ምክር ቤቱ ተጨማሪ 582 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ:– የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ለዕዳ ክፍያ፣ ለማኅበራዊ ድጎማ እና ለደመወዝ ጭማሪ የሚውል የ2017 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ 582 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ።

ረቂቅ በጀቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ የፀደቀው ተጨማሪ በጀት ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ዕዳ ክፍያ፣ ለማኅበራዊ በጀት ድጎማ (ለማዳበሪያ፣ ለመድኃኒት፣ ለምግብ ዘይትና ሌሎች ወጪዎች) የሚውል ነው።

ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፋፊያ፣ ለማኅበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም እንዲሁም ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ማሻሻያ እንደሚውልም ነው የተናገሩት።

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ተጨማሪ በጀቱ ለመደበኛ ወጪ ማለትም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ዕዳ ክፍያ 185 ቢሊዮን ብር፣ ለማኅበራዊ ድጎማ 208 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪ ለማኅበራዊ ሴፍቲኔት ማስፋፊያ 60 ቢሊዮን ብር እና ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስተካከያ 10 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ለማድረግ 119 ቢሊዮን ብር እንደሚውል ተናግረዋል።

ተጨማሪ በጀቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ ያካሄዳቸውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የሚገኘው በጀት በመጨመሩ ምክንያት ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑንም ተስፋዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ማሻሻያውን ተከትሎ የዋጋ መናር፣ ግሽበትና መሰል ችግሮች እንዳይባባሱ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የበጀት ማሻሻያው በተወሰነ መልኩ አስፈላጊ ነው፤ በተለይም ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድጉ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባውም ነው የጠቆሙት።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ በደመወዝተኛው ላይ ጫና ይፈጥራል፣ ጭማሪ ተደረገ ቢባልም ጫናውን በሚሸፍን መልኩ ያገናዘበ ማስተካከያ ሊደረግ ይገባ ነበር ብለዋል።

ተጨማሪ በጀቱ በዝቷል? በገበያው ውስጥ የዋጋ ግሽበትን ሊያስከትል ይችላል? ከተጨማሪ በጀት ውስጥ 282 ቢሊዮን ብር ከግብር የሚሰበሰብ እንደመሆኑ በግብር ከፋዮች ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል የሚሉና መሰል ጥያቄዎችና ስጋቶች የምክር ቤት አባላት ካቀረቧቸው መካከል ይገኙበታል።

የተጨማሪ በጀት ረቂቁን አስመልክተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ እንደገለጹት፤ ዘላቂ፣ የተረጋጋና ዘመናዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ምቹ ሀገረ መንግሥት ለመፍጠር ዘመናዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መተግበር ግድ ነው።

ግሽበት እንዳይባባስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ተጨማሪ በጀቱ ታሳቢ ያደረገው አዲሱን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነው። ተጨማሪ በጀቱ በኢኮኖሚ በማደግ ላይ ላለች ሀገር ብዙ የሚባል አይደለም። ገቢው እያደገ ሲመጣ በቀጣይ ዓመት ከዚህ ከፍ ያለ በጀት ሊቀርብ ይችላል ብለዋል።

ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ከሚገኝ ገቢ የሚሸፈንና ዝቅተኛ ተካፋይ ለሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም ለሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች የሚውል በመሆኑ በዋጋ ግሽበቱ ላይ ለውጥ አያመጣም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የፀደቀው በጀት ግሽበትን በመቆጣጠር በኩል በጣም ጠቃሚ ሥራ የተሠራበት መሆኑን አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ በትናንት ውሎው፤ አቶ ሐጂ ኢብሳን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር አድርጎ የሾመ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና የመድኃኒት ፈንድን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1354/2017 አድርጎ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅንም ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You