኬላና በኮይሻ የቱሪስት መዳረሻዎች ተገንብተው ጥቅም ላይ ውለዋል። በገበታ ለትውልድ ደግሞ በሌሎች ሰባት የሀገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ ናቸው። ይሄም ነባር አቅማችን በማውጣት ተጨማሪ ገቢዎችንና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር አስችሏል።
የኢትዮጵያን ከተሞች ለዜጎች ምቹ፣ ጤናማና አካታች ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደርሷል። በዚህ የዝመና ፕሮጀክት አማካኝነት መሠረተ ልማቶችን የማሟላት፣ ከተሞችን ፅዱና አረንጓዴ የማድረግ፣ በድህነት አኗኗር ውስጥ ላሉ ዜጎች ኢትዮጵያን የሚመጥን የመኖሪያ አካባቢዎችን የመስጠት፣ ሕጻናትና ወጣቶች ከሱስና ከአጉል ሕይወት እንዲርቁ የሚያስችሉ መዋያዎችን የማዘጋጀት፣ ማኅበረሰባዊ ትሥሥርን የሚፈጥሩ አደባባዮችንና መስኮችን የመፍጠር ሥራዎች ተሠርተዋል።
ለውጡ ካዘመናቸው ነገሮች አንዱ የፕሮጀክቶችን የሥራ ባሕል ነው። በቀናት እና በወራት የሚጠናቀቁ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ናቸው። ከለውጡ በፊት ቆመው እና ተበላሽተው የነበሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችም በልዩ ክትትል እየተጠናቀቁ ይገኛሉ። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለዚህ ዋነኛው ማሳያ ነው። የህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ በተደረገው ርብርብ የግድቡ ሥራ ከ97.6 ፐርሰንት በላይ ደርሷል። ግድቡ ትልቅ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ፈጥሯል። አሁን ላይ አራት ተርባይኖች በድምሩ 1443 ሜ.ዋ ኃይል እንዲያመነጩ ተደርጓል። ይሄም የብልፅግና ጉዟችንን ማንምና ምንም እንደማያስቀረው ምሳሌ ነው።
የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን ለማዘመን በተሠራው ሥራ ሰብዓዊ፣ መዋቅራዊና ቴክኖሎጂያዊ ብቃት ያላቸው የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ተፈጥረዋል። እነዚህ ተቋማት ሕገ መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርገው ተልዕኳቸውን እንዲያከናውኑ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነዋል። የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ሪፎርም በማድረግ ኢትዮጵያን የሚመጥኑ ተቋማት እንዲሆኑ እየተደረገ ነው።
የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና በመፍጠር የሀገርን አቅም እየገነቡ ናቸው። ለሠራዊታችን የሚያስፈልጓቸውን ትጥቆችና ስንቆች ለማሟላት ዳር ደርሰዋል። በዚህም ኢትዮጵያን ከባንዳና ከባንዳ ጠላቶች በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል የሚችሉበት ቁመና ላይ ይገኛሉ።
የኢኮኖሚ ሪፎርም፡- ለውጡ እንዲመጣ ከገፉት ሀገራዊ ስብራቶች አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቱ ሀገሪቱን ከአቅሟ በላይ ለሆነ ዕዳ የዳረገ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛነፍን ያስከተለ፣ የዋጋ ውድነትንና ግሽበትን ያመጣ ስብራት ነው። ይሄንን ስብራት ለመጠገን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመዘርጋት ሁሉን አቀፍ ሥራ ተሠርቷል። በዚህ ማሻሻያ አማካኝነትም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም፣ ሀገራዊ ገቢን በሀገራዊ ምርት ልክ የማድረግ ሪፎርም፣ ምርትና ምርታማነትን የመጨመር ሪፎርም፣ የባንኮች የውጭ ምንዛሪን ከሌሎች ገበያዎች ጋር የማጣጣም ሪፎርም፣ የዕዳ ቅነሳና ሽግሽግ የማድረግ ሪፎርም፣ የመንግሥትን የመበደር ሁኔታና መጠን የማስተካከል ሪፎርም፣ ተከናውነዋል። በዚህም ከዓለም አቀፍ ተቋማት የምናገኘው ብድርና ድጋፍ ጨምሯል። የዕዳ ሽግሽግና ቅነሳ ውይይቶች ወደ ውጤት ቀርበዋል። የሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ክምችት አድጓል። የሀገር ውስጥ ገቢን የማሰባሰብ አቅማችን ከፍ ብሏል።
የፖለቲካ ተሳትፎ፡ በለውጡ ዘመን ከተለወጡት ባሕሎች አንዱ የፖለቲካ ተሳትፎ ባሕል ነው። ማንኛውም ሰው ሕጋዊና ሠላማዊ እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ አይከለከልም። ከገዥው ፓርቲ የተለየ የፖለቲካ አደረጃጀትም በተፎካካሪነት እንጂ በጠላትነት አይታይም። በዚህም የተነሣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች በፌዴራልና በክልል የአመራርነት ቦታ ላይ ተመድበዋል። ይሄ ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባሕል ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የክልል ፕሬዚዳንቶች ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በየጊዜው ይመካከራሉ። በሀገር ዕቅዶች፣ በአፈጻጸሞችና በዋና ዋና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ይደረጋል። ይሄም የሠለጠነ የፖለቲካ ባሕል ለመገንባት መንገድ እየጠረገ ነው።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች መለየትና ማስከበር፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለመለየትና ለማስከበር የምትከተለው የዓይን አፋርነት አካሄድ ነበር። ይሄም በመሆኑ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር የሚያስችል ገቢራዊ አካሄድ እንዳንጓዝ አድርጎን ኖሯል። ለውጡ ይሄን አካሄድ ቀይሯል። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር ግልጽና ጉልሕ የሆነ መንገድን ትከተላለች። ባለፉት ዘመናት የተከሠተውን የባሕር በር የማጣት ስብራት ለመጠገንም ይሄንኑ መንገድ መከተል አስፈላጊ ነበር።
በዚህም የተነሣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ዓለም በብዛት እንዲቀበለው ለማድረግ ተችሏል። በዓለም አቀፍ መድረኮችም ብሔራዊ ጥቅሞቿን ሊያስከብሩ በሚችሉ የሁለትዮሽና ባለ ብዙ ዘርፍ ትብብሮች ላይ በጉልህ ትሳተፋለች። አባል ትሆናለች። እንደ ብሪክስ ባሉ ማሕቀፎች ላይ ያደረገችው የአባልነት ተሳትፎም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የለውጡ መሪም ውጤትም የሆነውን የብልፅግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት ስናከብር፣ ያለፉትን ስኬቶች ቆጥረንና አዳብረን በማስቀጠል፤ ፈተናዎቻችንን በመወጣትና ስሕተቶችን በማረም ይሆናል። የለውጡ ትግል፣ የለውጡ ሥራና ውጤት ከአንድ ፓርቲ በላይ ነው። ጥቅሙም ሀገራዊና ለሁሉም ዓይነት ማኅበረሰብ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ማሳያዎች የጅምራችንን ትክክለኛነት አመላካች ናቸው።
ነገር ግን መጀመራችንን እንጂ ማጠናቀቃችንን አያሳዩም። ስለሆነም የፓርቲያችን አመራርና አባላት፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራርና አባላት፣ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ለውጡ ሰክኖና ሥር መሠረት ይዞ፣ ይህ ዘመን የኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመን እንዲሆን በጋራ እንድንነሣና እንድንታገል በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!
ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም